የአዲስ አበባ ከተማ ጡረተኞች ማኅበር በአፍላ ዘመናቸው ለአገራቸው አገልግሎት የሰጡ፣ በዕድሜ ጣሪያና በጦር ሜዳ ቆስለው ፆታ ሳይለይ በክብር ጡረታ የወጡ አካላትን ያካተተ ነው፡፡ ማኅበሩም ባለ አሥር ወለል ሕንፃ ግንባታ አስጀምሯል፡፡ ሕንፃው አሁን ባለበት ሁኔታና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የማኅበሩን ፕሬዚዳንት አቶ ደበበ ለማን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሕንፃው የት ነው እየተገነባ ያለው? ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል?
አቶ ደበበ፡- ማኅበሩ የሚያሠራው ሕንፃ ባለ አሥር ወለል የሆነ ሁለገብ ሕንፃ ነው፡፡ የሚፈጀውም ገንዘብ 280 ሚሊዮን ብር ሲሆን እየተገነባ ያለውም ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ሃያ ሁለት ማዞሪያ አካባቢ ነው፡፡ የመሬቱም ስፋት 2,400 ሜትር ካሬ ሲሆን ማኅበሩ ይህንኑ ቦታ ያገኘው ከሊዝ ነፃ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ሕንፃው በአሁኑ ጊዜ መሠረት ወጥቶለት አሥር ምሰሶዎች ተገንብቷል፡፡ አጠቃላይ ሕንፃውን ዳር ለማድረስ ወይም ለማስፈጸም እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ የማኅበሩን አቅም ክፉኛ እየፈታተነው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአቅም ፈተና ከገጠማችሁ መሠረቱን ያወጣችሁት ወይም የገነባችሁት ከየት ባገኛችሁት ገቢ ነው?
አቶ ደበበ፡- መሠረቱን የማውጣት ሥራ ዳር ሊደርስ የቻለው በማኅበሩ ግቢ ዙሪያ ጊዜያዊ የቆርቆሮ በቆርቆሮ ሱቆችን በመሥራትና ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር የኮንቴይነር ድጋፍ በመጠየቅ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አንበሳ አውቶቡስ መሥሪያ ቤት አገልግሎቶቻቸውን የጨረሱ አውቶቡሶች ከፈናቸውን በመጠየቅ ጠግነን በተመጣጣኝ ዋጋ አከራይተን ባገኘነው ገቢ ተደማምሮ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሕንፃውን ይዘት ቢገልጹልን?
አቶ ደበበ፡- ከመጀመርያው እስከ አምስተኛው ያሉት ወለሎች ለቢሮ ሥራ መገልገያ የሚውሉ ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ያሉት ወለሎች ደግሞ ለመኖሪያ (አፓርትመንት) እንዲው ይደረጋሉ፡፡ ሕንፃው ከምድር በታች ደረጃውን የጠበቀ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ይኖረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህን መሰል ግዙፍ ሕንፃ ዳር ለማድረስ የማኅበሩ አቅም የማይፈቅድ ከሆነ ምን አማራጭ አላችሁ?
አቶ ደበበ፡- የተጀመረው ሕንፃ ግንባታ እንዳይስተጓጎል ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ማለትም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ልዩ ልዩ የግል የንግድ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ባለሀብቶች የዕርዳታ ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ አርቲስቶች የዕርዳታ እጆቻቸውን ዘርግተው ድጋፋቸውን እንዲቸሩን በመጎትጎት ላይ ነን፡፡
ሪፖርተር፡- ለሕንፃው ማስፈጸሚያ የዕርዳታ እጆቻቸውን እንዲዘረጉላችሁ በተጨባጭ የጠየቃችኋቸው ወይም በሮቻቸውን ያንኳኳችሁ ድርጅቶችና ግለሰቦች አሉ?
አቶ ደበበ፡- በተጨባጭ የጠየቅናቸው ወይም በራቸውን ያንኳኳናቸው ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ማዕድን ሚኒስቴር፣ ዘመን ባንክና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ይገኙበታል፡፡
ሪፖርተር፡- ምን መልስ አገኛችሁ?
አቶ ደበበ፡- ጥያቄያችንን ተቀብለውታል፡፡ ለተግባራዊነቱ በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡ በጎ ምላሽ እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከሁሉም ግን ዘመን ባንክ በቅርቡ ድጋፍ ሊያደርግልን ቃል ገብቷል፡፡ በባንኩ ድጋፍ ብቻ ሳንወሰን ከሌሎችም በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድጋፍ ለማግኘት የጀመርነውን ጥናት አጠናክረን እንድንቀጥል አሳስቦናል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የራሱ የሆነ ክሊኒክ እንዳለው ይነገራል፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ከክሊኒኩ ገቢ ለግንባታው ሥራ ለምን አትጠቀሙም?
አቶ ደበበ፡- ክሊኒኩ የተቋቋመውና የአባላት ወርኃዊ መዋጮ ሁለት ብር እንዲሆን የተወሰነው፣ በጉዳዩ ዙሪያ ተገቢ ጥናት ሳይደረግ በግብታዊነት ስሜት በመነሳሳት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በተለይ ለመድኃኒት መግዣና ለቤት ኪራይ የምንከፍለው ገንዘብ አጥተናል፡፡ ለጤና ባለሙያዎችም ደመወዝ ቀርቶ የትራንስፖርት አበል የመክፈል አቅማችን ዜሮ ሆኗል፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ክሊኒኩን ማንቀሳቀስ ስላልቻልን ዘግተነዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚታየው የአባላት ወርኃዊ መዋጮ በጣም ትንሹ ከመሆኑም በላይ በተለይ ወርኃዊ የጡረታ አበል ክፍያ በባንክ በኩል በመሆኑ የተነሳ በርካታ ጡረተኞች ትንሿንም መዋጮአቸውን ገቢ ከማድረግ አቋርጠዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ያለው የሕንፃ መሣሪያዎች የሚሸጡበት የገበያ ሁኔታ ከማኅበሩ አቅም ጋር እንዴት ያዩታል?
አቶ ደበበ፡- በአሁኑ ጊዜ ያለው የገበያ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው፡፡ አንድ መኪና ጠጠርና ሌላ አንድ መኪና አሸዋ በድምሩ 70,000 ብር ነው፡፡ አንድ ድንጋይ አሥር ብር ሲሆን አንድ መኪና ሙሉ ሲገዛ ግን ምን ያህል እንደሚያስወጣ መገመት አይከብድም፡፡ ከዚህም ሌላ አንድ ምሰሶ ቢያንስ 35 ኩንታል ሲሚንቶ፣ አንድ የብረት ዘንግ 600 ብር ይፈጃል፡፡ ከዚህ አንጻር ግራውንድ ፕላስ ቴን (ከምድር በላይ ባለ አሥር ወለል) ሕንፃ ለመገንባት የሚጠይቀውን ወጪ ማኅበሩ በምንም መልክ ቢሆን መሸፈን አይችልም፡፡ በድጋሚ ለመግለጽ የምፈልገው ነገር ቢኖር ለዚህ እንደ ብቸኛ መፍትሔ አድርገን የምናየው ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት ተቋማት፣ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ድጋፍና አብሮ መሥራት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ከሪል ስቴት አልሚዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ተወያይታችኋል?
አቶ ደበበ፡- አልተወያየንም፡፡ ይህም ቢሆን በተረፈው መሬት ሪል ስቴት ሊያለሙበት ይችላሉ፡፡ አብሮ የመሥራቱ ጉዳይ ግን ልንወያይበት እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ገና ከጅምሩ ሊያሠራ አስቦት የነበረው ባለ አራት ወለል ነበር፡፡ ይህ ሐሳብ የተሻረበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ደበበ፡- ጉዳዩ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ቦታው በሚገኝበት አካባቢ ከአሥር ወለል በታች መገንባት አይቻልም ስላለን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የቀድሞውን ዲዛይን ቀይረን ባለ አሥር ወለል ዲዛይን ለመቅረጽ በቅተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ መሠረቱን ለማውጣት ያበቃችሁ ምክንያት ምንድነው?
አቶ ደበበ፡- የሕንፃውን መሠረት ለማውጣት የበቃ ነው ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ውል ከተዋዋልንበት ቀን ጀምሮ በ12 ወራት ውስጥ ግንባታውን እንድትጀምሩ የሚል ማስጠንቀቂያ ስለደረሰን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ቀደም ሲል የጠቀስኩትን ልዩ ልዩ የገቢ ምንጭ በማሰባሰብ አሥር ምሰሶዎች ያሉበትን መሠረት ለማውጣት በቅተናል፡፡