Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወደ ውጭ ከተላከ እንጀራ 28 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ተተክተዋል

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከተላከ እንጀራ 28 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2008 ዓ.ም. አሻሽሎ ባወጠው የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር መሠረት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ከምክር ቤት አባላት በቃል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ ከእንጀራ ሽያጭ የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ ተናግረዋል፡፡

በምክር ቤቱ አሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 92 መሠረት፣ ሚኒስትሮች ከአባላቱ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች በቃል መልስ እንደሚሰጡ ቢገለጽም እስካሁን ሲተገበር አልተስተዋለም፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት አቶ መላኩ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአጠቃላይ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን በመግለጽ በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ስታንዳርድ ወጥቶለትና ታሽጎ ወደ ውጭ ከተላከ እንጀራ 28 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በእንጀራ የተገኘው ገቢ ጤፍ በጥሬው ቢላክ ሊገኝ እንደማይቻል ጠቁመው፣ በዚህ አሠራር ቡናም እሴት ተጨምሮበት መላክ ቢቻል በአንድ ጊዜ በጣም ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ወደ ውጭ ከተላከ የጨርቃ ጨርቅ ምርት 126 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የወታደር ዩኒፎርሞችን ለማምረት 18 ኢንዱስትሪዎችን በማሳተፍና ለ15,000 ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ወደ ውጭ ይወጣ የነበረን የ60 ሚሊዮን ብር ግብይት በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል ብለዋል፡፡

የወታደር ዩኒፎርም ለማምረት ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ ለረዥም ዓመታት ለመከላከያና ለፌዴራል ፖሊስ ቻይና ሆኖ እያመረተ ሲልክ የነበረው ኩባንያ፣ ወደ ኢትዮጵያ ፋብሪካውን ነቅሎ መጥቷል ተብሏል፡፡

በተጨማሪ ከውጭ ይመጣ የነበረን ብቅል በአገር ውስጥ እንዲመረት በማድረግ፣ ከአገር ውስጥ ምርት ፍላጎት በተጨማሪ ወደ ውጭ እየተላከ መሆኑን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በፀጥታ፣ በኮቪድ-19 እና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫና የተነሳ ሥራ አቁመው ከነበሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል 352 ያህሉ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ መመለሳቸውን፣ በዚህም ኢንዱስትሪዎቹ አሰናብተዋቸው የነበሩ ሠራተኞችን ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ስለመደረጉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ የውጭ ባለሀብቶች ፍሰት የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚታይ የጠቀሱት አቶ መላኩ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 67 አዳዲስ የውጭ ባለሀብቶች፣ 3,829 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዳስትሪዎች፣ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ 1,617 ኢንዱስትሪዎች አዲስ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ 18 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ከውጭ ደግሞ 125 ቢሊዮን ብር ሀብት ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች