በተያዘው በጀት ዓመት በ74 ተቋማት እየተተገበረ ያለው፣ በአንድ ክልል በማሳያነት የተጀመረውና ከመጪው ዓመት ጀምሮ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት በአስገዳጅነት እንደሚተገብሩት የሚጠበቀው የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ በ2017 ዓ.ም. በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በ2016 በጀት ዓመት 169 የፌዴራል ተቋማት የማኑዋል ግዥን አስቀርተው ሙሉ በሙሉ ይተገብሩታል ያለውን የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት፣ በሲዳማ ክልል በማሳያነት በማስጀመር በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ፣ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ 74 የፌዴራል ተቋማት ተግባራዊ ያደረጉትን የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት፣ ከቀጣዩ የበጀት ዓመት ጀምሮ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ከፌዴራል ተቋማት በተጨማሪ የግዥ ሥርዓቱ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሲዳማ ክልል እንደሚጀምር ተጠቅሶ፣ ከ2017 የበጀት ዓመት ጀምሮ ደግሞ ሁሉም ክልሎች ወደ ሥርዓቱ እንደሚገቡ ታውቋል፡፡
ወደፊት ወደ ዞንና ወረዳዎች በመውረድ የማኑዋል ግዥ ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሮኒክ ግዥ የሚቀየርበት ሁኔታ ይፈጠራል ተብሏል፡፡
እስካሁን ስምንት ሺሕ ያህል አቅራቢዎች እንደተመዘገቡ የተገለጸ ሲሆን፣ አንድ ድርጅት ከአንድ ዘርፍ በላይ ሊመዘገብ ስለሚችል ቁጥሩ 16 ሺሕ እንደሚደርስ፣ በቀጣይ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ወደ አሠራሩ ሲገቡ ከ30 ሺሕ በላይ አቅራቢዎች ወደ ሲስተሙ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
‹‹በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ እንዲፀድቅ መላኩ የሚታወስ ሲሆን፣ አዋጁ ሲፀድቅ 45 ቀናት የሚፈጅ አንድ ጨረታ በ15 ቀናት እንዲጠናቀቅ ይደረጋል፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ሐሙስ ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከተውጣጡ የግዥና የንብረት፣ እንዲሁም ተዛማጅ የሥራ ክፍል ከተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢሌሌ ሆቴል የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩም የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩት የፌዴራል ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ተሞክሯቸውን አቅርበዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ ከንክኪ የፀዳ፣ ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ፣ እንዲሁም ግልጽ መሆኑ ዘርፎቹ ለሙስና ያላቸውን ተጋላጭነት ከመቀነሱ በተጨማሪ፣ ነጋዴዎች (አቅራቢዎች) ምርትና አገልግሎታቸውን ያለ ውጣ ውረድ ተወዳድረው መሸጥ እንዳስቻላቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ጨረታ ከተከፈተ በኋላ ምክንያታቸው ሳይታወቅ ሲስተሙ ላይ የተሰበሰቡት ዳታዎች የሚደበቁ በመሆናቸው የሲስተም መቆራረጥ፣ አሸናፊ ተጫራቾች በዋጋ ማቅረቢያ ባሸነፉበት ዕቃ አለማቅረብና ተጠያቂነት አለመኖር በሒደቱ ያጋጠመው ችግሮች ተብለው ቀርበዋል፡፡
በተጨማሪም ትልልቅ አምራቾችና አቅራቢዎች በሲስተሙ ያልተመዘገቡና የማይወዳደሩ መሆናቸውን፣ በግዥ ሒደቱ ያሉት ሰነዶች መልሰው የሚገኙበት ሲስተም አለመዘርጋቱን በማውሳት፣ በቀጣይ ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አቅራቢዎች በሥርዓቱ እንዲመዘገቡ ተገቢ ቅስቀሳና ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ፣ ሶፍትዌሩ ያሉበትን ችግሮች ከሠራው ድርጅት ጋር በቅርበት በመሆን እንዲያሻሽል ተቋማቱ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም እንደተገለጸው በዘንድሮ የበጀት ዓመት በመጀመርያ ስድስት ወራት፣ የመንግሥት ተቋማት በኤሌክትሮኒክ ግዥ ከ38.8 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ፈጽመዋል።
በተያዘው ዓመት 74 የፌደራል ተቋማት ወደ ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ቢገቡም፣ በአሁኑ ወቅት ከ90 በላይ የፌዴራል ተቋማት ሲስተሙን አይጠቅሙም፡፡ ከቀጣዩ የበጀት ዓመት ጀምሮ የትኛውም የፌዴራል ተቋም ግዥውን በአዲሱ ሥርዓት እንዲያደርግ ይገደዳል ተብሏል፡፡