Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገሪቱን ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከግምት ውስጥ ያላስገባው የሕይወት መድን ጨረታ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያን የሕይወት ኢንሹራንስ አገልግሎት ከፍ ያደርጋል የተባለና በመቶዎች ለሚቆጠሩና ወደ ውጭ ለሥራ ለሚሄዱ ዜጎች የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት የሚያስችል ጨረታ ወጣ፡፡ የጨረታ መሥፈርቱ ግን እያነጋገረ ነው፡፡  

በዚህን ያህል ደረጃ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት እንዲቻል ተጫራቾች የተጋበዙበት ጊዜ ባለመኖሩ፣ በዚህ ጨረታ የኢንሹራስ ኩባንያዎች ከሕይወት የመድን ሽፋን ከፍተኛ የዓረቦን ገቢ ያገኙበታል ተብሎ እንደሚታመን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን የሕይወት መድን ሽፋን እንዲሰጡ ጨረታውን ያወጣው የሥራና የክህሎት ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ባወጣው ጨረታ ለምን ያህል ሰዎች የመድን ሽፋን እንደሚሰጥ እንደሚፈልግ  ባይገልጽም፣ 500 ሺሕ የሚሆኑ ሠራተኞች ይፈልጋሉ፡፡ በመባሉ አገልግሎቱ ሰፊ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ጨረታ ብዙዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢንሹራንስ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ በዚህን ያህል ደረጃ የሕይወት የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት እንዲቻል ጨረታ የወጣበትን ጊዜ እንደማያስታውሱ የገለጹት የአንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች፣ በተባለው ቁጥር ልክ የመድን ሽፋኑ የሚሰጥ ከሆነ የአገሪቱን የሕይወት የመድን ሽፋን በእጅጉ ሊቀርፍ የሚችል ነው ይላሉ፡፡

በሕጋዊ መንገድ እንደሚሄዱ የተገለጸው ሥልጠና ይወስዳሉ የተባሉት 36 ሺሕ ሠራተኞች ወደ ውጭ ለሥራ የሚሄዱትን ቁጥር ብቻ ቢወሰድ እንኳን፣ የአገሪቱን የሕይወት መድን ሽፈን መጠን ከፍ ያደርገዋል ብለው ያምናሉ፡፡ የኢትዮጵያ የመድን ኢንሹራንስ ዘርፍ በተለይም የሕይወት መድን ሽፋን ከጠቅላላው የመድን ሽፋን አንፃር ሲታይ ከአምስት በመቶ የዘለለ ባለመሆኑ፣ በዚህን ያህል ቁጥር የመድን ሽፋኑን መስጠት ከተቻለ፣ ተደራሽነትን በእጅጉ የሚለውጥ የዓረቦን ገቢውም እንደሚያስግድድ ይስማሙበታል፡፡

የሕይወት የመድን ሽፋን የሚሰጡ ኩባንያዎች የውጭ አገር የሥራ ዋስትና ሽፋን እየሰጡ ቢሆንም የተጠቃሚዎቹ ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡

በውጭ አገሮች ለሥራ የሚጓዙ ሠራተኞች ዋስትና እንዲገባላቸው በዚህ መልኩ አስገዳጅ መሆኑ ተገቢ እንደሆነ የሚገልጹት የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጨረታ ሰነዱ ግን ክፍተት ያለበት ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡

በዚህ ጨረታ ለመወዳደር እንደ መሥፈርት ሆነው ከቀረቡት መካከል፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ካፒታላቸው 50 ሚሊዮን ብር መሆን አለበት የሚለው አንዱ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ በብሔራዊ ባንክ የተረጋገጠ ፈቃድ ያላቸው በመሆኑ፣ የካፒታል መጠናቸው እንደ መሥፈርት መቀመጡ በጨረታ ላይ ከተገለጸው መጠን በታች ካፒታል ያላቸው ኩባንያዎች በዚህ ጨረታ እንዳይሳተፉ ይገድበዋል ብለው ይከራከራሉ፡፡ ኩባንያዎቹ ለሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የሚያስመዝግቡት ካፒታል ለብቻው በመሆኑ፣ የአብዛኛዎቹ ኩባንያዎች ደግሞ ካፒታል በመሥፈርትነት ከተቀመጠው በታች ስለሚሆን ብዙዎቹን ኩባንያዎች ከጨረታ ውጪ ማድረጉ ስለማይቀር የጨረታ መሥፈርት አንድ ችግር ነው ይላሉ፡፡

ሌላው መሥፈርት በዚህ ጨረታ መሳተፍ የሚቻለው አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ የሕይወት መድን ሽፋን የመስጠት ልምድ ያለው መሆን ይገባው የሚል ነው፡፡ ይህም ጥቂት የማይገባሉትን የኢንሹራንስ ኩባንያ ከውድድር ውጪ ስለሚያደርግ እንዲህ ዓይነቱ መሥፈርት ችግር የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢንሹራንስ ዘርፉ በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚደረግበት፣ ፈቃድ ሲሰጠውም አገልግሎቱን ለመስጠት ብቃት እንዳለው ታምኖበት የሚሰጥ ነው፡፡ የካፒታላቸው መጠን ዝቅኛው ይህ ነው ብሎ ጠቅሶ ይህንን መሥፈርት አሟልተው አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው በመሆኑ፣ ጨረታ ለመወዳደር ካፒታላችሁ ይህንን ያህል ይሁን ተብሎ መቀመጡ ትክክል ነው ብለው አያምኑም፡፡ የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር ባወጣው ጨረታ የሚፈልገው የመድን ሽፋንም ቢሆን፣ ልምድ የሚጠይቅ ባለመሆኑ፣ በዚህ ጨረታ ለመሳተፍ 10 ዓመት ልምድ ያለው መባሉ ትክክል እንዳልሆነም ይሞግታሉ፡፡ ይህ የመድን ሽፋን የሚታወቅና አንድ የአገልግሎት ዓይነት በመሆኑ፣ እንዲህ ያለ መሥፈርት በማውጣት የተሻለ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

በጨረታ ሰነዱ ላይ የተቀመጠው ሌላው መሥፈርት ‹‹የመድን ሽፋን የሚሰጥበት ኦንላይን ሲስተም ያለው›› የሚል ነው፡፡ ይህም መሥፈርት የተወዳዳሪዎችን ቁጥር የሚያሳንስና የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሁን ያሉበትን ደረጃ ያላገናዘበ በመሆኑ የጨረታ መሥፈርቱ አወጣጥ ክፍተት ያለበት መሆኑን ያሳያል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኦንላይን የመድን ሽፋን የሚሰጡ ኩባንያዎች አምስት የማይሞሉ  በመሆናቸው፣ ጨረታው ለተወሰኑ ኩባንያዎች ብቻ የወጣ ያስመስለዋል የሚል ትችት እያስነሳ ነው፡፡

ይህንን የመድን ሽፋን ለመስጠት በጨረታ ሰነዱ ላይ እንዲህ ያለ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ የመድን ሽፋን መስጠት የሚችል የኢንሹራንስ ኩባንያ ዓረቦኑን ያሳውቀን መባል ነበረበት ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የኢንሹራንስ ሽፋን የፖሊሲ ውል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀባይነት አለው፡፡ አገልግሎቱን እንዲሰጥ ብሔራዊ ባንክ ማረጋገጫ የሰጠበት እስከሆነ ድረስ፣ ከዚያ የተለዩ መሥፈርቶችን መደርደር ተገቢ ስላልሆነ ወደ ጨረታው ከመግባቱ በፊት ኩባንያዎቹ ማብራሪያ እንደሚጠይቁም እየተናገሩ ነው፡፡  

በጨረታ ሰነዱ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡትና ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የኢንሹራንስ ባለሙያ እንደገለጹት ደግሞ፣ ይህ ጨረታ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን ያምናሉ፡፡ በተለይ በዚህ ጨረታ ውስጥ እንደ መሥፈርት የተቀመጠው የመድን ሽፋኑ የዓረቦን ክፍያ 500 ብር መሆኑ መገለጹ ነው ይላሉ፡፡ የዓረቦን መጠኑ ከተገለጸ ኩባንያዎቹ መወዳደሪያቸው ምን ሊሆን ነው? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ውድድሩ የዓረቦን መጠን ላይ መሆን ሲገባው በሌሎች መመዘኛዎች አወዳድራሁ ብሎ መነሳቱ የጨረታ መሥፈርቱ መሠረታዊ የሆነ ስህተት እንዳለበት እንደሚያሳይ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡  

እንዲህ ዓይነቱ የኢንሹራንስ ሽፋን ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሰጥ ከተፈለገም እንደ ሦስተኛ ወገን አስገዳጅ የተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ዋጋው ከተወሰነ በኋላ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎቱን እንዲሰጡ ማድረግ እየተቻለ ብዥታን የሚፈጥር ጨረታ ማውጣት ተገቢ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ባለሙያው ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ነገር ግን አሁን ለታሰበው የውጭ አገር ሥራ ለሚሰማሩ ዜጎች የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ለአንድ ሰው 500 ብር ዓረቦን ይከፈልበታል ከተባለ፣ የመድን ሽፋኑ የሚሸፍናቸው ከታወቁ አስገዳጅ አድርጎ ሁሉም ኩባንያዎች ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ይችሉ እንደነበርም ይጠቁማሉ፡፡

እንዲህ ዓይነት የጨረታ መሥፈርት አውጥቶ አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለመምረጥ መነሳትም ተገቢ አይሆንም ተብሏል፡፡ እንዲህ ያለው የጨረታ መሥፈርት አንድን አካል ለመጥቀም ካልሆነ በስተቀር፣ እስከ 500 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች ሽፋን ለመስጠት የታሰበን አገልግሎት ለአንድ አሸናፊ ይሆናል ለተባለ ኩባንያ መስጠትም ፍትሐዊ አይደለም ብለዋል፡፡

ስለዚህ የኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃዎች በአዲስ አበባም ሆነ በሚመለከታቸው በክልል ከተሞች አገልግሎት እንዲያገኙ ከተፈለገ፣ ይህንን የመድን ሽፋን ለአንድ ኩባንያ ብቻ ለማሸከም መሞከር አግባብ ይሆናል ብለው እንደማያምኑም እኚሁ ባለሙያ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በጨረታ ሰነዱ ላይ በዝርዝር ለቀረበው የመድን ሽፋን ዓይነት፣ ኩባንያዎቹ የሚጠየቁት የዓረቦን መጠን 500 ብር ነው ማለቱ በራሱ በምን ዓይነት መንገድ ሥሌት ተሠልቶ እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ሆኖ አግኝተውታል፡፡

በጨረታ ሰነዱ የዓረቦን ዋጋ የሚሰጡ የመድን ሽፋኖች አምስት ሲሆኑ፣ እነሱም ኢንሹራንስ የተገባለት ሠራተኛ በተፈጥሮ፣ በድንገተኛ አደጋ ወይም ሥራ ላይ እያለ ራስን የማጥፋት አደጋ ሲያጋጥመው የሚለው በመጀመርያ ረድፍ ላይ ተቀምጧል፡፡  

በዚህ 500 ብር ዓረቦን የሚሸፈኑት ቀሪዎቹ የመድን ዓይነቶች ደግሞ ሠራተኛው በሄደበት አገር በተፈጥሮም ሆነ በድንገተኛ አደጋ የሞተ እንደሆነ የቀብር ማስፈጸሚያና የሠራተኛ ማጓጓዣ፣ ዘላቂ የአካል ወይም ከፊል የአካል ጉዳት የደረሰበት ከሆነ፣ የአዕምሮ መታወክ ካጋጠመውና የአስግደዶ መደፈር ድርጊት ተፈጽሞበት ዘላቂ ጉዳት ወይም የአዕምሮ መታወክ የደረሰበት ከሆነ የመድን ሽፋን ያገኛል ተብሎ ተቀምጧል፡፡

ይህንን ሁሉ የመድን ሽፋን በዓመት 500 ብር በሚከፈልበት ዓረቦን ለመስጠት ተወስኖ መቅረቡ በራሱ ትክክል ያለመሆኑን ባለሙያው አብራርተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ዘርፉን እንደ ሸቀጥ ማየትና በበቂ የኢንሹራንስ ዕውቀት የተሰናዳ የጨረታ ሰነድ አለመሆኑን እንደሆነም አክለዋል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት በዚህን ያህል ዋጋ የሚሰጥ የመድን ሽፋን ጥቂት ከመሆኑ አንፃር፣ በተቀመጠው ቁርጥ የዓረቦን ዋጋ ምን ያህሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተስማምተው የመድን ሽፋኑን ይሰጣሉ? የሚል ጥያቄ የሚያጭር እንደሆነ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ማለት እኔ የዓረቦን መጠኑን ዋጋ አውጥቻለሁ፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በ500 ብር የዓረቦን ሽፋኑ፣ ሠራተኛው አደጋው ሲደርስበት(ባት) 300 ሺሕና 400 ሺሕ ብር እንከፍላለን እንዲሉ ነው፤›› ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አሠራር ሪስኩ ተተምኖ ፕሪሚየም ይደረጋል እንጂ ከፕሪሚየም ወደ ሪስኩ አይመጣም፤›› አሁን የሆነው ግን በተቃራኒው በመሆኑ፣ የጨረታ ሰነዱ ድጋሚ መፈተሽ ይኖበታልም ተብሏል፡፡ ጨረታው መስፋቱ ብዙ ክፍተት አለበት የሚሉት ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያው፣ ጨረታው ድጋሚ መታየት የሚርኖበት እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ቢያንስ ከመድን ሰጪዎች ማኅበር ጋር እንኳን መመካከር ይችል እንደነበር ያስታወሱት የኢንሹራንስ ባለሙያው፣ እንዲያውም ሚኒስቴሩ በዝርዝር ካቀረባቸው የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋኖች ባሻገር ለተጨማሪ አገልግሎቶችም ፖሊሲ በማዘጋጀት፣ አገልግሎቱ በአስገዳጅነት በሁሉም ኩባንያዎች በኩል መስጠት ይቻል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

የሕይወት መድን ልክ እንደ ሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን አስገዳጅ ሲሆን፣ ዘርፉንም ለማሳደግና ችግሮችንም እንደሚቀርፍ ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች