በዓባይነህ ግርማ
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከአምስት ዓመታት በፊት በ2010/2011 ዓ.ም. በአገራችን መታየት ከጀመረው የፖለቲካ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የታዩ አዝማሚያዎችንና በቀጣይ መታሰብ ያለባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ የነበሩኝን ዕይታዎችና ምልከታዎች በማስታወስ፣ የእነዚያን ዕይታዎችና ምልከታዎች አሁናዊና ቀጣይ አዝማሚያዎችን ነፀብራቅ ለማሳየት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህን ብለን ነበር፣ ይህ ዕይታና ምልከታ ነበረን ያልነውን በጊዜ ሒደት መለስ ብሎ በማስታወስ ታዲያ ዛሬስ? በቀጣይስ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለማንሳትና ለመመለስ መሞከር ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
- በ2010 ዓ.ም. ወቅቱ አዲስ የለውጥ ንፋስ፣ ተስፋ ሰጪ ንፋስ የነፈሰበት ነበርና ስለአዲሱ ለውጥ እውነትነትና ተጨባጭነት ያልኩትም ነበር፡፡ የመንግሥታት ለውጥ በተደረገ ቁጥር ከሚፈጠር ሥጋት፣ እንዲሁም ተስፋ አንፃር የሚፈጠሩ ሦስት ሥነ ልቦናዎችን መገንዘብ ይቻላል ብዬ ነበር፡፡ አንደኛ የለውጡ ሒደት የሚፈጥረው ፍርኃትና ሥጋት የቀድሞው ወይም የትናንቱ ይሻል ነበር በሚል ያለፈውን የሚመኝ ሥነ ልቦና፣ ሁለተኛ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ወደ የትናንቱን የማይመኝ ሥነ ልቦና፣ ሦስተኛ የሚሆነው ይሆናል ብሎ የሚጠብቅ ሥነ ልቦና ናቸው ብዬ ነበር፡፡ እነዚህ ዓይነት የተመሰቃቀሉ የሥነ ልቦና ቢሆኖች በቀደምት የመንግሥታት ለውጥ ወቅቶች ተፈጥረው እንደነበረው ሁሉ፣ በ2010 ዓ.ም. በተጀመረው የለውጥ የሽግግር ሒደትም እየተፈጠሩ ይመስላል ብዬ ነበር፡፡ የለውጡ እውነትነት፣ ተጨባጭነትና ዘላቂነት የሚረጋገጠው መቼና እንዴት የሚል ጥያቄ በሚከተሉት አጠቃላይ መልሶች ውስጥ የሚታይ ይሆናል ብዬም ነበር፣ ይኸውም፣ መንግሥትና የመንግሥት አመራሮች፣ ሕዝቡና የሕዝብ አካላት፣ የንግዱና የማኅበራዊ ተቋት፣ ግለሰቦች ጭምር ለውጡ ለሚጠይቀው ምግባርና ተግባር ተገዥ ሆነን ስንገኝ ነው፣ ለውጡ የሚጠይቀውን ጊዜና ሁኔታዎች የሚያመዛዝን ምግባርና ተግባር ሲኖረን፣ ትልቁን ሥዕል ከትንሹ፣ የሩቁን ከቅርቡ፣ ጫካውን ከዛፉ መለየትና ማየት የሚችል ምግባርና ተግባር ሲኖረን ነው፡፡ የሰላምን፣ የሕግ የበላይነትን፣ የዴሞክራሲንና የነፃነትን ሁለንተናዊነት የሚያገናዝብ ምግባርና ተግባር ሲኖረን ነው የሚል ነበር፡፡ ሊኖረን የሚገባ ሥነ ልቦና የትናንቱን የሚመኝና የነገውን የሚጠራጠር ሳይሆን፣ በተስፋ የተሞላና የሚሆነው ይሆናል ብሎ የሚጠብቅ ብቻም ሳይሆን፣ የተፈለገውን የለውጥ ውጤት ለማየት ያለን ተስፋ ዕውን ይሆን ዘንድ ከፍ ሲል በተጠቀሱት ምግባርና ተግባር ጠንክሮ መገኘት ያሻልም ብዬ ነበር፡፡ ዛሬስ ታዲያ? በቀጣይስ?
የተጠቀሱት የሥነ ልቦና ቢሆኖች በለውጡ ሒደት በተፈጠሩ ከፍተኛ መንገራገጮች፣ መንሸራተቶች፣ ክህደቶች፣ ሸፍጦች፣ ሴራዎች፣ ዛሬ ዛሬ በሚባሉት ጽንፈኝነትና ቁማርተኝነት እንዲሁም ጦርነቶች፣ ኢሰብዓዊ ግድያዎችና ሕግ አልባነት በፈጠሩት ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት ምክንያቶች ይበልጥ የተመሰቃቀሉና መመሰቃቀል ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ነው የሚባል ሥነ ልቦና የማይንፀባረቅበትና እምነት የጠፋበት ሁኔታን መገንዘብ ይቻላል (Feeling of not knowing what to believe – baffled psychic). ይሁን እንጂ፣ የለውጡ እውነትነትና ተጨባጭነት ይረጋገጥ ዘንድ አስፈላጊ ናቸው የተባሉት ምግባራትና ተግባራት ዛሬም ወደፊትም ወሳኝ ናቸው እላለሁ፡፡ ዛሬ የምጨምረው ተፈላጊ ምግባርና ተግባር ተዓማኒነትንና ግልጽነትን ነው፡፡ እነዚህ በእጅጉ የጠፉበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡
- በሌላ በኩል በተለያዩ ወቅቶች ያሳለፍናቸውን መልካም የሚባሉ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ሳንጠቀምባቸው እንደቀረነው ሁሉ 2010 ዓ.ም. ያመጣልንን መልካም የሚባል ዕድል በአግባቡ ሳንጠቀምበት እንዳንቀር መወሰድ ባለባቸው ዕርምጃዎች ላይ ማትኮር ከኪሳራ ያድናል ያልኩትም ነበር፡፡ በዚህም መንፈስ መልካም ዕድሎችን ለመልካም ሕዝባዊ፣ አገራዊና ዴሞክራሲያዊ ዓላማ መጠቀም ያቃታቸውን ሁሉ ፈር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ የለውጡ አጋር ይሆናሉ ተብሎ በቀና መንፈስ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ጥሪ ተደርጎላቸው የገቡ አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና የእነሱ ሚዲያዎች “የአሸናፊነት” ስሜትን ይዘው በመምጣት የመልካም አጋርነት ሚና መጫወት ሲያቅታቸው ይታያልና ቶሎውኑ ፈር እንዲይዙ መደረግ ይኖርበታል የሚያሰኝ ምልከታም ነበረኝ፡፡ ከስኬት ወይም ከጥፋት አለመማር ጥፋትን መድገም እንዳይሆን የለውጡ ቲም የተባለው አካል በመነሻው ወቅት ያገኘውን የሕዝብ ድጋፍና ቅቡልነት የሚያሳጡ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት፣ ጊዜው እያለቀለት ያለው የኢሕአዴግ አገዛዝ የሄደባቸው የጥፋትና የውድቀት መንገዶች በሌላ መልክ እንዳይቀጥሉ ማድረግ እንደሚገባው፣ መልካም አሳቢዎች የሚሏቸውን ሥጋቶች ለምሳሌ የፖለቲካዊ ፍረጃን፣ የአድሏዊነትና የተረኝነት ዓይነት ጨዋታ እንዳይከሰት፣ ነግ በእኔ ባይነትን በማሰብ ወደ ሥልጣን መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም እንዳለ በማጤን አገራዊና ሕዝባዊ እውነታን አጥብቆ መያዝ ይገባል የሚሉ ምልከታዎችም ነበሩኝ፡፡ ዛሬስ ታዲያ? ወደፊትስ?
ምልከታዎቼ ከፍ ብሎ ከሥነ ልቦና መመሰቃቀል ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ጭምር የከሸፉ ይመስለኛል፡፡ የሚመለከታቸው ሁሉ የተጠበቀባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት ባለመፈለጋቸው ወይም ባለመቻላቸው የአገርና የሕዝብ አደራ በል ሊሆኑ በቅተዋል፡፡ ከለውጡ በኋላ በነበረው ሒደት ስላሳካናቸውም ሆነ ስላጠፋናቸው ድርጊቶች አልተማርንም፣ አላስተማርንም፡፡ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሳት ምን ልንማርና ልናስተምር ይገባል የሚሉ ጥቄዎች ሊነሱ የግድ ይላል፡፡ የሥልጣን ኃይልና ግብታዊነት፣ የእኩይነት አስተሳሰብና አገዛዝ ረጅም መንገድ የማያዘልቅ መሆኑንና የአገሪቱ ጉዳይ “የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” እንደሚባለው እንዳይሆን ልብ ይሏል፡፡
- በለውጡ መነሻ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ‹‹ስንኖርም ስንሞትም ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያ›› የተባለው ልብ የነካ ነበር፡፡ በደርግ ምሥረታ ወቅትም “ኢትዮጵያ ትቅደም” የተባለውን አሁንም ልንለው ይገባል ብዬም ነበር፡፡ ከዚያም ባለፈ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አረዳድ፣ ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነት መገለጫችን፣ ከዜግነትም በላይ ሰፊና ጥልቅ ሥነ ልቦና ያለፈውንም፣ የአሁኑንም፣ የወደፊቱንም የሚያጤን ሥነ ልቦና፣ የሕዝብ አንድነትና እምነት መገለጫ፣ ሁሉንም ማንነቶች አቅፎ የሚይዝ ማንነት፣ ሕጋዊነትም፣ ከመልክዓ ምድር ይዘት የላቀ፣ ወዘተ. ነው ብዬ ነበር፡፡ በአንፃሩም ኢትዮጵያነት ያልሆነውንም መገለጫ በሚመለከት፣ በተሳሳተ ትርክት እንደሚባለው ከተወሰነ ብሔርና ሃይማኖት ጋር ተያይዞ ያልነበረ፣ ከብዝኃነት ጋር የማይቃረን፣ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታንና ምክንያታዊነትን የማይጠይቅ፣ የብሔራዊ ተግባቦት መግለጫ ያልሆነና መሆን የሌለበት ነው ብዬ ነበር፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በሕግ የበላይነት፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ በዜግነት የመብት እኩልነትና ነፃነት፣ ግዴታና ተሳትፎ ሊረጋገጥና ሊጠናከር ይገባል ብዬም ነበር፡፡ ዛሬስ ታዲያ? ወደፊትስ?
ይሁን እንጂ፣ በለውጡ ሒደት በተለያዩ ጎራዎች የተፈጠረውን የሥልጣን ጥመኝነትና የብሔር ማንነትን ፖለቲካ ተከትሎ የተከሰቱ ጦርነቶች፣ የብሔር ብሔረሰብ ግጭቶችና ግድያዎች፣ ሕዝባዊ መፈናቀል፣ ሕገወጥነቶች፣ የደኅንነት ዋስትናና የሰላም ዕጦት፣ ብሎም እነዚህ በፈጠሩት ክፍተት የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ጥያቄ የገቡበትና ከናካቴው የኢትዮጵያን ውድመት፣ ብተና፣ ፍርሰት የሚመኝ ሟርት የሚሰማበት ወቅት ሊሆን በቅቷል፡፡ ከሟርተኝነት ምኞት ባለፈም አገሪቱ በአዲስ ኅብረ መንግሥትነት ትመሠረታለች የሚል ደባ ሲቀነቀን ይሰማል፡፡ የሟርቱና የደባው ምግባርና ተግባር ከፍተኛ ሥጋትንና ፍራቻን እየፈጠሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚያው ልክ እየተፈጠረ ያለው ቁጭትና ቀናዒነት (ቅናት) ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት የሚያበቃ ኃይል ይፈጥራል፣ መፍትሔም ይሆናል፡፡ ህልውናዋ በምንም፣ በማንም የሚተካ አይሆንም፡፡
4. በወቅቱም የሰላም ጉዳይ አሳሳቢ የነበረ በመሆኑም ሰላም ከፋይዳው ወዲህና ወዲያ በሚል አስተሳሰብ የዘር፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአስተዳደር ክልል፣ እንዲያም ሲል የሃይማኖትና ሌሎች የብዝኃነት ማንነቶችና ልዩነቶች ባለባት እንደኛ አገርና ኅብረተሰብ ለሰላም ዕጦት ምክንያት ሲሆኑ የሚታዩት የብዝኃነት ልዩነቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ይልቁንም በልዩነቶቹ አያያዝ ላይ የፖለቲካ፣ የሕግና አስተዳደር አፈጻጸም ስህተቶች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የመፍትሔ ዕርምጃ አወሳሰድ ዴሞክራሲና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መሆኑንና ዘላቂነቱም ከወዲሁ እየተረጋገጠ ካልሆነ ችግሮች ይባባሳሉ፣ ችግርን በአስቸጋሪነቱ ብቻ በታሰበ ጉዳይ የለበትም፣ የሰላም ጉዳይ ከፋይዳውና ከችግርነቱ ወዲህና ወዲያ የሚታሰብ መሆን አለበት የሚል ምልከታ ነበረኝ፡፡ ለምሳሌ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለመፍታትና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ የሚደረጉ የሽምግልና ጥረቶችና ውይይቶች የሚመለከታቸውን ሁሉ ያላሳተፉ ከሆነ የሰላም ጥሪዎችና ማሳሰቢያዎች በስማበሉ ይሆንና ዕርባና አይኖራቸውም፡፡ ስለሆነም ሰላምን በሚያውኩም፣ በሚያመጡም፣ በሚያዘልቁም ዕርምጃዎች መንግሥትም፣ ሕዝብም፣ ጠንካራ መግባባትና አቋም ሊኖራቸው ይገባል የሚሉ ዕይታዎች ነበሩኝ፡፡ የሰላም ፍለጋ ትኩረትና ሥልት ድህነትን በማስወገድ፣ ሕጋዊነትን በማረጋገጠና ዴሞክራሲን በማስፈን ብሎም የአገርና ሕዝብ ደኅንነት፣ የአገርና የሕዝብ አንድነት፣ የአገርና የሕዝብ ብልፅግና ሲሳካ አገርና ሕዝብ ሰላም ይሆናሉ የሚል ነበር፡፡ ይህ ማለት የሰላምን አስፈላጊነት ብቻ ማውሳት በቂ አለመሆኑንና ለሰላም መታጣት ወይም መስፈን በሚያበቁ ሁኔታዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል በማለት ነበር፡፡ ይህ ነበር ሰላምን ከፋይዳው ወዲህና ወዲያ ያስባለኝ ሌላው ዕይታዬ፡፡ ታዲያ ዛሬስ? ወደፊትስ?
የሰላም ጉዳይ ዛሬም ወደፊትም አሳሳቢነቱ እየጨመረ ነው፡፡ የብሔር የማንነት ፖለቲካ ቁማርተኝነትና ጽንፈኝነት፣ ሕገወጥነትና የመብት ጥሰት፣ የአሸባሪነት ሥጋት፣ የብሔር ግጭት ሥጋት፣ የመፈናቀል ሥጋት፣ የሃይማኖት ግጭት ሥጋት፣ የሕይወት ዋስትና ማጣት ሥጋት፣ የጦርነት ሥጋት፣ የአገር ሉዓላዊነት ሥጋት ሰላምን የሚነሱ ሆነው ይገኛሉ፡፡ “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው የመልካም አስተዳደር ድክመት፣ የሥራ ዋስትና ሥጋት፣ የኑሮ ውድነት ሥጋት በአጠቃላይ ሥጋት ልብሱ ሥጋት ጉርሱ ከሆነ የሰላም ጥያቄና ፍለጋ (Quest for Peace) በእጅጉ አሳሳቢ ይሆናል፡፡ ስለሆነም አሁንም ወደፊትም ትልቁ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ቀድሞ እንዳልኩትም የሰላም ዕርምጃ አወሳሰድ ፍትሐዊ፣ ሕጋዊና አሳታፊ ሆኖ የተዓማኒነትንና ቁርጠኝነትን ስሜት የሚፈጠር መሆን አለበት እላለሁ፡፡
- የወቅቱ አንገብጋቢ የሆነውን አገራዊ/ብሔራዊ መግባባት ጉዳይ በሚመለከት ጉዳዩ ከበርካታ ጥያቄዎች ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ በመጥቀስ፣ ሥልቱና አፈጻጸሙ ሥነ መንግሥታዊና ሕዝባዊ መንገድን የተከተለ መሆን አለበት የሚል ምልከታ ነበረኝ፡፡ አገራዊ/ብሔራዊ መግባባት ወይም ዛሬ እንደሚባለው አገራዊ ምክክር በኢትዮጵያዊነትና በአገረ ብሔርተኝነት መንፈስ የተመሠረተ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብራዊ ሥነ ልቦናና የተግባቦት ምግባርና ተግባር እንዲኖረን የሚያበቃ፣ ላለፈ ጥፋትም ሆነ ልማት የጋራ ኃላፊነትን ለመውሰድና ለመቀበል ዝግጁ የሚያደርገንና ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያበቃን ሊሆን ይገባል የሚል ምኞትን ለመግለጽ ሞክሪያለሁ፡፡ ዛሬስ ታዲያ? ወደፊትስ?
ለዓመታት ሲብላላ የቆየው የአገራዊ ወይም ብሔራዊ መግባባት ጉዳይ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞለት አጀንዳ እየተዘጋጀለት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ምክክሩ እየተካሄደ ስለመሆኑ አልፎ አልፎ የሚሰማ ቢሆንም፣ የምክክሩ ርዕሰ ጉዳዮችም ሆኑ የምክክሩ ሒደት ይፋዊ ሆኖ አይታይም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የሽግግር ፍትሕ አካልም መሰየሙ ይታወቃል፡፡ የእነዚህ አካላት ዓላማና አጀንዳ ከሞላ ጎደል የተቃርኖ ምንጭና ዕሳቦት በሚታይባቸው አገራዊ/ብሔራዊ ጉዳዮች ለምሳሌ የታሪክን አረዳድ፣ የኅብረ ብሕራዊ ሥርዓትን አወቃቀር፣ የአገረ መንግሥት አመሠራረትን፣ ሕገ መንግሥትን፣ ባንዲራን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን አተገባበር፣ የሰላምና ዕርቅ ፍለጋን፣ ከጦርነት ማብቂያና በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶች የሚበየኑበት የፍትሕ ሥርዓትና የዕርቅ ውሳኔን፣ ወዘተ. በሚመለከት እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የአካላቱ መሰየምና አጀንዳ መያዙ የአገራዊ/ብሔራዊ መግባባት ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የሚያረጋግጡ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለአገራዊ/ሕዝባዊ መግባባት በሚደረግ ምክክር ልንጨነቅ የሚገባን ስለታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም ስለአገራዊና ሕዝባዊ የወደፊት አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ድህነት ዕጣ ፈንታ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡
የምክክር ሒደቱን በሚመለከት ግልጽነት፣ ሕዝባዊ አሳታፊነት፣ ተዓማኒነትና ቁርጠኝነት የጎደለው እንዳይሆን ያሰጋል የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይሰማል፡፡ የፖለቲካው፣ የማኅበራዊና የደኅንነት ዓውዱና የጉዳዮቹ ይዘት በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጡና እየተወሳሰቡ ባለበት ሁኔታ የምክክሩና መግባባቱ ሒደት የቁርጠኝነት መንፈስን፣ የተቀናጀ ሥነ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ሥልትንና ፍጥነትን የሚጠይቅ ይመስላልና ይህ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ለምሳሌ በጦርነቱ ምክንያት በተቋሰሉና በተገዳደሉ ጎረቤታም ሕዝብ መካከል ብሔራዊ የፍትሕና የዕርቅ ምክክር ሥነ ሕዝባዊ ሥልትን የተከተለ ለማድረግ በምክክር ኮሚሽኑ አመቻችነት ደም በተቃቡት ወገኖች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ የፍትሕና የዕርቅ ምክክር ሊደረግ ይገባል ማለት ነው፡፡
- የፖለቲካ ድርጅቶች ቁመና ሲፈተሽ በሚል የኢሕአዴግ አገዛዝ በተመሠረተ ማግሥት በየትኛውም አገር ታይቶ በማይታወቅ ቁጥርና ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ግማሹ በብሔር፣ ግማሹ በኅብረ ብሔር መሰል ቅርፅ፣ ጥቂቱ ለሌሎች አጋር በመሆን ብቅ ብቅ ብለውና በገዥው ፓርቲ በጎ ፈቃድ በሚመስል በምርጫዎች ተሳትፈውና አንዳንዶቹ በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን ቀንቷቸው የፓርላማ መቀመጫ አግኝተው እንደነበርና በተለይ ከ1997 ዓ.ም. የቅንጅት ተሳትፎ በኋላ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዳልቻሉና ይልቁንም ይደረግባቸው በነበረ ተፅዕኖ ሲፈረካከሱ፣ ሲካሰሱና እያደርም አንዳንዶቹ ጠርዝ የረገጠ የብሔር ማንነት ፖለቲካን በማራመድ አይደለም የዴሞክራሲን ሒደት ማደናቀፍ፣ የአገርንና የሕዝብን አንድነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት የሕዝብን አመኔታ እያጡ የመጡ ይመስላል ብዬ ነበር፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ቀዳሚ ዓላማ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝና የመንግሥት አመራር ሰጪ ለመሆን እንደሆነ ቢታወቅም፣ ለዚህ የሚያበቃ አቅምና ዓውድ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፖለቲካ ድርጅቶች ተግዳሮት እንዳለባቸው (ይህ እውነት ነውና) ካወቁና ከተገነዘቡ በተለመደው የፖለቲካ የውድድር ሥልትና የተቃዋሚ ሚናን ከመጫወት ባሻገርና የፖለቲካ ሥልጣን ከመጨበጥ በመለስ ወይም ሳያሻና ሳያስፈልግ የሕዝብና ማኅበራዊ አገልግሎት የመስጠት ዓላማና ተግባር (Civic Action) በማቀድ፣ በማስተባበር፣ በመተግበር የትግል ቁመናቸውን በሕዝባዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎት ጭምር ቢያጠናክሩ ውሎ አድሮ ለሥልጣን የሚያበቃቸውን የሕዝብ አመኔታና ተቀባይነት ሊያስገኝላቸው ይችላል የሚል ምልከታ ነበረኝ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፖለቲካ ድርጅቶች ፖለቲካዊ አቋም ምንም ይሁን ምን፣ ለአገራዊና ሕዝባዊ ሥጋቶች በጋራ መፍትሔ ለመፈለግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለሕዝብ ሊያረጋግጡ ይገባል የሚልም አስተያየት ነበረኝ፡፡ ዛሬስ ታዲያ? ወደፊትስ?
የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች ቁመናቸው በግለሰቦችና በብሔር ዙሪያ የተንጠለጠለ መሆኑ አያስገርምም፣ ምክንያቱም የዴሞክራሲ ባህልና ሥርዓት በሌለበትና ብሔርተኝነት ባየለበት ዓውድ የተፈጠሩ በመሆኑ ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ በኩል የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ፣ የሕዝብ ተቀባይነት፣ ድርጅታዊ የብቃት ቁመና እንደሌላቸው ተደርገው መቆጠራቸውም አያስደንቅም፣ ምክንያቱም ብቃቱ እንዲኖራቸው አይፈለግምና ነው፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች ከሞላ ጎደልም ቢሆን በአገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች እንሠራለን የሚሉ እስከሆነ ድረስ በአራት ጉዳዮች ላይ ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት ይገባቸዋል፡፡ አንድ ለሕዝብ ያላቸውን/ያለባቸውን ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ ሁለት የድርጅትና የፖሊሲ አመንጭነት አቅማቸውን ለማጠናከር የእርስ በርስ ተግባቦትን መፍጠር፣ ሦስት ሊቀናቸው በማይችል ምርጫ ማግሥት በውጤት ከመካሰስ አስቀድሞውን የምርጫ አጃቢ ሆኖ አለመቅረብ፣ አራተኛ ሕዝብና ማኅበራዊ አገልግሎት የመስጠት ዓላማና ተግባር (Civic Action) በማቀድ መሥራት፡፡
- መገናኛ ብዙኃን ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ ሕዝብ የሚለውን በማስተጋባት፣ መንግሥት የሚለውን በማሰማት፣ መረጃ በመቀበል የሁሉም ድምፅ በመሆን የሚያገለግል ኃይለኛ መሣሪያ የመሆኑን ያህል አገልግሎቱን የሚጠብቅና የሚፈልግ ብዙ ነው፡፡ መንግሥት ይፈልገዋል፣ ሕዝብም ይፈልገዋል፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪሉ ማኅበረሰብ ይፈልጉታል፣ ሁሉም የየራሳቸው መሣሪያ ሊያደርጉት ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሚናውና ተልዕኮው ከሦስት አቅጣጫዎች በሚመነጩ ምክንያቶች እየተምታታና አልፎ አልፎም አሉታዊና አፍራሽ ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታ ሲፈጠር ይታያል፡፡ አንዱ ከመንግሥት፣ የራሱ መገልገያ ሊያደርገው ስለሚፈልግና ከዚያ ውጭ እንዳይሠራ ተፅዕኖና ክልከላ ስለሚያደርግበት፣ ሌላው የፖለቲካ ድርጅቶችም እንደዚያው መሣሪያ ሊያደርጉት መፈለጋቸው፣ አሁንም ሌላው ሕዝብ የሚጠብቀው በሆነ ባልሆነ ሁሉ መንግሥትን የሚተችና የሚነቅፍ ሚዲያ ትክክለኛና ተመራጭ ተደርጎ መታየቱ፣ አሁንም ሌላው የችግር ምንጭ ራሱ ሚዲያው አንድም በተፅዕኖዎቹ ምክንያት አሊያም በተደበቀ ወገናዊነት ሙያውና ተግባሩ የሚጠይቀውን ምግባር ተከትሎ ለመሥራት የማይችል ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ይህም ማለት ውስብስብና ከፍተኛ ታቃርኖና ተግዳሮት ያለበትና ባለበት ሁኔታ እንዲሠራ ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ በሚፈይደውም ሆነ በማይፈይደው ሚና ከሁሉም አቅጣጫ ይታማል የሚል ትዝብትም ነበረኝ፡፡ ያም ሆኖ ሚዲያ የላቀ የሞራልና የሐሳብ ልዕልናን የሚያንፀባርቅ ምግባርና ተግባር ያለው ሊሆን እንደሚገባ፣ ሊጫወት ከሚችለውና ከሚገባው አገራዊና ሕዝባዊ ሚና አንፃር ይህን መጠበቅ የሚበዛ አይደለም፡፡ በዚያውም ልክ የሚዲያ ተጠቃሚዎች አጠቃቀማቸው ሞራላዊና ፍትሐዊ ምግባርንና ተግባርን በተላበሰ መልክ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህን ሁሉ ታዝቤና ብዬ ነበር፡፡ ዛሬስ ታዲያ? ወደፊትስ?
ሚዲያ በሚፈይደውም ሆነ በማይፈይደው ሚና ከሁሉም አቅጣጫ የሚታማ መሆኑ ካልቀረ የማንም መሣሪያ ሳይሆን፣ ወይም ለመሆን ሳይሞክር የዴሞክራሲ መሣሪያ ብቻ ለመሆንና በመሆን ለማገልገል በሚያደርገው ጥረት ቢታማ ይሻላል፡፡ የሚመለከታቸውም ሁሉ ሚዲያን ሊያሙት የሚገባቸው ከዚህ መሣሪያነቱ አንፃር ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ በመጨረሻም ያልኳቸው ነበሩ የተባሉት ዕይታዎቼና ምልከታዎቼ ዛሬ ላይ ሆኖ ሲታዩ እንደተባለው ሆነው አለመገኘታቸው ዕይታዎቹና ምልከታዎቹ ስህተት ነበሩ የሚያሰኝ ሳይሆን፣ ስህተቱ ዕድሎችንና ተግዳሮቶችንም በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል ኃይልና ቁመና ሊፈጠር አለመቻሉ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የተዘጋጀው በጸሐፊው “ማንነት በምግባርና በተግባር” በሚል ርዕስ ጳጉሜን 2011 ዓ.ም. በታተመ መጽሐፍ መነሻነት መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡