በገነት ዓለሙ
እሑድ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. አስቀድሞ በይፋ ቀጠሮ ያልተያዘበትንና ድንገት ቴሌቪዥን እያየን የተቀላቀልነውን አንድ ሁነት አክብረናል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት (በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 72/1 መሠረት የአገሪቱ መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነትና የአስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው) በይፋ የፌስቡክ ገጹ፣ ‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ የጦርነት ምዕራፍ በመዝጋቷ ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት ታከብራለች፡፡ ‹ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና› ነው የዕለቱ መሪ ቃል›› በማለት ጭምር ነው ወደ ‹‹በዓሉ›› አከባበር የመራንና የወሰደን፡፡
በቴሌቪዥን ቀጥታ ሥርጭት ሦስት ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜ በወሰደው፣ በዚህ ‹‹ምሥጋናና ዕውቅና›› መስጫ ጭምር በሆነው መድረክ ላይ በቀረበበት ቅደም ተከተል መሠረት የደቡብ አፍሪካዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት፣ የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንትና ዋናው አደራዳሪ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሐመት፣ እንዲሁም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ንግግር አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም በዚሁ ተራ ቅደም ተከተል ንግግር አድርገዋል፡፡ ለበርካታ ሰዎችም (አርባ ይሆናሉ) ‹‹ምሥጋናና ዕውቅና›› የተደረገበት ሥነ ሥርዓት ተካሄዷል፡፡
ስድስኛ ወሩ ውስጥ ገብተን፣ ወይም አምስት ወር ተኩል ላይ ሆነን ያከበርነው፣ ያስታወስነው፣ ወይም የዘከርነው ይህ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ያለ ምንም ጥርጥር በገዛ ራሱ ምክንያት ታላቅ ስምምነት ታላቅ ድል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ ሕገ መንግሥታዊነት፣ በዚህ የማዕቀፍ ግቢ ውስጥ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ከእነ ስሙ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ግጭትን በቋሚነት በመግታት/በማቆም አማካይነት (ወይም በዚህ በኩል) ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ስምምነት ነው እያልኩ ደጋግሜ የማስረግጠው ከዚህ ቀደም ሲል ሰኔ 2013 ዓ.ም. እና መጋቢት 2014 ዓ.ም. እንዳየነውና እንደመሰከርነው ዓይነት የአንድ ወገን የግጭት ማቆም ዕርምጃ ብቻ ስላልሆነ ነው፡፡ የአንድ ወገን የብቻ ዕርምጃ አይደለም፡፡ የሰላም ስምምነት ነው፡፡ ይፋ ስሙ፣ ስያሜውና አርዕስቱ እንደሚገልጸው ደግሞ፣ የሰላም ስምምነት ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት ነው፡፡
እዚህ ለዘላቂ ሰላም ስምምነት ዝርዝርና ነቂስ ጉዳዮች ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ፣ ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም ላይ ዝም ብዬና ዘልዬ እገባለሁ አይልም፡፡ ዘላቂ ሰላም ላይ እደርሳለሁ የሚለው ግጭትን በማቆም አማካይነት ነው፡፡ ከአስቸኳይ ግጭት ማቆም ይጀምራል፡፡ ከአስቸኳይና ቋሚ እየሆነ ከሚቀጥልና ከሚከታተል ግጭት ማቆም ይነሳል፡፡ ከዚህም በመነሳትና በዚህ በኩል ዋናው ግብ ዘላቂ ሰላም ነው፡፡ ዘላቂ ሰላም ላይ ለመድረስ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር፣ መሠረቱንም ማደላደል ነው፡፡ ከአስቸኳይ፣ አሁኑና ወዲያውኑ ከሚጀምር ግጭት ማቆም የሚነሳው የስምምነት ዓላማ ግጭት ማቆምን ይበልጥ ቋሚ እያደረገ በመሄድ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስደውን ጎዳና እያደላደለ ይረማመዳል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻውና መቆንጠጫው ደግሞ ዝም ብሎ ‹‹መልካም ምኞት›› እና ‹‹በጎ ፈቃድ›› (ብቻ) አይደለም (ስምምነቱ መተማመንን ስለሚገነቡ ተግባሮችንና ባህርይዎችም ይወስናል)፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የስምምነቱ ዋና ማዕቀፍ ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊነት ነው፡፡ የስምምነቱ መግቢያ እና የመንደርደሪያ ድንጋጌዎች በመላው የስምምነቱ ወርድና ቁመት፣ እንዲሁም ይዘት ውስጥ ለተዘረዘሩት ሁኔታዎችና ውለታዎች (ተርምስ ኤንድ ኮንዲሽንስ) አከርካሪ ሆነው የሚያገለግሉ የመርህ ሐሳቦች አካተዋል፡፡ ለምሳሌ ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ ለዘለቄታው/በዘላቂነት የሚፈቱት በፖለቲካዊ መንገድ መሆኑን (መግቢያ)፣ ሁሉንም ዓይነት ፖለቲካዊ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መፍታት ይቻል ዘንድ፣ ግጭትን በቋሚነት የመግታት የስምምነቱ ሁኔታዎችና ውለታዎች ላይ መግባባትና መስማማት አስፈላጊነት (መግቢያ)፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ነውጥ (ቫዮለንስ) የትግል መሣሪያ አይደለም ብሎ እንቢ ማለት፣ ወዘተ ይወስናል፡፡
እናም ስምምነቱ ዴሞክራሲን (በመብቶቻችን፣ በነፃነቶቻችንና በመቻቻል ውስጥ መኖርን፣ ልዩነትንና አለመግባባትን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መፍታትን) ለሕግ መገዛትን፣ ሰላማዊና ሕጋዊ ተፎካካሪ/ተፋላሚ መሆን፣ ይህም የሚጠይቀውን ምግባርና ባህርይ መያዝን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አንድ ብቻ መሆኑን፣ የፖለቲካ ፓርቲና የጦር መሣሪያ መለያየትና መቆራረጥ ያለባቸው መሆኑን ይወስናል፡፡
ስምምነቱ ከሁሉም በፊትና ከመነሻው ግጭት ማቆምን ግዴታ በማድረጉ ተጨማሪ ሌላ ሞት እንዳይኖር አደርጓል፡፡ ለተከታይ ዕርምጃዎች በር ከፍቶ የተቻለውን ያህል ወደ ሰላም እየተጠጋን መጥተናል፡፡ የስምምነቱ ዋና ዋና አገዳዎችና ምሰሶዎች የአፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት በቃሉ ትክክለኛ ትርጉም መሠረት በስሙ እየተጠራ፣ እየተቆጠረ፣ አለ፣ ጎደለ፣ ሞላ ሊባል ይገባል፡፡
በአጠቃላይና በዚህ ምክንያት የስምምነቱ አፈጻጸም በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ልክ ‹‹መገምገም›› ተገቢ ሥራ ነው፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ብዙ ደፋ ቀና ማለትም፣ መዋረድም፣ መኮነንም መረገምም በታየበት የጨለማ ጊዜ ውስጥ ሳይቀር (እሳቸው ራሳቸው በንግግራቸው እንደገለጹት) ስምምነቱን በዋና አደራዳሪነት በመሩት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እዚህ መድረክ ላይ እንደነገሩን/እንዳሉን ይህ ‹‹ክብረ በዓል›› በዋናው የአገርና ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ የምንመራመርበት፣ ሞን ጎደለ? ምን ቀረ? የምንባባልበት መድረክ ነው፡፡ ኦባሳንጆ ያሉንንና የነገሩንን፣ ‹‹ክብረ በዓሉ››ም ከዚህ ማዕዘን ቢታይ ይበጃል ያሉትን ለማመላከት ከንግግራቸው ጥቂት ልጥቀስ፡፡
‹‹I wish to thank the Prime Minister and the Federal Government for organizing this important event that bring us together to take stock of lessons learnt from the African led and Ethiopian owned peace process as well as also to congratulate ourselves for the commendable work that has brought lasting peace to their beautiful country of Ethiopian.››
ከዚህ አፍሪካ እንደ አኅጉር በመራው፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ባለቤትነቷን አረጋግጣ (ሳታስነካ) ባካሄዱት የሰላም ስምምነትና የአፈጻጸም ሒደት ጭምር ምን እንማራለን? ቀላል ጥያቄ አይደለም፡፡ ለይስሙላና ለአንደበት ወግ ያህል ለክብረ በዓል የሚቀርብ ጥያቄ አይደለም፡፡ እንዳለፍንባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት ‹‹የውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ›› ዓይነት ወይም ትርጉም የለሽ ‹‹ግምገማ›› አይደለም፡፡
አንዳንድ ጉዳዮችን እንኳን እናንሳ ብንል ከስምምነቱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ለምሳሌ ትጥቅ የማስፈታቱ ማለት ‹‹ዲዲአር›› የሚባለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን የሚደነግገው የስምምነቱ አንቀጽ 6፣ ሀ ብሎ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመከላከያ ኃይል አንድ ብቻ ነው ብሎ ነው፡፡ ይህንን እናውቃለን፣ በዚህ እንስማማለን፣ ተስማምተንም ፈርመናል ይላሉ ተዋዋይ ወገኖች፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የስምምነቱ ድንጋጌ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር በተጣጣመ አሠራር ለሕወሓት ተዋጊዎች ኮምፕሪሄንሲቭ የ‹‹ዲዲአር›› ፕሮግራም ይቀረፃል፣ ሥራ ላይም ይውላል ይላል፡፡ ይህን ‹‹ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት በድምቀት›› ስናክብር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹‹ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና›› ስንል፣ ከሁሉም በፊትና በዚህ ምክንያት የምንጠይቀው በአንቀጽ 6 ቢ መሠረት፣ ለሕወሓት ተዋጊዎች የወጣው ኮምፕሪሄንሲቭ የ‹‹ዲዲአር›› ፕሮግራም ምን ይላል? የት አለ? በዚህስ መሠረት አፈጻጸሙ እንዴት ተከናወነ ማለት የዚህ ደማቅ በዓል አከባበር አካል የሆነ ጥያቄ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በተጠቀሰው ይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ እንደሚለው፣ ‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ የጦርነትን ምዕራፍ በመዝጋቷ ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት በድምቀት ታከብሯለች፡፡ ማለትም ‹‹Today Ethiopia marks a milestone by closing a chapter of war and celebrating the conclusion of the historic peace agreement.›› ልብ ይሏል፡፡ የእንግሊዝኛው ቅጂ ይበልጥ ግልጽ አድርጎ እንደሚያሳው፣ በድምቀት የምናከብረው የታሪካዊውን የሰላም ስምምነት መፈረም (ኮንክሉዥን) እንጂ የአፈጻጸሙን መጠናቀቅ አይደለም፡፡
በዚህ መሠረት ሕወሓት ከሌሎች መካከል ትጥቁን ፈትቷል ወይ? ሕወሓት እንደ ፓርቲ ከመሣሪያ ጋር ተፋትቷል ወይ? ወደ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ተመልሷል ወይ? የሚሉትና ሌሎች የምናከብረው፣ ‹‹በድምቀት የምናከብረው›› በዓል ተዘጋጅቷል ወይ? እያለ እየጮኸ የሚያስታውሰንን ቼክ ሊስት እየቆጠርን ምን ቀረ? ምን ጎደለ? ማለት አለብን፡፡ ጥያቄው በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይመለከታል፡፡ የምናደራጃቸው፣ ‹‹የምናማርጣቸው›› ፓርቲዎች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ወይም ተፎካካሪነት ውስጥ መታጠራቸውን የማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲ የሚባል ሥርዓት የሚጠይቀው የሠለጠነና የሰከነ ትግል ውስጥ የመወሰን፣ ደመ ነውጠኛነትን ሕገወጥና ወንጀል አድርጎ የመቁጠርና በዚህም የመገዛት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፓርቲዎች አደረጃጀትና አሠራር መንዕስ ዴሞክራሲያዊ ባህልና እሴት ውስጥ መታቀፍ አለበት፡፡
ሰላማችንን የምናከብረው፣ ‹‹ጦርነት ይብቃ ሰላምን – እናፅና›› ማለት የሚያምርብን፣ ከምናነበው ቼክ ሊስት እያነሳን፣ እየጣልን የምጠይቃቸው ጥያቄዎች ትርጉም ያለው መልስ የሚያገኙት ኦባሳንጆ በንግግራቸው የገለጹት፣ በአስቸኳይ መጀመር ያለበት የፖለቲካ ዲያሎግ ትርጉም ያለው መልስና መፍትሔ የሚያገኘው መሠረታዊው ዋና ጉዳይ ላይ ስንነጋገር ነው፡፡ ከልብና እውነት እውነቱን እየተነጋገርን፣ የትኛውም ወገን ሳይፈራ ሳይቸር እያነሳ የሚጠይቃቸው ጥቄዎች አሉ፡፡ ዛሬ አፋችንን ሞልተን የምንነጋገረው ስለሕወሓት ትጥቅ መፍታት፣ ከሕወሓት ጋር ስለተደረገው የጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ስምምነት ነው፡፡ በአጋጣሚ ይሁን ወይም ምናልባትም ይሁነኝ ተብሎ ማለትም በዕቅድ ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በወጣ የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የትርጉም ድንጋጌ እንደተወሰነው፣ ስምምነት ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትና በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በተከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ ታጥቆ በተደራጀ መልኩ ሲሳተፍ በነበረ ኃይል መካከል የተደረገ የግጭት ማቆም ስምምነት ነው፡፡ ከየትኛውም ታጥቆ ከተደራጀ ኃይል ጋር የሰላም ስምምነት ማድረግና ሰላምን መፈለግ ጥሩ ነው፣ ተገቢ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን አገራችን ኢትዮጵያ በገዛ ራሷ መንግሥትና አለፍ ሲልም በጎረቤት አገር ላይ የሚተኩስ የታጠቀ ቡድን የማይበቅልባት አገር እንድትሆን ምን መደረግ አለበት?
‹‹ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና›› ማለትም ሆነ ሲጀመር ጦርነትን ለመከላከል ጦርነት እንዳይነሳ ለማድረግ፣ አገሪቱ ከአምስት ዓመት በፊት፣ ማለትም ሁለት ዓመት የወሰደው ጦርነት ከመነሳቱ ከሦስት ዓመታት በፊት ወደተጀመረው ወይም ተጀምሮ ወደ ነበረው ዴሞክራሲን የማደላደልና የሕግ የበላይነትን የማቋቋም መሠረታዊ ጅምር መለስ እንበል፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለጸው ዴሞክራሲን የማደላደልና የሕግ የበላይነትን የማቋቋም ተግባር፣ የአገሪቱን ሥርዓተ መንግሥት ወታደራዊና ሲቪል ቢሮክራሲ ከፓርቲ ባለቤትነት፣ ቁጥጥርና የተፅዕኖ ሰንሰለት መለያየት አለባቸው፡፡ ፓርቲዎች ከባለጠመንጃነት መፋታት ይገባቸዋል፡፡ የታጠቀ ፓርቲ ብሎ ዴሞክራሲ የለም፡፡ በግልጽና ከምር መነጋገሪያ መሆን ካለባቸው ጉዳዮች መካከል፣ የኢትዮጵያን የመንግሥት አውታራት ከፓርቲ ባለቤትና ተፅዕኖ የማፅዳትና ነፃ አድርጎ እንደ አዲስ የማዋቀሩን ጅምር ማንና ምን እንዴት ቀጨው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
ኢሕአዴግ የተባለው ገዥው ግንባር የትኛውም ምርጫ እንዲያናጋው ሆኖ ዓምደ መንግሥትነትን ራሱ ተሾሞና ተተክሎ ሲገዛ የኖረው፣ ሕወሓት ይቆጣጠረው በነበረ የመንግሥት ዓምድ አማካይነት ነው፡፡ ዛሬም ሁለት ዓመታት የፈጀ፣ አገር ለውድመትና ለዕልቂት የዳረገ ዕልቂት ከተፈተጸመ በኋላ አሁንም ዛሬም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በአገር የመከላከያ ሠራዊት ላይ የተወሰደውን ጥቃትና ወረራ እውነቱና እውነት እየተነገረለት አይደለም፡፡ ዛሬም በሚገርም ሁኔታና ምክንያት የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ኮርፖሬት ሚዲያው (ከሞላ ጎደል) በሙሉ ጦርነቱ የተነሳው ዓብይ አህመድ የሰሜን ዕዝ ተጠቃ ብለው በወሰዱት ወታደራዊ ዕርምጃ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ ይህንን እውነት፣ ወይም የዚህን ጉዳይ እውነት አፍርጠን መነጋገር አለብን፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ዓይነት የትም ታይቶ የማይታወቅ የውስጥ ወረራ እንዴት አጋጠመ? በምን ምክንያት ወደ እዚህ የወሰዱን፣ ያደረሱን የትኞቹ ሁኔታዎችና ብልሽቶቻችን ናቸው? የሥልጣን አያያዛችን? የመንግሥታዊ ዓምዶች አወቃቀርና ከፓርቲ ጥገኝነትና መዳፍ አለመላቀቅ?
የፕሪቶሪያውን ስምምነት ምሥጋና ይግባነውና ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመከላከያ ኃይል አንድ ብቻ ነው›› ብሎ ‹‹ወስኖልናል››፡፡ የፕሪቶሪያው ሕገ መንግሥታችሁን ዕውቁ፣ ሕገ መንግሥታችሁን ኑሩ፣ መኗኗሪያ አድርጉ ብሎናል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51(6) እና 52/2/ሰ (የአገር መከላከያ የመንግሥት ሥልጣን የፌዴራል መንግሥቱ ብቻ መሆኑን፣ የክልል መንግሥት ሥልጣን በፖሊስ/ሕግ ማስከበር ላይ የታጠረ መሆኑን፣ የዚህም የደረጃ መለኪያ አውጪ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን) መኗኗሪያችን አለመሆኑ የሚናገር፣ የሚጮኽ ደም የሚሰማበት መልዕክት ነው፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት የሚቃኘውና የሚገራው የሰላም ውል ወይም ስምምነት ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተጋግዞ ባለ ዕዳ ያደረገውን የክልል አስተዳደርና የቀድሞውን ገዥ ፓርቲ ብቻ አይደለም፡፡ በየትኛውም ደረጃ ለተደራጀ/ለሚደራጅ አስተዳደርና ፓርቲ፣ የፖለቲካ ድርጅት ጭምር ነው፡፡ ፕሪቶሪያ (የፕሪቶሪያው ስምምነት) የሰው ደምና ዕንባ እየተፋ፣ ይህንን በሚያስተጋባበት ዓለምና አገር ውስጥ ሆነንም በታንዛኒያ ለተያዘ ሌላ የሰላም ስምምነት እገኛለሁ ብሎ የተፈጠመ ተዋዋይ ወገን፣ ከሌሎች መካከል መጠሪያ ስሜ/መጠሪያ ስያሜዬ ‹‹የ…ነፃ አውጪ ጦር›› ነው ብሎ ሲከራከር/‹‹መብት ሲያስከብር››ም ሲያሳክርም እንሰማለን፡፡
በአገራችን ስለሰላም፣ ስለኑሮ ውድነት፣ ስለሌሎች ብዙ ነገሮች፣ ከሞላ ጎደል ስለሁሉም ነገር ሲነገር ‹‹…ዱሮ ቀረ›› ማለት የተለመደ ነው፡፡ አዎ ባለፉት ሰላሳ ያህል ዓመታት በአፈናና በጥርነፋ የተጠበቀ ሰላም ነበር፡፡ አጠቃላይ ትግሉ እየበረታ መጥቶ በገዥው ፓርቲ ውስጥ መናጋትም ደርሶ አፈናውና ጥርነፋው ላላ ሲል፣ እንዲሁም ይፈለጉ የነበሩና ያልተጠበቁ የለውጥ ዕርጃዎች እየተከታተሉ ሲመጡ የሐሳብ ልዩነቶችንና ውድድሮችን የማስተናገድ/የማስተናበር ልምድ አይቶም አግኝቶም የማያውቀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ጭንቅ ጥብ ውስጥ ገባ፡፡ ልዩነትን በውይይት የመፍታት ዴሞክራሲና ጨዋነት እስትንፋሱ ቀርቶ ወጉ ያደረገ ግንኙነት ጠፋ፡፡ እንዲያውም ልዩነቶቻችን አብሮ መሥራት አያስችለንም ማለትን የመሰለ ሰላም የሚያሳጣ ግንኙነት መጣ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ወይም ዴሞክራት ነኝ እያሉ በዕውቀትና በመረጃ መከራከር፣ አለመግባባትን በውይይት መፍታት አለመቻል ችግርና ጣጣ ፈጠረ፡፡ ለዴሞክራሲ መደላደል መንደርደሪያ መሆን የሚገባው የነፃነት አየር በቃል መውጫ መብት ወደ መሆን ተለወጠ፡፡ በዚህ ላይ ትናንት፣ ከትናንት ወዲያ እነሱ በገዥነቱ ቁንጮ ላይ በነበሩበት ያስቀሩትን መብት ዛሬ በለውጡና በሽግግሩ ወቅት ምጥ ላይ ግፋ በለው ባይ እየሆኑ ለአደጋ አጋለጡት፡፡ የዴሞክራሲው ጭላንጭልም በተለይ በአዲስነቱ የግርግር መደገሻ አድርጎ ለሚማግጥበት፣ ኃላፊነት የጎደለው ታጋይነትና አታጋይነት እየተጋለጠ መጣ፡፡ በእነዚህና ይህንን በመሳሰሉ ምክንያቶች አገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አየር እየጠራ፣ ሻል እያለ ወደ ሰከነና ወደ ሠለጠነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ግብግብ አልለወጥ አለ፡፡ ፖለቲካውን መልክ ማስያዝ አቃተ፡፡ የፖለቲካው ሁኔታ ሰላምን በውጤትነት ስለማስከተሉ፣ የፖለቲካው መድረክ ለሁሉም ተፎካካሪዎች በእኩል ስለመከፈቱ፣ ሕዝብ ብሶቱንና ችግሮቹን የሚያስማማበትና መፍትሔ የሚያገኝበት ፍትሐዊ አሠራሮች መስፈናቸውን፣ ፖለቲካዊ ሒደት ውስጥ ማን ትክክል፣ ማን ስህተተኛ ስለመሆኑ መለያው መንገድ በጉልበተኞች በአብጤዎች በመወናበዱ፣ በአጠቃላይ ፓርቲዎች በተለይ ኃይሎችና ጉልበተኛ ፓርቲዎች ያዋጣናል፣ እናውቅበታለን ያሉት ከሰላማዊውና ከሕጋዊው ተፎካካሪነት ይልቅ ተቃራኒውን በመሆኑ፣ ከሰላማችን ጋር ሕግና ሥርዓት የማስከበር የመንግሥት አቅምና ሚና ሁሉ ለአደጋ ተጋለጠ፡፡
ይህን ሁሉ ማከም፣ ለዚህ ሁሉ መላና መፍትሔ መፈለግ አለብን፡፡ ‹ድሮ ቀረ ብሎ›› ነገር ‹‹ትርጉም›› ይኖረው ዘንድ አንዱን ከአንዱ ማወዳደር እንዲያምርብን ካስፈለገ፣ ለቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች ደም መቃባት በሌለበት መንገገድ ይፈታሉ? የፖለቲካ ጠቦች፣ የሕዝብ ቅሬታዎች ወደ ጠመንጃ የሚሄዱበት ዕድል እየጠበበ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶና ስብስቦሽ እየሰፋ ሄደ? ለሚሉት ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት አለብን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡