(ክፍል ስምንት)
በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)
“ምግብን የሚያጣፍጠው ምንድነው?”…
ባለፈው ታኅሳስ ወር ውስጥ ለአንድ የሥራ ጉዳይ ወደ በሰሜን አቸፈር ወረዳ ወደምትገኘው ቁንዝላ ከተማ ጎራ ብዬ በነበረበት ወቅት፣ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎችን የመጎብኘትና ነዋሪዎቹን የማነጋገር ዕድል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ ገበሬዎቹ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት ውስጥ በሕይወታቸው/በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ካሮት፣ ቀይ ስር፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ቆስጣ… ማምረትና መሸጥ፣ እናም ጥሩ ገቢ ማግኘት ጀምረዋል፡፡ ከሁሉ ደስ የሚለው ታዲያ እነዚህን አትክልቶች ለራሳቸውም በምግብነት ጭምር እየተጠቀሙ መሆናቸው ነው፡፡
አንዲት አርሶ አደር እንዲህ ነው ያለችኝ፣ ‹‹ካሮቱን፣ ቀይ ስሩን፣ ቲማቲሙን ለገበያ ከተማ ስንሄድ እናየዋለን እንጂ በልተነው አናውቅም ነበር፡፡ አሁን እንደልባችን ጣፍጦን እየበላን…›› (ይህን ውጤት ላመጣው ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ሰናይ ምሥጋና ይገባዋል፡፡)…
ሰውዬው፣ አብረውት ያሉትን ሰዎች፣ “ምግብን የሚያጣፍጠው ምንድነው?” በማለት ይጠይቃል፡፡ ሰዎቹ የተለያዩ መልሶችን ሰጡ፣ የሰውዬው መልስ ግን አሉታዊ ነበር፡፡
“ወጡ፡፡”
“አይደለም፡፡”
“የወጡ ቅመም፡፡”
“አይደለም፡፡”
“ጨው፡፡”
“አይደለም፡፡”
“ቅቤ፡፡”
“አይደለም፡፡”…
መልሱን ማግኘት እንዳልቻሉ ሲገባቸው፣ ራሱን መልሰው ጠየቁት፣ “አላወቅነውም፣ አንተው ንገረን፡፡”
“ረሃብ!” በማለት መለሰላቸው፡፡
ይኼ ትርክት የሚነግረን ቁምነገር፣ አንድን ምግብ እየጣፈጠን ልንበላው የምንችለው ሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን ሲርበን፣ የረሃብ ጥፍሮች ባልተወለደ አንጀታቸው ሆዳችንን ሲቧጥጡት መሆኑን ነው፡፡ እናም ለምግብ መጣፈጥ ወይም ጣዕም ማግኘት ሁነኛው መፍትሔ ረሃብ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ምግብ ጥፍጥና የሚኖረው ራሱ ምግቡ ባለው ይዘት (በተካተቱበት ንጥረ ነገሮች፣ ቅመም፣ አበሳሰል፣ ወዘተ.) ወይም “እጇ’ኮ ወርቅ ነው” በመባል ባለሙያነቷ የተመሰከረላት ሴት ስለሠራችው አይደልም፡፡ በአጭሩ የምግብን ጥፍጥናም ሆነ ጣዕም የሚወስነው፣ ከምግቡ ውጭ ያለ ነገር ነው፡፡ “ምን?” ከተባለ፣ ረሃብ፡፡
ስለዚህ “ምግቡ አይጣፍጥ ይሆን?” ብሎ መጨነቅም የለም፡፡ “ሆረጠ፣ ጨው በዛ ወይስ ጨው አነሰው ይሆን?” “ጎረና፣ ሆመጨጨ ወይስ መሻገት ጀመረ ይሆን?” “አፍለኛ ሆነ፣ አብሲት በዛበት ወይስ አብሲት አነሰው ይሆን?” … ብሎ መጨነቅ-መጠበብ የለም፡፡ ብቻ ይገኝ እንጂ፣ ይህን ሁሉ ችግር በዜሮ በማባዛት ለምግቡ መጣፈጥ ሙሉ ዋስታና የወሰደ አካል አለ፡፡ ማን? አጅሬው ረሃብ!
ምሳሌያዊ አነጋገሩ ፊት ለፊት ከሚነግረን “እውነታ” ትንሽ ራመድ ብለን ስናስብ፣ መረዳት የምንችለው ቁም ነገር፣ ሐበሾች ከአቅማቸው በላይ በሆነ ምክንያት ለረጅም ጊዜ በምግብ እህል እጥረት ከመሰቃየትም አልፈው በረሃብ መጅ እየተደቆሱ፣ በጠኔ መዶሻ እየተወገሩ ለመኖር ከመገደዳቸው የተነሳ፣ ረሃብን የምግብ ጥፍጥፍና መለኪያ አድርገው እስከ መቁጠር መድረሳቸውን ነው፡፡
እንደገና ከዚህ አንድ ዕርምጃ ወደ ፊት ትንሽ ዕልፍ ብለን ስንመረምር ደግሞ፣ ራሱን ችግሩን (ማለትም ረሃብን) መፍትሔ አድረገው እንደ ወሰዱት እንረዳለን፡፡ ምግብ ይጣፍጥ ዘንድ፣ ተመጋቢው ቢያንስ በትንሹም ቢሆን መራብ አለበት፡፡ ለምግብ አለመጣፈጥ ችግር ሁነኛው መፍትሔ ረሃብ ነው፡፡ ረሃብ ችግር ነው፣ እሱ ራሱ ግን ለሌላ ችግር ሁነኛ መፍትሔ ነው ምግብን ያጣፍጣልና፡፡ የቀረበው ምግብ ቢፈልግ እጅ እጅም፣ እንጨት እንጨትም ወይም ምንም ምንም ይበል፣ ችግር የለም፡፡ ብቻ ረሃብ ይኑር፣ ረሃብ ካለ ይጣፍጣል፡፡
ስለዚህ ሐበሾች ሊታረቁት የማይገባ ጠላታቸውን (ረሃብን) የምግብ አለመጣፈጥ ችግር መፍትሔ (ወዳጅ) አድርገው የወሰዱበት ሚስጥር፣ ከረሃብ ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው ከቀየሷቸው ብልኃቶች አንዱ እንደ ሆነ መገመት ይቻላል፡፡ እስቲ የሚከተለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ልብ ብለን እንይ፡-
“ለራበው ከማዘን፣ ለጠገበው ማዘን፡፡”
ምሳሌያዊ አነጋገሩ ፊት ለፊት ሲያዩት፣ መልዕክቱ አሳማኝና ገራገር ይመስላል፡፡ ይህ የሆነው ምናልባትም እየተነገረንና እኛም እየተጠቀምንበት ስለኖርን፣ ትክክለኛነቱ ጎልቶ ሊሰማን ስለሚችል ጭምር ነው… የተራበ ሰው ከማንም አይደርስ፣ ረሃብ ሆዱን ከመሞርሞርም አልፎ፣ ጉልበቱን ነጥቆታል፣ ጭንቅላቱንም “ምግብ ከየት አባቴ ላግኝ?” በሚል ጥያቄ ወጥታሮል፡፡ ረሃብ እየቦከሰው ያለ ሰው፣ ከሰው ጋር “አምባጓሮ ልግጠም” አይልም፡፡ ይልቁንም እንደ ባዶ ጆንያ ጥቅልል ብሎ ነው የሚተኛው፡፡ የጠገበ፣ እምብርቱ እስኪገለበጥ የበላ ከሆነስ? ከአምባጓሮም አልፎ ተርፎ ጦጣ የማትዘለውን ገደል “ካልዘለልኩ”፣ የደነበረንና እንደ ጎራ ያበጠን በሬ “ቀንዱን ይዤ ካላስቆምኩት” በማለት “ያዙኝ ልቀቁኝ” ከማለት ላይመለስም ይችላል፡፡
ሆኖም ብሂሉ ችግር ላይ የሚወድቀው፣ “የጠገበ ሁሉ ያን ያደርጋል? በእርግጥ ይኼ የአብዛኛው የጠገበ ሰው መገለጫ ነውን?” የሚል ጥያቄ ስናነሳ ነው፡፡ በእውነትም አይደለም ወይም ሊሆን አይችልም፡፡ የምግብ ዋስትናውን ያላረጋገጠ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ባለበት አገር፣ ብዙ የተራበ እንጂ ብዙ የጠገበ ማግኘትም ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ እኒያ የኛዎቹ የድሮ አባት እናቶች ከስንት ሰው መሀል የሚገኝ አንድ ጥጋበኛ “ይፈጽመዋል” ብለው ያሰቡትን የዕብሪት ተግባር ለማውገዝ በመሻት፣ ምነው የተራበውን ፈረዱበት? ምነው ለተራበው እንዳይታዘን ክፉኛ ሰበኩ?
እንዳትፈርዱባቸው ብሂሉ ከረሃብ ጋር አብሮ የመኖር ሥልት አንድ አካል ነው፡፡ እሺ፣ እንዘን ቢባልስ ለስንቱ ይታዘናል? ለስንቱ ጥርስ ይመጠጣል? በዚህ መንገድ እያዘኑ መኖርስ እንዴት ይቻላል?… “ረሃብን ታግሎ መጣል አልተቻለም” ማለት፣ “አብሮ መኖር ግድ ሆኗል” ማለት ነው የተለማመዱት መጥፎ ከሌለ ይቆጠራል ዓይነት፡፡ በሌላ በኩል ተሸናፊ ሆኖ፣ ከአሸነፈ “አካል” ጋር አብሮ መኖር ግድ ሲሆን፣ አሸናፊው በኅብረተሰቡ ትርክት ውስጥ የሚያገኘው ቦታ አለ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ “የበላይነቱን” የሚናገርለት፣ መናገሩ ቢቀር ያን የሚያሳብቅ የወግ ባህል፡፡ እዚህም የሆነው ይኼው ነው፡፡
ከረሃብ ለጊዜውም ቢሆን መላቀቅ ወይም ለአንዴም ቢሆን ዕፎይታ ማግኘት እንኳን እንደ ጥሩ ላይታይ ይችላል፡፡ ለአብነት እስቲ የሚከተለውን አባባል እንይ፡-
“ባለጌ የጠገበ ዕለት፣ ይርበው አይመስለውም፡፡”
እዚህ ላይ ጥጋብ ወይም መጥገብ በቀጥታ ሲወገዝ፣ ረሃብ ግን በተዛዋሪ እንኳን አልተነካም፡፡ እናም የአሸናፊነት ክብሩን እንደያዘ ቀርቧል፡፡ “ባለጌ” የድርጊቱ ባለቤት ስለሆነ፣ “ወትሮስ ከባለጌ ምን ይጠበቃል?” ብላችሁ እንዳትፈርዱ፡፡ እንዲያ ከሆነ፣ “የጠገበ ለራበው አያዝንም” የሚለውን አነጋገር ምን ልትሉት ነው? በዚህ ብሂል ውስጥ መጥገብ እንደ ልማዱ የውግዘቱን ናዳ ተሸክሞ፣ ረሃብም እንደ ልማዱ የ”አይነኬነት” ሰንደቅን ከፍ አድርጎ እናገኘዋለን፡፡
ረሃብን የሚመለከቱ ትርክቶች፣ ምሳሌያዊ ንግግሮች፣ ተረቶች፣ ግጥሞች… በአጭሩ ከረሃብ ጋር የተያያዙ አብዛኛዎቹ የሐበሻ ወጎች (Discourses) ረሃብን ሙልጭ አድርጎ ለመስደብ ይቅርና ለመተቸት፣ ለማውገዝና ለመገሰፅ ድፍረት የሚያሳዩ አይመስልም፡፡ ረሃብን እንደ ደርግ ወይም እንደ ኢሕአዴግ የሚፈሩት ሆነው ነው የሚታዩት፡፡
“የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽ” ነገር ሆኖባቸው፣ ረሃብን ጎሸም ለማድረግ ከሞከሩ እንኳ መናጆ ሊጨምሩ ይችላል አብሮ የሚወቀስ ወይም የሚደቆስ፡፡ ምሳሌ እንጥቀስ፡-
ረሃቤ፣ ጥማቴ፣ እርዛቴ ሦስቱ
ይደበድቡኛል በአንድ እየዶለቱ፡፡
“ገጣሚው” ሦስቱንም (ረሃብ፣ ጥማትና እርዛትን) በጋራ እያሴሩ ጥቃት እንደሚፈጽሙበት ሲናገር፣ በእሱ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንደ አቅማቸው መጠን የተለያየ መሆኑን አልነገረንም፡፡ ይልቁንም “ይደበድቡኛል በአንድ እየዶለቱ” በማለት እኩል ወይም ተመጣጣኝ ኃይል ያላቸው መስሎ እንዲታየን ነው ያደረገው፡፡ በጉዳት ደረጃ ከከባድ ወደ ቀላል እናስቀምጣቸው ካልን፣ ከሁሉም የከፋውና ጊዜ የማይሰጠው ጥማት ነው፣ ከዚያ ረሃብ ይከተላል፣ ከዚያም እርዛት፡፡
ሆኖም ከመገኘት አንፃር ካየነው፣ ውኃ የመገኘት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ወንዝ በመውረድ፣ ወንዙ ቢደርቅ አካባቢን በመቀየር ውኃ ሊገኝ ይችላል፡፡ ወንዝ በመውረድም ሆነ አካባቢ በመቀየር ምግብ የማግኘት ዕድል ግን እጅጉን ጠባብ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው እርዛት፣ ከጨከኑ የመግደል አቅም ካላቸው (ረሃብና ጥማት) ጋር እኩል ወይም ተቀራራቢ ደረጃ ተሰጥቶ ነው የቀረበው፡፡ በአጭሩ ረሃብ ዋናው መጥፎ፣ ዋናው ጨካኝ፣ ዋናው ገዳይ ሆኖ እያለ፣ በጉዳት መጠናቸው ከእሱ ጋር ፍፁም በማይወዳደሩት መናጆዎች ታጅቦ የቀረበ ከመሆኑም በላይ፣ መናጆዎቹ ከእሱ ጋር ተመሳሳይ ጉዳት አድራሾች መስለው እንዲታዩም ተደርጓል…
በክፍል አንድ ያወያዩን ምሳሌያዊ አነጋገሮች (“ሆድ ባዶ ይጠላል፣ ድንጋይም ቢሆን”፣ “ከሆድ የገባ ያገለግላል”) እራሳቸው፣ ከረሃብ ጋር “ተስማምቶ” አብሮ የመኖር “ብልኃት” የፈጠረው ብሂል ተጨማሪ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ወይም በቀጥተኛ አነጋገር፣ የሽንፈት መገለጫዎች ናቸው፡፡ እየሰበኩ ያሉት ሠርቶ፣ ለፍቶና ጥሮ ግሮ የድህነት ጦስ የሆነውን ረሃብን በማንበርከክ፣ ለአካልምና ለጤናም የሚበጅ የተሻለ ነገር መርጦ መብላት እንደሚቻል ሳይሆን፣ ያገኙትን አሰሱንም፣ ገሰሱንም በመብላት ለረሃብ እጅ መስጠትን ነው፡፡
ተረትና ምሳሌው፣ ለሆድ የአሸናፊነትን ኒሻን የሚሸልም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን አባባል እንይ፡- “ሆዳችን በጀርባችን ቢሆን ኖሮ፣ ገፍቶ ገደል በጣለን፡፡” ሆድ አሸናፊነቱን የሚቀዳጀው ረሃብን መሣሪያ አድርጎ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
አንዳንዶቹ አባባሎች ደግሞ፣ “ረሃብ”ም ሆነ “ሆድ” የሚል ቃል ላይጠቀሙ ይችላል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ በሆድ ምክንያት ስለሚከሰተው ሥቃይ፣ ማለትም ስለረሃብ ምንም አይናገሩም፡፡ ሆኖም ሥረ መሠረታቸውን ገባ ብለን ስንመረምር ለረሃብ እጅ የመስጠት መገለጫዎች ከመሆን አይዘልም፡፡ ለአብነት ያህል ሁለት ብሂሎች እንመልከት፡-
“እራት በእንቅልፍ ያልፋል”
ይህ አባባል “አህያውን ፈርቶ፣ ዳውላውን” ዓይነት ነው፡፡ የሚበሉት እራት የሌላቸው ሰዎች፣ እራት ባለመኖሩ ምክንያት የሚመጣውን የሆድ ጥያቄ ማለትም የሚሰማቸውን ረሃብ እንቅልፍ ውስጥ ተደብቀው ማሳለፍን መርጠዋል፡፡ ሆኖም “ረሃብ በእንቅልፍ ያልፋል” ማለት አልፈለጉም፡፡
“ቁርጥ ያጠግባል”
“ግማሽ” ኪሎ ሥጋ አዞ (እንደ ገና ቢመዘን ግማሽ ላይሞላ ቢችልም “ግማሽ ነው” ብለው ሰጥተውታል) ሩቡን ለቁርጥ፣ ሩቡን ለጥብስ አድርጎ የሚበላ ሰው፣ “ቁርጥ ያጠግባል” የሚለውን አባባል፣ “ቁርጡ ባያጠግብ፣ ጥብሱ ሲጨመርበት ያጠግባል” ብሎ ቢያስብ አትፍረዱበት፡፡
አባባሉ ግን ስለሥጋም ሆነ ስለተቆረጠ እንጀራ አይደለም “እያወራ” ያለው፡፡ “ቁርጥ ያጠግባል” ማለት፣ ቀርቦ ሊበላ የሚችል ምግብ ቤት ውስጥ እንደሌለ፣ የተነገረው ሰው ከጠገበ እንደሚቆጠር ነው እየነገረን ያለው፡፡ “ዛሬ ቁርስ” ወይም “ምሳ” ወይም “እራት የለም” የተባለ ሰው፣ ቁርጡን ያውቃል፡፡ ቁርጡን ሲያውቅ፣ የምግብ ፍላጎቱ በቀጥታ ወደ ዜሮ ይወርዳል፡፡ አቶ ሆድ “ምግብ አምጣ” የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ያቆማል፡፡ ምግብ እንደሌለ ቁርጥን ማወቅ፣ ራሱ ምግብ ሆነ ማለት ነው፡፡
ለረሃብ እጅ ወደ ላይ ማለት ተገቢ መሆኑን የሚሰብኩት አንዳንድ አባባሎች ከዚህም በጣም ረቀቅ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ አንድ ምሳሌ እንይ፡-
“‘ምን ለብሳ ወጣች እንጂ፣ ምን በልታ ወጣች’ ማን ይለኛል?”
አንዳንድ በአነስተኛ የገቢ ምንጭ የሚተዳደሩ ሴቶች፣ ለተለያየ ጉዳይ (በተለይ ለሠርግ፣ ለገበያ፣ ለበዓል) ከቤታቸው ሲወጡ ሽክ ብለው፣ በቻሉት መጠን ሁሉ ተሽቀርቅረውና ዘንጠው ነው፡፡ በጆሯቸውና በጣታቸው ላይ በአብዛኛው ወርቅ አይጠፋም፡፡ ጥያቄው ከኑሯቸው ጋር የማይጣጣመው አለባበስ “ከየት መጣ ነው? የኢኮኖሚ አቅማቸው ‘ከሚሸከመው’ በላይ ማጌጡ እንዴት ተሳካ ነው?”
መልሱ ያለው፣ “‘ምን ለብሳ ወጣች እንጂ፣ ምን በልታ ወጣች’ ማን ይለኛል?” ከሚለው ተረትና ምሳሌ ውስጥ ነው፡፡ ሴትየዋ በቤቷ ውስጥ የምትበላውን የምግብ ዓይነትም ሆነ መጠን ማንም ሊያየው ስለማይችል፣ በጥራቱም ሆነ በመጠኑ ዝቅተኛ የሆነውን በመመገብ፣ በአደባባይ ሊታይና ሊያስተቻት በሚችለው ልብስና ጌጣጌጥ ላይ “ኢንቨስት” ማድረግ መምረጧን እንረዳለን፡፡ በድህነት ውስጥ የመጨረሻ ዝቅተኛ ከሆነው አመጋገብ አንዱ፣ የሽሮ ዱቄትን በውኃ በመበጥበጥ በእንጀራ እያጠቀሱ መብላት ነው፣ የእንጀራውም ጥራት ዝቅተኛ መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፡፡ ከሴትየዋ አንፃር ስናየው በዚህ አመጋገብ ቢያንስ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ ጨውና እንጨት ተቆጥቧል፡፡ በነገራችን ላይ በተወሰነ ደረጃ እንጀራም ሊቆጠብ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ማባያው (ወጡ) ጥሩ ሳይሆንና ጥሩ ሲሆን የሚበላው የእንጀራ መጠን ይለያያል…
ሲጠቃለል ሰዎች አንድ ችግር ሲያጋጥማቸው፣ “ችግሩን ለማስወገድ ይጠቅማል” ያሉትን ዕርምጃ ሁሉ ይወስዳሉ፡፡ ሆኖም የወሰዱት ዕርምጃ ሁሉ ችግሩን ማስወገድ ካልቻለና ችግሩ ለረጅም ጊዜ ተጣብቷቸው የሚኖር ከሆነ፣ ችግሩ ከቅኝ ግዛቱ መዳፍ ስር አውሏቸው ህልውናቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥለው ጭምር በሚያካሂዱት የሞት ሽረት ትግል ውስጥ፣ ከችግሩ ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው ይማራሉ፣ ራሳቸውን “ያሠለጥናሉም”፡፡ ረሃብንም በተመለከተ የሆነው ይኼው ነው፡፡ እስካሁን ያየናቸው ብሄሎች የተሸከሟቸው ጥልቅ መልዕክቶች አንድምታዎቻቸው፣ ረሃብን እንዴት መታገልና ማሸነፍ እንደሚቻል ሳይሆን፣ ከረሃብ ቫይረስ ጋር እንዴት “ተወዳጅቶ” መኖር እንደሚቻል የሚሰብኩ ናቸው ቢያንስ በተዘዋዋሪ… በነገራችን ላይ በአንድ ማኅበረሰብ ወይም የፖለቲካ ሥርዓት ለረጅም ዘመን የተጨቆኑና በሒደቱ ውስጥ ጭቆናውን የተቀበሉ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም የሚከተሉት ሥልት ከሞላ ጎደል የዚህ ዓይነት ነው… (በክፍል ዘጠኝ እንገናኝ)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡