የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮችንና ኩባንያዎችን በአክሲዮን አባልነት በመያዝ ፋይናንስ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን የተለመው ናሽናል ፋይናንስ አካዳሚ አክሲዮን ማኅበር በ40 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተመሠረተ።
የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ያለባቸውን ብቃት ያለው የሰው ኃይል እጥረት በመገንዘብ፣ ሥልጠናና ትምህርት ለመስጠት የተቋቋመው አክሲዮን ማኅበር ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. የምሥረታ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ የምሥረታ ጉባዔውን በተመለከተ የማኅበሩ አደራጆች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ናሽናል ፋይናንስ አካዴሚ አክሲዮን ማኅበር በ10 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ተመሥርቶ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን አጠቃላይ የተፈረመ ካፒታሉ ግን 40 ሚሊዮን ብር ነው።
አካዴሚውን ወደ ሥራ ለማስገባት ለአንድ ዓመት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን፣ በስተመጨረሻም 43 ባለአክሲዮኖችን ይዞ መመሥረቱን ከኩባንያው አደራጆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ተሾመ በየነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህ ተቋም ከፋይናንስ ዘርፉ ጋር በፍጥነት ለማደግና የዘርፉን የሰው ኃይል ፍላጎት ለሟሟላት በትጋት የሚሠራ ተቋም እንደሚሆን የሚገልጸው የአክሲዮን ማኅበሩ መረጃ ያመለክታል።
የፋይናንስ ባለሙያዎችን የማሠልጠን ተመሳሳይ ዓላማ ያነገበ ‹‹ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አክሲዮን ማኅበር›› የተባለ የሥልጠና ማዕከል መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም መመሥረቱን ሪፖርተር ዘግቦ ነበር።
ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል ለፋይናንስ ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚችል የተደራጀና የተጠናከረ የምርመር፣ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎቶችን ለማስጠት ያለመ ሲሆን፣ የፋይናንስ ልህቀት ማዕከሉ በ61.6 ሚሊዮን ብር የተፈረመና በ34.8 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከልን የመሠረቱት ዘጠኝ ባንኮች (ንግድ ባንክ፣ ወጋገን፣ ቡና፣ ንብ፣ አዋሽ፣ ዳሽን፣ ደቡብ ግሎባል፣ አዲስ ኢንተርናሽናል፣ ጎህ ቤቶች)፣ ዘጠኝ የመድን ኩባንያዎች (አፍሪካ፣ ኒያላ፣ ናይል፣ ቡና፣ ንብ፣ ሉሲ፣ ዓባይ፣ አዋሽ፣ ፀሐይ)፣ አንድ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም (ዋሳሳ)፣ ሁለት የፋይናንስ ዘርፍ ማኅበራትና (የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች፣ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ማኅበር) እንዲሁም ግለሰቦች ተሰባስበው ነው።
ናሽናል ፋይናንስ አካዳሚ አክሲዮን ማኅበር ተመሳሳይ ዓላማ ይዘው ከሚሠሩት እንደ ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል ያሉ ተቋማት ጋር በቅርበትና በመደጋገፍ የመሥራት ህልም እንዳለው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህንን አክሲዮን ማኅበር በማደራጀት ረገድ በቀዳሚነት የተጠቀሱት የኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራስ ኩባንያ አደራጅና የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ተሾመ በየነና የዚሁ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን እያገለገሉ ያሉት አቶ ሽመልስ ገብረ ጊዮርጊስ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ በተጨማሪ በአደራጅነት የተሳተፉት አቶ ደሱ ታምራትና አቶ ተሾመ ሞሲሳ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከ43 ፈራሚዎች ባለአክሲዮን መካከል አቶ ጉዲሳ ለገሰ የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ አቶ ዳዊት ዋቅጋሪ የንስር ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም አቶ አብርሃም ሃይለማርያም የኤ.ኤች.ኤም አማካሪዎች ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ይገኙበታል፡፡
የወጋገን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አክሊሉ ውበት፣ የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ መሥራች ባለአክሲዮን የሆኑት አቶ ኪሮስ ጂራኔ የሚገኙበት ሲሆን፤ በኩባንያ ደረጃ ባለ አክሲዮን ከሆኑት መካከል ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹንስና ናይስ ኢንሹራንስ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
ናሽናል ፋይናንስ አካዴሚ፣ በአጭር ጊዜ ዕቅዱ በስልጠና አማካኝነት ለውጥ የማምጣትና የዘርፉ የአቅም ጉድለቶችን በፍጥነት ለመሙላት ያለመ ሲሆን ፣ በቀጣይ ደረጃውን የጠበቀና ተከታታይነት ያለው፣ ጥናትና ምርምር የታከለበት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ውጥን ይዟል።
የመጨረሻውን የማደራጀት ምዕራፍ በማጠቃለልም ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ሥራውን ለመጀመር ያቀደ ሲሆን፣ ይህን ዕቅዱን ለማሳካትም ለሥልጠና ማዕከሉ የሚሆን ሕንፃ በአዲስ አበባ በጉርድ ሾላ አካባቢ መከራየቱንና በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት መዘጋጀቱን አደራጆቹ አመልክተዋል፡፡
በሥልጠና፣ በብቃት ማሟያና በከፍተኛ ትምህርት ለማተኮር የወሰኑት አደራጆችና ፈራሚዎች ወደፊት ሰፊ ካፒታል በማንቀሳቀስ ዘመናዊ የሥልጠና ማዕከል በአዲስ አበባ የመገንባት ራዕይ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡