Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ለፋሲካ በዓል ከጀርመን ከመጡ ወዳጆቼ ጋር ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርን ስንዝናና ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ዓይቻቸው የማላውቃቸውንና አዳዲስ የመዝናኛ ሥፍራዎች ጎበኘሁዋቸው፡፡ ከፒያሳ እስከ ካዛንቺስ፣ ከቦሌ እስከ ሃያ ሁለት ውስጥ ለውስጥ ያሉትን መጠጥ ቤቶች፣ እንዲሁም በከተማው አሉ የሚባሉትን ክለቦች ተራ በተራ ዞርንባቸው፡፡ እነዚህን ቦታዎች እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ይታደሙባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ሁሌም ሙሉ ናቸው፡፡ ለእኔ ዓይነቱ በትዳር ከታሰረ ዓመታት ለተቆጠሩበት ሰው እነዚህ ያየኹዋቸው ቦታዎች በጣም ለየት ይላሉ፡፡ ለየት ይላሉ ብቻ ሳይሆን በጣም ያስፈራሉ፡፡ ለምሳሌ ፒያሳና ሰሜን ሆቴል አካባቢ ያሉ መጠጥ ቤቶች በወጣት ሴተኛ አዳሪዎች የተሞሉ በማለት ብቻ አይገለጹም፡፡ ሃያ ሁለት፣ ካዛንቺስና ቺቺኒያ ደግሞ እጅግ በጣም ይብሳሉ፡፡ ይኼ እንግዲህ እንጀራ ፍለጋ መንገድ ላይ የተሰማሩትን እህቶቻችንን አይጨምርም፡፡ በአጠቃላይ ግን ሁኔታው ያስፈራል፡፡

ለገጠመኜ መነሻ የሆነችው በአንደኛው የፒያሳ ሆቴል ውስጥ ያጋጠመችኝ ወጣት ዕድሜዋ ከ18 አይበልጥም፡፡ የታሸገ ውኃዋን እየጠጣች የተስተናጋጆችን ቀልብ ለመሳብ ወዲህና ወዲህ እያለች ስትውረገረግ በሥራው ጥርሷን የነቀለች ትመስላለች፡፡ በዓይኔ ጠቀስ አድርጌ አጠገባችን እንድትቀመጥ ጋበዝኳት፡፡ በደስታ እየተፍለቀለቀች መጥታ ተቀመጠች፡፡ ከሁኔታዋ መጠጥ እንደማትፈልግ በመረዳትና ለዚህች ታዳጊም መጋበዝ አስፈላጊ ባለመሆኑ ያለ ግብዣ አዋራት ጀመር፡፡ የተለመደው ማን ነሽ? ከየት ነሽ? ለምን እዚህ ሥራ ውስጥ ገባሽ? ማለት አስፈላጊ ባለመሆኑ፣ ‹‹የተስማማሽ ትመስያለሽ ሥራ እንዴት ነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹የእኛ ሥራማ በኃጥያት የተሞላ ነው…›› አለችኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› አልኳት፡፡ ‹‹አልሰማህም? ኑሮ ካሉት ፍሪጅ ይሞቃል ማለቷን ኮካ?›› ብላኝ፣ ‹‹እባክህ ተወኝ ካንተ ጋር ስለፋለፍ ቢዝነስ እንዳያመልጠኝ…›› ብላ ተነሳች፡፡

ልጅቷ በአልባሳትና በጌጣጌጥ ብትዋብም ውስጧ የታመቀ ቁጭት ያለ ስለሚመስል ልለቃት አልፈለግኩም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲገኝ የሰዎችን ብሶት ማዳመጥ ስለሚያስፈልግ አንድ መላ መታሁ፡፡ ‹‹ለአንድ ቢዝነስ ልክፈልሽና እዚህ ሆነሽ አዋሪኝ?›› ስላት አላመነችም፡፡ ‹‹አምስት መቶ ብር አምጣ ሃያ ደቂቃ ይፈቀድልሃል…›› ብላኝ ለመሄድ ተነሳች፡፡ ወዲያውኑ ኪሴ ገብቼ ያለችውን አስጨብጫት ወሬ ጀመርን፡፡ ጓደኞቼ መጠጣቸውን እየተጎነጩ የጦፈ ወሬ ስለያዙ የእኔና የልጅቷ ወሬ አልሳባቸውም፡፡ ልጅቷ፣ ‹‹በእርግጥ ብሩን የሰጠኸኝ ልታዋራኝ ብቻ ነው?›› በማለት አላምንህም በሚል ስሜት ጠየቀችኝ፡፡ መዋሸት ስለነበረብኝ፣ ‹‹ከቆንጆ ጋር ከመዳራት ይልቅ ዓይን ዓይኗን እያየሁ ማውራት ስለምወድ ነው…›› ብዬ እያሳሳቅኳት ወሬያችንን ቀጠልን፡፡

ልጅቷ እዚህ ሥራ ውስጥ ከገባች ሁለት ዓመት እንዳለፋት፣ በእነዚህ ዓመታት ከታዳጊ እስከ አዛውንት ድረስ አንሶላ መጋፈፏን ነገረችኝ፡፡ ‹‹አብረውኝ የተኙ ቢሠለፉ ከፒያሳ ቦሌ ይደርሳሉ፤›› ስትለኝ ገረመኝ፡፡ መጠጥ እየጠጣች የደረሰባትን ስቃይ ስታስታውስ ስለሚያንገሸግሻት ላለፉት ሦስት ወራት መጠጣት እንዳቆመች ነግራኝ፣ ከዚህ ሕይወት ውስጥ ለመውጣት ብትሞክር ግን እንዳልቻለች አወጋችኝ፡፡ እሷ እንደምትለው ፒያሳ፣ ካዛንቺስ፣ ሃያ ሁለትና ቺቺኒያ ድረስ ትንንሽ ሴት ልጆች በሴተኛ አዳሪነት ይተዳደራሉ፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ አነሰ ቢባል ከሃያ በላይ ሴቶች ይገኛሉ፡፡  ሁሉም ለመኖር ሲሉ ሥጋቸውን ሸጠው ያድራሉ፡፡ ሥነ ምግባር ከጎደለው ባለጌ ጀምሮ የተከበሩ የተባሉ ድረስ ይጎበኙዋቸዋል፡፡

እሷ ለምሳሌ ባለትዳርና የትልልቅ ልጆች አባት የሆኑ ደንበኞች አሉዋት፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ግንኙነት የሚያምራቸው ከጠጡ በኋላ ነው፡፡ ከመጠጥ በፊት አንዳንዶች ቢመጡም አብዛኞቹ ጠገብ ካሉ በኋላ ስለሚመጡ የሚያቀርቡት ጥያቄ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ያለ ኮንዶም መገናኘት ከሚፈልገው ጀምሮ ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ካልሆነ ብለው ድርቅ የሚሉ በሽ መሆናቸውን ነገረችኝ፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት ምክንያት ውድድሩ አንገት ለአንገት በመሆኑ ሕይወት ጥቀርሻ ሆናባታለች፡፡ ‹‹እኔ ዛሬ እንቢ ካልኩ ደንበኞቼ ወደሌላ ስለሚሄዱ ሳልፈልግ በግድ የታዘዝኩትን መፈጸም ጀምሬያለሁ…›› ስትለኝ ደነገጥኩ፡፡

ይህች አንድ ፍሬ ልጅ በሕፃንነቷ በሥቃይ ያለ እናት አባት ማደጓን፣ የረባ እንኳ ትምህርት ሳትቀስም ወደ ሴተኛ አዳሪነት በልጅነቷ መግባቷን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ምድረ ሰካራም እየረገጠና እየደበደበ፣ አስገድዶ እየደፈራት፣ ከዚያ አልፎ ተርፎም ይኼንን መራራ ኑሮ ለመቋቋም የታዘዘችውን እየፈጸመች እንደምትኖር ነገረችኝ፡፡ ‹‹አንዳንድ ብርቱዎች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኞቹ ሴተኛ አዳሪዎች ገንዘብ ይዞ በሚመጣው ሰው ፍላጎት ተፅዕኖ ሥር ናቸው…›› ስትለኝ በጣም አዘንኩ፡፡

ልጅቷ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚፈጽሙ ‹‹ባለትዳር ነን›› የሚሉ ጅንኖች ጭምር ናቸው ትላለች፡፡ ‹‹አንዳንዱ ሚኒስትር ወይም የአገር አስተዳዳሪ ይመስል ዝንጥ ብሎ ተኮፍሶ ሲጠጣ ስታየው ሰው ይመስላል፡፡ ክላስ ውስጥ ሲገባ ግን ወይ አውሬ አሊያም ሰይጣን ሆኖ አስደንጋጭ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ አለበለዚያም በጉልበት አስገድዶ የልቡን አድርሶ ይሄዳል…›› ስትለኝ ገረመኝ፡፡ ይህች ልጅ ብዙ የምትለው ነገር ቢኖርም አንዱ ጠቀሳት መሰለኝ፣ ‹‹በል ሰዓቱ አልቋል ልሂድ…›› ብላኝ ተነሳች፡፡ ‹‹በአጠቃላይ ይህ ሕይወት ምን ይመስላል?›› በማለት ስጠይቃት፣ ‹‹የምንኖርበት ሕይወት ገሃነም ነው፣ እኛ ሸሌዎቹና ደንበኞቻችን ደግሞ የተኮነኑ ነፍሶች…›› ብላኝ ተሰናበተችኝ፡፡

ወገኖቼ የአገራችን ችግሮች እጅግ በጣም ጥልቅና ሰፊ ከመሆናቸው የተነሳ እንቅልፍ የሚነሱ ቢሆንም፣ እኛ ግን ለየትኛው ቅድሚያ ሰጥተን ደረጃ በደረጃ ከችግሮቹ ለመላቀቅ የሚያስችለን ሁኔታ ውስጥ ያለን አንመስልም፡፡ ድህነት ቤቱን የሠራባት ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርን የሚያሳስቡን ነገሮች ለማንም የማይጠቅሙ መሆናቸውን ሳስብ ደግሞ ውስጤ በንዴት ይጨሳል፡፡ ያልበላንን እያከክን እርስ በርስ ለመፋጀት ከምናደባ ይልቅ፣ ሥጋና ነፍስን የሚያስጨንቁ ችግሮቻችንን ለማስወገድ ብንጣጣር ስማችን በዓለም የተመፅዋቾች መዝገብ ውስጥ በቁጥር አንድ ደረጃ ላይ አይገኝም ነበር፡፡

(ዘውዱ ተገኝ፣ ከኦሊምፒያ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...