በተሾመ ብርሃኑ ከማል
ዘከሪያ፣ ሸኽ (በኋላ አለቃ ነዋየ ክርስቶስ (ከ1845 እስከ 1920) በጎንደር፣ ጋይንት አውራጃ ነገላ ውስጥ አውሸንዲባ ከሚባል ቀበሌ ተወለዱ፡፡ አባታቸው በወቅቱና በአካባቢው ከፍ ያለ ሀብትና የኑሮ ደረጃ የነበራቸው ገበሬ፣ ነጋዴና ሸማኔ ሲሆኑ፣ እናታቸው ወይዘሮ በፍታም ከዚያ አካባቢ ተወለዱ፡፡ እናታቸው ወይዘሮ በፍታ ሰለምቴ ክርስቲያን ሲሆኑ ዘከሪያን ጨምሮ ዋሴ፣ ኢሣና እህሊቱ የተባለች ሴት ልጅ ወልደዋል፡፡
በመሠረቱ፣ በወሎና በጎንደር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሙስሊም ወንዶች በልዩ ልዩ ምክንያቶች ክርስቲያን ሴቶችን ያገቡ ስለነበር የዚህ ሁኔታ እንብዛም የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ወይም አንዳንድ ሰዎች በዘከሪያ የኋለኛ ሕይወት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለው ለመግለጽ እንደሚሞክሩት አይደለም፡፡
የሆነ ሆኖ ዘከሪያ ትምህርት የሚገባቸው በመሆኑ በአካባቢያቸው ተወስነው ወይም እንደሌሎቹ ትምህርቱን አቋርጠው ወደ ሥራ አልተሰማሩም፡፡ ስለዚህም በወቅቱ ይደረግ እንደነበረው ከቁርዓን ቀጥሎ የሚገበዩትን ትምህርቶች ለመገብየት በደላንታ፣ በሸድሆ፣ በመቄት፣ በደብረ ታቦር፣ በጎንደር ወዳሉት ሸኾች በመሄድ የኢስላማዊ ትምህርቶችን ይከታተሉ የነበረ ሲሆን ከሚታወቁት ሸኾች መካከልም ሸኽ ዑመር የተባሉት አንዱ ናቸው፡፡
ዘከሪያ ከሌሎች ደረሳዎች ለየት ያለ ባህርይ የነበራቸው ሲሆን በተለይም የቁርዓን ትርጉምንና ዓረብኛን ሲማሩ አንዳንድ ጥያቄዎችንም ይጠይቁ ጀመር፡፡ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ቁርዓንን ካለመገንዘብና ከጥራዝ ነጠቅነት የመነጩ ሲሆኑ እነዚያን አዝማሚያዎች ግን አስተማሪዎቻቸውም ሆኑ ደረሶች አልወደዱላቸውም፡፡ እንዲያውም ከዕለታት አንድ ቀን ቁርዓንን በመንቀፍ ‹‹ለምን እንዲህ አይሆንም›› በማለታቸው ሸኻቸው ተናደው ‹‹አንተን ማን አባህ ቁርዓን ቀያሪ አደረገህ፤›› በማለት በጥፊ መትተዋቸዋል ይባላል፡፡
በወቅቱ ተማሪን መምታት ከአባታዊ ተግሳጽ እንጂ ከጥላቻ ይቆጠር እንዳልነበረ መታወስ አለበት፡፡ አንድ ልጅ ወላጆቹ በሌሉበት አጥፊ ሆኖ ከተገኘ ‹‹ለምን አትመታውም፣ ለምን አትቆነጥጠውም፤ ላንተስ ልጅህ አይደል›› ይባል እንደነበር ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይም ሆኖ ሸኽ ዑመር ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ነገላ መጥተው የዘከሪያ ቤተሰቦች ጋር በተገናኙ ጊዜ የምቾት ኑሮውን ትቶ ለትምህርት የመጣ ልጅ መሆኑን መገንዘባቸውና ከአባታቸውም የበለጠ አደራ በመቀበላቸው ከዚያ በኋላ ሊረዱት መሞከራቸው አልቀረም፡፡
እንዲህ እያሉ የከፍተኛ እስልምና ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ዳና አቀኑ፡፡ በእርሳቸው ዘመን የዳና ሸኽ የነበሩት ዳንዩል አወል (ሸኽ አህመድ አደም 1821-1892) ሲሆኑ እርሳቸውም ዘንድ ኪታብ መቅራት ጀምረው ነበር፡፡ ዳናም ሄደው ንቁ ደረሳ ለመሆን ጥረት ያደርጉ የነበሩ ሲሆን ዳሩ ግን የሚጠይቁት ያልተለመደ ጥያቄ በተለይም ከደረሶች ጋር ይፈጥሩት የነበረው አተካራ ግጭት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ሸኻቸው የሁሉም ደረሶቻቸው ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ስለነበረባቸው በዘካሪያ ባህሪይ ባይደሰቱም ደረሶቻቸው ጥቃት እንዳይፈጽሙባቸው ይመለከቱ ነበር፡፡
ዘከሪያ በእኒያ ታላቅ ዓሊም እየተማሩና ጥበቃ እየተደረገላቸውም ሞገደኛነታቸው ሊገታ አልቻለም፡፡ ትዕቢታቸውና ማን ነክቶኝ ባይነታቸው እንብዛም ባይገድም ቁርዓንን እንደሚያስተምሯቸው ሳይሆን እንደተረዳቸው የመናገራቸውና የመከራከራቸው ጉዳይ ግን ሥር እየሰደደ መጣ፡፡ ለደረሶች ጓደኞቻቸው የነበራቸው ንቀት ወደ ሌሎች አደገ፡፡ ስለዚህ ደረሶች ሊቋቋሙት ከማይችሉት ደረጃ ደረሱ፡፡ በዚህም መሠረት በምስጢር ሊገድሏቸው አሰቡ፡፡ ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት መረጃ ያገኙት ዘከሪያ ስለዚህም ከዳና ተነስተው በላስታ በኩል ወደ ነገላ አፈተለኩ፡፡
ደረሶችም ይህን እንደሰሙ ወደ ሸኻቸው ሄደው ‹‹ዓውፍ ይበሉን ይህን ሙናፊቅ አገር ከማጥፋቱ በፊት ተከታትለን ልንገድለው ነው›› ሲሉ ፈቃዳቸውን ጠየቁ፡፡ ሸኻቸውም ‹‹አላህ የቀደረው አይቀርም፣ ነገር ግን የጁንና ላስታን የሚለየውን ወንዝ ከተሻገረ እንዳትነኩት›› በማለት አሰናበቷቸው፡፡ ደረሶቹ እግር በእግር ተከታትለው ቢሄዱም ዘከሪያን ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ ወንዙን ተሻግረዋልና ተመለሱ፡፡ እዚህ ላይ መስተዋል ያለበት ትልቅ ቁም ነገር ምንም እንኳን የዳና ደረሶች ‹‹ሙናፊቅ›› እንጂ ሌላ እንዳልሆኑ ቢገልጹም ዘከሪያ ግን ራሳቸውን ትክክለኛ ሌሎችን ደግሞ የተሳሳቱ፣ የሚቃወሟቸውም ስለሚበልጧቸውና በምቀኝነት ተነሳስተው እንደሆነ ያምኑ የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡
ይልቁንም ከእርሳቸው በዕውቀት ያነሱ ሰዎች ጋር ሲገናኙ የአዋቂዎች አዋቂ መስለው ስለሚታዩ ክብርና ተቀባይነትን ማግኘታቸው አልቀረም፡፡ ስለዚህም ወደ ትውልድ ቦታቸው ጋይንት እንደገቡ ነገላ ልዩ ስሙ እስላም አምባ በተባለ መንደር ልጆችን ማቅራት፣ በአካባቢው ከነበሩት ሸኾችም የተሻለ ግንዛቤ ስለነበራቸው ማሰገድና ኅብረተሰቡን ማስተማር ጀመሩ፡፡
ዘመኑ ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ በትረ ሥልጣኑን ከትንሹ ራስ ዓሊ ለመንጠቅ የሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የነበረ ሲሆን፣ በመጀመሪያ የሙስሊም ሊቃውንት ድጋፍን ለማግኘት ጥረት አድርገው እንደነበርና የጎንደር ሙስሊም ሊቃውንትም እንደተቀበሏቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም በትረ ሥልጣኑን ከያዙ በኋላ ‹‹ኢትዮጵያን አንድ አድርገህ ለመግዛት ከፈለግህ በአንድ ሃይማኖት፣ ማለትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጽና›› የሚል ምክር ከአባ ሰላማ (የወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ) በማግኘታቸው ይህም በ1847 ደብረ ታቦር በተደረገው የሃይማኖት ጉባኤ ስለተወሰነ ወደ ሥልጣን እንዲወጡ የረዷቸውን ሙስሊሞች ክርስቲያን እንዲሆኑ ግፊት ማድረግ ጀመሩ፡፡
በተለይም ከጎንደር የሃይማኖት አባቶች ጋር የነበራቸው ግጭት ተካረረ፡፡ እሺ ያለውን በሰላም፣ እምቢ ያለውን በማስገደድ ክርስቲያን አደረጉ፡፡ የሸፈተውን አሳዶ በመግደል መንግሥታቸውን ለመምራት ሞከሩ፡፡ ሆኖም አስገዳጅነቱ ወደ ነገላ ስላልገባ፣ ይልቁንም በትውልዳቸው ባላባት የሆኑት የእናታቸው ወገኖች ‹‹እኛ አባብለን ክርስትና እንዲቀበል እናደርጋለን፣ እርሱ እንደሌሎች አይደለም ክርሰቲያን ወገኖቹን ይወዳል›› እያሉ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋ ያማልዷቸው ስለነበረ ዘከሪያ ምንም አልሆኑም ነበር፡፡
የአፄ ቴዎድሮስ ዘመን አብቅቶ ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ቀጥሎ የአፄ ዮሐንስ ዘመን ሲተካ ዘከሪያ በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኙ የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ ወልይ ነኝ ባይ ስለነበሩ ብዙ ያልተማሩ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች ባለሙያዎች እየመጡ ከበሽታ እንዲፈውሷቸው፣ ሀብት እንዲሰጧቸው፣ ከጠላት እንዲጠብቋቸው፣ ዕድላቸውን እንዲነግሯቸው፣… ይጠይቁ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዝናቸውም በአካባቢው ሳይወሰን ወደ በለሳ፣ ሰቆጣ፣ ቡግና፣ ላስታ፣ ሸደሆ፣ መቄት ገብቷል፡፡
እንግዲህ እኝህ ሰው በእስልምና የጠለቀ ዕውቀት እንዳልነበራቸው የሕይወት ታሪካቸውን ከጻፉ ሰዎች ሥራዎች መረዳት የሚቻል ቢሆንም በወቅቱ ከስመ ገናናዎቹ «ወልይ ነን» ባዮች መካከል አንዱ የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ ደጃች በዝብዝ ካሣ ምርጫ አፄ ዮሐንስ ተብለው ከነገሡ በኋላ አፄ ቴዎድሮስ የተከተሉትን አንድ አገርና አንድ ሃይማኖት የመገንባት ፍላጎት አጠናክረው ስለቀጠሉበት፤ ሙስሊም የማድረግ ዘመቻውም ከማስገደድም አልፎ በብዛት መግደል ስለተጨመረበት በየቦታው ሙስሊም የሃይማኖት አባቶች በሚቻላቸው አቅም ሁሉ መዋጋት ጀመሩ፡፡ ይህ በትግራይ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በሸዋ የታየ ተጋድሎ የአፄ ዮሐንስን ግድያ አባሰው እንጅ አልቀነሰውም፡፡
ይልቁንም ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ ደብረ ታቦር በመጡበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ከየአካባቢያቸው በአዋጅ ተጠርተው እንዲመጡና በአንድ ላይ እንዲጠመቁ አደረጉ፡፡ በዚህ ጊዜ ይመጣሉ ተብለው የተጠበቁት ዘከሪያ አልሄዱም፡፡ ስለዚህም የአካባቢው ሰው በሰላምና በሽምግልና ቢነገሩ ይሻላል ስለተባለ ብላታ ኪዳነ ማርያም የተባሉ ባላባትና ነጭለባሽ ተላኩባቸው፡፡ ብላታ ኪዳነ ማርያምም ንጉሠ ነገሥቱ ደብረ ታቦር እንደመጡና ክርስትናን ተቀብለው እንዲያስተምሩ እንደፈለጉ ነገሯቸው፡፡ ዘካርያ ጥሪውን ባለመቀበላቸው ብላታ ኪዳነ ማርያም አስገድደው እንዲያመጧቸው ትዕዛዝ ተሰጡ፡፡ በዚህም ምክንያት ጦርነት ገጠሙና ዘከሪያ አሸነፉ፡፡ ይልቁንም የንጉሠ ነገሥቱን መልዕክተኛ በማሸነፋቸው ከፈጣሪ የተሰጣቸው ልዩ ኃይል እንደነበራቸው ተደርጎ ተወራ፡፡ ሌሎች ሙስሊሞችም ጥላ ከለላቸውን ለመፈለግ መጡ፡፡
የንጉሡ መልዕክተኞች መጥተው እጃቸውን በሰላም ሰጥተው እንዲኖሩ ጥሪም ቢቀርብላቸውም ንጉሠ ነገሥቱ የማስገደድ ተግባራቸውን እስካላቆሙ ድረስ አሻፈረኝ ብለው ጦራቸውን ይዘው በተከዜ በረሃዎች ሸፈቱ፡፡ መኖሪያቸውን አይና ቡግና በተለይም ጣርና ተብሎ በሚታወቀው ወጣ ገባ የበዛበትና ለመከላከል የሚያመች ስፍራ መቀመጥ ጀመሩ፡፡
ያ አካባቢ ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም ዘመን ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው ሙስሊሞች መኖሪያ የነበረ ከመሆኑም በላይ ባለቤታቸው የወ/ሮ አስያ መከረ ዘይኑ ትውልድ ስፍራ ስለነበር የሸፈቱት በወገን መካከል ነው፡፡ ከዚያም ሆነው በበለሳ (ምሥራቅ ጎንደር) እና በደሃና (ምዕራብ ዋግ) ሸፍተው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም በወልይነታቸው የሚያውቋቸው በርካታ ተከታዮች ነበሯቸው፡፡ በተከዜ በረሃ ዙርያ በነበሩበት ጊዜም ብዙ ተዓምራትን አሳይተዋል እየተባለ ይነገርላቸዋል፡፡
አፄ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ ሥልጣን የያዙት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም በአፄ ዮሐንስ ላይ የደረሰውን ጥፋት በመመልከትና በሌላ ዘዴ ለመምራት በነበራቸው ፍላጎት «ሀገሪቱ የሙስሊምም የክርስቲያንም መሆኗንና ሕዝቡ ተቻችሎ እንዲኖር ‹‹ሀገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው›› የሚል አዋጅ ባወጁ ጊዜ ሸኽ ዘከሪያም «ኢስላምኮ ቢሆን ተቻችለህ ኑር እንጅ ወንድምህን ግደልም ሆነ በክርስቲያን አትገዛ አይልም፡፡ በቁርዓኑ ውስጥም ሙስሊም፣ ክርስቲያንና፣ አይሁድ በአንድ ፈጣሪ የሚያምኑ መሆናቸውን ያስተምራል፡፡ ማርያም በሙስሊሙ ዘንድ የተወደደችና በእጅጉ የተከበረች ናት፡፡ ክርስቶስም ቢሆን ቃል የነበረና ከድንግል ማርያም ያለ አባት የተወለደ እንዲሁም የአንድ አምላክን ትምህርት አስተምሮ ያረገ ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊሙ ከክርስቲያኑና ከአይሁድ ወንድሙ ጋር ተባብሮ መኖር ይችላል፡፡ ቁርዓኑም ይህንን ያዛል» በማለት በአደባባይ ይገልጣሉ፡፡
«ሙስሊሙና ክርስቲያኑ አንድ ነው፡፡ በአንድ አምላክ አማኝ ነው» የሚለው አመለካከት ግን በወቅቱ የተለያየ እንደሆነው ለሚያምነው ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ወዲያውኑ አልተገለጠለትም፡፡ ይልቁንም «ክርስቲያኑ ካፊር፣ ሙስሊሙን ከሀዲ» ይሉ የነበሩ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች «ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል» እንዲሉ ሙስሊምና ክርስቲያን እንዴት አንድ ይሆናል በማለት አልተቀበሉትም፡፡ በተለይም የጎንደር፣ የዋግ፣ የትግራይና የወሎ የእስልምና የሃይማኖት መሪዎች ተቃወሙት፡፡ እርሳቸውም «እንግዲያው ልክ ካልሆንኩ ቁርዓኑ ይገለጥና ይታይ» በማለት ቁርዓን ስለ አይሁዶችና ክርስቲያኖች የሚያወሳውን እየጠቀሱ ተከራከሩ፡፡ በዚህ ጊዜ በቁርዓኑ ጥልቅ ዕውቀት ያልነበረውና ትርጉሙን ጠንቅቆ የማያውቀው ሙስሊም የመከፋፈል ሁኔታም አሳየ፡፡
ሸኽ ዘከሪያ አነስተኛ ቢሆን ቁርዓኑን የመተርጎም ዕውቀት ስለነበራቸው ብቻ ሳይሆን ያውቃሉ፣ ትንቢትም ይናገራሉ ተብሎም ስለሚገመት፤ እንዲሁም በዙሪያቸው ብዙ የሚያውቁም የማያውቁም፣ ዕድላቸውን እንዲነግሯቸው የሚፈልጉም፣ ሀብት ለማግኘት ምኞት የነበራቸውም ተሰባስበው ስለነበር ዝናቸው በአካባቢው የታወቀ ነበር፡፡
ከዚህ ላይ ድቤ እየተመታ ዜማ እየተዜመ፤ ባለውቃቤው እያጎራ፤ ጠላት ያለው ጠላቱን እንዲያውቅ፤ ወይም እናውቃለን በሚሉ ሲፈጥሩለት፣ የሌለውም እንዲመረቅ የሚፈልገው ብዙ ስለነበር አድናቂያቸው በዋዛ የሚታይ አልነበረም፡፡
በዚህ ጊዜ የሸኽ ዘከሪያ አካሄድ የተገለጠላቸው የእስልምናና የክርስትና አባቶቹ ሳይሆኑ የፖለቲካ ሰዎቹ ነበር፡፡ ስለዚህም በሸኽ ዘከሪያ የተነሳውን አስተሳሰብ የደገፉ መስለው በመነሳትና እርሳቸውን ከፍ ከፍ አድርገው ወደ ቤተ መንግሥቱ በማቅረብ ከሙስሊም አባቶች ጋር ያከራክሯቸው ጀመር፡፡
በመሠረቱ፣ ዘከሪያ ክርክር በመጀመሪያ ላይ በሚያውቁት መጠን «ሙስሊምና ክርስቲያን ምንጩ አንድ ኦሪት ነው፡፡ ሁለቱም የሚያመልኩት አንድን ፈጣሪ ነው፡፡ በቁርዓን ውስጥም ስለክርስቶስ፣ ስለማርያም፣ ስለ ሙሴ፣ ስለአብርሃም፣ ስለ ኖህ፣ ስለዮሴፍ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግእዝ፣ ቁርዓን ደግሞ በዓረብኛ በመጻፉ እንጅ ሁሉም የሚሉት በአንድ ፈጣሪ እመኑ ነው፡፡ ክርስቲያኖች በአውላዶች ማመናቸውንና በታቦት መጠቀማቸውን ቢተው ልዩነቱ የጎላ ባልሆነ ነበር፤» በማለት ሁለቱም ወገኖች ተስማምተውና ተቻችለው እንዲኖሩ ሞክረው ነበር፡፡
ይሁን እንጅ እስልምናን ከእርሳቸው በተሻለ ሁኔታ የሚረዱ ሰዎች እርሳቸው የሰጡትን ትርጉም አንድ በአንድ በማሳየት «አንድ ነው» ከሚለው ይልቅ ልዩነቱን በማጎላት ከማቅረባቸውም በላይ «ሃይማኖታችንን በርዘዋል» በሚል አጥብቀው ተቃወሟቸው፡፡ የውስጥ ለውስጥ ፉክቻውም ወደ አደባባይ ደረሰና ሁለቱም ጎራ ለይተው መከራከር ጀመሩ፡፡
በመሠረቱ፣ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ዘከሪያ ለዚህ ሁሉ የበቁት ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ በዘመናቸው ለንግድ ወደ አሥመራ ይሄዱ የነበሩ ዘመዶቻቸው፣ ስዊድናውያን ቁርዓንን በመጀመሪያ ወደ ስዊዲንኛ ከዚያም ወደ ዓረብኛ ለራሳቸው እንዲያመች አድርገው የተረጎሙትን ማለትም በ‹‹ቁርዓን›› ህዳግ ላይ ማብራሪያ ወይም ትንታኔ (ተፍሲር) የሰጡበትን መጽሐፍ አግኝተው ነበር ይባላል፡፡ ይህም የቁርዓን ህዳግ ትንታኔ ሙስሊም ሊቃውንት ከሰጡት ትንታኔ በእጅጉ የሚለያይና የሚቃረን ነበር፡፡ ስለሆነም ዘከሪያ ስዊድኖች ትንታኔ የሰጡበትን (የፈሰሩትን) አጥንተው ‹‹እስልምናና ክርስትና ተቀራራቢ ነው›› ከሚል አስተሳሰብ ተነስተው ‹‹ተመሳሳይ ነው›› ወደሚል ተሸጋገሩ፡፡ ይህም መጽሐፍ ምስጢሩን በማያውቁት ዘንድ በእጅጉ አደናጋሪ ሁኔታ ፈጥሮ ነበር፡፡ ይልቁንም በትክክለኛው ቁርአን ላይ ትርጉም ያላቸውን ኪታቦች እያዳቀሉ ይጠቀሙ ስለነበር የአዋቂዎች አዋቂ መምሰላቸው አልቀረም፡፡ አንዳንድ ሰዎችም በዚህ ረገድ የአለቃ እምባቆም አስተምህሮት አራማጅ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
አለቃ እምባቆም ዓረብኛ ተናጋሪ፣ የየመን ይሁዲ ሲሆኑ እርሳቸውም የቁርዓንን አንቀጾች ሙስሊሞች በማይቀበሉት ሁኔታ የተረጎሙ በዚህም ምክንያት ከሀገራቸው የተሰደዱና ደብረ ሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ መነኩሴ ናቸው፡፡ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አልቓዚ ይህንን ያውቁ ስለነበር ሲያሳድዷቸው ነበር፡፡ ‹‹የአባታቸው ገዳይ ለመበቀል ሲሉ አብያተ ክርስቲያናትን ያቃጥሉ ነበር›› የሚባለውም በከፊል ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህን በሚመለከት ኢማም አሕመድ ኢብራሂም፣ የሀረር አሚሮችና በሌሎችም መጻሕፍቴ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ እንደሚለው ደግሞ በእናታቸው ይሁዲ እንኳን ቢሆኑ በአባታቸው ሙስሊም ነበሩ፡፡ እምነታቸውን ወደ ክርስትና ከመለወጣቸው በፊትም አቡልል ፈትሕ ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ እሳቸውም እንዳ ዘከሪያ በወጣትነት ዕድሜያቸው ከአስተማሪዎቻቸው ጋር በአንዳንድ የቁርአን አንቀጾች ይከራከሩ የነበሩ ሲሆን ይህንን አመለካከታቸውንም ‹‹አንቀጸ አሚን›› ተብሎ በሚጠራው መጽሐፋቸው አስቀምጠውታል፡፡ ስለሆነም አለቃ ዘከሪያ የተነሱት የአለቃ ዕምባቆምን የመከራከሪያ ሐሳብ ይዘው ነው የሚሉ አሉ፡፡
ስለሆነም ሙስሊም ሊቃውንት አለቃ ዘከሪያ በቁርዓን ትርጉም ላይ ያላቸው ግንዛቤ ትክክል እንዳልሆነ ሲነገሯቸውና በክርክሩ መዝለቅ እንደማይችሉ ሲገነዘቡ «እኔ የምናገረውን እንዳስተምር ፈጣሪ ተገልጦልኛልና ያልኩትን ብል፣ ፈጣሪ የገለጠልኝንም ባስተምር ምን አገባችሁ፡፡» ስለሚሉና በየእርከኑ የነበሩ የወሎ፣ የትግራይ፣ እና የጎንደር የመንግሥት ባለስልጣኖች ሐሳባቸውን ስለደገፉ እንደረቱ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡
ዘከሪያ፣ በወቅቱ ያነሷቸው ከነበሩት መካከል «አሊፍ፣ ላም፣ ሚም» የሚለውን «አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ከመተርጎማቸውም በላይ «ቢስሚላሂ፣ ረሕማን፣ ረሒም» የሚለውንም «አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስን ለመጥቀስ ካልሆነ በስተቀር ለምን ቢስሚላሂ ብሎ አይተወውም ነበር» የሚል የራሳቸውን ትርጉም መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቁርዓን ውስጥ «እኛ» በሚል ፈጣሪ ራሱን በሚገልጥበት ጊዜ የተጠቀመበትን ቃል በቀጥታ በብዙ ቁጥር በመውሰድ «እኛ የሚለው ከማን ጋር ሆኖ ነው? ከአብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በስተቀር!» በማለት መከራከር ጀመሩ፡፡ ይህም የክርስቲያን ደጋፊዎቻቸውን የለበጣ አድናቆት ጭምር አተረፈላቸው፡፡
ያም ሆነ ይህ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መልክ እየተሰጠው ስለሄደ ክርክሩም እስከ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሸንጎ ደረሰ፡፡ ብልሁ ዳግማዊ አፄ ምኒልክም «እንኳን ግደል ብለው ልከው ሰደውት እወገብ ላይ ሆኖ ያበራል ጥይት» እንዲሉ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ የሚከፋፍልላቸው ሲያገኙ ከዚህም በተጨማሪ ከዘከሪያ ጋር ለክርክር የቀረቡትን ታዋቂ የኢትዮጵያውያን ሙስሊም አዋቂችን (ዓሊሞችን) «ሐሳባችሁን በመልካም ሁኔታ ገልጻችኋል፡፡ እንዲህ ያለ ችሎታ ያለው ወገን በመኖሩ ደስታችን ከፍተኛ ነው፡፡ በእውነቱ ዕውቀታችሁንም እናደንቃለን፡፡ ለመንግሥታችን ጽናት የናንተን እርዳታ እንሻለን፡፡ በያላችሁበት ሁሉ በጸሎታችሁ አትርሱን በሚል ዓይነት ለተከራካሮቹ ሙስሊም ሸኾች ካባ ሸልመው፣ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትም ስንቅና ገንዘብ ሰጥተው፣ «ደስም አሰኝተው» በአንድ በር ሲሸኙ በሌላ በኩል ደግሞ «እንዲህ ነው እንጅ ዕውቀት፣ እንደ አንተ ያለ ትልቅ ሰው ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እምነትህን ያለ አንዳች ተጽእኖ እንድታራምድ አዋጅ እናወጣልሃለን፡፡ ተጨማሪ አሽከር እንሰጥሃለን፡፡ የምታሳርሰው ሰፊ ሁዳድም ከግብር ነፃ አድርገን እንሰጥሃለን፡፡ አንተ ብቻ በርታልን፡፡ በጸሎትህም አትርሳን፡፡» በሚል ዘከሪያ በሌላ በር ይሸኟቸዋል፡፡
እንዲህም ተደረገና ዘከሪያ ውስጥ ለውስጥ ብቻ ሳይሆን በግልጽ የመንግሥት ድጋፍ ማግኘት ጀመሩ፡፡ «ጠላቶቻቸው እንዳይገድሏቸው በሚል 100 የጦር መሣሪያ የታጠቀ አጃቢ» ተሰጣቸው፡፡ ይህም ከነበራቸው 32 የቤተሰብ አጃቢ ጋር ሲደመር 132 ሆነላቸው፡፡ እምነታቸውን ያለ አንዳች ተጽእኖ እንዲያራምዱም አዋጅ ወጣላቸው፡፡ ቤተ መንግሥቱ ዘንድም ብድግ ብለው የሚቀበሏቸው ሆኑ፡፡
ዘከሪያም በእስልምና ላይ ጥልቅ ዕውቀት ባይኖራቸውም እንዳላቸው ተቆጥረው በብዙ ጭፍን አማኞች ዘንድ ወደር የሌላቸው አዋቂ ሆኑ፡፡ የመንግሥት ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ፣ ‹‹ፈጣሪ በኸልዋ በተገለልኩበት ጊዜ ተገልጦልኛል›› ብለው ከትንቢት ተናጋሪ ጋር መቆጠራቸው ጋር ተደምሮ የትልቆች ትልቅ አሰኛቸው፡፡ እናም ራሳቸው «ከፊል ኢስልምና፣ ከፊል ክርስትና» ሲያራምዱ ከቆዩ በኋላ እስከ ሃያ ሺሕ የሚደርስ ሙስሊም ወደ ክርስትና አስገብተዋል፡፡ በኋላም ክርስትናን ተቀብለው አለቃ ነዋየ ክርስቶስ ተብለዋል፡፡
እርግጥ ነው የአለቃ ነዋየ ክርስቶስ አመለካከት ከኦርቶዶክስ ክርስትናም የማይጣጣም አንዳንዱም በጣም ተቃራኒ ነበር፡፡ ለምሳሌ በአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ እንጅ በማርያም ሆነ በሌሎች «አውላድ» በሚሏቸው አያምኑም፡፡ መስቀል አይሳለሙም፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የታቦትን ህልውና ይቃወማሉ:፡ ለመሞት እስኪቃሩ ድረስም የመካን እቅጣጫ አይከተሉ እንጅ ይሰግዱ ነበር፡፡ ይጾሙ ነበር፡፡ ሲያሰኛቸውም በአሽከሮቻቸው ታጅበው መስጊድ ገብተው ይሰግዱ ነበር፡፡ ቢሆንም የእስልምና ጎራን «በሰላማዊ መንገድ ኢስላምን ያፈራረሱ ቅዱስ ሰው» አድርገው የሚያቀርቧቸው ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ሚሲዮናውያን ተከታዮች በተለይም በዝርያቻቸው ዛሬም ከፍተኛ ስፍራ አላቸው፡፡ በዚህ ሰው ዙሪያ የሚነሱ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች ቢኖሩም ወደፊት በሰፊው ለመዳሰስ ይቻል ዘንድ ለጊዜው እንቆየው፡፡
ይህ ጽሑፍ የተጠናቀረው በቀጥታ የልጅ ልጃቸው ተሾመ ወርቁን፣ የሰቆጣ ታላላቅ ሰዎችን፣ ታሪኩን የሚያውቁ የዓፋር፣ የተምቤን፣ የግጀት፣ የጸሐፊው ቤተሰብ አባላትን በተለይም በዘከሪያ የተጠመቁ ታላላቅ ሰዎች የልጅ ልጆችን፣ የዶላንድ ክረሚ (“Shaikh Zäkaryas: an Ethiopian Prophet”, Journal of Ethiopian Studies, 10, no. 1 (January 1992), 55-66; J ጆናስ ኢወርሰን (Jonas Iwarsson, “A Moslem Mass Movement Towards Christianity,” Moslem World, Vol. XIV, 1924, pp. 286-289.)፣ የቶማስ ላምቤ (A Doctor without a Country (New York, 1939), p.277. )ጥሩነህ ወልደሥላሴ (Adventisism in Ethiopia 2005), ጥሩነህ ወልደስላሴ፣ ሸህ ዘከሪያ (አለቃ ነዋየ ክርስቶስ) ከእስልምና ወደ ክርስትና፣ ቄስ ብርሃኑ ንጉሤ ‹‹ኢትዮጵያዊው ነብይ ሸህ ዘከሪያ 1837-1912›› የተጻፈውን መሠረት በማድረግ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ቀደም ሲልም ለመጥቀስ እንደተሞከረው እንደዚህ ያለው ሁኔታ የተከሰተው በአገራችን ብቻ አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በናይጀሪያ ክሪስቶ-ኢስላም ተመሥርቶ ነበር፡፡ በአውሮፓም ጉረጄፍ (Gurdjieff 1872–1949) የተባለ የክርስትና እምነት ተከታይ የሱፊዝምን ሥርዓት ተቀብሎ ነበር፡፡ ይህ ሰው በኢትዮጵያና በግብፅ ለሦስት ወራት ያህል የቆየ ሲሆን፣ በተለይም ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ አገሩ እንደሚቆጥራትና ጡረታ ሲወጣ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ቀሪ የሕይወት ዘመኑን እንደሚያሳልፍ በማስታወሻው ላይ አስፍሯል፡፡ ከዚህ ሰው ጋር ያሳለፉ ሱፊ አባቶች እንደራሳቸው አድርገው ይቆጥሩት እንደነበር ይታወቃል:፡ አለቃ ዘከሪያ በሙስሊሙ መካከል ሆነው ብዙ ሰዎችን ወደ ክርስቲያን እንደሳቡ ሁሉ ጉረጂፍም በክርስትና ዓለም ሆኖ የሱፊዝምን ታላቅነት ያወቀ ሰው ነበር፡፡ ሆኖም በኑዛዜው መሠረት የተቀበረው በሩሲያ ሥርዓተ ቀብር ደንብ መሠረት ነው፡፡ ነገሮች ምን ያህል ተቀራራቢና ዓለም አቀፍ ይዘት እንደነበራቸውም በዚህ አጋጣሚ በጨረፍታ መመልከት ተገቢ ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ በመጠኑ ተሻሻለ እንጅ ‹‹ዓይን አብራዎቹ›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካበቃሁት መጽሐፍ፣ 2011፡ 177-188 የተወሰደ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡