‹‹በጦርነት የወደሙ ከተሞችን መልሶ ለማቋቋም የሚቻለው በገንዘብ ብቻ ነው ብለን አናምንም፤›› ሲሉ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ አስታወቁ፡፡
የሰሜኑ ጦርነት በነበረባቸው ከተሞችና በኦሮሚያ ክልል በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ የወደሙ ከተሞችን መልሶ ለማቋቋም የሚቻለው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ ከተሞች እርስ በርሳቸው እንዲደጋገፉ በማድረግም ጭምር ነው ሲሉ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት ሚያዝያ 21 እና 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከ300 በላይ የከተማ ከንቲባዎችና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ይገኙበታል የተባለውንና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የተዘጋጀውን ‹‹የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች መድረክ›› አስመልክተው፣ ሐሙስ ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
‹‹በኦሮሚያ ክልል ወለጋ የተወሰኑ ከተሞች የወደሙበት አጋጣሚ አለ፣ እንዲሁም ደግሞ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከተሞች በከፍተኛ ደረጃ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ እርስ በርሳችን የእህትማማችነት መድረክ በማጠናከር፣ እነሱን መልሰን የምንገነባበትና የሕዝባችንን መንፈስ የምናድስበት የኢትዮጵያ ከተሞች የከንቲባዎች ፎረም ተዘጋጅቷል፤›› ሲሉ ወ/ሮ ጫልቱ አብራርተዋል፡፡
በጦርነት ምን ያህል ከተሞች እንደወደሙ፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግና ምን ዕቅድ እንደተያዘ ጥያቄ የቀረበላቸው ሚኒስትሯ፣ ‹‹በጦርነት የወደሙ ከተሞችን መልሶ ማቋቋም የሚቻለው በገንዝብ ብቻ ነው ብለን አናምንም፡፡ አጠቃላይ እንደ አገር ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልጋል የሚለውን እንደ አገር የወጣ የገንዘብ መጠን አለ፡፡ የከተሞችንም በራሳችን መንገድ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ቀጥታ ቁጥሩን መናገር ቢያስቸግርም፣ ከፍተኛ ውድመት በከተሞቻችን ላይ እንደደረሰ ሁላችንም ማየት እንችላለን፡፡ ያን መቀየር የምንችለው በገንዘብና በበጀት ብቻ ነው ብለን አናምንም፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከምንም በላይ የመከባበርና የመተጋገዝ ከፍተኛ ልምድ ያለ በመሆኑ፣ ከውጭ አገሮች ጋር ሲካሄዱ የነበሩ የከተሞች እህትማማችነትን በቀጥታ ወደ አገር ውስጥ በማምጣት፣ ጦርነት ያልነበረባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች በጦርነት የተጎዱትን ለመርዳት የሞራልም የሀብትም ብቃት አላቸው ብለው እንደሚያኑም ተናግረዋል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት ምክንያት በማድረግ በአጠቃላይ በከተሞች ላይ የደረሱትን ውድመቶች ከሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመሆን ሳይንሳዊ ጥናቶች ሲያካሄዱ እንደቆዩ፣ ይህንን ጉዳይ ሲመሩ የነበሩት የፋይናንስ የከተማና መሠረተ ልማት፣ የሰላም፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴሮችና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች አባል የሆኑበት አንድ የፌዴራል ኮሚቴ የወደሙ ከተሞችን መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ መያዙን ሚኒስተሯ ገልጸዋል፡፡
ኮሚቴው በሦስተኛ ወገን ከየክልል ተጠንተው የሚመጡለትን ሳይንሳዊ ጥናቶች እየተከታተለ እንደሆነ፣ ከተሞች የየራሳቸውን በራሳቸው መንገድ እየሠሩ ቢሆንም፣ በጦርነት የተጎዱ ከተሞች ያልተጎዱትን የሚያቋቁሙበትን መደላድል ለመፍጠር መታቀዱንም አክለዋል፡፡
‹‹በተለይ በሰሜኑ ጦርነት ከተሞቻችን ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ዛሬ ያለፈውን ሁሉ ይቅር ብለን ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ፣ የከተሞች የአመራር ለአመራርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለን እናምናለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በፎረሙ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ ነገር የ‹‹ሲስተር ሲቲ ኢንጌጅመንት›› መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ከተሞችን ውጭ አገር ካሉ ከተሞች ጋር የእህትማማችነት መድረክ ከአሁን በፊት ሲካሄድ ቢቆይም፣ ያ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪ በአገር ውስጥ ያሉ ከተሞችን እርስ በርስ ማጠናከር ነው ተብሏል፡፡
‹‹ከተሞች ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት እንደ ዕንብርት የሚወሰዱ ናቸው፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ያለ ከተማ ዕድገት ሊገለጽበት የሚችል አንዳችም መንገድ ስለማይኖር የየትኛውም አገር የኢኮኖሚ ዕድገት በከተማ ዕድገት የሚታይበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ፣ ከተሜነት በቀጥታ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ይያያዛል ብለዋል፡፡
የከተሜነት ሒደት በኢትዮጵያ ለረዥም ዘመን ያስቆጠረ ቢሆንም ዕድገቱ ከዕድሜው አኳያ ሲታይ ዘገምተኛ እንደሆነ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የኋላቀርነት እንደነበረበትና የኢትዮጵያ ከተሞች ዕድገት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አክለው ተናግረዋል፡፡
‹‹ከተሜነትና አምራችነት የሚያያዙ መሆናቸውን ለብዙ ጊዜ ዘንግተናል፤›› ያሉት ወ/ሮ ጫልቱ፣ ‹‹ለአብነትም ከተማ ማለት ከአምራችነት ውጪ እንደሆነ ያለን ዕሳቤ ነው፤›› ብለዋል፡፡