Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእየተባባሰ የመጣው የወንጀል ድርጊት

እየተባባሰ የመጣው የወንጀል ድርጊት

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው እየተባባሰ በመጣው የወንጀል ድርጊት በርካታ ዜጎች እየተማረሩ ነው፡፡ በተለይ የሥራ አጥ ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን እንዲሁም ወደ ከተማዋ የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ የወንጀል ድርጊቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከሁሉም በላይ ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላት በቡድን ሆነው በመሆኑ፣ ችግሩን ለመከላከል አዳጋች አድርጎታል፡፡

በከተማዋ የሚስተዋለውን የወንጀል ድርጊት ለመከላከል ከ121 ወረዳዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ኦፊሰሮች ከአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አካሂደዋል፡፡  

የውይይቱን መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት በአዲስ አበባ የሰላምና የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የፀጥታ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ሮማን በቀለ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቀነስ ከዚህ በፊት የሚሠሩ አሠራሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ቀደም የፀጥታ አካላት ከማኅበረሰቡም ሆነ ከወጣቱ ጋር በመሆን ወንጀልን የመከላከል ሥራ ይሠሩ እንደነበር፣ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ አሠራር እየላላ በመምጣቱ የወንጀል ድርጊቱ ሊባባስ መቻሉን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

የፀጥታ አካላት ከፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በመተባበር የሚሠሩት ሥራ የወንጀል ድርጊትን ከመቀነስ ባለፈ፣ ወጣቶች የተለያየ ክህሎት የሚያዳብሩበት መንገድ እንዳለ አክለዋል፡፡

በፀጥታ ማዕከላት ውስጥ የደንብ ልብስ፣ የወረቀት እንዲሁም የሌሎች ግብዓቶች ችግር መኖሩ እንደ ክፍተት የሚታይ መሆኑን ገልጸው፣ እነዚህንም ክፍተቶች ለመሙላት በቀጣይ የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አይናለም በየነ እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከማኅበረሰቡ ጋር መሥራት የግድ ነው፡፡

በተለይ ሺሻ፣ ቁማርና ጫት ቤቶችና ሌሎች ቦታዎች ውስጥ የሚሠሩ የወንጀል ድርጊቶችን ለመለየት ወጥ የሆነ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል ሲሉ ረዳት ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡  

በአዲስ አበባ ከተማ ከተለያየ ቦታ እየፈለሱ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሯ፣ እነዚህን ሰዎች በትክክለኛ ተጎድተው ነው የመጡት? ወይም ደግሞ የወንጀል ድርጊትን ለመፈጸም ነው? የሚለውን የመለየት ሥራ መሠራት እንደሚኖበት አብራርተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የጎዳና ተዳዳሪዎችም የወንጀል ድርጊት ፈጻሚ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

በጥበቃ ተሰማርተው የሚሠሩ ሰዎች የደንብ ልብስ ከመደበኛ የፀጥታ አካላት ጋር የመመሳሰል ሁኔታ መኖሩንና ይህንን ችግር በቀጣይ ለመቅረፍ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰላም ሠራዊቶች ሥልጠና መውሰዳቸውን፣ ነገር ግን የሠለጠኑ የሰላም ሠራዊቶች በአልባሳትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራቸውን እያቆሙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለሰላም ሠራዊቶች መልሶ ሥልጠና በመስጠት የወንጀል ድርጊቱን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ እንደ አዲስ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከማኅበረሰቡም ሆነ ከዕድርተኞች፣ ጋር ይሠሩ የነበሩ ሥራዎች እየተዘነጉ በመሆኑ፣ በከተማዋ የወንጀል ድርጊት ሊባባስ ችሏል ያሉት የየካ ክፍለ ከተማ የማኅበረሰብ አቀፍ ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ታየች ዘገየ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች፣ ከዚህ በፊት ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ለየት ያሉ መሆናቸውን፣ አብዛኛውን ጊዜም ወንጀለኞቹ ድርጊቱን የሚፈጽሙት በመኪናና በቡድን በመሆን በስለትና በመሣሪያ በማስፈራራት እንደሆነ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

አብዛኛውን የወንጀል ድርጊትን የሚፈጽሙ ሰዎች ማኅበረሰቡ ዘንድ የተሸሸጉ መሆኑንና በዚህም የተነሳ እነዚህ ወንጀል ፈጻሚ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መቸገራቸውን አስታውሰዋል፡፡

በከተማዋ በየጊዜው የሚሰሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመቀነስ በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት መድረኮች መዘጋጀት አለባቸው የሚሉት ኃላፊዋ፣ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ለውጥ ይመጣል ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡን ከፀጥታ አካላት ጋር በማጣመር በከተማዋ የሚስተዋለውን የወንጀል ድርጊት መከላከል እንደሚቻል ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ አሠራር ብዙ ስለማይታይ ችግሩ መባባሱን አክለዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ድርጊትን የሚፈጸሙ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር መቸገራቸውን የገለጹት ኮማንደሯ፣ በተለይም በቡድን ሆነው በመኪና የሚሰርቁ ወንጀለኞች ተንሰራፍተዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከኑሮ ውድነት፣ ከተለያዩ ቦታዎች ከሚፈልሱ ሰዎችና የሥራ አጥ ቁጥር መብዛት፣ የወንጀል ድርጊቶች ለመፈጸም ምክንያት መሆናቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ፖሊስ መምርያ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዲቪዚዮን ኃላፊ ኢንስፔክተር ደርበው ተፈራ እንደገለጹት፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ በአብዛኛው የሚፈጸመው የወንጀል ድርጊት በመኪና ነው፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የብዙ ኢንዱስትሪ መናኸሪያ በመሆኑ ለወንጀል ድርጊት ምቹ መሆኑን፣ በዚህም የተነሳ በአካባቢው ችግሩ በተደጋጋሚ እንደሚታይ ኃላፊው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ መውጫና መግቢያ በሮች የወንጀል ድርጊት በቀላሉ ሲፈጸም የሚታይ መሆኑን፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር በኩል የተሰጠው ሥልጠና ለፀጥታ አካላት ጉልበትና አቅም ከመፍጠርም በላይ ያሉትን ችግሮች ለመፈተሽ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከታዳሚዎች ከተነሱ ሐሳቦች ውስጥ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሠራር አለመኖርና የግብዓት ችግር መኖር እንቅፋት ናቸው የሚሉት ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...