Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሕጋዊነት እስከምን?

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሕጋዊነት እስከምን?

ቀን:

በኢትዮጵያ ትክክለኛ ፈቃድ ሳይኖራቸው ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተምሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በተደረገ የማጣራት ሥራ ተረጋግጧል፡፡

በተለይ የውጭ አገር የትምህርት ደረጃን ጠብቀው በአገር ውስጥ የተቀመጠውን መሥፈርት ያላሟላ አሠራርን የሚከተሉ ተቋማት በርካታ እንደሆኑም ሲነገር ቆይቷል፡፡

በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች አንድም ሕጋዊነታቸውን ሳያረጋግጡ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ዕውቀውና ፈልገው እንደሆነ በማጣራት ወቅት የተገኘ መሆኑን የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል፡፡ ባለሥልጣኑ እንደዚህ ዓይነት አሠራሮች እንዲቀረፉ ተማሪዎች በተደጋጋሚ መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ሥራ እየሠራ፣ ቢሆንም ዛሬም ችግሩ አልተፈታም፡፡

የባለሥልጣኑ የኢንስፔክሽንና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቸሩጌታ ገነነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕገወጥ አሠራርን ሲከተሉ በተገኙ የዓለም አቀፍና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው ነው፡፡

 በፌዴራል ደረጃ የሚቋቋሙ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ፈቃድ የሚያገኙትም ሆነ ቁጥጥር የሚደረግባቸው በባለሥልጣኑ በኩል እንደሆነ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በ2014 ዓ.ም. ከ600 በላይ ተቋማት ላይ ፍተሻ ተደርጎ፣ 240 የሚሆኑ ተቋማት አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ ውሳኔ መተላለፉን አስረድተዋል፡፡

ማስተካከያ እንዲያደርጉ ከተወሰነባቸው ተቋማት ውስጥ በ132 ፍተሻ መደረጉን፣ ከእነዚህ ውስጥም 68 ተቋማት ድጋሚ ዕርምጃ ሊወስድባቸው መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. በ192 ተቋማት ላይ ፍተሻ ተደርጎ 12 ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳይሰጡ ዕርምጃ መውሰዱንም አቶ ቸሩጌታ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ አብዛኛዎቹ ተቋማት ሕገወጥ አሠራርን የሚከተሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መሥፈርት ካላሟላ አሠራር እንዲወጡ ማኅበረሰቡም ጭምር የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በባለሥልጣኑ ዕርምጃ ሲወስድ ተቋማቱ ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረግም በተጨማሪ በፍትሐ ብሔርም ሆነ በወንጀል ሕግ እንዲቀጡ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ዕርምጃ ሲወስድ የተለያየ አሠራር እንዳለው፣ በተለይም በተቋሙም ሆነ በተማሪዎች ላይ ችግሩ ሲታይ ተማሪውንም ተቋሙንም እስከ መጨረሻው ድረስ አገልግሎት እንዳያገኙ እንደሚደረግም አክለዋል፡፡

 አንድ ተቋም ፈቃድ በሌለው ፕሮግራም ወይም የትምህርት ዓይነት መዝግቦ ሲያስተምር ከተገኘ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ፈቃድ እንዳይጠይቅና የሚያስተምራቸውንም ተማሪዎች እንዲበትን የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ፈቃድ ባላቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲያስተምሩ ቆይተው በመሀል ሌላ ሕገወጥ አሠራር ቢከተሉ በዛ ተቋም ሥር የሚማሩ ተማሪዎች ወደ ሌላ ተቋማት ሄደው መማር እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ተቋማትም ሆኑ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ሕገወጥ አሠራርን ተከትለው እንደሚጓዙ ገልጸው፣ በተለይ ተማሪዎች የሚማሩበት ተቋም ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥና ልፋታቸው መና ሆኖ እንዳይቀር መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

አብዛኛው ተማሪ ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ ሊዘዋወር ሲል (ደረጃ አራት) የብቃት ማረጋገጫ ፈተና (ሲኦሲ) ወስዶ መቀላቀል እንዳለበት፣ ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የማናለብኝ ስሜት ውስጥ ገብተው ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑም አገልግሎቱን ለሚሰጡ ተቋማት ፈቃድ ሲሰጥ ፈቃድ የተሰጣቸው ተቋማት ከተፈቀደላቸው ፕሮግራም ውጭ በማስፋፋት ሕገወጥ አሠራርን የሚከተሉ በመሆኑ ተማሪዎች እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ አሠራሮችን ወደ ጎን በመተው ፈቃድ በተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች ብቻ መማር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ለሚገቡባቸው ተቋማት ሕጋዊነትና በተፈቀዱ ፕሮግራሞች ዙሪያ ከባለሥልጣኑ መረጃ ማግኘት እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...