በሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ ጎሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በጥይት የተገደሉት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የአቶ ግርማ የሺጥላ (1967-2015)፣ የቀብር ሥነ ሥርዓት በተወለዱበት መሀል ሜዳ እንደሚፈጸም ታወቀ፡፡
ምንም እንኳን ቤተሰቦቻቸው የአቶ ግርማን አስከሬን ለመቀበል ከሚያዝያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ንጋት ጀምሮ እየተጠባበቁም ቢሆንም፣ ከትናንት በስቲያ ሚያዝያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው እንዳስታወቀው፣ የአቶ ግርማ አስከሬን ዛሬ ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በወዳጅነት አደባባይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ሽኝት ይደረግለታል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ በመሆን በታኅሳስ ወር 1988 ዓ.ም. የአመራርነት ሥራ እንደጀመሩ የተገለጸው አቶ ግርማ፣ በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸውንና ለሰባት ዓመት መሥራታቸው ታውቋል፡፡
በጥር ወር 1995 ዓ.ም. ከወረዳ ወደ ዞን በመሸጋገርም፣ የቀድሞው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሰሜን ሸዋ ዞን ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ እንደነበሩና ለአንድ ዓመት በኃላፊነት ቦታ መቆየታቸው የተገለጸው አቶ ግርማ፣ ከጥር 1996 ዓ.ም. ጀምሮ በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሹመትን አግኝተዋል።
በ2002 ዓ.ም. የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) ትምህርት ዘርፍ ያገኙት አቶ ግርማ፣ በዚያው ዓመት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪም ሆነው እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ፣ በዚያው ዓመት የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው ተሾመዋል።
በምክትል አስተዳዳሪነት ለአራት ዓመታት የቆዩት አቶ ግርማ፣ ዞኑን የመምራት ኃላፊነት በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ተረክበዋል። የሰሜን ሸዋ ዞንን ለሁለት ዓመታት የመሩት አቶ ግርማ፣ በ2012 ዓ.ም. በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መያዛቸውንና ክልሉን በከፍተኛ ኃላፊነት እየመሩ እንደነበር ሪፖርተር ካገኘው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡
ከአቶ ግርማ የሺጥላ ጋር ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዱ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሾፌር የነበሩት አቶ ልየው መንጌ መሆናቸውንና እንደ ክልሉ መግለጫም፣ ከአቶ ግርማ ጋር ግድያ የተፈጸመባቸው አምስት ግለሰቦች መሆናቸው ተነገሯል፡፡ አቶ ግርማ ባለትዳርና የልጆች አባት መሆናቸውም ታውቋል፡፡