Thursday, June 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አሠራርን ለማዘመን ተብሎ ትርምስ መፍጠር ተገቢ አይደለም!

የነዳጅ ሽያጭን በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ለማከናወን የተጀመረው አዲስ አሠራር ትርምስ ፈጥሯል፡፡ በበርካታ አካባቢዎች በነዳጅ ማደያዎች የተስተዋሉ ረጃጅም ሠልፎች፣ አዲሱ አሠራር ክለሳ እንደሚያስፈልገው በሚገባ ያመላከቱ ናቸው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ለዲጂታል አሠራሮች ባዕድ በሆነበት፣ በቂ የመሠረተ ልማት አቅርቦት በሌለበት፣ እንዲሁም ዲጂታል አሠራርን በሙከራ ማለማመድ ባልተቻለበት ሁኔታ ሁሉንም ተገልጋዮች በአንደ መነጽር በማየት ትርምስ መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ነዳጅን በቴሌ ብር ወይም በሌላ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ለመቀየር ሲታሰብ፣ ጎን ለጎን ሌሎች የክፍያ አማራጮች መታየት ነበረባቸው፡፡ የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ብር ላይ ‹‹ለአምጪው እንዲከፈል ሕግ ያስገድዳል›› የሚለው ሕጋዊ አሠራር ተጥሶ፣ በነዳጅ ግብይት ወቅት ጥሬ ገንዘብ አንቀበልም ማለት አይቻልም፡፡ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን ቀድመው በጀመሩት በሠለጠኑ አገሮች ሳይቀር፣ የፍጆታ ዕቃዎችንም ሆነ ነዳጅን በጥሬ ገንዘብ መገብየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው ፈቃደኝነቱን እስካልገለጸ ድረስ በማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ወይም ከመንግሥት ተቋማት ጋር ባለው ግንኙነት የኤሌክትሮኒክ መልዕክትን እንዲጠቀም፣ እንዲያቀርብ ወይም እንዲቀበል አይገደድም ተብሎ በኤሌክትሮኒክ ግብይት አዋጅ ቁጥር 1205/2012 መደንገጉም አይረሳ፡፡

ከላይ የተጠቀሰው አዋጅ ሳይሻር ወይም ሳይሻሻል በአስገዳጅ ጥሬ ገንዘብ አንቀበልም ማለት አይቻልም፡፡ የኤሌክትሮኒክ ግብይት እንደ አማራጭ ጠቃሚ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በአገር ሰላም እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝሙ አስጨናቂ የነዳጅ ወረፋዎችን ከተማ ውስጥ ማየት፣ ምን ያህል ግዴለሽ አሠራሮች መንሰራፋታቸውን አመላካች ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከዲጂታል አሠራር ጋር ያለው ትውውቅ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ እየታወቀ፣ በአጭር ማሳሰቢያ ከዚህ ቀን ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ይከናወናል ሲባልም የሚፈጠረው ትርምስ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ቀድሞ ማሰብ ተገቢ ነበር፡፡ ሁሉንም ተገልጋዮች በአንድ ቅርጫት ውስጥ በማጨቅ በቴሌ ብር ከፍላችሁ ተገልገሉ ማለት፣ አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ በዜጎች ጊዜና ገንዘብ መቀለድ ነው፡፡ ተገልጋዮች ስለዲጂታል አሠራር ዕውቀት እንዲኖራቸው ተከታታይ ትምህርት መስጠት ይቻል ነበር፡፡ በቴሌ ብርም ሆነ በሌሎች የመገበያያ ዘዴዎች እኩል ማለማመድ አያቅትም ነበር፡፡ ሌሎች አማራጮችንም እንዲሁ፡፡

እንኳንስ ተገልጋዮች ብዙዎቹ ማደያዎች ለኤሌክትሮኒክ ግብይት ዝግጁ ባልሆኑበት፣ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በግዳጅ ዲጂታል ካልሆናችሁ ማለት ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች አካላት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በአንዳንድ ወገኖች ለውጥን እንዳለመፈለግ ወይም እንደ መቃረን ተደርጎ ሲነገር ይደመጣል፡፡ አላስፈላጊ የሆኑ ምሳሌዎችም እየተጠቀሱ አዲሱን አሠራር የሚቃወሙ ተብሎም ይፈረጃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጠቅልሎ መሰልቀጥ ዓይነት አካሄድ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የነዳጅና የኢነርጂ ባለሥልጣንም ሆነ ኢትዮ ቴሌኮም አዲሱን አሠራር በትብብር ሲያስጀምሩ፣ ከምንም በፊት መቅደም የነበረበት የሙከራ ፕሮጀክት ነበር፡፡ የሙከራ ፕሮጀክት አሠራሩን በሚገባ በመገምገም ያለውን ጠቀሜታና ተቀባይነት ማጤን መልካም ይሆን ነበር፡፡ አሁን ትርምስ ተፈጥሮ ተቃውሞ ሲሰማ ችግሩን ወደ ሌሎች መግፋትና ማሳበብ ተገቢ አይደለም፡፡ የሥራ ጊዜያቸው በነዳጅ ወረፋ ከባከነባቸው ጀምሮ፣ ገቢያቸውን በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የመሠረቱ ወገኖች ጭምር ከፍተኛ ጉዳት ገጥሟቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ለደረሰባቸው እንግልት ካሳ ባያገኙ እንኳ እንዴት ይቅርታ የሚል ይጠፋል? አሠራርን ማዘመን ተገቢና ተቀባይነት ያለው ተግባር ቢሆንም የሰዎችን መብት መጋፋት አይገባም፡፡

ብዙዎቹ ተገልጋዮች የባንክ ተጠቃሚ በመሆናቸው ከአካውንታቸው የሚከፍሉበትን አሠራር ተግባራዊ ማድረግም ይቻላል፡፡ ባንኮች በነፃ ገበያ ውድድር እንደ ኢትዮ ቴሌኮም አማራጭ መተግበሪያቸውን ይዘው መሰማራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ዋነኛ ዓላማ ጤነኛና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር ነው፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት ሞኖፖሊ ስለማይፈቀድ ውድድሩ ፍትሐዊ እንዲሆንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲገኝ ማስቻል ላይ ይተኮር፡፡ ከነዳጅ በተጨማሪ ሌሎች ግብይቶችም በኤሌክትሮኒክ ዘዴዎች ሲንቀሳቀሱ ተገልጋዮች በርካታ አማራጮችን እንዲያገኙ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የኢንተርኔት መሠረተ ልማቱን ማስፋፋትና ተደራሽነቱን መጨመር ይገባል፡፡ እንዲሁም ከዲጂታል ዓለም የራቁትን ቀስ በቀስ በማለማመድ ወደ ገበያው መሳብ አስፈላጊ ነው፡፡ ድንገት እየተነሱ አገሪቱን ጥሬ ገንዘብ አልባ ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ፣ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ሕጋዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ሕጋዊ ጥያቄ ሲነሳ በሕጋዊ መንገድ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ አላስፈላጊ ምሳሌዎችን እያጣቀሱ ጣትን ሌላ ወገን ላይ መቀሰር ተገቢ አይደለም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ150 በላይ የሚሆኑ ነዳጅ ማደያዎች በረጃጅም ሠልፎች ከተጨናነቁና ትርምስ ከተፈጠረ በኋላ፣ ይመለከታቸዋል ከሚባሉ አካላት ይሰጡ የነበሩ ማብራሪያዎችና ማሳሰቢያዎች ቀደም ሲል መከናወን የነበረባቸው ናቸው፡፡ የነዳጅ ግብይቱ በዲጂታል የክፍያ ዘዴ ብቻ እንደሚሆን ለተገልጋዮች ሲነገር፣ ቀደም ብለው ዝግጅት እንዲያደርጉ ሰፋ ያለ ጊዜ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ሕጋዊነቱንም መገንዘብ ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ ከዲጂታል ክፍያው ጋር ሌሎች አማራጮችን ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻል ነበር፡፡ የቴሌ ብር ተገልጋዮች ብቻ የሚጠቀሙባቸው የተመረጡ ማደያዎች መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ እነዚህ ተገልጋዮች ለአራትና ለአምስት ሰዓታት ተገትረው ወረፋ ከሚጠብቁ፣ የተወሰነ ርቀት ተጉዘው በዲጂታል ክፍያ ቢስተናገዱ ይመርጡ ነበር፡፡ የባለሙያዎች ምክረ ሐሳቦች ቢደመጡ ደግሞ ሌሎች ጠቃሚ ግብዓቶች ይገኙ ነበር፡፡ አሁንም እየተሰሙ ያሉ እሮሮዎችንና አቤቱታዎችን በማዳመጥ ችግሩን ለማቃለል መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት አሠራር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይብሳል፡፡

እዚህ ላይ ሌላው መነሳት ያለበት መሠረታዊ ነጥብ የሰዎች መብትና ነፃነት ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውም የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንደሚኖርበት በሕግ ተደንግጓል፡፡ መንግሥት አሠራሩ ለሕዝብ አመቺ በማይሆንበት ጊዜ የማስተካከል ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ግዴታውን መወጣት ካልቻለ ዜጎች መብታቸው እንደተጣሰና ነፃነታቸው እንደተገፈፈ ይቆጥሩታል፡፡ ዘመናዊ አሠራር አሰፍናለሁ ብሎ የተነሳ መንግሥትም ሆነ ሹማምንቱ ቅሬታ ሲቀርብላቸው፣ ችግሩን በፍጥነት በመረዳት የመፍትሔ ዕርምጃ የማይወስዱ ከሆነ አሠራሩ የዜጎችን መብት እየጎዳ እንደሆነ ነው የሚታሰበው፡፡ በተጨማሪም የሚፈለግባቸውን ግዴታ እየተወጡ ከንግድ ውድድሩ ፍትሐዊ ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው ወገኖችም፣ በኢፍትሐዊ አሠራር መብታቸውን እያጡ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ለዚህም ነው አዲሱ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ግራና ቀኝ ማማተር ነበረበት የምንለው፡፡ ዘመናዊ አሠራርን የማስፈን ተገቢነት ላይ ተቃውሞ መኖር የሌለበትን ያህል፣ አሠራሩ ሲተዋወቅ ደግሞ ሕግ እየጣሰ ጉዳት ማስከተል አይኖርበትም፡፡ አሁንም የተፈጠረውን ችግር በመገንዘብ ለመፍትሔ መረባረብ ይገባል እንጂ፣ ዘመናዊ አሠራር ለማስፈን ተብሎ ትርምስ መፍጠር ተገቢ አይደለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...

በተቃርኖዎች መሀል የሚዋልለው የብልፅግና መንግሥት

ርዕዮተ ዓለም እንኳ የሌለው ይሉታል የሚቃወሙት ወገኖች፡፡ እሱ ግን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...