Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሳተላይት ቴሌኮም ዘርፍ ስመጥር የሆነው ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፈቃድ ጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የሳተላይት ቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ስመጥር የሆነው አቫንቲ ኮሙዩኒኬሽን ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ዓላማ እንዳለው ተናገረ። 

ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ያቀደው የአገሪቱን የኢንተርኔት ግንኙነት ማሳደግ ነው ሲሉ የአቫንቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካይል ዋይትሂል ለውጭ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። 

ይህንን ዕቅድ ለማሳካትም ኩባንያው የቴሌኮም የሥራ ፍቃድ ከኢትዮጵያ መንግሥት እንደጠየቀ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቴሌኮም ተቋማት ጋር አጋርነትን ለመፍጠር ኩባንያው ፍላጎት እንዳለው የገጹት ኃላፊው፣ በዚህም ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ውይይት መጀመሩን ዋይትሂል ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል። በተጨማሪም አቫንቲ በምሥራቅ አፍሪካ ለሚካሄደው መስፋፋት ሶማሊያን ቀጣዩ መዳረሻው የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል። 

አቫንቲ ባለፈው መስከረም ወር ተመሳሳይ ስምምነት ከቱርክ ቴሌኮም ኩባንያ ቱርክ ሳት (TurkSat) ጋር ማድረጉ ታውቋል።

ከፍተኛ የሳተላይት አቅም አቅራቢ አቫንቲ ኮሙዩኒኬሽንስ ከቱርክ ኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ኦፕሬተር ቱርክሳት ጋር የአምስት ዓመት የአጋርነት ስምምነት መፈራረሙን ኩባንያው ያወጣው መግለጫ ያመለክታል። አቫንቲና ቱርክሳት ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምሮ ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ በቅርቡ ያደረጉት ስምምነትም ምድራዊ መሠረተ ልማት ውስን በሆነባቸው ክልሎች ለሚገኙ ለአቫንቲና ቱርክሳት ደንበኞች እንዲሁም በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ሰፊና ቀጣይነት ያለው ሽፋንን ለማቅረብ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

ኩባንያዎቹ በፈጸሙት ስምምነት መሠረት የአቫንቲ ሁለት የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይቶች Avanti’s HYLAS 4 እና HYLAS 2 ሳተላይቶችን አቅምና ሽፋን ቱርክሳት ካመጠቃት አዲስ Türksat-5B ሳተላይት ጋር በማጣመር ለደንበኞቻቸው ዘመናዊና ከ100 Gbps በላይ ፍጥነት ያለው የግንኙነት አቅምን መፍጠር ያስችላቸዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት አልሚዎች ላይ የተጣለው ዕገዳና የቴሌኮም መሠረተ ልማት ከአገር ውስጥ ኦፕሬተሮች የመከራየት አስገዳጅ አሠራር የኢትዮ ቴሌኮም የገበያ አቅምን ፈጥሯል። 

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውጭ የግል የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ያገኘው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በዚሁ አስገዳጅ ሕግ መሠረት የራሱን የቴሌኮም መሠረተ ልማት መገንባት ስለማይችል የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት በኪራይ የመጠቀም ግዴታ ውስጥ ገብቷል።

ይሁን እንጂ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያና ኢትዮ ቴሌኮም በመሠረተ ልማት መጋራት ስምምነትና በክፍያ ውል ላይ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ሽምግልና በመሠረተ ልማት መጋራት ዕቅድ ላይ በሁለቱ ኦፕሬተሮች (ኢትዮ ቴሌኮምና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ) መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በመጨረሻ መፍትሔ አግኝቷል። 

በዚህም መሠረት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት መጠቀም የጀመረ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥም ከኢትዮ ቴሌኮም ለሚያገኘው የመሠረተ ልማት መጋራት አገልግሎት 743.6 ሚሊዮን ብር ክፍያ ፈጽሟል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች