Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉሰላምን ለማፅናት የጦርነት መንስዔዎችን ከምንጩ ማድረቅ!

ሰላምን ለማፅናት የጦርነት መንስዔዎችን ከምንጩ ማድረቅ!

ቀን:

 

በገባዎት ጥበቡ

ባለፈው ሳምንት እሑድ ምሽት በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ታሪካዊ ሁነት የሁላችንንም ትኩረትና ድጋፍ የሚሻ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝ ፈልቅቆ የሚያወጣ ጥልቅ መሪ ሃሐብ ይዞ ማየቴ ከመደሰት ባሻገር ይህንን ጽሑፍ እንድከትብ አነሳስቶኛል። የዚህ ታሪካዊ ሁነት መሪ ሐሳብ፣ “ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና!” የሚል ነው። መሪ ሐሳቡን አብራርተን ካልተመለከትነው የአንድ ሥነ ሥርዓት መገለጫ ወይም ማድመቂያ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሰላምን ማፅናት ከጦርነት እኩል የሁሉንም ድጋፍ የሚሻና አገርን የሚያድን ትልቅ ፕሮግራም ነው። ምክንያቱም ሰላምን ማፅናት ያለ ሥራ በጸሎትና በተዓምር የሚመጣ አይደለምና።

- Advertisement -

ሰላምን ማፅናት ለጦርነት ከሚደረግ ዝግጅት ካልበለጠ በስተቀር የሚያንስ ባለመሆኑ እኔም “ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና!” በሚለው የሁነቱ መሪ ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሀሳቤን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ውድመት፣ የሕዝብ ሥነ ልቦና ጉዳትና የአገርን ህልውና የፈተነ አደጋ፣ ዛሬ በዕርቅና በሰላም ጎዳና ላይ ቆመን በምልሰት ስንቃኘው በእጅጉ ልብ የሚሰብር፣ የሚያስቆጭና ወደፊትም ወደ ግጭት የሚወስዱ መንገዶችን በመዝጋት የሐሳብ ልዩነቶችን በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል ማዳበር ተመራጭ አማራጭ ብቻ ሳይሆን፣ ወደር የማይገኝለት ከሥልጡን ዕሳቤ የሚመነጭ ድንቅ መንገድ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ኅዳር 2 ቀን 2022 በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ በተደረገው የሰላም ስምምነት የተቋጨውና አሸናፊ አልባው አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል የዜጎችን አካል ያጎድልና ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ይቀጥፍ እንደ ነበር ሲታሰብ፣ በእርግጥም በሰላም ስምምነት ዕልባት ማግኘቱ ለነገ ሊባል የማይችል ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ 

የጦርነቱ መቋረጥና በሰላም ስምምነት መቋጨት የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከዚህም ያለፈ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን የሚስተዋለው የምርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ በሕገወጥነት የሚደነቃቀፈው የንግድ እንቅሰቃሴ፣ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ዜጎች በከፍተኛ የኑሮ ጫና እንዲፈተኑ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ግጭቱ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ የጦርነቱ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆኑትን የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልል ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገራችን ክፍሎችም የሚኖሩ ዜጎች ጭምር ለከፋ የኑሮ ውድነት ጫናና ጉስቁልና ይዳርግ እንደነበር ዕሙን ነው፡፡

በመሆኑም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ማስቀረት መቻሉ፣ እንደ አገር በተረጋጋ ሁኔታ ሙሉ ትኩረታችንን ወደ ልማት በማዞር ኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ዕድገታችንን እንድናፋጥን ያግዘናል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚንገላታውን ሕዝብ በተገቢው መንገድ በማድመጥ፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ፣ ችግሮቹን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉና በተግባር እየፈተኑ የሚዳብሩ ተከታታይ የአሠራር ማሻሻያ ዕርምጃዎችን በመውሰድ፣ የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ለማሳደግ ምቹ መደላድል ይፈጥራል፡፡

ከዚህም ባሻገር በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ጥርጣሬና አለመተማመን የሚያሰፍኑ ሁኔታዎችን ከመሠረቱ በመቀየር፣ በምትኩ የጋራ ጎጆኣችን ብለን ለምንጠራት አገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና አቅም፣ ዕውቀትና ጉልበታችንን አስተባብረን በምልዓት ለመሥራት ያስችለናል፡፡

ስለሆነም በመንግሥትም ሆነ በሕወሓት በኩል ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የተወሰደው ዕርምጃ፣ ይበል የሚያሰኝና በእርግጥም ሌላው የጀግንነት ዓውድ ተደርጎ የሚወሰድ መልካም ተግባር ነው፡፡ በጦርነቱ ወቅት ሁኔታዎች በነበሩበት መንገድ ችግሮችን በኃይል ብቻ ለመፍታት ከመሞከር በመታቀብ፣ ይልቁንም ጠባቧን የሰላም አማራጭ በመከተልና በማስፋት፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ኬንያ በዘለቀ ተከታታይ ውይይትና ድርድር፣ ዛሬ ላይ የተደረሰበት የሰላም ስምምነት ዕውን እንዲሆን በሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች በኩል አዎንታዊ ሚና የተወጡ ተደራዳሪዎች፣ እንዲሁም ድርድሩ በስኬት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ በማድረግ በኩል የአደራዳሪነት ሚናቸውን የጠወጡ አካላት በሙሉ ታሪክ የሚዘክረው አሻራቸውን አሳርፈዋልና በእርግጥም ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ 

ከዚህ አንፃር የዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብሩ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በአንፃሩ የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማስፈን፣ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናትና ወደፊትም መሰል አውዳሚ ጦርነቶች በአገራችን ምድር እንዳይከሰቱ ለማድረግ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎች የሚጠብቁትን የፍትሕና ርትዕ ጥያቄ ለመመለስ አስተማሪ የዕርምት ዕርምጃ መውሰድ ወደ ጎን ሊባል አይገባም፡፡ 

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተካሄደው ጦርነት እንደ አገር ያወደመው ሀብትና ንብረት ሳይዘነጋ፣ ይህ አውዳሚ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጎጂ ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአገርና የሕዝብ ሀብት ማውደሙም ይታወቃል፡፡ ጦርነቱ በዜጎች ሥነ ልቦና ላይ ያሳደረው ጠባሳ በቀላሉ የሚታከምና የሚደበዝዝ አይደለም፡፡ ጦርነቱ የአገርን የዕድገት ጉዞ በማደናቀፍ በሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖም በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ 

እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጦርነቱ ያስከተላቸው ጉዳቶች በሉበት ሁኔታ፣ ከሰላም ማስፈኑ የዕውቅና አሰጣጥ ስነ ሥርዓት በተነፃፃሪ በጦርነቱ ሳቢያ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ጥፋት እንዲደርስ ያደረጉ አካላት የሚጠየቁበትን አሠራር ተግባራዊ አለማድረግ ፍትሕን የሚያቀጭጭ፣ የሕግ የበላይነትን የሚፈትን፣ በህዝብና በመንግሥት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት የሚያሻክርና ወደፊትም በአገራችን ሰላምን ለማፅናት በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር መገመት አያዳግትም፡፡ 

ስለሆነም ልክ እንደ ሰላም ማስፈኑ ተዋንያን የምሥጋናና የዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብሩ ሁሉ፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ለተካሄደው ጦርነት ተጠያቂ የሆኑ አካላትን፣ ተዓማኒና ግልጽ በሆነ አሠራር፣ እውነትና እውነትን ብቻ ማዕከል ባደረገ መንገድ ጥፋተኞችን እንደ ተሳትፎ ደረጃቸው ለይቶ በጥፋት ኃይሎች ላይ አስተማሪ የሆነ የዕርምት ዕርምጃ የሚወሰድበት የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ያለበለዚያ ነገም የፈለገ ኃይል ተነስቶ በኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት እየጋገረና እየጠመቀ፣ ዘግናኝ ጥፋትና ውድመት እንዲደርስ ካደረገ በኋላ በዕርቅና በሰላም ማውረድ ሰበብ ከወንጀል ተጠያቂነት የሚያመልጥበት ሁኔታ እየተለመደ መምጣቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ 

ስለሆነም ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ ከዚያም ባሻገር ግጭት አምጪ የሆኑ አሠራሮችን፣ ልምምዶችንና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን አስቀድሞ በመግታት የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት በተሟላ መንገድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...