Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ነጋ ጠባ ‹‹ሲስተም የለም›› እና ዲጂታል ገበያ አይጋጩም?

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የተለያዩ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶቻቸውን እየሰጡ ናቸው፡፡ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎታቸውን እንደ አንድ መወዳደሪያ እያደረጉትም ነው፡፡ በተለይ የ‹‹ኤቲኤም›› ተጠቃሚዎቻቸውን ቁጥር አሳድገዋል፡፡ የኢንተርኔትና የሞባይል ተገልጋዮች ቁጥርም ከዓመት ዓመት እያደገ ነው፡፡ በሞባይልና በሌሎች የዲጂታል ገንዘብ ማዘዋወሪያ ዘዴዎች የሚደረጉ የገንዘብ መላላኮችም ቢሆኑ እየተለመዱና ብዙ ተጠቃሚዎችን ማፍራት አስችሏቸው ነው፡፡

ከተቋማት ጋር በመስማማት የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችን በዚሁ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ቋት ውስጥ እያስገቡ ነው፡፡ በአጠቃላይ በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች በኩል የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን እየጨመረ መምጣት፣ በጥሬ ገንዘብ የሚደረገውን ክፍያዎች እየቀነሱ እንዲሄዱ እያስቻለ ነው፡፡ ደንበኞችም ባሉበት ቦታ ሆነው የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙና ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እያገዘም ነው ማለት ይቻላል፡፡ 

ከ100 ሚሊዮን በላይ የባንክ የቁጠባ ደብተር ያላቸው ደንበኞችን ማፍራት የቻሉት የአገራችን ባንኮች በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ባይኖራቸውም፣ እነዚህን ሁሉ ደንበኞቻቸውን በአግባቡ ማስተናገድ ባልቻሉም ነበር፡፡

አነስተኛም ሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለማውጣትና ለማስገባት ይህ ሁሉ ደንበኛ ወደ ባንክ ቅርንጫፎች መሄድ የሚገደድ ቢሆን ኖሮ፣ እንዴት ሊስተናገዱ ይችሉ እንደነበር ሲታሰብ፣ ጊዜ አመጣሹን ቴክኖሎጂ ማመስገን ግድ ይላል፡፡ የአንዳንድ ባንኮች መረጃ እንደሚጠቅሰውም፣ አብዛኛው የገንዘብ እንቅስቃሴያቸው በዚሁ የዲጂታል አገልግሎት በኩል እየሆነ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አነስተኛ ብድሮች በሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም ብቻ መጠቀም የሚያስችል አሠራር እየዘረጉ ነው፡፡ 

ይህንን አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባንኮች ብዙ ዜጎችን መድረስ የሚችሉበት ዕድል እያሳዩ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን አገልግሎት ሌሎችም ባንኮች በቅርቡ ይጀምራሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ አነስኛ ብድሮችን ለብዙዎች ለማድረስ እንደ አንድ አማራጭ ታይቷል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ባንኮች ብድር ከ350 ሺሕ ላልበለጡ ሰዎችና ኩባንያዎች ብቻ የሚሰጡ መሆናቸውንና ይህንን ክፍተታቸውን ለማጥበብ የሚያግዝ መሆኑ ይታሰባል፡፡ 

እስከዛሬ ባንኮቹ የጥቂት ተበዳሪዎች ብቻ መሆናቸው አስደንጋጭ ከመሆኑ አንፃር፣ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የሚሰጡት ብድር ዜጎች ቆጣቢዎች ብቻ ሳይሆኑ ተበዳሪዎች መሆን እንዲችሉ ጭምር ዕድል ይሰጣል፡፡ ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ብድር የተበዳሪዎችን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ አንዳንድ ብልሹ አሠራሮችንም ያስቀራል፡፡

ባንኮቻችን በቴክኖሎጂ እስካልተጠቁ ድረስ እስካሁን በለመዱት መንገድ መጓዝ የማያዋጣቸው መሆኑን አምነው እየሠሩ ያሉት እንዲህ ያለው ተግባር ሌላው ትልቁ ጠቀሜታ ሙስናንና ያልተገቡ ተግባሮችን የሚከላከል በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በሞባይል መተግበሪያ አነስተኛ መጠን ያላቸውን ብድሮች ሲያቀርቡ በአብዛኛው ከሰው ንክኪ ነፃ የሚሆን መሆኑና በቅደም ተከተል አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችልም ነውና የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶች በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያሳየናል፡፡  

በአጠቃላይ ሲታይ ባንኮች ዘመናዊ የክፍያ ዘዴዎችን ለማስፋፋት የጀመሯቸውን ሥራዎች በእጅጉ የሚጠቀሙ የመሆናቸውን ያህል አገልግሎታቸው የጥራት ጉዳይ ግን ማነጋገሩ አልቀረም፡፡ በዘመናዊ መንገድ ገንዘብ የማንቀሳቀስና የማስተላለፍ ልምድ እያደገ ነው ቢባም፣ በኔትዎርክ መቆራረጥና የሲስተም ችግር አገልግሎታቸው ሰንካላ እንዲሆን እያደረገ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ዛሬም ወደ ቅርንጫፉ የሚሄዱ ደንበኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኙ የኔትዎርክ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ሲስተም የለም በሚል ገንዘብ ለማስገባት እንኳን ያለውን ችግር በተደጋጋሚ እያየን ነው፡፡  

በአንዳንድ ባንኮች ቅርንጫፎች ውስጥ ኔትዎርክ የለም በተባለ ቁጥር ደንበኞች ለሰዓት የሚጠብቁበት ሁኔታ እየበዛ ነው፡፡ በባንክ ቅርንጫፎች መጨናነቅን ለማስቀረት ሁነኛ ሚና ያለው የኤቲኤም አገልግሎትም ቢሆን በተመሳሳይ ችግር የሚታይበት ነው፡፡ አንዳንዴ አገልግሎት የማይሰጡ ኤቲኤም ማሽኖች በቶሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ አለማድረግ አንዱ ነው፡፡ ገንዘብ የጨረሰ ኤቴኤምን ተከታትሎ ገንዘብ የመተካት ችግርም አለ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በስህተት በኤቲኤም የሚባሉ የደንበኞች ገንዘብን በቆሎ የመመለስ ችግርም በብዙዎቹ ባንኮች ላይ ይታያል፡፡

አንዳንድ የኤቲኤም ማሽኖች ደግሞ መብራት ቢቋረጥ እንኳን በጄኔሬተር እንዲሠሩ ቢጠበቅም፣ ይህ ዓይነቱ መሠረተ ልማት የላቸውም፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ እየተስፋፋ የመጣውን የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ለማሳለጥ ወሳኝ የሆነው ኔትዎርክ ነውና በኔትዎርክና በሲስተም ችግር የሚፈጠሩ የባንክ አገልግሎቶች እየበዙ ከመጡ የቴክኖሎጂውን መሠረተ ልማት መያዝ ብቻ ግብ ሊሆን እንደማይችል መታሰብ አለበት፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ደግሞ በዓላትን አስታከው የሚደረጉ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ከፍ ስለሚል አንዳንድ ባንኮች ለአገልግሎት የዋሉት ቴክኖሎጂ በመጨናነቅ ደንበኞችን በቶሎ ለማስተናገድ ሲቸገሩ መመልከታችን ነው፡፡  

አንድ ደንበኛ የተላከለትን ገንዘብ ወዲያው በሞባይል ስልኩ ማረጋገጫ ማግኘት ሲገባው፣ ማረጋገጫው ሁለትና ሦስት ቀናት ቆይቶ ከደረሰው ችግር አለ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ገንዘብ በተላላኩ የባንክ ደንበኞች መካከል አለመተማመን የሚፈጥርም ይሆናል፡፡ ከዚህም በላይ ገንዘብ የተላከለት ደንበኛ ገንዘብ እንዲገባለት ለማረጋገጥ የግድ ወደ ቅርንጫፎች የሚያስገድደው ከሆነ የዲጂታል የባንክ አገልግሎቱን አጓደለ ማለት ነው፡፡ ከሰሞኑ እኔም ከተለያዩ የባንክ ደንበኞች እንዲህ ያለውን ቅሬታ ሰምቻለሁ፣ በግሌም አረጋግጫለሁ፡፡ 

በአካውንቴ ገባ የተባለውን ገንዘብ እንደገባ ማረጋገጥ የቻልኩት ገንዘቡ ከገባ ከሦስት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ወደ አንድ ቅርንጫፍ ሄጄ ‹‹ለምን ይኼ ይሆናል?›› ስል የኔትዎርክ ችግር ነው ሲስተም ላይም ችግር ነበር የሚል ምላሽ ተሰጥቶኛል፡፡ ይህ ለችግሩ አንድ ማሳያ ሊሆን ቢችልም፣ በኔትዎርክ ችግር ብዙ መጉላላቶች ይታያሉ፡፡ ኔትዎርክ ከሌለ ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንደማይቻል የተረጋገጠ ሲሆን፣ በሲስተም ችግር የሚጓደል አገልግሎት የሚደጋገም ከሆነ፣ ነገ ከነገ ወዲያ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ሲሰፋ የበለጠ ችግር ሊገጥመን ይችላል የሚል ሥጋት ያሳድርብናል፡፡ 

ስለዚህ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ይደረግ ከተባለ ነጋ ጠባ የሚሰማውን የ‹‹ኔትዎርክ የለም›› እና የ‹‹ሲስተም›› ችግር ይዞ ወደፊት መራመድ አይችልም፡፡ ስለዚህ ዘመናዊ ግብይትን ለማስፋፋት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የገንዘብ ዝውውርን የበለጠ ለማላመድና በዚህ ቴክኖሎጂ የሚሰጡ አገልግሎቶችን እያሰፋን ከሄድን በኔትዎርክ የለምና በሲስተም ችግር ሊደነቃቀፍ የሚችለውን አገልግሎት ለመቅረፍ በብርቱ መሠራት አለበት፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የኔትዎርክ ባለቤት ከመሆን ባሻገር፣ እሱም በዚሁ ኔትዎርክ ተጠቅሞ ገንዘብ እያቀባበለ ነውና ለእሱም ጭምር ብሎ ይህንን ችግር ሊቀርፍ ይገባል፡፡ ባንኮችም ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለውን ምክንያታቸውን ለማስቀረት ጊዜ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ ይጠቀሙ፡፡

   

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት