Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የትምህርት ተቋማት ሰፋፊ ቦታዎችና ቤተ ሙከራዎች ለሥራ ፈጣሪዎች ክፍት እንዲሆኑ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሰፋፊ ቦታዎች፣  ቤተ ሙከራዎችና በውስጣቸው የሚገኙ ትልልቅ ማሽኖች ለሥራ ፈጣሪዎች ክፍት እንዲሆኑ ጥያቄ ቀረበ፡፡

ጥያቄው የቀረበው አዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ለጀማሪና በሥራ ላይ ላሉ የሥራ ፈጣሪዎች ሥልጠናዎችን የመስጠት፣ የገበያ ትስስር የመፍጠር፣ እንዲሁም የፋይናንስ ችግራቸውን በተወሰነ ደረጃ የመቅረፍ ዓላማ ሰንቆ ወደ ሥራ ያስገባውን የቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከል ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ በተደረገ የፓናል ውይይት ላይ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሁሴን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ከሚገጥሟቸው  ችግሮች መካከል የመሥሪያ ቦታ ዕጦት አንደኛው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 1,800 ያህል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች በሰፋፊ መሬቶች ላይ የተገነቡ መሆናቸውንና ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ወጣቶች የሚፈልጓቸው ትልልቅ ማሽኖች ያለ ሥራ ተሸፍነው እንደሚገኙ በመጥቀስ ተቋማቱ በተለይ ለሥራ ፈጣሪዎች ክፍት የሚሆኑበት ሁኔታ መታሰብ አለበት ብለዋል፡፡፡

በተለይ ከሥራ ፈጣሪዎች ማብቂያ ማዕከል (Incubation Centers) ጋር በተገናኘ የሚደረጉ ሥራዎችን መሀል ከተማ ማዕከል አድርጎ ከመሥራት በተጨማሪ፣ ወደ ክልሎች ወጣ ብሎ ሊሠራ እንደሚገባ ሐሰን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

 የንግድ ምክር ቤቱ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ ሥራ አጥነት በኢትዮጵያ ቁልፍና ቅድሚያ የሚሰጠው የማክሮ ኢኮኖሚ አጀንዳ እንደሆነ፣ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ያህል አዳዲስ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ሥራ ገበያው እንደሚቀላቀሉ ተናግረዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሥራ ፈጠራ ጋር በተገናኘ ያለውን ክፍተት በማጥናት ብሔራዊ የድርጊት ዕቅድ በማዘጋጀት በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ያህል ሥራዎች በመፍጠር፣ እ.ኤ.አ. በ2030 ሰላሳ ሚሊዮን ዘላቂ ሥራዎች ይፈጠራሉ ብሎ ዕቅድ መያዙን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመት በመንግሥት የታቀደው የሥራ ዕድልና ቅጥር 3.7 ሚሊዮን እንደሆነ ተጠቅሶ፣ ከዚህም ውስጥ ሰባ በመቶ የሚሆነው ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም ይሆናል ተብሎ መታቀዱ ተጠቅሷል፡፡

አቶ ንጉሡ እንደገለጹት፣ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ የሚገኙ ጀማሪ የሥራ ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች የሚከስሙበት ሒደት ሰፊ ነው፡፡ የመክሰም ዕድል እንዲበራከት ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ የክህሎት ክፍተት፣ የገንዘብ ዕጦት፣ የተቋማት የአቅም ግንባታ ዕጥረት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ አቅም አለመዳበር፣ በተጨማሪም በቂ የቴክኒክ ዕውቀት አለመኖርና የሥራ ዕድል ፈጠራ ግንዛቤ ከገንዘብ አጠቃቀም ጋር ተዳምሮ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የኢንተርፕሬነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ አዳዲስ ቢዝነሶችን ለመጀመር ሦስት ዋነኛ ማነቆዎች አሉ፡፡

የመጀመርያው ቢዝነሱን ለማስጀመር የሚያስችል ከባቢ አለመኖር ነው፡፡ ይህም ንግድ ፈቃድ ከማውጣት፣ ታክስ ከመክፈል፣ ወዘተ ጋር የሚያያዝ መሆኑን፣ በተለይም ትልቁን የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ኢንተርፕራይዞች በመንግሥት በጣም ጫና ስለሚደረግባቸው ወይም ምቹ ከባቢ ስለማይፈጠርላቸው በተፈለገው ልክ ወደፊት አይመጡም ብለዋል፡፡ ስለሆነም በመንግሥትና በግለሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር የሁሉም ርብርብ አስፈላጊ ነው፡፡

ሁለተኛው ማነቆ ከአስተሳሰብ (Mindset) ወይም ከተወዳዳሪነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብዙዎቹ ኢንተርፕራይዞች እንጀራ ለመብላት ወይም ለመኖር እንጂ፣ ትልቅ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታትና አሻራቸውን ለማስቀመጥ የሚንቀሳቀሱ እንዳልሆኑ ሐሰን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ የአገሪቱ የትምህርትና የሥልጠና ሥርዓት በጣም ኋላቀር በመሆኑ፣ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ውስጥ ባላቸው ቆይታ ቢዝነስ ለመጀመርና ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ክህሎት ሳያገኙ ይቀራሉ ብለዋል፡፡

ሦስተኛው የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ከማስያዣ (ኮላተራል) ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከትልልቅ ተቋማት በስተቀር አዳዲስና ትንንሽ ተቋማት ፋይናንስ ለማግኘት የሚያስችል ሀብት ባለቤት አለመሆን ትልቁ ተግዳሮት ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ያቋቋመው የቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከል ፕሮጀክት ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ይፋ ሲደረግ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ የተለያዩ መሥፈርቶችን በማዘጋጀት ወጣቶችን ወደ ቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከል በማስገባት የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስደው የሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በማሰብ ዕድሉን ማመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡

ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበለት ፕሮጀክት ለአራት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረግ፣ 500 ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች