Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉማን ነው ፌዴራሊስት? ማነውስ የአንድነት ኃይል?

ማን ነው ፌዴራሊስት? ማነውስ የአንድነት ኃይል?

ቀን:

በኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር)

የአገራችን የፌዴራል ሥርዓት ተከትሎ በአገራችን ባለው የፖለቲካ አሠላለፍ ራሳቸውን የፌዴራሊስት ኃይል ብለው የሚገልጹ ያሉትን ያህል፣ ራሳቸውን የአንድነት ኃይል ብለው የሚገልጹ ኃይሎችን ያቀፈ የፖለቲካ አሠላለፍ ይታያል፡፡ ሆኖም የፌዴራሊስትና የአንድነት ኃይል የሚለው ስያሜ ከፌዴራል ሥርዓት መሠረታዊ መርሆዎችና ከአገራችን ማኅበረሰባዊ ውቅር ጋር በማያያዝ ስያሜዎቹን ዘርዘር አድርጎ ማየት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፌዴራል ሥርዓት ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ የመጡትንና አሁንም የቀጠሉትን ብዥታዎች ለማጥራትና ስያሜዎቹ በእርግጥ ገላጭ ናቸው ወይ ብሎ ለመጠየቅ ያስችላል፡፡

የፌዴራሊዝም አስተሳሰብ ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደር ናቸው፡፡ የራስ አስተዳደር ከባቢያዊ የሆኑ አቅሞችንና ፍላጎቶችን መሠረት አድርጎ ራስን የማስተዳደር፣ ቋንቋንና ባህልን የማሳደግ፣ በቅርበት መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማግኘትና የመሳሰሉትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ የጋራ አስተዳደር ደግሞ አገራዊና የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ፣ ለአገራዊ ልማት፣ ለደኅንነት፣ ለሰላም፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ማድረግ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡፡ ከእነዚህ ሁለት መርሆዎች ጋር ተያይዞ ከባቢያዊ ማንነትና አገራዊ ማንነትን አስተሳስሮ መሄድን ይጠይቃል፡፡ እንግዲህ ፌዴራሊዝም ሁለቱ መርሆዎች ተሳስረውና ሁሌም ሚዛን ጠብቀው መሄድን ታሳቢ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ፍልስፍና መነሻው የጋራ ፍላጎትና ጉዳይ መኖርና በጋራ በአንድነት ለመቀጠል መወሰን ነው፡፡

- Advertisement -

በመሆኑም ፌዴራሊዝም የራስ አስተዳደርን ወይም የጋራ አስተዳደርን በተናጠል ይዞ የሚሄድ ፍልስፍና ሳይሆን፣ ሁለቱን አስተሳስሮ ሁሌም ሚዛን እየጠበቁ መሄድን መሠረት ያደረገ በውጤቱም ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባች፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ አካታችና የሁሉም መብት እኩል የሚከበርባት፣ ሁሉም ማኅበረሰብ የእኩል ተጠቃሚነት ዕድል የሚያገኝባት፣ የራሱን መብትና ነፃነት፣ የሌሎችን መብትና ነፃነት  የሚከበርባት አንድ ትልቅ አገር መገንባትን ታሳቢ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው፡፡ በመሆኑም ከፌዴራሊዝም ዕሳቤ ስንነሳ የራስ አስተዳደርና ከባቢያዊ ፍላጎትና ማንነት ብቻ የሚያቀነቅን ኃይል ፌዴራሊስት ኃይል ሊሆን ያለ መቻሉን ያህል፣ የጋራ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያቀነቅን ኃይል የአንድነት ኃይል ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ጠባብ ነው፡፡

ምክንያቱም በፌዴራል ሥርዓት ሁለት ኃይሎችን አንድ ወደ መሀል የሚስብና አንድ ወደ ውጭ የሚስብ ቢኖሩም፣ ትክክለኛው የአንድነትና የፌዴራሊስት ኃይል የሁለቱን ሚዛን ጠብቆ መሄድ የሚችለው ኃይል መሆኑ ከፍልስፍናው መሠረታዊ መነሻዎች የሚቀዳ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት እንደ ጸሐፊው ዕይታ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ትክክለኛ የፌዴራሊስት ኃይል የአንድነት ኃይል የመሆኑን ያህል፣ የፌዴራል ሥርዓትን ታሳቢ ያደረገ የአንድነት ኃይልም የፌዴራሊስት ኃይል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ሥርዓቱን መሠረት አድርገው የፌዴራሊስትና የአንድነት ኃይል በሚል ስያሜ የሚገለጹ የኃይል አሠላለፎች፣ የፌዴራሊዝም ፍልስፍና መሠረት ያደረጉ መሆናቸው አጠራጣሪ ነው፡፡

ዋናውን የስበት ማዕከል የራስ አስተዳደር ጋር ብቻ የተያያዙ ጥያቄዎች፣ መብቶች ወዘተ. ብቻ አድርጎ የጋራ ጉዳዩን ረስቶ የሚንቀሳቀስ ኃይል የፌዴራሊስት ኃይል ሊያሰኘው የሚችል አንድም ፌዴራላዊ አመክንዮ አይኖረውም፡፡ መነሻውም  በፌዴራሊዝም ላይ የያዘው ዕሳቤ የተሟላ አለመሆን፣ ወይም ፌዴራሊዝምን በተሳሳተ መንገድ ለራስ ፍላጎት መጠቀሚያ ለማድረግ መፈለግ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ብዙኃን ባሉበት አገር ውስጥ ለብዝኃነት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህላዊ፣ የማኅበራዊና የአስተዳደራዊ ፍላጎቶቻቸውን የሚያከናውኑበትን ዓውድ የሆነውን የራስ አስተዳደርን የረሳ፣ የጋራ አስተዳደርንና የጋራ ጉዳዮችን ብቻ ይዞ መንቀሳቀስ የአንድነት ኃይል የሚሰኝበት ፌዴራላዊ አመክንዮ የለውም፡፡

ሆኖም አሠላለፎቹ ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ የሚኖርን ዓውድ ታሳቢ ያደረጉ ከሆነ፣ እንደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ የፌዴራሊስትም ሆነ የአንድነት ኃይል የብተና ኃይል የሚሆንበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በአገራችን የፌዴራል ሥርዓት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ፣ የፌዴራሊዝም ፍልስፍናና ፌዴራላዊ ፖለቲካ አደረጃጀት መሠረት አድርጎ  ሁሌም በራስ አስተዳደርና በጋራ አስተዳደር መካከል የሚኖረውን ሚዛን ጠብቆ  የሚተገብር ኃይል፣ የፌዴራሊስትና ከዚያው ሳለም የአንድነት ኃይል ሆኖ የሚወጣበት ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡

ዋናው ቁምነገር በፌዴራል ሥርዓት የበላይ ወይም የበታች የሚሆን ማኅበረሰብ የሌለበት፣ ሁሉም የራሱን ጉዳይ በራሱ በየደረጃው የሚያስተዳድርበትና በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፍበትን ለጋራ አገራዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚደረግበትና እኩል ዕድል  የሚፈጠርበት መሆኑን በመገንዘብ ለዚህ ስኬት በመነጋገር፣ በመመካከር፣ በመደጋገፍ፣ በመተባበር፣ በመከባበር፣ ዕውቅና በመስጠት፣ የሌሎችን ችግር እንደ ራስ አድርጎ በማየት፣ አሽናፊና ተሸናፊ የሚል የፖለቲካ ቁርቁስ ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆንባቸው ሚዛናዊ ሒደቶችን መከተል የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብና ለተግባራዊነቱ መትጋት ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓትን ተመራጭ የሚደረጉትን ብዝኃነትን ለማስተናገድ ያለውን ዕምቅ አቅምና በብዝኃነት የተዋበ አንድነትን ለመገንባት፣ የሥርዓቱ መኖር መሠረታዊ ምክንያት በትክክል በሚተገበርበት መልኩ የሚንቀሳቀስ ኃይል ከዚያው ሳለ፣ የአንድነትና የፌዴራሊስት ኃይል ባህሪያትን የሚላበስበት ሀኔታ መፈጠሩ አይቀርም፡፡

ከዚህ አኳያ በአገራችን አሁን ከዚህም ከዚያም የሚሰሙት የኃይል አሠላለፍ ብያኔዎች ከፌዴራል ሥርዓት አመክንዮ አንፃር ሲታዩ የተሳሳቱና ማኅበረሰቡንም በፌዴራል ሥርዓት ዙሪያ ያለውን አረዳድ የበለጠ ትክክለኛ ወደ አልሆነ አቅጣጫ የሚመሩ፣ ሥርዓቱንም ከሥርዓቱ ባህሪያት ወጣ ባለ መልኩ የፖለቲካ ልሂቃኑ በሚፈልጉት መንገድ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ በማድረግ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በጣም ተፈላጊ የሆነውን ሥርዓት በአግባቡ እንዳይተገበር እንቅፋት ከመሆን በዘለለ  ፋይዳ የሌለው በመሆኑ፣ በፌዴራል ሥርዓት ዙሪያ ትክክለኛ ዕይታዎች እንዲያድጉና በተግባርም እንዲውሉ የሁሉንም የጋራ ጥረት የሚጠይቁ ይሆናል፡፡

በአገራችን ከብዝኃነታችን ጋር ተያይዞ ለሚኖሩ ብዝኃ የሆኑ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የአስተዳደራዊ ጥያቄዎች በአንፃራዊነት በተሻለ ሁኔታ ማስተናገድ የሚችለው የፌዴራል ሥርዓት የማይሆነን ከሆነ፣ ምን ዓይነት ሥርዓት ሊሆነን እንደሚችል ብዝኃነትና አንድነትን መሠረት አድርጎ ሲፈተሽ  አማራጩ ከመበተን የዘለለ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ውስን መሆኑ ነው፡፡ ችግሩ በአገራችን የማኅበረሰባዊ ውቅር፣ አሠፋፈር፣ አኗኗር፣ አስተሳሰብ፣ ሥነ ልቦና፣ ወዘተ.  አንፃር እርስ በርስ ከመጠፋፋት በዘለለ በሰላም የምንለያይበት አማራጮች የሉም ብሎ መደምደም የሚያስችል ዓውድ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የፌዴራሊዝም ዕሳቤዎችን በተገቢው መረዳት፣ የፌዴራላዊ አስተዳደር ሥርዓቱን በትክክለኛው መንገድ መተግበር አሳሳች የሆኑ የኃይል አሠላለፍ ብያኔዎችን መፈተሽ፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ትክክለኛ ወደ አልሆነ አቅጣጫ እንዳይመሩት በማኅበረሰቡ ውስጥ የፌዴራሊዝም አስተሳሰብና የፌዴራል ፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ግንዛቤ እንዲኖር መሥራት ይጠበቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌዴራሊዝም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...