Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ፖለቲካ የሚባለውን ነገር ከባህሪው አለያይተን ከብሔር ጋር በማጣበቃችን ነው ሰላም የማይኖረን›› ሙሉዓለም ተገኘ (ዶ/ር)፣ የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (ዶ/ር)፣ ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ነበር በጥርስ ሕክምና ዶክትሬት የተመረቁት፡፡ ከሕክምና ውጪም በ2005 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ሥነ ጽሑፍ ገፍተው ሦስት የግጥም መድብሎችን ለማሳተም የበቁት ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ በሒደት ግን ወደ ፖለቲካው እንደተሳቡ ይናገራሉ፡፡ የኢዜማ አባል ሆነው የተፎካካሪ ፓርቲ ተሳትፎ ከጀመሩ በኋላ፣ በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ፓርቲውን ወክለው ተወዳድረዋል፡፡ ፓርቲያቸው በወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ስለሚከተላቸው አቋሞች ከሪፖርተር ቲዩብ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ቆይታውንም ዮናስ አማረ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ሪፖርተር፡- በትግራይና በአማራ ክልሎች አዋሳኞች አካባቢ ያሉ ውጥረቶች እንዴት መፈታት አለባቸው ብላችሁ ታምናላችሁ?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- ኢዜማ እነዚህን መሰል ውጥረቶች በሰላም መፈታት አለባቸው ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ሲጀመር ውጥረቶቹ በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ናቸው ብሎ አያምንም፡፡ በፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ ልዩነት የሚፈጠሩ መሆናቸውን ይረዳል፡፡ በአማራም ሆነ ትግራይ ክልል ያሉ ወገኖቻችን ችግሮች በሰላም ስምምነት ተፈተው፣ የሰላም እንቅልፍ የሚተኙበትና መደበኛ ሕይወታቸውን የሚቀጥሉበት ዕድል ይፈጠራል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ 

በሁለቱ ክልሎች ያለው ማኅበረሰብ አብሮ ብዙ ነገር ያሳለፈ፣ የጋራ ባህልና ሃይማኖት የሚጋራ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የመጣብንን መከራ አሻግረን የሁለቱ ክልሎች ማኅበረሰቦች ያለፉበትን ታሪክ ካየን አገር ሊወር የመጣን በጋራ የመከቱ፣ ብዙ መስዋዕትነት አብረው የከፈሉ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ከጊዜ በኋላ የመጡ መቋሰሎችን የሚፈጥሩ ጊዜያዊ ስሜቶች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን መስከንና ወደ ቀደመው አብሮነት መመለስ አስፈላጊ ነው እንላለን፡፡

ለ30 ዓመታት ስንሞክረው የኖርነው የብሔር ፖለቲካ በመጨረሻ ያመጣብን ገፈት ቀማሽ የሆነ ማኅበረሰብ በመሆኑ በጣም እናዝናለን፡፡ ባይፈጠርና ባይሆን የምንወደው ነገር ነው፡፡ ተመሳሳይ ነገሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሕዝቡ ከመከራ እንዲማር የፖለቲካ ሰዎች በሚሰጡት የተሳሳተ ውሳኔ አስተምረውታል ብለን እናምናለን፡፡ የሕወሓትን ተንኳሽነት የምንክደው አይደለም፡፡ ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ ይህን ባህሪውን በማስተካከል ለሕዝብ በሚጠቅም መንገድ እንደሚንቀሳቀስ ይጠበቃል፡፡ ከሥልጣንም ሆነ ከግል ጥቅም አልፈው መከራ ያየውን ማኅበረሰብ በእውነት ለመካስ እንዲሠሩ ከአደራ ጭምር ጋር መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በወልቃይትና በራያ ጉዳዮች ኢዜማ የያዘው አቋም ምንድነው?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ኢዜማ የሚያየው ዘላቂ ሰላም የሚመጣባቸውን መንገዶች ነው፡፡ ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በምን መንገድ ነው የሚለውን በተመለከተ፣ እንደ ኢዜማ ቋንቋና ብሔር ተኮር በሆነው ፌደራሊዝም ወይም የክልል አወቃቀር ላይ መስተካከል ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ ብለን ነው የምናምነው፡፡ ሕወሓት የሥልጣን የበላይነትን በያዘባቸው 30 ዓመታት በጣም ብዙ ግፎች ተፈጽመዋል ብለን እናምናለን፡፡ እነዚያ ግፎች ማኅበረሰቡን የተበዳይነትና የመከፋት ስሜት ውስጥ እንዲገባ እንዳደረጉትም እናምናለን፡፡ ግን አገር ከመበደልም ሆነ ከመከፋትም አልፎ መታየት አለበት ብለን እናስባለን፡፡ በተለይ ዘላቂ ሰላም በሚያስፈልገን፣ እጅግ መረጋጋትና አርቀን ማየት በሚያስፈልገን በዚህ ሰዓት ላይ ለዘላቂ ሰላም እንቅፋት የሆኑና ከፋፋይ የሚባሉ አጀንዳዎችን መሠረታዊ ጉዳይ አድርገው እያነሱ፣ በሕዝቦች መካከል ቅራኔን ማስፋት አግባብ ነው ብለን አናስብም፡፡ እንደ አገር መፈታት ያለባቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ይህን ጉዳይም እንደ አገር ከምንፈታቸው ችግሮች አንዱ መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜማ የጠራ አመለካከት ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ በአገር አቀፉ ምርጫ ያገኘው ድምፅና የፓርላማ መቀመጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ በምክር ቤት እየተገኙ ከሕዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ ተፅዕኖ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ነገር ግን ኢዜማ ይህን ሲያደርግ የማይታየው ለምንድነው?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- አድርጓል፡፡ ለምሳሌ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ሲወጣ ጥያቄ አቅርበን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥተው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሌሎች ጉዳዮች ሲኖሩም እናቀርባለን፡፡ በየወሩ ባለሥልጣናትን እያስጠሩ መጠየቅ ይቻላል ማለት፣ የግዴታ በየወሩ መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡ በተጨባጭ የሚሆነው ጥያቄ ሲኖርህና አስፈላጊ ሲሆን ነው ተጠርተው የሚጠየቁት፡፡ በግሌ የማስበው ያለፍንባቸው አራት ዓመታት ሁኔታ ጤናማ የፖለቲካ ጉዞ የታየበት አልነበረም ብዬ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በፖለቲካ ምኅዳራችን ውስጥ ጤናማ ፖለቲካ ተጀምሯል ለማለት ይከብዳል፡፡ በጣም ብዙ ስሜታዊነት የበዛበትና አንዳንዱ ችግርም ከበደልና ከመገፋት የሚመነጭ ነው፡፡ ሰው ቤቱ እየፈረሰበት ፓርላማ በየወሩ ስብሰባ እየጠሩ ማውራቱ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ በጣም ብዙ ችግሮች ስላሉ መንግሥት ታች ማኅበረሰቡ ጋር ወርዶ ችግሮችን መፍታት እንዳለበት ይሰማናል፡፡

ይሁን እንጂ ባሳለፍነው የጦርነትና የውጥረት የበዛበት ፖለቲካ ውስጥ ሆነን አገሪቱ ልትፈርስ ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ ጭንቅ በሆነበት ሁኔታ፣ ሌሎች ችግሮችን በአግባቡ ለማንሳት የነበረው ዕድል በቂ አለመሆኑ ይሰማናል፡፡ በየቦታው የነበረው ግጭትና ቀውስ ጨምሮ የሚፈጠሩ ወቅታዊ ጉዳዮች ተከታታይና ፋታ የማይሰጡ ነበሩ፡፡ ተረጋግቶ ዘላቂ የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ኢዜማ እንዲያውም ይለይ የነበረው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እናተኩር በሚለው አቋሙ ነው፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ዝም ትላላችሁ እየተባለ የምንወቀሰው በጊዜያዊ ችግሮች ተጠልፈን፣ መሠረታዊ በሆኑ የአገር ጉዳዮች ላይ በቸልታ ላለማለፍ በሚል ነው፡፡ አንገታችንን አስጎንብሰን ስንሠራ የቆየነው ብዙ ችግሮችን በዘለቄታው ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን ነው፡፡ መዋቅራዊ ቅራኔዎችን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ስናተኩር ነበር፡፡

በምርጫው ወቅት ስንሠራ የነበረው በፖሊሲ መታገል ላይ አተኩረን ነው፡፡ ከዚያ በኋላም የምናወጣቸው መግለጫዎች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ችግሮችን ከማመላከት ባለፈ ምክረ ሐሳቦቻችንን ከመስጠት ወደኋላ ብለን አናውቅም፡፡ ለአገር ይጠቅማል ብለን በምናስበው የትኛውም ጉዳይ ላይ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ወደኋላ ብለን አናውቅም፡፡ የምንችለውንና ለአገር ይጠቅማል ያልነውን ከመስጠት ሰስተን አናውቅም፡፡ ስለዚህ በየወሩ የመንግሥት ሰዎችን እያስጠሩ የመርሐ ግብር ውይይቶችን ከማድረግ ይልቅ፣ መዋቅራዊ ቅራኔዎች የሚፈቱበትን መንገድ መፈለግን ነው የምናስቀድመው፡፡ አንዳንዴም እያመመን፣ ከእነ ዕንባችን፣ ከስሜታዊነት በወጣ መንገድ ቁጭ ብለን መሠረታዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት እየሠራን ነው ያለነው፡፡ ከሌሎች ጋር በዚህ መርህ ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- በፓርላማው ፓርቲው ካገኘው ወንበር አንፃር ዝም ይላል፣ ያን ያህል ተፅዕኖ ሲፈጥር አይታይም ይባላል እኮ?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- በፓርላማ ፓርቲው ዝምታን መርጧል የሚለውን መቀበል እቸገራለሁ፡፡ ፓርላማው ሕግ የማውጣት ኃላፊነት ያለው ሲሆን የራሱ የሆነ ሕግና አሠራር አለው፡፡ በፓርላማው በቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ በሰብሳቢነት ጭምር እንሳተፋለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሌም ሲቀርቡ ጥያቄ ከማንሳት ያለፍንበት ጊዜ የለም፡፡ በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ እንሰጣለን፡፡ አዋጆች ሲፀድቁ የራሳችንን ገንቢ ሐሳቦች እንሰጣለን፡፡ አይሆኑም የምንላቸውንም ጉዳዮች በግልጽ እናስቀምጣለን፡፡ በእኛ ግምገማ በፓርላማው ያለን ሚና እጅግ የተቀናጀና ጠንካራ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡– ካገኛችሁት ወንበር አንፃር ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ በማንሳት፣ ማብራሪያዎች ላይም ተጨማሪ ውይይት በማድረግ ብዙ ርቀት ትሄዳላችሁ?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- እኛ ብዙ ርቀት ሄደናል ነው የምንለው፡፡ የሄድንበት ርቀት እንዴት ነው የሚታየው የሚለው ግን ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ብዙ ጊዜ ጥያቄ እናቀርባለን፡፡ በሚወጡ አዋጆች ላይ ጥልቅ አስተያየቶችን እንሰጣለን፡፡ መዋቅራዊ ቅራኔዎችን በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ የምናተኩር በመሆኑ፣ ለዚህ የሚረዱ ናቸው በምንላቸው ለምሳሌ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉዳይ ላይ ሐሳብ ሰጥተናል፡፡ የጤና መድን አዋጅን ጨምሮ ብዙ ወሳኝ ጉዳዮች ሲነሱ ገንቢ ሐሳቦችን እናዋጣለን፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ሕወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ ሲነሳ የእኛን አቋም ከእነ መፍትሔው ግልጽ አድርገናል፡፡ ምናልባት እኛ ከእነ መፍትሔው የምናቀርብ መሆኑና የተለመደውን መንገድ ተከትለን ጥያቄዎችን ባለማቅረባችን ካልሆነ በስተቀር፣ በሚጠበቅብን ልክ እየተንቀሳቀስን ነው ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያት ላይ የተደገፈ፣ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያሳይና ችግሩን መተንተን የሚችል አቀራረብ ነው እኛ የምንከተለው፡፡ ይህ አቀራረብ የተቆጣንም ሆነ የተበሳጨን አይመስልም፡፡ ጩኸት የበዛው ባለመሆኑ ምንም ያልን የማይመስላቸው ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ ከመንግሥት ጋር ስለመሥራት ሲወስን 73 አባላት ተቃውመው ነበር፡፡ የፓርቲው መሪ የመንግሥት ፖሊሲ አስፈጻሚ ተሿሚ በመሆናቸው ይህን ፓርቲው እንዴት ያየዋል?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡– ኢዜማ ከመንግሥት ጋር መሥራትን በፓርቲ ደረጃ በጠቅላላ ጉባዔ ገምግሞ በማፅደቁ ከሁሉም ፓርቲ ይለያል፡፡ በጣም ብዙ ፓርቲዎች ሥልጣን ተቀብለው እየሠሩ ነው፡፡ ኢዜማ ግን ከመንግሥት ጋር መሥራት ምን ማለት ነው? ለምን መሥራት አሰበ፣ በምን ጉዳዮች ላይስ ይሠራል? የሚሉት ተቀምጦ ተወያይቶ በግልጽ በመተንተን ነው የወሰነው፡፡ ጉዳዩ የግለሰቦች ሹመት እንዳይሆን ማጥራት አስፈልጓል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ውስጥ የማይቀበሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሁንም ቢሆን የኢዜማ አባል ሆነው ከመንግሥት ጋር መሥራቱን የማይቀበሉት አሉ፡፡ የጉባዔውን ውሳኔ ያከብራሉ፣ ነገር ግን ይህ ነገር ይስተካከል ብለው ሐሳባቸውን በግልጽ ያቀርባሉ፣ ይቃወማሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ካለበት ከራስ መጀመር አለበት በሚል ነው ወደዚህ የገባነው፡፡

የገባንበት ውሳኔ መመዘን ካለበት ግን ፕሮፌሰሩ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ምን ሠሩ የሚለው ነው መቀመጥ ያለበት፡፡ የባህልና ቱሪዝም ተሿሚው ምን ሠሩ ተብሎ ፓርቲዎቹ በተሰጣቸው ኃላፊነት የሠሩት ሥራ ነው መገምገም ያለበት፡፡ ከመንግሥት ጋር መሥራት ማለት በምትሠራው ሥራ ውስጥ ምን እየሠራህ ነው? ውጤታማና ስኬታማ ነው ወይ? የሚለው ነው መገምገም ያለበት፡፡ ለምሳሌ የመከላከያን ሥራ ፕሮፌሰሩ የትምህርት ሚኒስትር ከመሆናቸው ጋር ካገናኘነው የአረዳድ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ውሳኔው በጉባዔ የተወሰነ ነው፡፡ ሁላችንም የጉባዔውን ውሳኔ አክብረን ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ በቀጣይም በዚህ ጉዳይ የሚደረጉ ውሳኔዎች ካሉም በጉባዔ የሚወሰኑ ነው የሚሆነው፡፡ ከጉባዔው በፊት ጀምሮ ከመንግሥት ጋር ተለጥፋችኋል ይሉን የነበሩ ሰዎች አሁንም ያንኑ ቢሉን የምንቀበለው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ወደ ጉራጌ ዞን የፓርቲያችሁ መሪ ሄደው ነበር፡፡ የጉራጌ ክልልነት ጥያቄን እንደማይቀበሉትም ተናግረው ነበር፡፡ ይህ የግል አመለካከታቸው ነው? ወይስ የፓርቲውን አቋም የሚያንፀባርቅ ነው?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- በግልጽ መግለጫ አውጥተንበታል፡፡ የእሳቸው አቋም አይደለም፡፡ ፓርቲው ይህን ጉዳይ የወሰነው ሲመሠረት ነው፡፡ ፕሮግራሙ ላይ የክልል አደረጃጀትን ወይም ፌደራሊዝምን ሲያነሳ በግልጽ ያስቀመጣቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ አገር የሚያስፈልገን ማኅበረሰቡ ተረጋግቶ፣ በዕድገትና በሰላም መሠረታዊ አገልግሎቶችን እያገኘ እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ እንደዚያ ለማድረግ የመንግሥት መዋቅር በአግባቡ መቀረፅ እንዳለበት አስቀምጠናል፡፡ አሁን ያለው መዋቅር ይህንን አያሳካም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ያጋጫል፡፡ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ አብሮ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በተግባር ሕወሓት ያደረገውን ዓይተናል፡፡ በሌሎች ክልሎችም ብዙ ግጭቶች አሉ፡፡ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብን በአንድ አካባቢ ማጠር አግባብ አይደለም፡፡ አገር አያሳድግም፣ ኢኮኖሚ አይለውጥም፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ አያደርግም፡፡ ከወደ ጉጂና ቦረና አካባቢ ያለው ጥያቄ የዚሁ ነፀብራቅ ነው፡፡ ሕዝብ መንግሥት ከሚባለው ተቋም የሚፈልገው ማኅበራዊ አገልግሎት በመሆኑ፣ የመንግሥት አወቃቀር ይህን የሚያሳካ እንዲሆን እናድርገው ነው፡፡ በብሔርና በፖለቲካ መካከል ያለው ጋብቻ ሕዝብን እንዳይመቸው አድርጓል፡፡ ይህንን አቋማችንን በአደባባይ በግልጽ በመግለጫ አውጥተናል፡፡

ኢዜማ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ነው እንደ አገር የሚያዋጣን ሲል ቆይቷል፡፡ አንዳንዶች በተለያዩ ምክንያቶች ይህን መንገድ አይቀበሉትም፡፡ ከሚያገኙት የወረዳ፣ የዞን ወይም የክልል ሥልጣንና ጥቅም ጋር አነፃፅረው አይቀበሉትም፡፡ የዜግነትን ፖለቲካ የማይቀበሉት የዜግነት ፖለቲካ በዚህ አገር ቢነግሥ፣ ችሎታና ብቃት ምዘና ውስጥ ይገባል ብለው የሚሰጉ አካላት ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ወገኖች ኢዜማን እንዴት ይደግፋሉ ተብሎ ይገመታል? እነዚህን መሰል ወገኖች ሲደግፉን ነው መደንገጥና ምን ስህተት ሠራን ብለን ቆመን ማሰብ ያለብን፡፡ ዓላማ ይዘህ፣ ላሳካው የምፈልገው የፖለቲካ ግብ ይህ ነው ብለህ ስትሠራ ተቃውሞ ማጋጠሙ የማይቀር ነገር ነው፡፡ የሚቃወምህ ምን ዓይነት አመለካከት ያለው ነው የሚለውን ነው መለየት ያለብህ፡፡ የሚሰጡ ትችቶችና አስተያየቶች ለምን ግብ ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የብሔር ፖለቲካ እንዲስፋፋ የሚፈልገው በበዛበት በዚህ ጊዜ እንደ ኢዜማ ባለ ፓርቲ ላይ የማይለጠፍ ስም የለም፡፡ ከኢዜማ ውጪ አንድም ሌላ ፓርቲ ከመንግሥት ጋር በመሥራቱ ሲተች ሰምተህ ታውቃለህ? ዴል ካርኒጌ፣ ‹‹የሞተን ውሻ ማንም አይደበድበውም›› ይላል፡፡ እኛ በሕይወት መኖራችንም ሆነ ለመሥራት የምንሞክራቸው ነገሮች የሚታዩና የሚዳሰሱ በመሆናቸው ነው፣ ከእኛ በተቃራኒ ለቆሙ ኃይሎች እንደ ሥጋት የምንታየው፡፡ እዚህ አገር በፍረጃ ላይ የተመሠረተ ጥሩ ያልሆነ የፖለቲካ ባህል አለ፡፡ እኛን እንደ ሥጋት የሚያዩን ኃይሎች በሚሰጡን ስምና ፍረጃ እንዴት ሊደግፉን ይችላሉ ብለን ነው የምናየው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ ከአብን ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወሳል፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች ካላቸው የፖለቲካ ልዩነት አንፃር እንዴት ነው በጋራ የሚሠሩት?     

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- በሚያግባቡን ጉዳዮች፡፡ ከብልፅግናም ጋር እየሠራን ነው፡፡ ስንመሠረት ጀምሮ ያልነው ነው እኛ በአገር ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር በጋራ እንሠራለን፡፡ ጉዳዩ ይፋ ሲሆን ከወቅቱ አንፃር ከሌላ ነገር ጋር ለማገናኘት የተሞከረ ነገር ካልሆነ በስተቀር፣ በአገር ጉዳይ ከማንም ጋር በጋራ መሥራትን ስንለው የኖርነው ጉዳይ ነው፡፡ ኢዜማ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መሥራትን በተመለከተ ሲመሠረት ጀምሮ ያቋቋመው ኮሚቴ አለው፡፡ ኢዜማ የተመሠረተው በአንድነት የሚያምኑ የጋምቤላ፣ የከምባታና የተለያዩ ፓርቲዎች ከስመው ነው፡፡ ኢዜማ ውስጥ በፍፁም ብሔር አይፀየፍም፡፡ ብሔር የሚባል ነገር ከናካቴው ይጥፋ የሚል አክራሪ ድርጅት አይደለም፡፡ ባህል፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ ቋንቋ ሊከበሩ ይገባል ብለን የምር እናምናለን፡፡ ብሔር የለም የሚል አስተሳሰብም የለንም፡፡ ብሔር አለ፡፡ መርሐችን ከብልፅግና፣ ከአብን ወይም ከሌላ ፓርቲ ጋር ስንሠራ ብቻ አይደለም፡፡ በሚያግባቡን ጉዳዮች እንሠራለን ስንል ኢዜማ በአገር ጉዳይ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ ከሌሎች በርካታ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እንደምንሠራ ይፋ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ ሕወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ ስሙ ወጥቷል፡፡ ኢዜማ ይህንን እንዴት ያየዋል?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- በመግለጫችን ሰባት ነጥቦችን ዘርዝረናል፡፡ ከዚያ ውስጥ አንዱ የሥልጣን ሞኖፖሊን የተመለከተ ይገኝበታል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ መከላከያን አደራጅቶ የመንቀሳቀስ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የትኛውም ኃይል ከመንግሥት ጋር ይሥራም ሆነ ከመንግሥት ዕውቅና ይሰጠው የራሱን ትጥቅና ኃይል አደራጅቶ መንቀሳቀሱ ትክክል አይደለም፡፡ ሕወሓት ልዩ ኃይሉን ተጠቅሞ መከላከያን ከመምታቱ በፊት ጀምሮ ልዩ ኃይልን በተመለከተ ስንለው የነበረው ሕገ መንግሥታዊ አይደለም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው በወቅቱ ልዩ ኃይሉ ይደራጅና ይታጠቅበት የነበረው መንገድ አግባብ አልነበረም፡፡ ከጦርነቱ በፊት በየሳምንቱ ይደረጉ የነበሩ ፉከራዎችና ሽለላዎች አረጋዊያንን ጭምር መሣሪያ እያስያዙ መሠለፉ ትክክል አይደለም ስንል ነበር፡፡ መንግሥትም ማድረግ የነበረበትን ነገር አለማድረጉ ተጨምሮ ወደ ጦርነት ተገባ፡፡ ወደ ጦርነት የወሰደን ዋነኛ ምክንያት የተደራጀ ትጥቅ የያዘ ኃይል መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ጉዳይ የሚያስፈጽም ሚዲያም በመበራከቱ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎችና ሚዲያዎች ባሉበት ሁኔታ ያን ሁሉ ሽብር ያደረገውን ኃይል ነፃ ማድረግ አግባብ አይደለም፡፡ ሕወሓት የፈጸመው ሽብር መቼም የሚረሳ አይደለም፡፡ ለእነዚያ ነገሮች ምንም መፍትሔ ሳይሰጡ ነፃ ነው ማለቱ አደገኛ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁንም ቢሆን በድንበር አካባቢዎች ውጥረቶች አሉ፡፡ እነዚህ ውጥረቶች ሳይፈቱ፣ ትጥቅ የመፍታት ሥራው በአግባቡ ባልተሠራበት ሁኔታ ከሽብር መዝገብ ማንሳቱ አግባብ አይደለም ነው ያልነው፡፡ መግለጫችንም በግልጽ የሚለው ሕወሓትን ከሽብርተኝነት መሰረዝ ለሕዝብ ዘላቂ ሰላምን፣ ዕፎይታንም ሆነ ቅቡልነትን አያመጣም ነው፡፡ ሕወሓትን ከሽብርተኝነት ስላስወጣህ የትግራይ ሕዝብ፣ የአጎራባች አማራና አፋር ሕዝብ ዕፎይ አይልም፡፡ የሕወሓትን ባህሪ ጠንቅቀን እናውቃለን ብለን እናስባለን፡፡ የሰላም ስምምነቱ ከባህሪው እንዲታረም ዕድል ሰጥቶታል ብለን እናስባለን፡፡ ወደ ሰላም የሚያመሩ ናቸው ወይ የሚለው በትክክል መታየት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በስምምነቱ መሠረት ከአሸባሪነት እንደሚሰረዝ ተመላክቷል እኮ?

ሙሉዓለም (ዶ/ር)፡- ስምምነቱ ውስጥ የተቀመጡት ነገሮች እኮ አንዱን አዘግይተህ ሌላውን እያስቀደምክ የምታደርጋቸው ነገሮች አይደሉም፡፡ ይህን ስምምነት በተግባር ለመተርጎም የመጀመሪያው ዕርምጃ ተኩስ ማቆምና መሣሪያ መፍታት ነው፡፡ ሰላሙን ያጠፋው መሣሪያ የታጠቀ ኃይል ውጊያ በመክፈቱ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ያ መታጠቅ ቆሟል፣ የጦር ዝግጅቱ ቆሟል ወይ የሚሉ ነገሮች መታየት አለባቸው፡፡ ከሽብርተኝነት የመሰረዙ ጉዳይ ከመነሳቱም ሆነ ከሌላ ጉዳይ በፊት ይህ ነገር ሆኗል ወይ ብለን ነው የጠየቅነው፡፡ በመረጃ አስደግፈን አልሆነም ነው እያልን ያለነው፡፡ ይህ ሳይሆን የሚወሰዱ ሌሎች ዕርምጃዎች የፕሪቶሪያውን ስምምነት በአግባቡ ለማክበር አስቸጋሪ ነው የሚሆኑት፡፡ ሌላው ይቅርና የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ለማቋቋም እየተሄደበት ያለው መንገድ አግባብነት ያለው ነው ወይ? እንዲያውም የትግራይን ሕዝብ ድምፅ እንኳ ያማከለ ነውን? እኛ ይህን ዓይነቱን አካሄድ ነው የተቃወምነው እንጂ፣ በአንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚተቸው የሰላም መምጣቱን አይደለም፡፡ ሰላም መምጣቱን የሚቃወም ማንም ኃይል የለም፡፡ በተለይ በመከራ ውስጥ ያለ ሕዝብ የሰላምን ዋጋ በቅጡ ይረዳዋል፡፡ ግን ሰላሙ ለጊዜያዊ ሳይሆን በዘላቂነት መስፈን አለበት፡፡ ሕዝቡን ደግሞ እፎይ ማስባል አለበት፡፡ ሕዝቡ አሁን ዕፎይ እያለ ነው ወይ? ለምሳሌ በትግራይ በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ተሹማችሁ ነበር ተብለው እስከ 17 ሺሕ ሰዎች  ታስረዋል፡፡ እነሱ በውድቅት ሌሊት መከላከያን በተኛበት ገድለውና ብዙ ነገር አድርገው ግን አልተጠየቁም፡፡ ሕወሓት ከመቀሌ በወጣ ጊዜ በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች አሁን ድረስ እየታሰሩና እየተከሰሱ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ብድር ክፈል እየተባለ ነው፡፡ ድሮ የተበደርከውን አምጣ እየተባለ ነው፡፡ ይህ አይሰማንም ወይስ አሁንም የሚመጣው ሥርዓት የሕወሓትን የበላይነት እንዲያስቀጥል ነው የሚፈለገው? ይህ ትክክል አይደለም ነው ያልነው፡፡ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለአገር ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ከሆነ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ መንግሥት ይህን ማረጋገጥ አለበት ነው እያልን ነው ያለነው፡፡ ይህን ሳያረጋግጡ መሄድ በታሪክም ያስጠይቃል እያልን ነው ያለነው፡፡ ይህን እያረጋገጥክና በስምምነቱ መሠረት እየሄድክ አደለም እያልን ነው፡፡ ይህን ሳታደርግ ደግሞ ከሽብርተኝነት ማንሳት ነገ ጠዋት ጦርነት የሚወልድ ከሆነ፣ ዘላቂ ሰላም የማይሰጥና ለሕዝቡ ዕፎይታ የማያመጣ ከሆነ ተጠያቂው ይህን የደገፋችሁ የምክር ቤት አባላትና መንግሥት ናቸሁ ነው ያልነው፡፡ ይህ ደግሞ የምናምንበት አቋም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሸገር ከተማ በአዲስ አበባ ዙሪያ መቋቋም በአዲስ አበባ ፖለቲካ ላይ ምን ዓይነት አንድምታ አለው ትላላችሁ? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ዙሪያ አካባቢ ብዙ ቤቶችም እየፈረሱ ነውና ይኼንንስ እንዴት ታዩታላችሁ?

ሙሉዓለም ተገኘ (ዶ/ር)፡- ኢዜማ ውስጥ ትይዩ ካቢኔዎች አሉን፡፡ ከዚያ ውስጥ አንዱ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በባለሙያዎች ማስጠናት ነው፡፡ ከፖለቲካ ዕይታ ውጪ በባለሙያዎች ነገሮችን እያጠናን መረጃ ላይ ተመሥርተን እናቀርባለን፡፡ በቅርቡ እነዚህን አስመልክተን በጥናት ላይ የተመሠረተ ጥሩ ገለጻ ይኖራልና ይህን ጉዳይ ባልነካካው፣ ባለሙያዎች በደንብ እንዲያብራሩት ብተወው ደስ ይለኛል፡፡ ፖለቲካ የተወሰኑ ፖለቲከኞች ብቻ ወጥተው የሚተነትኑት ጉዳይ ብቻ መሆኑ መቆም አለበት፡፡ የባለሙያ ግምገማና ዕይታን የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሰዎች ስለግብርናውም፣ ኢኮኖሚውም፣ ጤናውም፣ ስለሁሉም ነገር ያወራሉ፡፡ አማካሪዎችን ተጠቅመውና መረጃዎችን ዓይተው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን በየዘርፉ ያሉ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች አንዳንድ ጉዳዮችን ከእነ መፍትሔ ሐሳቡ ጭምር ተንትነው ቢያቀርቡት የተሻለ ነው ብለን እናምናለን፡፡ የዜጎችን ቤት መፍረስ በተመለከተ ግን ወረራንም አንደግፍም፣ በሌላ በኩል ሰብዓዊ መብቶችን በሚጥስ መንገድ ቤቶችን ማፍረስም አንደግፍም፡፡ አንድ ሰው መሬት ወርሮ ቤት ስለሠራ ብቻ መኖር መብቱ ነው እንደማንለው ሁሉ በላዩ ላይ ቤት እንዲፈርስ፣ እንዲደበደብም ሆነ እንዲፈናቀልም አንፈልግም፡፡ እያፈረሱ የሚጨፍሩ የፀጥታ ኃይሎች የእውነት የፀጥታ ኃይሎች ናቸው ወይ የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡ እነዚህን መሰል አንገብጋቢ ጉዳዮች በጥናት እንዲታዩ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእምነት ተቋማትም ሳይቀሩ እየፈረሱ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዴት ይታያል?

ሙሉዓለም ተገኘ (ዶ/ር)፡- የእምነት ተቋማት ቅጥራቸውና ደጃቸው ብቻ እኮ አይደለም፣ ውስጣቸው ድረስ ተገብቶ ለማፍረስ የሚደረገውን አንዳንድ ጥረት እያየን ነው፡፡ እኛ የምናየው የብሔር ፖለቲካ የደረሰበትን ጥልቀት በትክክል ቁጭ ተብሎ ካልታየ ልንረዳው አንችልም በሚል ነው፡፡ እያንዳንዱን ነጥብ ብታገናኘው ተቀጣጥሎ የሚገናኘው ከብሔር ፖለቲካ ጋር ነው፡፡ አንድ ብሔር የእኔ የሚለው ክልል ሲሰጠው የመጀመሪያው የሚፈጠረው አስተሳሰብ፣ እኔን የማይመስል በሙሉ ከዚህ ይጥፋ የሚል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ነፃነትም ሆነ የግለሰቦች ነፃነት ቢኖርም፣ የእኔ ክልል የሚለው አስተሳሰብ ግን የእኔ ብቻ እንጂ የአንተ አይደለም የሚል መንፈስን እየፈጠረ ነው፡፡ ይኼ የእኔ ነው፣ ሌላው ጠላት ነው የሚል ፖለቲካ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት ደግሞ ሸገር ከተማ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ደግሞ ኦሮሞ ብቻ ነው መኖር ያለበት የሚል ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለዚያ ነው እኛ በቋንቋና በዘር ማንነት የሚደራጅ ክልል አንደግፍም የምንለው፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ ቦታ አዲስ ክልል ሲደራጅ ተመሳሳይ ችግር ነው የሚፈጠረው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ሌላው ያደረሰብን ጉዳት ወንጀል ሠርቼ እንኳን ብያዝ በብሔሬ ምክንያት ነው የተያዝኩት የሚል አመለካከት መፍጠሩ ነው፡፡ ወንጀል ሠርቼ እንኳ ብታስረኝ በብሔሬ ምክንያት ነው የያዝከኝ እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በወንጀል ከመጠየቅ በፊት ብሔር ስለሚቀድም፡፡ የብሔር ፖለቲካ የፈጠረብንን ዝቅጠት ለመረዳት እንዴት እንደማይቻል አይገባኝም፡፡ የእኔና የእነሱ የሚል አመለካከት በሰፊው ይስተዋላል፡፡ ወለጋ ውስጥ እነዚያ ሁሉ ንፁኃን ዜጎች ሲገደሉ የሌላ ብሔር ተወላጆች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ብቻ አንድም ቀን የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች በፍፁም መግለጫ አይሰጡም፡፡ ሞተብኝ የሚለው ወገን ደግሞ ኡኡ ይላል፡፡ የትግራይ ጉዳይን የአማራው፣ ወይም የአማራው ጉዳይን የትግራዩ አይናገርም፡፡ የብሔር ፖለቲካ በሞትና በበደል ሳይቀር እንድንከፋፈል አድርጎናል፡፡ በዳዩ ማነው? እንዴት ነው የተበደለው? በሕጋዊ መንገድ ይታይ ከሚል ይልቅ የተበደለውና የበደለው ወገን ማነው የሚለው ይቀድማል፡፡ በዳዩ የእኔ ወገን ሲሆን ምንም ችግር የለውም፡፡ ተበዳዩ የእኔ ወገን ከሆነ ደግሞ በደሉ የዓለም መጨረሻ ነው ብሎ መሳል ይጀመራል፡፡ ይህ አሳዛኝ ጽንፍ የያዘ ፖለቲካ ደግሞ መንግሥት ውስጥ ጭምር በዚህ አስተሳሰብ የተዘፈቁ አካላትን እየፈጠረ ነው፡፡ ሕጋዊ በሆነ ሽፋን የሚደረገው ነገር ብሔር ተኮር፣ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚደረገው ነገር ብሔር ተኮር ሆኗል፡፡ መሆን የማይገባቸው ብዙ ነገሮች ብሔር ተኮር ሆነዋል፡፡ የዚያ ውጤት ደግሞ ገና ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ አንድ አገር ኖሮን በጋራ መኖርም ሆነ እርስ በእርስ ተከባብሮ መኖር የማይታሰብ እየሆነ ነው የሚለው ሥጋት ጠንካራ ነው፡ ነገርዬው ያጠፋፋናል፣ በዚያ ልክ ሊታሰብ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የገባችበትን ውስብስብ ፖለቲካ ኢዜማ እንዴት ያየዋል? መፍትሔውስ ምን መሆን አለበት ይላል?

ሙሉዓለም ተገኘ (ዶ/ር)፡- የብሔር ፖለቲካ ላይ የተንጠለጠለ፣ የእኔ ወይም የአንተ የሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ የዘውግ ፖለቲካ እስከቀጠለ ድረስ በኢትዮጵያ የተረጋጋና ተደጋግፎ ወደ ዕድገት ማምራት የሚችል ማኅበረሰብ መፍጠር እንችላለን ብለን አናምንም፡፡ የችግሩ ሰንኮፍ ያለው እዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ብሔርና ፖለቲካ የተጋቡበት መንገድ ጤነኛ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የመሰለ ልምድ ሌላ አገር ላይ ገጥሞ ያውቃል ወይ ብለን ጠይቀናል፡፡ ያልገባንና ያላየነው ነገር ካለ ብለን ጠይቀናል፡፡ ብሔር ይጥፋ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ሲወለድ ጀምሮ የብሔር ማንነት ይኖረዋል፡፡ ነኝ ብሎ የፈለገውን ማንነትን በመቀበል ብሔር ሊኖረውም ይችላል፡፡ ግን ነኝ ያልከውን ማንነት ለመሆንህ ደሜ ምናምን ብለህ ማረጋገጫ ልታቀርብልኝ አትችልም፡፡ ስለዚህ አንተ የሆነ ቦታ ትወለዳለህ፣ ነኝ የምትለውን ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ ታሳድጋለህ፡፡ እነዚህን እሴቶች ማሳደግ በጣም ትክክለኛ ነገር ነው፡፡ አንድ አካባቢ ላይ ቋንቋውንም ሆነ ባህሉን የሚያውቅ ሰው እንዲያስተዳድር ማድረጉም ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ብሔር መሆንን የሚያመጣው ምንድነው የሚለው ጉዳይ መጠየቅ አለበት፡፡ እኔና አንተ ከምናገኘው ግብር እንከፍላለን፡፡ ነገር ግን የብሔር ማንነታችን ታይቶ የምንከፍለው ግብር ልዩነት ይደረግበታል፡፡ የሚመጣልን የቧምቧ ውኃ በብሔራችን ምክንያት ጥራቱ ይለያያል፡፡ እኔና አንተ የምናገኘው መንግሥታዊ ጥበቃ ለምሳሌ መከላከያ ድንበር ላይ ሲዋጋ የሚዋጋው ለአንድ ብሔር ነው፡፡ አገርን እየጠበቀ ያለው የፀጥታ ኃይል አገሩን የሚያስጠብቀው በብሔር ዕሳቤ ነው፡፡ ፖለቲካ የሚባለውን ነገር ከባህሪው አለያይተን ከብሔር ጋር በማጣበቃችን ነው ሰላም የማይኖረን፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ያልሞተ ወይም ያልተገደለ ብሔር አለ? በዚህ ሒደት ውስጥ እንደ ሰው ሰብዓዊ ክብሬና መብቴ ተከብሮ እየኖርኩ ነው የሚል ብሔር አንድ እንኳ ጥራልኝ፡፡ ተከብሬያለሁ ይህ ሥርዓት ይበጀኛል የሚለው ማነው? የብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተው ፌደራላዊ ሥርዓት ጠቅሞኛልና ወደፊትም ልቀጥልበት የሚለው ማነው፡፡ የድንበር ጥያቄ የማያነሳው የትኛው ነው? ሁሉም አልተመቸኝም ለውጥ ያስፈልገኛል ብሎ ነው የነበረውን ሥርዓት የተቃወመው፡፡ መሠረታዊ ችግሩ እስካልተፈታ ድረስ ነገም ችግሩ ይቀጥላል ነው የምንለው፡፡ ኦሮሞና ሶማሌ ነገ በድንበር ላለመጋጨታቸው፣ ከዚያ ደግሞ ኦሮሞው ጉጂና ቦረና እያለ፣ አማራው ጎንደርና ጎጃም እያለ ግጭቶች ላለመቀጠላቸው ማረጋገጫ የለንም፡፡ በክልል የሚካሄደው ነገ ደግሞ ወደ ጎሳ ይገባል፡፡ ብሔርተኝነት አድጎ ሄዶ ‹‹አገርን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ›› የሚል ጥጋብ ውስጥ እንደሚከት በተግባር ሕወሓት አሳይቶናል፡፡ ያለፉት 30 ዓመታት ቀውስ አስተምረውናል ነው የምንለው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ስካት ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...