Thursday, June 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሐረሪዎች ለምን ሸዋል ዒድን ያከብራሉ? ለቱሪዝም ያለው ፋይዳስ ምንድነው?

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

መግቢያ

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሸዋል ዒድ ምንድነው? ሸዋል ዒድ ከቅድመ ኢስላም እምነት ጋር የተያያዘ ይሆን? ወይስ ሌላ ምስጢር ይኖረው ይሆን?  በዓሉ ለረዥም ጊዜ ሲከበር ኖሯል። ዛሬም በአገር ውስጥና ሐረሪዎች በሚገኙበት አገር ሁሉ ይከበራል። ለመሆኑ የሐረሪ አባቶች ይህን በዓል የተረዱበት መንገድ ምንድነው? ሐረር ድርብ በዓል በማክበር ወይም ጥንታዊ በዓልን በፈለገችው መንገድና ዓላማ ለውጣ በማክበር ብቸኛዋ የሙስሊም ‹‹አገር›› ናት? ለምን ከዚህ በዓል ጋር እጅግ ድንቅ የሆነው የበርቲ በርቲ ጨዋታ አይካሄድም? ክልላዊም፣ ብሔራዊም ጥቅም አለውኮ።

ይህን በሚመለከት ብዙ ተጉዣለሁ። በዚህ ረገድ በዓለም በርካታ ሙስሊም የሚገኝባቸው አገሮች፣ ዛሬ እንደ ኢስላማዊ በዓል ወይም ከኢስላማዊ በዓላት ጋር ደርበው የሚያከብሯቸውን በዓላት እግረ መንገዴን ለማጥናት ሞክሬያለሁ። 

ለማንኛውሞ ስለሐረሩ ሸዋል ዒድ ከማቅረቤ በፊት የሌሎችን አገሮች ተሞክሮ ለማቅረብ እሞክራለሁ። የመጀመሪያዋ ኢንዶኔዥያ ናት።

ኢስላማዊ በዓላት በኢንዶኔዥያ

አብዛኛው ሕዝብ ሙስሊም በሆነባት ኢንዶኒዥያ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ 6ቱ ከሁሉም በላቀ ደረጃ የሚከበሩ ሲሆን፣ ከእነሱም ውስጥ አንድ ወር የተጾመው ረመዳን ሲጠናቀቅ ዒደል ፊጥር የሚከበረው በከፍተኛ ድምቀት ነው። ደማቅነቱም የተገኘው ‹‹ብዙ ነገሮች ድል የተደረጉበት ነው›› ከሚል ስሜት የተገኘ ነው። ብዙ ወደ ከተማ ሄደው የሚኖሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው ጋር በዓሉን ለማክበር ወደ ገጠር ይሄዳሉ። በዒድ አልፊጥር ሁሉም ቤቶች በራቸውን ከፍተው እንግዶቻቸውን ጣፋጭ ነገሮችን (ብስኩት፣ ተምር፣ ከረሜላ፣ ለስላሳ መጠጥ እያቀረቡ የሚያስተናግዱ ሲሆን፣ ደስታም የነገሠበት ነው። ይህ በዓል ድሆች የሚያገኙበት ልጆች የበዓል ተሰጥቷቸው የሚፈነድቁበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ስለሆነ ለኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች ከፍተኛው ፌሽታ ነው።

በኢንዶኔዥያ ብሔራዊ ኢስላማዊ ልምዶች መሠረት አዲስ ዓመትም ባህላዊ ከሚባሉት በዓላት አንዱ ሲሆን በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። ሠራተኞችም የእረፍት ቀናቸው ነው። በዓሉ የሚከበረውም ወደ መስጊድ ሄዶ ጸሎት በማድረግ ሊሆን ይችላል። 

ሆኖም ሆኖም ኢንዶኒዥያውያን በተለይም የጃቫ ሙስሊም ነዋሪዎች እስልምናን በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተቀበሉት ሩዋታን (Ruwatan) የተባለ ጥንታዊ የባህል ጨዋታቸውን ይዘው ነው። ሩዋታን በአጭሩ ከእርግማን መለኮት፣ ከመጥፎ አጋጣሚ፣ ጸርና አጽራር፣ ከመጥፎ ዕድል፣ ከመጥፎ አደጋ፣ በአዋቂዎች ጸሎትና በራሳቸው ላይ ፈሳሽ እየፈሰሰባቸው በመፈወስ ወይም ከእርኩስ መንፈስ በመላቀቅ የህይወት ዘመናቸውን በተረገጋና ሰላማዊ በሆነ ስሜት እንዲኖሩ መደረግ ነው። በዓሉ ከሂንዱ ቡድሂስቶች የተወሰደ ሥርዓት የቀጠለ ነው። ይህም ባህላዊ በዓል የዒደል ፊጥር በዓላቸውን ያደምቅላቸዋል። ሩዋታን መከላከያው ብቻ ሳይሆን መርገምት የደረሰበትን፣ ዕድሉ የተመሳቀለበትን፣ ወዘተ ማዳን ጭምር ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሶሎ ነዋሪ የሆኑ ኢንዶኔዥያውያን ኮቤ ኬቦዋን የተባለ የበፋለው (Buffalo) ጎሽ ጥቁር ቀንድና ቆዳ በሰው ሠራሽ መንገድ አዘጋጅቸው ያንን ልጆችና ወጣቶች በብዛት ወደ ጎዳና በመውጣት እየተዘዋወሩ በኢድ አልፈጥርና በሙሐረም መግቢያ የሚያሳዩት ትርዕይት ነው።  ሌላውና አስደናቂው ባህላዊ ጨዋታ ትልቅ የጨርቅ ወይም ሌላ አሻንጉሊት ሠርተው እየጨፈሩ እየተደሰቱ መጫወት ነው።  ኢንዶኔዥያውያን ባህላዊ በዓሎቻቸውን ደግነትን፣ ከምንም እንከን መላቀቅን፣ መጽዳትንና መዳንን ‹‹ደግነት ከራስ ይጀምረው›› የአገራችን አባባል በተምሳሌትነት የሚጠቀሙበት እንደሆነ ይነገራል።

የናይጀሪያውያን የሙስሊሞች ተደራቢ በዓላት

ከናይጀሪያ ሕዝብ ግማሹ ሙስሊም ነው። የናይጀሪያ ሙስሊሞች በዋነኛነት ሁለት ኢስላማዊ በዓላት ሲኖራቸው፣ እነርሱም ዒደል ፊጥርና ዒደል አድሃ ናቸው። በተለያዩ ሥፍራዎች የሚኖሩ ሙስሊም ናይጀሪያውያን በዓላቱን የሚያከብሯቸው በተመሳሳይ መንገድ ነው።

ዒደል ፊጥር በናይጄሪያ የሚከበረው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲሆን ከእነዚህ በዓላት ቀጥሎ ዱራብ (Durab Festival) የተባሉ ለብዙ መቶ ዓመታት የቀጠሉ ባህላዊ በዓላት አሏቸው። እነዚህም በዓላት ከዳውራ ኢሚሬት (Daura Emirate-የዳውራ ሱልጣኔት መሪዎች) ጋር የተያያዙ ናቸው። ጥንት ፈረሰኞች የጦር ውጊያ ጥበብ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት ትርዕይት ያሳዩባቸው ነበር።  ይኸውም በሐረር አሁን ቀረ እንጂ ‹‹በርቲ በርቲ›› እንደሚባለው የዱላ ምክቶሽ ብሎም የጦርና የጎራዴ ምክቶሽ ወይም ፍልሚያ የማሳያ ጥበብ ትርዕይት እንደነበረው ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ ዛሬ ናይጀሪያውያን ከዒድ በኋላ ያለውን ቀን የሚያከብሩት በሰልፍ ትርዕይትና የጎዳና ትርዕይት በማሳየት ወደ መሪዎቻቸው በመሄድ ምስጋና ያቀርባሉ። በዚህ ጊዜ ፈረሶች በቀለማት የተሽቆጠቆጠ ኮርቻ፣ ግላስ ልጓም፣ ልባብ ልብስ ይለብሳሉ። ፈረሰኞቹም የባህል ልብስ ይለብሳሉ። ነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያም ይይዛሉ። ሠልፈኞች ከዚህም በተጨማሪ በነጋሪት፣ በድቢ፣ በከበሮ፣ በዜማ ይታጀባሉ። (ሐረሪዎች በሸዋል ዒድ ዕለት ኢማም አሕመድንና ልሎች ጀግና መሪዎቻቸውን በህሊናቸው ያስታውሳሉ እንጂ ይህ ትውልድ እንደሚያውቀው ጦር ሰብቀው ጎራዴ ወድረው ያንን ስሜት እንደማያከብሩ ያስታውሷል። ወደፊት ግን እንደ ቱሪስት መስህብ ትርዕይቱን ያሳዩ ይሆናል።)

ናይጀሪያውያኑ ሙስሊምች የሠልፍ ትርዕይታቸውን እያሳዩ አሚሩ (ሡልጠኑ) ፊት ሲደርሱ ጎራዴያቸውን ወደላይ ከፍ በማድረግ የክብር ሰላምታ ያቀርባሉ። በአሁኑ ጊዜ ግን ይኸው ትርዒት የቱሪስት መስህብ ሆኖ ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ላይ ይገኛል። 

ናይጀሪያውያን የነብዩ ሙሐመድ (ሰዓወ) የልደት ቀንን በብሔራዊ ደረጃ የሚያከብሩ ሲሆን አከባበሩም እንደየ አካባቢው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጉዳይ ወደፊት በሚቻል መንገድ ሁሉ ሰፋ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

በዓላት በኢስላማዊ መንግሥቷ ፓኪስታን

ምናልባት ብዙዎቻችሁ አሳምራችሁ እንደምታውቁት ፓኪስታን በደቡብ እስያ የምትገኝ 243 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት፣ በዓለም በሙስሊሞች ቁጥር ከኢንዶኔዥያ ቀጥላ ሁለተኛ አገር የሆነች ናት። ስለስፋቷ፣ ስለጎረቤቶቿ አገሮች እናንተው ፈልጋችሁ አግኙት።  ለማንኛውም ፓኪስታን ከህንድ ተገንጥላ በሕዝቧ ፍላጎት ኢስላማዊ መንግሥት ያቋቋመች ብቸኛዋ አገር ናት። ፓኪስታን አሁን እዚህ የማልዘረዝራቸው ነገር ግን በሙስሊሙ ዓለም እጅግ የተደነቁና በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን የጻፉ፣ በዓለምም ኢስላምን ያስፋፉ ዑለማዎች ነበሯት። አሁንም አሏት። እዚያ አገር ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያተረፉ አሥር ወይም ሃያ ኪታብ መጻፍ ብርቅ አይደለም። ያን ያህል ጻፍኩ ብሎ መኮፈስም የለም። ለስማቸው መጥሪያ አንድ መጽሐፍ እንኳን ሳይጽፉ የሚያልፉ ዓሊምች ‹‹አላህ ይርሃማቸው። የሰማይ ቤታቸውን ያሳምርላቸው›› ተብሎ ከመሸኘት በስተቀር የአዋቂዎች አዋቂ መስለው አይታዩም። ሳይታወቀኝ ወደ ሌላ አጀንዳ ገባሁ መሰለኝ።

እና በዚች አገር ሙስሊሞች በየዓመቱ የሚያከብሯቸው በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ሲኖሩ እነዚህም በዓላት የራሳቸው ጥቅም፣ የአከባበር ሥርዓት፣ ቦታና ጊዜ አላቸው። ከፓኪስታን ጥንታዊና ዘመናዊ ልምድ ጋር የተያያዙ ስለሆኑም በሙዚቃ (በመዙማ፣ በነሺዳ፣ በዚክር፣ በጭፈራ፣ በርችት፣ ምግብ በማዘጋጀትና አብሮ በመገባበዝ፣ ልዩ ልዩ ትርዕይቶችን በማሳየት የሚታሰቡ ናቸው። በፓኪስታን ከሚከበሩት ኢስላማዊና ባህላዊ በዓላት መካከልም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሻብ በራት (Shab-e-Barat)

ይህ በዓል በብሔራዊ ደረጃ የሚከበር ሳይሆን ማክበር አለብን ብለው የሚያምኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የሚያከብሩት በዓል ሲሆን ይህም በዓል ሻዕባን (ኢስላማዊ ወር) በገባ በ15ኛው ቀን ይከበራል። በዚህም ዕለት ሰዎች በሠሩት ስህተት በመፀፀት አላህን በጋራ ምሕረት የሚጠየቅበት ነው። ምሕረቱም ቁርዓን በመቅራት፣ በመንዙማ በነሺዳ፣ ይከናወናሉ። ነዋሪዎቹም ‹‹ሐላዋ›› የሚባለው ጣፋጭ ምግብ በማምጣት ከወዳጆቺቼውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ይመገባሉ።

መላ ቺራቓን (Mela Chiraghan)

ይህ በዓል የብርሃን በዓል እንደማለት ሲሆን ይህም በዓል ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚከበር ሲሆን የሚከበረውም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት የራሆሩ ዓሊም ሽኽ ሑሴንና ገጣሚ ያለፉበትን ቀን ለማስታወስ የሚበር ነው። ቁባቸውም ማሕዶ ላል ሑሴን ተብሎ ይታወቃል። በዓሉም የሚደረገው ላሆር በሚገኘው በሻሊማር መስክ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የሚከበረው ግን በ1958 በተሠራው ቁባቸው ወይም ቀብራቸው በሚገኝበት ቦታ ነው። በዓሉ ፑንጃብ ተብሎ በሚጠራው የፓኪስታን ግዛት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ የነበረው ሲሆን አሁን ግን የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል።

ጀሻን ኖውሩዝ (Jashan-e-Nowruz)

ይህ በዓል ከማርች 21 እስከ 23 ቀን ባለው ጊዜ የሚከበር ሲሆን የአከባበር ሥርዓቱም ሆነ ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታው ከኖውሩዝ (ኢራን)፣ ከአፍጋሃኒስታን፣ ከማዕከላዊ ኤስያ አገራት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ይከበራል። በዚህ ዕለት በተለይም ባልቲስታንት በተባለው ሥፍራ በቤት ውስጥ በቀለም የተዋቡ እንቁላሎችን ለወዳጅ ማበርከት የተለመደ ነው። ከቤት ውጭ ማለትም በአደባባይ ደግሞ በባህላዊ ሙዚቃ፣ ፖሎ የተባለውን ባህላዊ የስፖርት ጨዋታ በመጫወት፣ እሳት በመዝለል ይከበራል። እሳት የመዝለል ባህል ከእስልምና በፊት ማለትም በአቸሜነስና በሳሲናይድ ሥርወ መንግሥት ዘመነ ከነበረው የቀጠለ ሲሆን ፓኪስታኖች በዚህ ዕለት አዲስ ልብስ ለብሰው መታየት የተለመደ ነው። ለአገሪቱ ዕድገትና ልማት ዱዓ ይደረጋል። ሑዝና በተባለው ሥፍራ ደግሞ ከግብርና ምርት ጋር በተያያዘ መልኩ ይከበራል።

ሐረሪዎች ሸዋል ዒድን ለምንና እንዴት ያከብሩታል?

ለመሆኑ ሸዋል ዒድስ ምንድን ነው? ሐረሪዎችስ ይህን በዓል እንዴትና ለምን ያከብሩታል? ሸዋል ኢድ ከሌሎች ከባቢያዊ ባህሎች ጋር የተያያዘ ይሆን? ወይስ ታሪካዊ ምክንያት አለው?

በሸዋል ወር የሚከበር ልዩ በዓል ሲሆን ይህንንም በዓል ባህላዊ እንጂ ሃይማኖታዊ (ሸሪዓዊ) እንዳልሆነ ሐረሪዎች ያስረዳሉ። በእርግጥም ይህ በዓል ከባቢያዊ ባይሆን ኖሮ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ እስልምናን ያስፋፉት የሐረር ሊቃውንት በሁሉም ዘንድ እንዲከበር ተፅዕኖ ማድረጋቸው አይቀርም ነበር። ይህ ጉዳይ ከትግራይ፣ ከወሎና ከጎንደር በስተቀር በሌሎች አይታይም። በነዚህ አካባቢዎችም ቢሆን በሸዋል 8ኛ ቀን ዶሮም፣ በግም፣ ፍየልም በማረድና በዱዓ ይከበራል እንጂ ሌላ የለም። በየመስጊዱም ቢሆን ከመታሰብ የላቀ አይደለም። ታዲያ ለምን በሐረር ብቻ?

ጉዳዩን ከታሪክ ጋር የሚያያይዙት ሊቃውንት ሸዋል ዒድ የሚከበረው ኢማም አህመድ ኢብራሂም በሽምብራ ኩሬ ድል ያደረጉበት ዕለት እንደሆነ ያስረዳሉ። ዳሩ ግን ኢማም አሕመድ በሽምብራ ኩሬ ድል የተቀዳጁት በሸዋል 8 ቀን ነውን? ብለን ስንጠይቅ አይደለም። በመሠረቱ በድሉ ቀን የተለያዩ አስተያዬቶች አሉ።

 አንዳንዱ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም የሽምብራ ኩሬን ድል የተቀዳጁት እ.ኤ.አ ማርች 7 ቀን 1529 ማለትም ወርሃ ጁማደል ካልአይ 935 ሲሆን በእኛ አቆጣጠር መጋቢት 1 ቀን 1521 ይሆናል።  ሌሎች ደግሞ የሽምብራ ኩሬ ጦርነት ድል ማርች 11 ቀን 1529 በእኛ አቆጣጠር መጋቢት 3 ቀን 1521 ማለትም ረጀብ 1 ቀን 935 ነው ይላሉ።  በሁለቱ አቆጣጠር ያለው ልዩነት 3 ቀን ነው። ስለሆነም ሸዋል ዒድ ከኢማም አሕመድ አሕመድ ጋር የሚያያዝ ከሆነ ሸዋል ወር የአራት ወራት ልዩነትን ስለሚያሳይ ድል አድርገው ወደ ሐረር የተመለሱበትን ቀን ለማስታወስ ሊሆን ይችላል።

ሌላው የሸዋልዒድ መላ ልምታ (hypothesis) ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ዛሬ እስልምና በምሥራቅ አፍሪካ ከመስፋፋቱ በፊት በሐረርና በአካባቢዋ ባዕድ አምልኮ የሰፈነበት ሁኔታ በሰፊው እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ። ዛፎች የሚመለኩበት፣ ወንዞች የሚከበሩበት፣ ጠንቋዮችና ኮከብ ቆጣሪዎች የሚመለኩበት ዘመን ነበር። አንዳንዱም አምልኮም ሰው እስከ መሰዋዕት ሊደርስ ይችላል። ለአማልክቱ መዝፈን መጨፈር፣ መገበር ግዴታ ነበር።  ይሁንና እንደዚህ ያለው ለቀቅ ያለ ባህል በኢስላም ስለማይፈቀድ መከልከል አስላጊ መሆኑ አይቀርም። ስለሆነም ሊቃውንቱ ‹‹ለረዥም ዘመናት የነበረው ልማድ ከከለከልን በምን እንተካው?›› የሚለው ጥያቄ ማስጨነቁ የሚቀር አይመስልም። በሌሎች አገሮችም ጥንታዊ ነገር ግን ኢስላማዊ ያልሆኑ ልምዶችን ለማስቀረት በምትካቸው ከእስልምና ጋር የተያያዙ አዲስ ልምዶችን መተካታውን ከናይጀሪያ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከፓኪስታን አይተናል በዚህ ጽሑፍ ላይ አልቀረቡም እንጂ በግብጽ፣ በኢራን፣ በየመን፣ በቱኒዝያ፣ በሞሮኮ፣ በሴኔጋል በማሌዥያ፣ በአፍጋሃኒስታንና በሌሎችም ከኢድ አል አድሃና ከዒድ አልፊጥር በተጨማሪ የሚከበሩ በዓላት አሉ፡፡ ስለዚህ ጥንታዊ የሐረር አባቶች ሸዋል ኢድን አላህን እያመሰገኑ እንዲያሳልፉ ታስቦ የተደረገ ይሆን ይሆናል፡፡  

ያም ሆነ ይህ፣ ሸዋሊድ እንደሌሎች ሐረሪዎች ረቂቅና ተጨባጭ ባህላዊ ቅርሶች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዩኔስኮ እንዲመዘገብም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ለመሆን የሚያስችሉት ባህሪያት እንዳሉም ተለይተው ታውቀዋል።  የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል ባህልንም እንደሚያንጸባርቅ ተቀባይነት አግኝቷል።

ማለት የሚቻለው ‹‹ሐረር ሸዋል ዒድን የማክበር የራሷ የሆነ ባህል አላት። ባህሉ የረዥም ጊዜ የታሪክ ሒደትንና ምክንያትን ተከትሎ የመጣ እንጂ በአንድ ጊዜ ዱብ ያለ አይደለም። የየዘመኑ በርካታ የሃይማኖት አባቶች አክብረውታልና የእነርሱ ይሁንታን ያገኘ ነው። ሊቃውንቱ በአገር ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ አገሮች ታዋቂነትን ያተረፉ ናቸውና ምስጢሩን እነሱ ያውቁታል።››

የሐረር ሸዋልዒድ እንደ ቱሪስት መስህብ

በኢትዮጵያ ካሉት ከተሞች ረዥም ዕድሜ ማለትም 1000 ዓመት ያህል ዕድሜ ያስቆጠረችና አሁንም በእንቅስቃሴ የምትገኝ ሐረር ብቻ ናት።

  • በሐረር ውስጥ 100 ያህል ሡልጣኖች፣ ኢማሞችና ዐሚሮች በጊዜ ሒደት በቅደም ተከተል መርተዋል፣
  • የብዙዎቹ መሪዎች ቀብርና መታሰቢያ ተለይቶ ይታወቃል፣
  • 300 ያህል ቅዱሳን መቃብሮችና መታሰቢያዎች ይገኛሉ፣
  • መቶ ያህል መስጊዶች አሉ፣
  • ለዘይላዕና ለበርበራ ወደቦች ቅርብ ከመሆኗም በላይ ከነዚህ ወደቦች ጋር ያላት ትስስር ከፍተኛ ነው፣ መንገዶቹም ለቱሪዝም እጅግ በጣም ማራኪ ናቸው፣
  • በርካታ አውሮፓውያን፣ ዐረቦችና የሩቅ ምስራቅ ወደ ሐረር በእግራቸውና በአጋስሶች መጥተው ጎብኝተዋታል፣
  • በዓለም ካሉት ጥንታዊ ኢስላማዊ ከተሞች አንዷና ብርቋ ናት። ብርቅነቷም እንደ ቲንባክቱና ላሙ ነው፣
  • ለዓፋር ሱልጣኖችና ኢማሞች፣ ለሱማሌ ዑጋዞች፣ ለባሌና ለአርሲ ሸኾችና መሻኢኾች ዐይን ናት
  • ሐረሪኮ ከአፍራን ቃሉዎች፣ አላዎች፣ ኖሌዎች፣ ጃርሶዎች ከጋራ ሙለታ ኦሮሞዎች ጋር ድርና ማግ ናት፣
  • በሐረሪ ክልል ያሉ ቀበሌዎች ሁሉ ታሪካዊ ናቸው፣
  • ጅጎል የተሰኘው ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ያለው ግንቧ አስደናቂ ነው።
  • ታሪካዊዎቹ አምስቱ በሮቿና ወደበሮቹ የሚያደርሱ የመንገድ መስመሮቿ አስደማሚ ናቸው።
  • በአጭሩ ሐረር ዙሪያዋን ማለትም ከሐር እስከ ዘይላዕና በርበራ፣ ከሐረር እስከ ጅግጅጋ፣ ከሐረር እስከ ባሌ፣ ከሐረር እስከ አውሳ፣ ከሐረር እስከ አዋሽ እየተባለ ሲገለጽ ለቱሪዝም በእጅጉ የምትመች ናት፣
  • ከአክሱም ቀጥሎ የራሷ ገንዘብ የነበራትና ለአጼ ምኒልክ ሳንቲም ቀረጻ መጀመር አስተዋጽኦ ያደረገች እርሷ ናት፣
  • ለኤርትራና ለትግራይ፣ ለጎንደርና ለወሎ፣ የአው አባድርና ሸኽ ሐሺም የልጅ ልጆች ሁለተኛዋ ክልላቸው ናት፣
  • ከጅማ ሡልጣኔት ጋር እጅና ጓንት ናት፣

ስለሆነም ለዚች ጥንታዊ ከተማ በሐረሪዎች ልጆቿ ተጠብቆ መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ሌሎች የተረሱ ባህሎቻችን ለማስታወስ፣ ለማሳደግና ለቱሪስት መስህብ ለማድረግም እጅግ ከፍተኛ ጠቃሚነት አለው፡፡

ሸዋል ዒድ አምና ሲከበር

ሸዋሊድ እና ከሚያዝያ 30 ቀን 2014 እስከ ግንቦት 3 ቀን 2014 እጅግ ባማረ ሁኔታ በሐረር ከተማ ተከብሯል። በዚህ በዓል በሐረር የሚገኙ ሙዚየሞች፣ መስጊዶች፣ አምስቱ ጥንታዊ በሮች፣ ከሐረር ከ5-10 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው በኮረሚ፣ በአውሱፊና በአው ቡርቃ የሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ቤተመንግሥቶች፣ መስጊዶችና ጥንታዊ የመቃብር ስፍራዎች ተጎብኝተዋል። ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን በጥናታዊ ጽሑፎቹ ውይይት ተካሂዷል። በመጨረሻም የሐረር እንግዶች የተገነዘቡትን በውሳኔ ሐሳብ መልክ አስተላልፈዋል።

የሸዋሊድ እጅግ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበርም ከክልሉ ፕሬዚዳንት ከክቡር አቶ ኦርዲ በድሪ ጀምሮ ሁሉም የክልሉ ቢሮዎች ከኃላፊዎችና በልደረቦቻቸው ግንባር ቀደም በመሆን ተንቀሳቅሰዋል። የዲያስፖራ ኤጀንሲ ከዒድ እስከ ዒድ ፕሮግራም ነድፎ በመንቀሳቀሱ ከፍተኛ ኃይል ሆኗል። የሐረር ባለሀብቶችና ሌሎች ለበዓሉ ድምቀት በገንዘብም፣ በሐሳብም፣ በጉልበትም አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይህ በዓል እንዲሳካ የሐረር ሴቶች ያደረጉት እንቅስቃሴ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ፈቃደኛ ወጣቶች አካባቢያቸውን በማጽዳትና በማስተባበር የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። የሐረር መሻኢኾችና የሐረር ሽማግሌዎች ይህ ዝግጅት ዕውን እንዲሆን ለፍተዋል። የሐረር ሙዚቀኞች፣ የእደጥበብ ባለሙያዎች ያበረከቱት እሰተዋጽኦ በዓሉን አይረሴ አድርጎታል።  በተለይ የዓፋርና የአፋርና የኦሮምያ የኪነት ቡድኖች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።  ምሁራን ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ብዙ ጊዜ ደክመውበታል። በርካታ ጋዜጠኞች በዓሉን ተከታትለዋል። ስለሆነም ተጋባዥ እንግዶች በሕይወታቸው የማይረሳ ልምድ አካብተዋል። ተለምነው የመጡት እንግዶች በተለይም ወጣት ሊቃውንቱ ለምነው በመምጣት፣ ምናልባትም ከሐረር ርቆ መቆየት እስኪያስቸግራቸው ድረስ ተቆራኝተው ስለሐረር ኢስላማዊ ሥልጣኔ የላቀ ሥራ ያበረክታሉ ብዬ እገምታለሁ።

አዲስ አበባ በመቻሬ ሜዳተከበረው ሸዋል ዒድ

‹‹የሐረሪ ብሔረሰብ የሸዋል ኢድ በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው›› በሚል ርዕሰ ዜና ያሰራጨው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በበዓሉ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪን ጨምሮ ሚኒስትሮችና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ጠቀሶ የሸዋል ኢድ በዓሉ ላይ የሐረሪ ብሔረሰብ መገለጫ የሆኑ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ጨምሮ አውድ ርዕይ መዘጋጀቱን አውስቷል።

‹‹በዝግጅቱ ላይ በርካታ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆችና የሐረሪ ክልል አጎራባች ሕዝቦች ተወካዮችም እየተሳተፉ ይገኛሉ፤›› ሲልም ኢዜአ አስገንዝቧል። ከዚህም በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ አምባሳደሮችም ተገኝተዋል

በበዓሉ ከተገኙት መካከል የጀበርቲና የዓዲ ኸቢረ ዝርያዎች፣ አርጎባዎች ሲገኙ ሌላው ሐረሪ የሆነው ብሔረ ሥልጤ በዓሉን አድምቆት ውሏል። ይልቁንም የክብርት ጊስቲ ሙፍሪሓት ካሚል፣ ክቡር አምባሳደር ጌሲ ሬድዋን ሑሴን፣ ድምጻዊ ጌሲ ሙሐመድ ሲርጋጋና የታወቁ የሥልጢ ታላቅ ሰዎች መገኘት ክብሩን ከፍ አድርጎት ነበር ማለት ይቻላል። ሥልጢዎች የአባድር ልጆች ሲሆኑ እነጊስቲ ዘበሬት፣ እነጊስቲ መኪዬ፣ እነጊስቲ ፋጢመት የኢማም አሕመድ ኢብራሂም ሙጃሂዶች መሆናቸው በታሪክ ጊዜ፣ ቦታና ማንነት የተረጋገጠ ሐቅ ነው።

የሐረር ሸዋሊድ ፌስቲቫል ሐረር ካሏት በመቶዎች የሚቆጠሩ በዓሎች አንዱና ደማቁ ሲሆን የበዓላቱ መብዛትም ከታሪኩ ጥንታዊነት ብቻ ሳይሆን ተመዝግቦ መገኘት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ሆኖ መገኘቱ ነው። ‹‹ሐረር የኢስላማዊ ሥልጣኔ ምንጭ ናት›› ሲባልም የሚነግረን ብዙ ነገር ሲሆን አንዱ ያልተጠኑት ረቂቅና ተጨባጭ ቅርሶች ሳይጨመሩ መረጃ ያላቸው በርካታ መሆናቸውን ያስገነዝበናል። 

ሐረርን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሥራ ቢሠራ በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ቱሪስቶች ሊገኝ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል።

አዱኛ ሙጨ የተባለው ጸሐፊ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንደገለጸው፣

ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ጅግጅጋ በነበረን ቆይታ ‹‹ለአገረ መንግሥት ግንባታ የዲያስፖራው ሚና›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ በነበረው ሲንፖዚየም የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ አስገራሚ ነበር። ከኢድ እስከ ኢድ መርሐ ግብር አንዱ የሆነው ‹‹ሸዋልን በሐረር ኤግዚቢሽንና የባህል ፌስትቪል›› የሐረር ክልል መንግሥት በደማቅ ሁኔታ ተዘጋጅቷል። የዝግጅቱን ዓላማ ያብራሩት የክልሉ መንግሥት የሐረርን ባህልና ቅርሶች ከማስተዋወቅ በተጨመሪ ገናናው የሐረር ኢስላማዊ ሥልጣኔን በማስታወስ በአዲሱ ትውልድ ላይ ለማስረፅ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ነድፈዋል።  የቅርስ ጉብኝት የልማት ሥራዎች ምረቃ፣ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡኡበት ሲፖዚየምና ውይይት እንዲሁም የሸዋሊድ ታሪካዊ ዳራ እንዲሁም አከባበርን የመርሐ ግብሩ አካል ናቸው። በነገራችን ላይ ‹‹ሸዋል ዒድ›› የሚባል ሀደሬዎች አያውቁም። የሚያውቁት «ሸዋሊድ» ነው።

ሐረሮች የራሳቸው የሀደሬዎች ‹‹ባህል›› አላቸው። እንደ ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የራሳቸው የአኗኗር ዘይቤ አላቸው። ለቅሶአቸው ሠርጋቸው፣ የመተጫጨት ወጋቸው ከሌሎች የሚለዩበትም አንድ የሚሆኑበትም ባህል አላቸው። ለምሳሌ የጎጃም ሙስሊም ጥር ወር አልያም ከሚያዚያ እስከ ሰኔ እንጂ ሰርግ አልተለመደም። ከሽምግልና አላላክ ጀምሮ እስከ ሰርጉና ምላሽ እንዲሁም የጫጉላ ሁኔታ‹ ‹ብርአምባር ሠበረልዎ›› የሚባልበት ሒደት ልብስ ቆጠራና ትውውቅ የራሱ ቀለምና ቃና አለው። የሌሎችም እንዲሁ። 

ሐደሬዎችን የመተጫጨት ባህላቸው ሸዋሊድ ላይ ነው። ሸዋሊድ ከየትኛው ቦታ ያለ ሰው ወደ ሐረር መጥቶ ከቤተሰቡ ጋር የሚዘያየርበትና ያላገባ የሚተጫጭበት ባህል ነው።  በጨለንቆ ጦርነትም ሆነ ከዚያ በፊት የሐረርን ኢስላማዊ ስልጣኔ ለማጥፋት ጥላት ወረራ ያበዛባት ስለነበር በተለይም በጨለንቆው ጦርነት በዙ ሰው ስለረገፈ እሱን ዘር ለመተካት በሸዋሊድ ባህል ላይ ያላገቡት እንዲተጫጩ ይበረታታ ነበር። 

በፕሮግራሙ ላይ ስለ ሸዋሊድ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ምሁር እንዳሉት ‹‹እስልምና ሁለት ኢዶች ብቻ እንዳሉት» አስረግጠው ከተናገሩ በኋላ ‹‹ሸዋሊድ›› የሐረሪዎች ባህል እንደሆነ ታሪካዊ አመጣጡም ከኢማም አህመድ የሽንብራ ኩሬ ድል ጋር የተያያዘ እንደሆነ አብራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ ከጦርነቱ ባቲድልወንበራ የተመለሰችውና ጾሟን የጨረሰችው ስድስት ቀኑን በተከቱታይ በመፆም በበሸዋል 8 በማጠናቀቅ አብራ የኢማም አህመድ የድል ቀንን ተደስታ እንዳከበረችው ተብራርቷል። ይህንን የድል ቀን ታሳቢ በማድረግ ሐረሪዎች በልዩ ልዩ ሁነቶች ቀኑን ታሳቢ አድርገው ታሪኩን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያደረጉበት መንገድ አስገራሚ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከተቀየረው መስጅድ ፊት ለፊት ባለው መታሰቢያ አደባባይ ላይ የባህል ሁነት በመከወን የሞራል ከፍታቸውንና የሰላም እሳቢያቸው ተሻጋሪ መሆኑን በማሳየት ይከውኑታል።

ለሦስት ቀን በተጋበዝንበትና ከኢድ እስከ ኢድ መርሃ ግብር አንዱ በሆነው ሸዋልን በሐረር እግዚብሽኑም፣ ሲፖዚየሙም የባህል ዝግጅቱም ለክልሉ ሕዝብና መንግስት ፋይዳው የጎላ ነው። በተለይ ባህሉ የሁሉም እንዲሆን ካልቸራል እንደሆነ የተብራራበት መንገድ ለአሳታፊነቱ በብዙ መጨነቃቸውን አመላካች ነው። የሐረሪንና የሐረርን ባህልና ቅርስ በማስተዋወቁ ረገድም ሚናው የላቀ ነው። በታሪክ ሙህራን የቀረበው ሐሳብና ጥናታዊ ጽሑፍም ያልሰማው ይሰሙው ዘንድ ሁሉም ሚዲያዎች ሳይቆሩርጡ ቢለቁት መልካም ነው።

በብዕር ስሙ ዲሎቪች ኢል ሐረሪ በሚባል የሚታወቀው የሐረሪ ክልል ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ባልደካ ደግሞ ሸዋል ዒድን እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡

ሐረር ልዩ የሆነች ባለ ብዙ ታሪኮች፣ ቅርሶችና የብዙ ሕዝቦች ስብጥር መኖሪያ ቲኒሿ ኢትዮጵያ ተብላ እምትጠራ የፍቅር ከተማ ነች።  ሐረር ከተማ ውስጥ ሁሉም ተቻችሎ፣ ተከባብሮና ተደጋግፎ በልዩ ሁኔታ እሚኖሩባት ምርጥ ከተማም ነች።  እንግዲህ በዚህች ታሪካዊት ከተማ በየአመቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ እሚውል ልዩ የሆነ ባህላዊ ክብረ በአል ያላት ሲሆን ‹‹ሸዋሊድ›› ይባላል።

ሸዋል ማለት የታላቁ የረመዳን ወር ፆም ካለቀና ኢድ አል-ፊጥር ኢስላማዊ በአል ከተከበረ በኋላ የምናገኘው ወር ሸዋል በመባል ይጠራል። ማንኛውም ሙስሊም የረመዳንን ወር ፆም ከፆመ በሗላ ስድስት የሸዋል ቀን ፆሞችን ጨምሮበት ከፆመ በአንድ ዓመት ስለሚቀየርለት ትልቅ ምንዳ ያገኛል። በተለይ ሴቶች በየወሩ የወር አበባ ስለሚመጣባቸው በረመዳን የጎደሉባቸውን ቀናት እሚከፍሉት በእነዚህ ስድስት ቀናት ውስጥ ነው። ታድያ ይህ በሸዋል ወር ስድስቱ የሱና ፆሞች ከተፆሙ በሗላ ሐረሪዎች ሸዋሊድ ብለው የሚጠሩት የራሳቸው የሆነ ባህላዊ ክብረ በአል አላቸው። ይኼንን ክብረ በዓል ሐረር ከተማ ውስጥ ማክበር የተጀመረው ከኢማም አህመድ አል ጋዚ የሡልጣንነት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ አዋቂዎች ይናገራሉ። 

ታዲያ ይህ የሐረሪዎች ዓመታዊው ክብረ በዓል የተጀመረው በዛ ዘመን የነበረውን የሐረሪዎች የሕዝብ ብዛታቸው መቀነስና ለዲን አስተምህሮዎች፣ ለጦርነቶች ከተማቸውን ጥለው በሚሄዱበት ጊዜ በሌሎች የአገሪቷ ልዩ ልዩ ከተማዎች መኖር ግድ ስለሚሆንባቸው እዚያው ሕይወታቸውን በመቀጠል የዲን ትምህርቶችን በማስተማርና በማጠንከር ሕይወታቸውን ያሳልፋሉ። እንግዲህ ኢማሙ አህመድም ይህን ክስተት በመመልከታቸው የተነሳ ከአገራቸው የዲን አዋቂዎችና የሐገር ሽማግሌዎች ጋር በመወያየት፣ በመመካከርና ዘዴ በመቀየስ ከስድስቱ የሸዋል ቀናት በኋላ ዓመታዊው ክብረ በአል እንዲወሰን አወጁ። 

 ታድያ በዚህ ባህላዊው ዓመታዊ ክብረ በአል ላይ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚኖሩት ከየአቅጣጫው ተሰባስበው መገናኘት ይችሉ ዘንድ መንገድ ለመክፈት፣ የሐረርን ከተማ ኢኮኖሚያዊ ሒደቶችን ለማጠንከርና ለማጎልበት እንዲሁም ከተማዋ ሁሉንም ማስተሳሰር እንድትችል ተደርጎ የተቀየሰ ከመሆኑ በተጨማሪ በዚህ ክብረ በአል ላይ ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች የትዳር አጋራቸውን የሚፈልጉበት፣ የሚመርጡበትና ሽምግልና የሚልኩበትን ሁኔታዎቻቸውን ባህላዊ ልብሶቻቸውን በመልበስ በደማቅ ሁኔታ አምረው፣ ተውበውና ከተማዋን አሸብርቀው በኅብረት የሚያከብሩበት ልዩ የሆነ ባህላዊ ክብረ በአል ነው። 

ይህ ባህላዊ ክብረ በዓል የሐረር ከተማ ልዩ ቅርስ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በUNESCO ለመመዝገብ ዘንድሮ በልዩ ሁኔታዎች ከአጎራባች ክልል የባህል ቡድኖች፣ ወጣቶችና ትላልቅ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች አብረው በጋራ ያከብሩበታል፣ ትስስራቸውንም ያጠነክሩበታል፣ ታሪካዊቷን ከተማቸውንም ያሳድጉበታል፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትውውቆች እንዲጎለብቱና ቀጣይነት ይኖራቸው ዘንድም ታሪካዊ አሻራዎቻቸውን ያሳርፉበታል፣ የጋራ የሆነ ታሪኮቻቸውንም አብረው ያድሱበታል ትክክለኛውንም ከፋላሲው በመለየት ጥልቅ በሆነ ሁኔታ ከትበው ለትውልድ ያስተላልፉበታል።

ማጠቃለያ

አንዳንድ ሰዎች ከዒድ አልፈጥርና ከዒድ አልአድሃ ሌላ በዓል መከበር የለበትም ይላሉ፡፡ ማስረጃቸውንም ያቀርባሉ፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ እንዲህ ባዮች ተጨማሪ በዓሎችን አለማክበር መብታቸው ነው፡፡ ሆኖም የአክባሪዎችንና የመንግሥትን መብት ደግሞ መጋፋት የለባቸውም፡፡ በተለይም ጥንታዊ በዓላት ለኢኮኖሚውና ለማኅበራዊ ኑሮው ጠቃሚ ሆነው ከተገኙ ተጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም ነው፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles