Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ ላይ ‹‹መሠረታዊ ቅኝት›› እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የትግራይ ክልል ተሳታፊዎች የተገኙበት የኢንቨስመንት ፎረም ተካሄደ

ለማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገትና ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ‹‹ጠቃሚ ጉዳይ›› በመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ ‹‹መሠረታዊ ቅኝት›› እየተደረገበት መሆኑ ተገለጸ፡፡

በምንዛሪ ሥርዓቱ ላይ መሠረታዊ ቅኝት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ሲሆኑ፣ ምንዛሪን በሚመለከት የአገሪቱ ሁሉም ፖሊሲዎችና ደንቦች እየታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‹‹ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊነቶች ውስጥ አንደኛው የውጭ ምንዛሪ መረጋጋትን ማረጋገጥ›› እንደሆነ የተናገሩት ገዥው፣ ይህንንም ለማረጋገጥ ጉልህ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸውና እየተሠሩ እንደሆነም ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› (Invest Ethiopia) በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አዘጋጅነት ከሚያዝያ 18 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በርካታ የመንግሥት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ አቶ ማሞ ከሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎችና እንግዶች ጋር ባደረጉት የፓናል ውይይት፣ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ያለውን ጠቀሜታና ዕድል ለተጋባዥ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሀብቶች አስረድተዋል፡፡

የተለያዩ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጋቸውን፣ የባንክ አገልግሎት ዓይነት ዘርፎች ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ ክፍት ተደርገው ሌሎች የሕግ ማዕቀፎች በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገዥው ተናግረዋል፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የባንክ ሥራ አዋጅን ጨምሮ እየዘጋጁ ያሉትን ሌሎች ሕግጋቶች በማጠናቀቅ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ እንደሚላኩ፣ ከዚያም የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለማግኘት ማመልከት እንደሚችሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

የቴሌኮም አገልግሎት ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በመሆኑ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውሰው፣ በኬንያው ሳፋሪኮም ሥር ያለው ኤምፔሳ (MPesa) የሞባይል ገንዘብ መተግበሪያ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ፈቃድ ሊሰጠው እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ካደረጉት የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና ሚኒስትር ደኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ይገኙበታል። በፎረሙ መክፈቻ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው እዮብ (ዶ/ር) መንግሥት ለመተግበር ይፋ ሊያደርገው እያዘጋጀው ስላለው ሁለተኛው አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚውን ሁኔታ ለማሻሻል እያከናወናቸው ስላሉ ሥራዎች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ስላሉት ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ሚኒስትር ደኤታው ለተሳታፊዎቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግና ማደግ ጊዜው አሁን ነው›› በሚል አጀንዳ የተካሄደው ፎረሙ፣ የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮን ጨምሮ የሁሉም ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎች፣ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮምንና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለተሳታፊዎች ዓውደ ትዕይንት አዘጋጅተው ነበር፡፡

በአብዛኛው ከቻይና ነገር ግን ከ22 አገሮች የመጡ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በሦስቱ ቀናት ፎረም ላይ በመገኘት፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች