Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየጤናማ አመጋገብ አስፈላጊነት እስከምን?

የጤናማ አመጋገብ አስፈላጊነት እስከምን?

ቀን:

ጤናማ አመጋገብ ላደጉት አገሮች ሕዝቦች እንጂ ለደሃ አገሮችና በቀን ሁለቴ እንኳን በልተው ለማያድሩ ሰዎች እንደ ቅንጦት ነው ብለው ለጤናማ አመጋገብ ቦታ የማይሰጡ ጥቂት አይደሉም፡፡

ጤናማ አመጋገብ ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ ጤናማ አመጋገብን አቅም ካለው ጋር ብቻ ማገናኘት፣ ጤናማ ምግቦች በአቅራቢያና በእጅ ላይ እያሉ ቦታ አለመሰጠትም በጤናማ አመጋገብ ላይ የተሠሩ ጥናቶች ክፍተት ብለው ካስቀመጧቸው ይጠቀሳሉ፡፡

ጤናማ አመጋገብ ላይ የማኅበረሰብ ግንዛቤ ለመጨመር የተሠሩ ሥራዎች በቂ ባለመሆናቸውም በርካታ ዜጎች በተለይ ተላላፊ ላልሆኑ ዘላቂ በሽታዎች ሲዳረጉ ይስተዋላሉ፡፡

- Advertisement -

ምግብ ሞልቶ በተትረፈረፈባቸው በሀብት በበለፀጉ አገሮች ጭምር ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን ባለመከተል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ሲጋለጡና ሲሞቱ ይስተዋላል፡፡

በድህነት ውስጥ ለሚኖሩና በልቶ ለማደር በተቸገሩ ሕዝቦ ዘንድ ችግር ሆነው ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን አለመከተልም እንዲሁ በርካቶችን ለዘላቂ ሕመም ሲዳረግና ሲቀጥፍ ይታያል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ብዙውን ጊዜ ሥር የሚሰዱና ዕድሜ ልክ የሚዘልቁ ሲሆን፣ ለረዥም ጊዜ የሚቆዩ የጀነቲክ፣ የፊዚዮሎጂ፣ የአካባቢና የባህሪ ውጤቶች የሚያስከትሏቸው መሆኑን የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ምክትል ዋና ይሬክተር አቶ አክሊሉ ጌትነት ይናገራሉ፡፡

የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች፣ ስትሮክ፣ ካንሰር፣ ሥር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ሕመሞች፣ እንዲሁም የስኳር በሽታ በአብዛኛው ጤናማ አመጋገብና የአኗኗር ዘይቤ ካለመከተል የሚከሰቱ እንደሆኑም ያክላሉ፡፡

ለበሽታዎቹ አጋላጭ ከሚባሉት መካከል ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ትምባሆ የአልኮል መጠጦችና ጫት መጠቀም፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡

ስኳር፣ ጨው፣ የሚረጋ ዘይትና የአትክልት ቅቤ፣ ፈጣንና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችና መጠጦችን ዘወትር አብዝቶ መጠቀምም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እንደሚያጋልጡ ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዕድገትና ከአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች በከፍተኛ ደረጃ እየቀረቡ ነው፡፡ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምርቶች ደግሞ ስኳርና ጨው የሚበዛባቸው፣ ማቆያ ግብዓት የሚጨመርባቸው፣ በአብዛኛውም በሚረጋ ዘይትና በአትክልትና ከእንስሳት ተዋጽኦ በሚገኙ ቅባቶች የሚሠሩ መሆናቸው ችግሩን ያበዛዋል፡፡

ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚጠቁና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ‹‹ቤትስባይ›› የሚል የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በዚህ ፖሊሲ ውስጥም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አንድ መንስዔ የሆነውን ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ለመቆጣጠር፣ አገሮች አስገዳጅ ሕግ እንዲያወጡ ምክረ ሐሳብ አስቀምጧል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምርቶች የፊት ለፊት ማሸጊያ ላይ የማስጠንቀቂያ ምልክት እንዲኖር፣ የገበያ ቁጥጥር እንዲደረግ፣ የማስታወቂያ ገደብና ከፍተኛ የግብር ምጣኔ መጣል የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያ በታሸጉ ምግቦችና ጣፋጭ መጠጦች ላይ የሚሠሩ ማስታወቂያዎች ይዘት ምርቱ ከያዛቸው ግብዓቶች ጋር ተመጣጣኝና ተስማሚ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ታይቶ ከማስታወቂያ እንዲወርድ የሚደረግበት አሠራር ቢኖርም፣ ከፍተኛ የጨው፣ የስኳርና ስብ መጠን የበዛባቸው የታሸጉ ምግቦች ከፊት ለፊታቸው የማስጠንቀቂያ ምልክት እንዲያስቀምጡ የሚያስገድድ አሠራር የለም፡፡

ነገር ግን ቺሊ፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮና ሌሎች ይህንን መተግበር የቻሉ አገሮች፣ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች ግዥ እንዲቀንስና ሸማቹ ኅብረተሰብ የሚመገበውን የታሸገ ምግብ መርጦና አውቆ እንዲመገብ ዕድል ከፍቷል፡፡

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ ኤክስፐርት ሙሴ ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ካለመከተልና ጤናማ አመጋገብን የሚያጠናክሩ ሕጎችና ፖሊሲዎች ተሟልተው አለመኖርና በአግባቡ አለመተግበር የሚያስከትሉት የጤና ጉዳት በሕዝቡና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ያደርሳል፡፡

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ከማዘውተር በተጨማሪ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ መገለል፣ የከተማ ዲዛይን ደካማ መሆን (ለአብነትም በቂና ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች አለመኖር)፣ ድህነት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች ማስታወቂያ መስፋፋት፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ በቂ ግንዛቤ አለመኖር ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ መንስዔ ናቸው ብለዋል፡፡

በዓለም በዓመት ከሚሞቱት 57 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 71 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንት መሆኑን ያስታወሱት ሙሴ (ዶ/ር)፣ ከእነዚህ ውስጥ 30 በመቶ በልብ፣ 16 በመቶ በካንሰር፣ ሦስት በመቶ በስኳርና 15 በመቶ በኩላሊትና ሌሎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2016 ከሞቱት ሰዎች መካከል 52 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣ በጉዳትና ግጭት መሆኑን በማስታወስም፣ ከዚህ ውስጥ 43.5 በመቶ ተላላፊ ባለሆኑ በሽታዎች መሆኑን፣ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል ደግሞ በልብና በካንሰር ሕመም የሞቱት 54 በመቶ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን ጫና አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት 2019 ሪፖርትን ጠቅሰው ሙሴ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ 43 በመቶ ሞት የሚከሰተው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 የተሠራ ጥናት ደግሞ፣ በዓመት 65 ሺሕ አዳዲስ የካንሰር ሕሙማን እንደሚመዘገቡ፣ 96 በመቶ ኢትዮጵያውያንም ከልክ ያለፈ ጨው እንደሚመገቡ፣ 97.6 በመቶ አዋቂ ኢትዮጵያውያን በቂ አትክልትና ፍራፍሬ እንደማይመገቡ ማሳየቱንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ተመራማሪ አቶ ክፍሌ ሀብቴ በበኩላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ የስኳር፣ የጨው፣ የረጋ ዘይትና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶና በተከታታይ ባለመመገብ የበኩሉን ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን በመጠቆምም፣ ጣፋጭ ምግቦችንና መጠጦችን ለልጆች አብዝቶ በተደጋጋሚ መስጠት ጉዳቱ በአብዛኛው ወዲያው ባይታይም ከጥርስ ጀምሮ ዘላቂ ለሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስለሚዳርግ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያቀርቡትን ማዕድ ጤናማነት እንዲከታተሉ መክረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ብዙም ግንዛቤ የሌለው፣ ለልጆቹ የሚያስጠቅማቸው ለስላሳ መጠጦች፣ ጁሶች እንዲሁም የታሸጉ ምግቦች መብዛት እንደሌለባቸው፣ ለምሳሌ ጣፋጭ መጠጦች በሳምንት ሁለት ጊዜ መጠቀም ብዙ እንደሆነና አንዴ እንደሚበቃ ገልጸዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የሚመክረውን በማስታወስም፣ በቀን ከ20 ግራም እስከ 50 ግራም የጠረጴዛ ስኳር፣ ለጎልማሳ በቀን አምስት ግራም ጨው መጠቀም፣ የተቀነባበሩ ምግቦችን መቀነስና የምግቦችን ተለያይነት ማብዛት፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና ጥራጥሬ መጠቀም፣ ስብ የበዛበት ሥጋ አለመመገብ፣ ብዙ ቅቤ ያለው ወተት አለመደጋገም እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡

እንደ አገር ችግሩን ለመቅረፍ ጤናማ ያልሆነ ምግብ ቁጥጥር አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን በማስታወስም፣ ይህ ዕውን ሲሆን ክፍተቶችን ለመሙላት ያግዛል ብለዋል፡፡

የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ጤናማ ያልሆኑ ምግብና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሚል ባዘጋጀው የግንዛቤ መድረክ ላይ ጤናማ ያልሆነ ምግብ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ ተጠናቆ በሥራ ላይ እንዲውል የሚመለከታቸው አካላት ግፊት እንዲያደርጉ ተጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...