Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትጥምር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድን ማካተት የሚያስችል አሠራር እንዲሻሻል ተጠየቀ

ጥምር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድን ማካተት የሚያስችል አሠራር እንዲሻሻል ተጠየቀ

ቀን:

በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን ውስጥ እንዲካተቱ የሚያስችል አሠራር እንዲሻሻል ተጠየቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን በመገኘት በተለያዩ ጉዳዮች ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ የጥምር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች አገራቸውን ማገልገል የሚያስችሉ አሠራሮች መሻሻል እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው የመሠለፍ ፍላጎት እንዳላቸው ሲነገር ቢቆይም፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሲያቀርባቸው በነበሩት የተለያዩ ምክንያቶች ሳያካተቱ ቆይተዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ወደ አገር ቤት አስመጥቶ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ለማካተት የተለያዩ ችግሮች ገጥመውት እንደነበረና ይህም ተጫዋቾችን ወደ አገር ቤት ማስመጣት እንዳልተቻለ ሲጠቀሰ ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት ባለመፍቀዷና ትውልድ ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገር ቤት ለማስመጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቅ መሆኑ ሒደቱን እንዲወሳሰብበት ፌዴሬሽኑ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይህም ብሔራዊ ቡድኑ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ክለቦች ውስጥ እየተጫወቱ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መጠቀም አለመቻሉ ሲያስተቸው ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ የተወሰኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በቡድን ውስጥ ማየት ቢቻልም፣ ከዚያ ወዲህ ግን ተጫዋቾቹን መመልከት አልተቻለም፡፡ ከዓመታት ቀደም ብሎ በትውልድ ኢትዮጵያዊው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ዴቪድ በሻ አማካይነት ከ38 በላይ ኢትዮጵያዊ የዘር ሐረግ ያላቸውን ተጫዋቾች መርጦ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በጊዜው የተመረጡት ተጫዋቾች በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡

ብሔራዊ ቡድኖች በአኅጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ሲካፈሉ የዘር ሐረጋቸው ከሌላ አገር የሚመዘዝ ተጫዋቾችን ዕድል ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ በዚህም አብዛኛው ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ ሲሆን ይታያል፡፡ በዓለም ዋንጫ እንዲሁም በአኅጉራዊው የእግር ኳስ ውድድር ላይ ፈቃደኛ የሆነ የውጭ አገር ተጫዋቾችን ማካተት ብሔራዊ ቡድኑን የማጠንከርና የማስቻል አቅም እንዳለው የሚታመን ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ዕድል መስጠት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የስታዲየም መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶት ብሔራዊ ቡድኑ በአገሩ እንዲጫወት ማድረግ እንደሚገባም ተወያይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከውጪ የሚገቡ ዕቃዎች በተለይም የመጫወቻ ኳስ ከቅንጦት ዕቃዎች መካከል በመመደቡ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ እንደናረና ይህ መስተካከል በሚቻልበት ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መንግሥት ትኩረት እንዲያደርግና ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።  

በቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቅሰው ማሞና የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኸይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የተመራው ቡድን በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት በመገኘት ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር የተወያየ ሲሆን፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያለበትን ተቋማዊ ቁመናና መንግሥት ለእግር ኳሱ ማድረግ በሚገባው ድጋፍ ዙሪያ ምክክር መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

በተለይ የብሔራዊ ፈዴሬሽኑ የፋይናንስ አቅም ወጪዎችን እየሸፈነ ውድድሮች እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ በመንግሥት መደገፍ እንደሚገባው፣ የሌሎችን አገሮች ተሞክሮ በማቅረብ ሰፊ ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን በክለቦች ውጤታማነት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ቋሚ ኮሚቴውም ለእግር ኳሱ ውጤት መሻሻል ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መሥራች መሆኗን ተከትሎ፣ አገሪቷን የሚመጥን የእግር ኳስ ውጤት ለማምጣት ከታች ጀምሮ ከክለቦች በመቀናጀት ተተኪ በማፍራት ፌዴሬሽኑ ጠንክሮ መሥራት ይገባዋል ተብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር በእግር ኳሱ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ መተግበር እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፣ ፌዴሬሽኑ የአገሪቱን እግር ኳስ ውጤት ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ የበጀት እጥረትና ክለቦች ተተኪ ለማፍራት አቅደው አለመሥራት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከውጭ አገሮች አምጥቶ ለማጫወት ያሉ የሕግ ክፍተቶች፣ ከተለያዩ አካላት ለእግር ኳሱ የሚሰጠው ትኩረት ማነስና ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ያለመኖር የእግር ኳሱን ዕድገትና ውጤት እንደጎዳው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...