Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናለቀጣይ ዓመት የበጀት ዝግጅት የዕቅድ ምክክር ተጀመረ

ለቀጣይ ዓመት የበጀት ዝግጅት የዕቅድ ምክክር ተጀመረ

ቀን:

  • እያለቀ ላለው በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት አልተጠየቀም
  • የዴሞክራሲ ተቋማት የበጀት ዕቅዳቸውን ለፓርላማው እያቀረቡ ነው

ለመጪው 2016 በጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ ዝግጅት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር የበጀት ስሚ መርሐ ግብር ማካሄድ ጀመረ፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ከተለያዩ ሚኒስቴሮች ኃላፊዎች ጋር ለቀጣዩ ዓመት የበጀት ዕቅዳቸው ላይ ውይይት መጀመሩን፣ ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡

በበጀት ስሚ መርሐ ግብሩ የመጀመሪያ ቀን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ፣ የሦስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችንና በሥራቸው ያሉ ተጠሪ ተቋማትን የቀጣይ ዓመት የበጀት ዝግጅቶች ተቀብሎ መወያየቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና ሚኒስትር ደኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በመሩት በዚህ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የሚኒስቴሮቹ የመሥሪያ ቤታቸውን በጀት ‹‹በተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ መሠረት›› ማቀድ እንዳለባቸው ተገልጾላቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም መሥሪያ ቤቶቹ ‹‹በሒደት ላይ ያሉ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ›› ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ማሳሰቢያ መሰጠቱን ሚኒስቴሩ ያወጣው መረጃ ይጠቅሳል፡፡

- Advertisement -

በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ስሚ መርሐ ግብር ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይን ጨምሮ የሦስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋሞቻቸውን ኃላፊዎች ስለበጀት ዕቅዶቻቸው ተነጋግረዋል፡፡ መሥሪያ ቤቶች ‹‹የአገሪቱን ሀብትና የመንግሥትን በጀት በዕቅድ ለተያዘላቸው ዓላማ ብቻ በቁጠባ›› እንዲጠቀሙ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች አቅጣጫ እንደተቀመጠላቸው ሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ መረዳት ተችሏል፡፡

መንግሥት ለ2015 በጀት ዓመት ከ786 ቢሊዮን ብር በላይ አፅድቆ ዓመቱን እየገፉ ሲሆን፣ ዓመቱ ሲጀመር አፅድቆት በነበረው በጀት ብቻ ያለ ተጨማሪ በጀት እየሠራ ነው፡፡ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ቢቀርም፣ እስካሁን ድረስ ግን የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተጨማሪ በጀት እንዲያፀድቅለት ጥያቄ አለማቅረቡን፣ ሪፖርተር ከተወካዮች ምክር ቤት ለመረዳት ችሏል፡፡

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካሁን ለምክር ቤቱ የቀረበ የተጨማሪ በጀት ጥያቄ የለም፡፡

ባለፉት ዓመታት በነበረው አሠራር መሠረት መንግሥት የተጨማሪ በጀት ጥያቄ በዓመቱ አጋማሽ ወይም መጨረሻ አካባቢ ያቀርባል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ጫና ምክንያት መንግሥት ባለፈው ዓመት አጋማሽ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀድቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ፀድቆ ከነበረው 562 ቢሊዮን ብር በጀት ከ20 በመቶ በላይ ነበር፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጥታ ተጠሪ የሆኑ እንደ ምርጫ ቦርድ ዓይነት የዴሞክራሲ ተቋማትን፣ እንዲሁም ራሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀጣይ ዓመት የበጀት ዕቅዳቸውን ለምክር ቤቱ የማቅረብ ሒደት መጀመሩን አቶ ደሳለኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ተቋማት የበጀት ፍላጎታቸውን እየላኩ ሲሆን፣ እኛም ወደ ንዑሳን ኮሚቴዎች መርተን በዝርዝር እያየን ነው፤›› ሲሉ አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

የአስፈጻሚ አካላትን የበጀት ዕቅድ በገንዘብ ሚኒስቴር አማካይነት ተሰብስቦ ከተጠናቀቀና ከተዘጋጀ በኋላ፣ ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር አብሮ በተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ብለዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም መጨረሻ ላይ በአንድ ላይ እያየን በእኛ ዕይታ መስተካከል ካለበት እያስተካከልን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልከን እናፀድቃለን፤›› ሲሉ አቶ ደሳለኝ የሥራ ሒደቱን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...