Saturday, June 15, 2024

የሱዳን ቀውስ በጎረቤት አገሮች ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 1957 ነበር በሱዳን መዲና ካርቱም የተመሠረተው፡፡ ሱዳን ያኔ ከጎረቤቶቿ ኢትዮጵያና ግብፅ ጋር ሆና ነበር ለመላው የአፍሪካ አኅጉር መዝናኛ የሆነውን የእግር ኳስ መድረክ የፈጠረችው፡፡ ወደ 46 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትና በአፍሪካ በቆዳ ስፋት ሦስተኛ የሆነችው ሱዳን፣ ከጎረቤቶቿ ጋርም ሆነ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ኳስ ብቻ ሳይሆን የምትጋራቸው ብዙ ጉዳዮች አሏት፡፡

ሱዳን በተለይ ከጎረቤት ኢትዮጵያ ጋር 753 ኪሎ ሜትር ያህል የሚረዝም ድንበር ትጋራለች፡፡ ኢትዮጵያና ሱዳን ከጂኦግራፊያዊ ጉርብትና ባለፈም በክፉም በደግም ብዙ የታሪክ ውጣ ውረድን በጋራ ማለፋቸው ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ በፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ወቅት ለኢትዮጵያ ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ለአርበኞችም ሱዳን መጠጊያ ነበረች፡፡ ከድል በኋላ አፄ ኃይለ ሥላሴ አርበኞችን እየመሩ ከሱዳን በኦሜድላ በኩል ወደ መሀል አገር መግባታቸው ተደጋግሞ የሚነገር ታሪክ ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ከጥንት እስከ ዛሬ›› በሚል ርዕስ በ2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ውጭ ግንኙነት የሚዳስስ መጽሐፍ ያበረከቱት አቶ አክሊሉ ከበደ ኢረና፣ ሁለቱ አገሮች ያለፉባቸውን ውጣ ውረዶች ዳሰውታል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት ሱዳን ከእንግሊዝ ነፃነቷን ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ ሱዳን ነፃ ከወጣች ጊዜ ጀምሮ የተፈራረቁ መንግሥታት በሚያራምዷቸው የሃይማኖት አክራሪነትና በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የተነሳ ግን መረጋጋት አጥታ መቆየቷን ጽሐፊው ያወሳሉ፡፡

‹‹በአንድ ወቅት የሱዳን መንግሥት ከአልቃይዳ ኔትወርክ ጋር በመተባበሩ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በተለይም በአሜሪካ ሽብርተኝነትን በመደገፍ ሲወገዝና ማዕቀብ ሲጣልበት ቆይቷል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ለመካፈል አዲስ አበባ የነበሩትን የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ለማስወገድ የመግደል ሙከራ ሴራ የጠነሰሱ ኃይሎችን ሱዳን በማስጠለሏ ከኢትዮጵያ ጋር አጋጭቷት ቆይቷል፤›› ሲሉም ጸሐፊው ያስታውሳሉ፡፡

የሆስኒ ሙባረክ ግድያ ሙከራን ተከትሎ የኢትዮ ሱዳን ግንኙነት እንዴት እንደሻከረ የሚዘረዝሩት ጸሐፊው፣ ኢትዮጰያ በወሰደችው ዕርምጃ የሱዳን ዲፕሎማቶች ቁጥር እንዲቀንስ መደረጉን ያወሳሉ፡፡ የሱዳን አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን እንዳይበሩ መደረጋቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በጋምቤላ የነበረው የሱዳን ቆንስላ ተዘግቶ የሱዳን ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት አስገዳጅ ቪዛ እንዲጠቀሙ መደረጉንም ያመለክታሉ፡፡ ሁለቱ አገሮች መልሰው ከታረቁና ግንኙነታቸው ከተሻሻለ በኋላ ሱዳን ከዓለም ሽብር መዝገብ እንድትሰረዝ ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ብታደርግም፣ ነገር ግን ሁለቱ አገሮች በውስጣቸው በሚፈጠሩ የፖለቲካ ለውጦች መዘዝ ግንኙነታቸው አንዴ ሲጠብቅ ሌላ ጊዜ ሲላላ ነው የኖሩት ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በድንበር፣ በባህል፣ በታሪክ በኢኮኖሚና በሕዝቦች ትስስር ተጎራብታ እንደ መኖሯ መጠን በሱዳን የሚከሰቱ የፖለቲካ ለውጦች በኢትዮጵያም ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ ኖረዋል፡፡ ከሰሞኑ የተፈጠረው የሱዳን ግጭትና ጦርነትም ቢሆን በሁለቱ ተጎራባች አገሮች ላይ ጥላውን እንዳያጠላ እየተሠጋ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን የተፈጠሩ የፖለቲካ ለውጦች የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሲጫኑ ቆይቷል፡፡

እ.ኤ.አ. ሰኔ 2019 የሱዳን አብዮትን ተከትሎ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ኢትዮጵያ አሸማግላ ነበር፡፡ በሱዳን የተመሠረተው የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ግን ሁለቱ አገሮች በይደር ያቆዩትንና ለረዥም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱበትን የአልፋሽቃ አዋሳኝ ድንበርን የመያዝ ዕርምጃ መውሰዱ አይዘነጋም፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከባድ ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ባለፉት ሁለት ዓመታት የሱዳን ፖለቲካ ኃይሎች በድንገት አወዛጋቢውን የአልፋሽቃ መሬት መውረራቸውና ከኢትዮጵያ ጋር ተጨማሪ ውዝግብ መፍጠራቸው ፈተና ሆኖ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የሱዳን የሽግግር መንግሥት በጦር ሠራዊቱና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ልዩነቱ በመስፋቱ የሦስት ዓመት ጊዜ ገደቡ አልቆ ያለ ውጤት አበቃ፡፡ ወዲያው ደግሞ በወታደራዊ ምክር ቤቱ ውስጥ በተለይ በአብዱልፈታ አል ቡርሃንና በመሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል ልዩነቱ መስፋት ጀመረ፡፡ በዚህ የተነሳ በሁለቱ የጦር መሪዎች መካከል ጦርነት ፈነዳ፡፡ ከሰሞኑ እንደተሠጋውም ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው የሱዳን ጦርነት ሰዎችን ወደ ኢትዮጵያ እያሰደደ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ከ3,500 በላይ ሰዎች ግጭቱን ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተሰምቷል፡፡ የተለያዩ አገሮች ዜጎች ከሱዳን ጦርነት ለመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው ከሚለው ጎን ለጎን ደግሞ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ 270 ሺሕ ሰዎች ከሱዳን ወደ ጎረቤት አገሮች ሊፈልሱ ይችላሉ መባሉ ተጨማሪ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ስለወቅቱ የሱዳን ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር)፣ ‹‹ለሱዳን ሰላም አበክረን ነው የምንሠራው፤›› ሲሉ ዓርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር፡፡

በሁለቱ ተጎራባች አገሮች ውስጥ የሚፈጠር ችግር የአንዱ በሌላኛው ላይ ያለው ተፅዕኖ ቀላል እንደልሆነ ያመለከቱት አምባሳደሩ፣ ለዚህ ሲባል በሱዳን ሰላም እንዲፈጠር ኢትዮጵያ ገንቢ ሚና እንደምትወጣ አመልክተዋል፡፡ የሱዳን ችግርን ለመፍታት ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ያለበት ራሳቸው ሱዳናዊያን ናቸው የሚለውን ያሰመሩበት መለስ (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገሮች ሱዳናዊያኑ ወደ ሰላም እንዲመጡ መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በሱዳን ካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሐሙስ ዕለት የሚገኝበት አካባቢ የውጊያ ቀጣና መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ከባድ ውጊያ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በርካታ ሲቪሎች ለጉዳት እየተዳረጉ ነው የሚል መግለጫ ከሳምንት ቀደም ብሎ ያወጣው ኤምባሲው፣ ውጊያው መሠረታዊ አገልግሎት ለመስጠት እክል እንደፈጠረበት በሐሙሱ መረጃው አመልክቷል፡፡

‹‹በአካባቢያችን ኤሌክትሪክ ተቋርጧል፣ የምግብ ቁሳቁስ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል፣ ከኤምባሲ ቅጥር ወጥቶ መግባት አዳጋች ሆኗል፣ በዚህ ሁኔታ ዜጎችን መርዳት ቀርቶ የኤምባሲ ሠራተኞችም ሕይወት አደጋ ላይ በመውደቁ የተወሰኑ ሠራተኞች እንዲቀሩ በማድረግ አምባሳደሩን ጨምሮ ገዳሪፍ ከሚገኘው የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ሥራቸውን ያከናውናሉ፤›› በማለት ነው የኤምባሲው የሐሙስ መግለጫ ስለሁኔታው ያተተው፡፡

በሱዳን እየተካሄደ ስላለው ግጭት መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ዓርብ ዕለት ከሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ የጦር መሪዎች ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡

‹‹ታላቁ የሱዳን ሕዝብ ሰላም ያስፈልገዋል፤›› ማለታቸው የተሰማው ዓብይ (ዶ/ር)፣ ሁለቱ የጦር ተፋላሚ ኃይል መሪዎች ወደ ሰላም በሚመጡበት ሁኔታ ላይ በስልክ እንዳወያዩዋቸው በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ ውሏል፡፡

በሱዳን ስለተፈጠረው ግጭትና ጦርነት በተለያዩ የዓለም መገናኛ አውታሮች የሚነገረው ብዙ ነው፡፡ ስለሱዳን ቀውስ የተለያዩ ዓለም አገሮች የሚያንፀባርቁት አቋምም የተለየያ መልክና አቅጣጫ የያዘ ነው፡፡

ሁሉም በየአቅጣጫው ከራሱ ጥቅም በመነሳት የሱዳንን ጉዳይ ሊዳኝ በሚነሳበት በዚህ ወቅት ግን፣ ጉዳዩ ይበልጥ ይመለከተዋል ተብሎ የሚታመነው የአፍሪካ ኅብረት ነው ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በአስቸኳይ ግጭት እንዲያቆሙ ጥያቄ ያቀረበው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሀማት ባወጡት መግለጫ፣ ሁለቱ ኃይሎች በአስቸኳይ ግጭት አቁመው በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች አስቸኳይ ዕርዳታ የሚቀርብበት መንገድ እንዲከፈት ጠይቀዋል፡፡

ስለዚህ ቀውስ መሠረታዊ መንስዔና የመፍትሔ አቅጣጫ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሱዳናዊያንም ቢሆኑ፣ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ነው የጠየቁት፡፡ ሱዳናዊያኑ እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገሮች፣ ኢጋድና የአፍሪካ ኅብረት የሱዳን ጦርነት በአጭሩ እንዲያበቃ ገንቢ ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ሉትዊ ቴቢን (ዶ/ር) የተባሉ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ የአፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ሱዳናዊ ምሁር እንደሚናገሩት፣ የሱዳን ወቅታዊ ቀውስ ምንጭ የውጭ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡

‹‹የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳለ ጥርጥር የለውም፣ ወደዚህ ደረጃ ያደረሱንም እነሱ ናቸው፡፡ እነዚህ የውጭ ጣልቃ ገቦች ደግሞ በሚዲያ ዘመቻዎች ጭምር ችግሩን በማባባስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፤›› በማለት ነው ምሁሩ የችግሩ መሠረታዊ ምንጭ ያሉትን ያስረዱት፡፡

በሱዳኖች መካከል የፖለቲካ ልዩነት መኖሩ ብቻውን ለዚህ እንደማያበቃ የተናገሩት ሉትዊ (ዶ/ር)፣ ግጭቱ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የፈለጉ በርካታ ኃይሎች የተሠለፉበትና ወደ ጎረቤት የአፍሪካ አገሮች የመሠራጨት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ፣ በአፍሪካ ኅብረት ቅድሚያ ተሰጥቶት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌላኛው የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ በኢትዮጵያ ነዋሪ በሽር ናስር ሱዳናዊ በበኩላቸው፣ የሱዳን ግጭት በታጠቁ ኃይሎች መብዛት የተፈጠረ ነው ይሉታል፡፡

‹‹በየፊናው እንደ ልቡ የሚንቀሳቀስ ሠራዊት ፈጥረህ አገር መምራት እንደማይቻል ለሱዳን ፖለቲከኞች ሲመከር ነበር፡፡ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ዓለም አቀፍ አጋሮች ጭምር ከአብዮቱ ጀምሮ የታጠቁ የሱዳን ኃይሎች ወደ አንድ ዕዝ እንዲመጡ ሲያሳስቡ ነበር፡፡ አሁን የምናየው ግጭት መነሻም ይኼው ነው፡፡ ፈጥኖ ደራሽ የሚባለው ኃይል ትጥቅ ፈትቶ በመከላከያ ሥር መግባት አለበት፡፡ ተፋላሚ ኃይሎች በሁሉም ነገር ላይስማሙ ይችላሉ፣ ነገር ግን የሕዝቡን ፍላጎት ማክበርና ወደ አንደ መምጣት አለባቸው፤›› በማለት ነው የችግሩን ገጽታ ያብራሩት፡፡

ከሰሞኑ ለሦስት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተፋላሚዎቹ መድረሳቸው ቢነገርም፣ ነገር ግን በሁለቱም ወገን እየተጣሰ እንደሚገኝ በሽር ይናገራሉ፡፡ ጦርነቱ ከቀጠለ የሱዳንን ሕዝብ የበለጠ ተጎጂ ከማድረግ ባለፈ ወደ ጎረቤት አገሮችም ግጭቱ ሊዛመት እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ተፋላሚ ኃይሎች በማንኛውም መንገድ ግጭቱን ማቆም አለባቸው፡፡ ‹‹የሱዳን አብዮት ያመጣቸውን የነፃነት፣ የፍትሕና የሰላም እሴቶች ማክበር አለባቸው፡፡ ጦርነቱ አብዮቱ ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀውን ሰላማዊ የፖለቲካ ለውጥ ያደናቀፈ ነው፡፡ ተፋላሚ ኃይሎች ለአብዮቱ እሴቶች እንዲሁም ለጁባው ስምምነት መገዛት አለባቸው፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡

ሁለቱ ሱዳናዊ የፖለቲካ ምሁራን ጦርነቱ ተባብሶ አገራቸው ልክ እንደ ሶማሊያ ወደ መንግሥት አልባነት ልትቀየር ትችል ይሆናል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አገራቸው ያን የመሰለ ሁኔታ እንደማይገጥማት ተከራክረዋል፡፡

ሱዳን እንደ ሶማሊያ ልትሆን አትችልም የሚሉት ሉትዊ ቴቢን (ዶ/ር)፣ ‹‹የውስጥ ድክመታችን መንግሥትንም ሆነ አገራችንን ደካማ አድርጓል፡፡ ነገር ግን አንድነታችንን ማጠናከርና ችግራችንን በራሳችን መፍታት እንችላለን፡፡ የሚያስፈልገን ነገር ቅን ልቦና ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሽር በበኩላቸው፣ ‹‹የሱዳን ባህል፣ ሥነ ልቦናም ሆነ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እንደ ሶማሊያ ዓይነት ዕጣ እንዳይገጥማት የሚያደርግ ነው፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ ሱዳን ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ጊዜ ጀምሮ ብዙ ቀውሶችን ስትጋፈጥ እንዳለፈች የተናገሩት በሽር፣ ‹‹የውጭ ጣልቃ ገብነቱ ከቆመ ሱዳናዊያን የአሁኑንም ቀውስ የሚፈቱበት በቂ ልምድና ዕውቀት አላቸው፤›› ብለዋል፡፡

ሁለቱ ሱዳናዊ የፖለቲካ ሃያሲያን እንደሚናገሩት፣ የአሁኑን የሱዳን ቀውስ ለመግታት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የጎረቤት አገሮችና አኅጉራዊ ተቋማት ከፍተኛ ገንቢ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ወገኖች ዕይታ ኢጋድ፣ የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ ለሱዳን በጎ አሳቢ አገሮች በሱዳን ሰላም የማስፈን ጥረታቸው የሚሰምረው የራሳቸው የሱዳናዊያን መልካም ፈቃድ የታከለበት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

በሱዳን የተፈጠረው ግጭት ለአክራሪ የፖለቲካ ኃይሎች መፈልፈል፣ ለጠብ አጫሪ ፖለቲከኞች ወደ ሥልጣን መምጣትና ለሌላም ችግር አገሪቱን ተጋላጭ ያደርጋታል የሚለው ሥጋት የብዙዎች ነው፡፡ የአገሪቱ ጦርነት እስከቀጠለና

 በጠብመንጃ የሚፋለሙት የሱዳን ጦር መሪ አብዱልፈታህ አል ቡርሃንና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ (ሄሜቲ) ወደ ጠረጴዛ ውይይት በፍጥነት መምጣት ካልቻሉ፣ ሱዳናዊያኑ ከተመኙት በተቃራኒ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -