Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዋሁ ሕዝባችን!

ሰላም! ሰላም! ያው እንደሰማችሁት ‹‹ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና›› ተብሎ ዓለም በቀጥታ ሥርጭት እያየን ለሰላም እንተጋለን ተብሏል፡፡ ቃልና ተግባር ከተገናኙ እሰየው ነው፡፡ ካልሆነ ግን በሰላም ፋንታ አሳራችንን እንዳንበላ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሥጋት አለኝ፡፡ በየሳምንቱ አዳዲስ ነገር ፍለጋ ላይ የሚያሰማራኝ ሕይወቴ ስንቱን ያሰማኛል፣ ስንቱን ያሳየኛል መሰላችሁ? እንደ እኔ ሥጋት ያላችሁ አደራ በምድር አደራ በሰማይ እያላችሁ ፖለቲከኞችን ወጥራችሁ ብትይዙ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ግን ፈጣሪያችሁን በፀሎት ወይም በዱአ ተለማመኑ፡፡ የምድሩ አልሆን ሲል የሰማዩ እንደሚሰማ አትጠራጠሩ፡፡ ከፀሎቱ ወይም ከዱአው የለንበትም የምትሉ ደግሞ አገራችሁን አትበድሉ፡፡ በንፁህ ህሊና ሰላም እንዲሰፍን ተግታችሁ ሥሩ፡፡ ‹‹ወንድም አንበርብር ድሮ በዘመነ ደርግ ሰላምን ከክብ ጠረጴዛ የማይፈልጉ ከጦር ሜዳ እንዲያገኙት ይገደዳሉ የሚል መፈክር ነበር፡፡ እንደምታየው ጦር ሜዳ ላይ የዛለ ክንድ አደባባይ ላይ እየተደገፈ የሰላም ያለህ ቢል አትመን፡፡ ቂምን በሆዱ አጭቆ ጥርሱን የሚገለፍጠው ሁሉ ሲያስመስል ሊሆን ይችላልና ጠርጥር፡፡ እውነተኛ ሰላም የሚገኘው በፖለቲከኞች መዳፍ ውስጥ ሳይሆን በሕዝባችን የዋህ ልብ ውስጥ ነው…›› ያለኝ፣ የሰላም መድረኩን የቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት አብሮኝ ሲከታተል የነበረው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እውነት እኮ ነው ልበ ቀናውና የዋሁ ሰፊው ሕዝብ በሰላም እየኖረ የሚነጅሱት እኮ እነማን እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ማወቁንስ እናውቃለን…!

አዛውንቱ ባሻዬ ባለፈው ሰሞን በከተማው ስለሚናፈሰው ቤታቸው ፈርሶ ስለሚፈናቀሉ ወገኖች ወሬ ተጠምደው፣ ባገኙኝ ቁጥር ነገሩን አንስተው ሲነዘንዙኝ ሰነበቱ። ‹‹በቤትና በመሬት ጉዳይ ብንፈናቀልም፣ የምንፈናቀለው በልማት ስም በቁም ሳለን ብቻ ይመስለኝ ነበር…›› ይሉኛል በድርጊቱ ማዘናቸው እያሳበቀባቸው። ባሻዬ ከወዲሁ ስለገዛ መቃብራቸውና ስለሥነ ሥርዓቱ የጻፉት ኑዛዜ አንድ መጽሐፍ ይወጣዋል እየተባለ አንድ ሰሞን በሠፈሩ ስማቸው ይብጠለጠል ነበር። ‹‹የዘንድሮ ሰው እንዲህ ብሎ በማውራቱ እንደማዝነው በሌላ በምንም አላዝን አንበርብር…›› አሉኝ አንድ ቀን። ‹‹እንዴት ባሻዬ?›› ብላቸው፣ ‹‹አብዛኛው ሰው በሕይወቱ እያለ ሳይደላው ነው የሚኖረው። በቁሙ ላዩ ላይ ቤት እየፈረሰበት እኔ ዘለዓለማዊ እንቅልፍ ተኝቼ ስለማርፍበት የመቃብር ቤቴ ስጨነቅ ያሽሟጥጠኛል። አመድ በዱቄት ሲስቅ ይታይህ…›› አሉኝ፡፡ የእሳቸውን የመቃብር ቤት አስታኮ በሾርኒ የሚተላለፈው መልዕክት የደረሰበትን ርቀት ሳስብ ሳቄ ሊያመልጠኝ ነበር፡፡ ግና የወገኖቻችንም ሆነ የአዛውንቱ ባሻዬ ምሬት ብዙም አላስኬደኝ፡፡ እንዲያ ነው!

ታዲያ አንዳንዱ ደረስኩ ባይ ወግና ሥርዓት የማያውቅ የዘመኑ ሰው ‘ፋስት ፉድ’ በለመደበት ቀብርም በ‘ፋስት ሙድ’ ካልተጠናቀቀ እያለ እነ ባሻዬን ሲያስቸግራቸው ስታዩ ጉድ ያሰኛችኋል። በቀብርና በለቅሶ በሚጠፋው ጊዜ የማንደሰተው እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነን፡፡ በአንድ ጀንበር የተኖረበትን የአባቶች ልማድ ካልሻርን ብለው የሚጋጩ ዘመነኞችን ስናይ ደግሞ እንበሳጫለን። ከግልብ ማወቅ ልግምነት እንደሚቀድም ማን ቢነግረን ልብ እንል ይሆን? ዘመናዊነትን የዕውቀት ቁንጮ አድርገው ለማሳየት የሚመፃደቁ አንዳንዶች የያዙትን ዘመናዊ ሞባይል ስልክ አጠቃቀም አለማወቃቸውን ስትረዱ ‹‹ድንቄም›› ማለታችሁ አይቀርም፡፡ አለባበስ፣ ፀጉር አቆራረጥ፣ አካሄድ፣ አነጋገር፣ ወዘተ ብቻውን ምን ይረባል? በላዩ ላይ ዕውቀት ካልታከለበት ባዶ ጉራ ምን ይረባል? ብቻ ተውት፡፡ ራስ ያማል!

 የእኛ ሰው አንዳንዴ ምኑም ባልተጨበጠ ወሬ እየታመሰ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየትምህርት ቤቱ፣ በየገበያው ጉድ ሲባባል እያየሁ ስገረም ሰነበትኩ። አንዳንዱማ ሲያወራ ከ2000 ዓመታት በፊት የተፈጸመውን የትንሳዔ ታሪክ ዛሬም ተደገመ ለማለት የሚፈልግ ይመስላል። እውነት ሆኖ መገረሙ ነውር ባልነበረው። ግን ምነው የእኛ በቁም ማንቀላፋት በራሱ ትንሳዔ እያስፈለገው በሆነ ባልሆነው ወሬ ሥራ ባንፈታ ወዳጆቼ? ‹‹ለአገራችን ትንሳዔ መነሳሳታችን የወሬን ያህል ቢሆን ምን ነበረበት?›› ስለው የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ነበር ምን ዋጋ አለው፡፡ የእናት አገር ፍቅር በትርጉም አልባ የእርስ በርስ ጥላቻና መናናቅ አከርካሪው ተመታ እንጂ…›› ቢለኝ ክው አልኩ። መቼም አንድ ነገር ሰምቼ ሌላ የሚጎተተው ነገር እየበዛብኝ ተቸግሬላችኋለሁ። ነገር ሰንጣቂ የሚባለው እንደ እሱ ዓይነቱ ይሆን? አንዳንዱ የተማረ የሚባለው ግን በአብዛኛው ለምን ይሆን ነገር ሰንጥቆ ሲያበቃ፣ ከመልካሙ ነገር ይልቅ ቅንነት የጎደለው ነገር ላይ ሲያተኩር የምንታዘበው? ‹‹የአገር ፍቅር ዕውን አንተ በምትለው መንገድ አከርካሪው ከተመታ ዛሬ ምን ተካው ትላለህ ታዲያ?›› ስለው፣ ‹‹የሥልጣንና የገንዘብ ፍቅር ነዋ። ጨዋታው ሁሉ ሥልጣንና ገንዘብ ብቻ ሆነ…›› አለኝ ጡንቻውን እየወጠረና ጣቶቹን ብር በሚቆጥር ስሜት እያንቀሳቀሰ፡፡ ‹‹የሕይወት ቁምነገሩ በሥልጣንና በፍቅረ ነዋይ ሲተመን የኑሮ ውድነቱ ጣራ በስቶ ወደ ሰማይ እየወጣ ነው። ይኼው ሌብነት ላያችን ላይ ድሩን እየደጋገመ ያደራል። እናማ አገር ካለችበት ይህን ከመሰለ የዘቀጠ ሁኔታ ትወጣና የትንሳዔ ዘመን እንዲመጣላት ሲፈለግ፣ የሚሠራላት ሳይሆን የሚገድላት ተሸላሚ ሆኖ አረፈው…›› ሲለኝ፣ ‹‹ኧረ አንተ ሰውዬ እንዳታስጨርሰን እባክህ…›› ብዬ ራሴን ያዝኩ፡፡ ምን ላድርግ ታዲያ!

አዛውንቱ ባሻዬ እንደነገርኳችሁ እንዲህ እንዲህ ላለው ተዓምር መሰል ወግ መናኸሪያ ናቸው። ማለቴ ያው ከዕድር ሰዎቻቸው ጋር እንዲህ ዓይነት ወሬ ካገኙ ቁጭ ብለው ሲሰልቁ ነው የሚውሉት። ታዲያ ሲያገኙዋችሁ እናንተም የመቀላቀል ግዴታ ይኖርባችኋል። በተረፈ የምትሠሩት ሥራ ወይም የምትሄዱበት ቀጠሮ ለእሳቸው ምንም ነው። በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ ሰዎች እኮ ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ ጣደፍ ጣደፍ እያላችሁ ስትጓዙ እጃቸውን በሁለቱ የጃኬት ኪሳቸው ከተው ጅንን እያሉ የሚራመዱ የምታውቋቸው ሰዎች ያጋጥሟችኋል። ዘንድሮ አክብሮ ሰላምታ የሚሰጥ ሰው እንደሚናቀው ሌላ የሚናቅ ሰው ጠፍቷል፡፡ ከአንገታችሁ ጎንበስ ብላችሁ ሰላምታ ትሰጡና መጓዝ ልትቀጥሉ ስትሉ፣ ‹‹አንተን አይደል እንዴ ስፈልግ የነበረው?›› ይሏችኋል ክንዳችሁን ጨብጦ በያዘው በደህና ቀን ብዙ ጠቅልሎ በጎረሰ እጃቸው እያሳመሙ። ‹‹የአንዳንዱ ሰው እኮ የመዳፍ ስፋት የድሮ እህል መሥፈሪያ ነው የሚያክለው…›› ይላሉ ባሻዬ። ባሻዬን በኖሩበት ዘመን እንዲህ ያለ ንፅፅር ሲያቀርቡ ልጃቸው በበኩሉ፣ ‹‹የእኔ ትውልድ ደግሞ ችግሩም መፍትሔውም ወረቀት ላይ ሆኖበት፣ የሚበጀውን በምርጫ ሊወስን ቢፈልግም ኑሮ ሰማይ ወጥቶ እጁ አመድ አፋሽ ሆነበት…›› ይላቸዋል ልዩነቱ በደንብ እንዲገባቸው። ሁሉም በመሰለው መንገድ የሚፈልገውን ሲናገር እኔ ሥራዬ ማዳመጥ ብቻ ነው፡፡ የግድ ነው!

የምግብ ጥያቄ በተመለሰበት አገር የታደለ የሚባለው ናሳ መርጦት ጠፈርን ያሳየው ሰው መሆን አለበት። በእኛ አገር ደግሞ በደህና ቀን እህል በገፍ ሲሠፈር ያየው ነው ብንል አንሳሳትም። ይህች ይህች ደግሞ ትጥፋን እንዴ? ድህነትና የምግብ እጥረት ከዚህ ውጪ እንድናስብ ስለማይፈቅዱ ዕድል በዚህ ቢፈታ አንገረም። እናም ስለዚያ ስላስቆማችሁ ሰው ስጨርስላችሁ፣ የባጥ የቆጡን ወሬ ሊያወራችሁ ሲፈልግ በአንዴ ሥራ አጥ አድርጓችሁ ያርፋል። እናንተ የሚጠብቃችሁ ሥራ ወይም ጉዳይ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ይኼ ወጠምሻ ደግሞ እንቅ አድርጎ ይዞአችሁ፣ ‹‹እንዴት ነው እባክህ? ጠፋህ እኮ…›› እያለ ወሬውን ያደራል፡፡ ወደ ሥራችሁ እንደምትቸኩሉ ስትነግሩት፣ ‹‹ምን ከዘንድሮ ጠብ የማይል ሥራ የተሠሩትን ሕንፃዎችና መንገዶች እየዞሩ ማየት ይሻላል…›› እያለ ሲስቅ፣ ከጤነኛ ጋር እየተነጋገራችሁ መሆኑን ትጠራጠራላችሁ፡፡ በምግብ ነው ወይስ በመድኃኒት እንዲህ ሰፊ የሀብታም እርሻ መስሎ የሚንቀሳቀሰው ማለታችሁም አይቀር፡፡ ብቻ አያጋጥም ነው!

ባሻዬ የስምንተኛው ሺሕ ምልክት የሚሉት ሰሞነኛ ጨዋታ አምጥተዋል። ምን መሰላችሁ? ሁሉም ነገር በሺሕ መተመን፣ መጠራትና መቆጠር ከጀመረ እንደ ባሻዬ አባባል በቃ የስምንተኛው ሺሕ ምልክት እሱ ነው። እስኪ ጥቀሱ ሲባሉ ‘የጤፍ ዋጋ፣ የቤት ኪራይ ንረት፣ ጉቦው፣ የሕዝብ ብዛት…’ እያሉ ብዙ ይዘረዝራሉ። እኔም ሳዳምጣቸው እቆይና ሁሌ የማይዘሉትን ‘ጉቦ’ ‹‹ደግሞ እሱ ምኑ ይሆን በመሠረታዊ ምልክትነት ያስቆጠረው?›› ብዬ ግራ ገብቶኝ እጠይቃለሁ። ‹‹አይ ልጅ አንበርብር፣ ጉቦማ መቼም ቢሆን አብሮን የሚኖር ባላንጣ ደባላችን ነው። ትተነው ማስተው ስላልቻልን እንደ መብት በየመሥሪያ ቤቱና በየጉራንጉሩ የሚጠየቀው የእጅ መንሻ መጨመር ሊያሳስበን ይገባል። ምን ነካህ? ዋናውን?›› ሲሉኝ አንገቴን ደፋሁ። በድርጊቴ ተፀፅቼ ቀና ብዬ ዓይናቸውን ማየት አፈርኩ። እሳቸውም ገብቷቸው፣ ‹‹ተወው ልጄ፣ ተወው፡፡ ብቻህን ተናደህ አትችለውም ልጄ፣ ብቻህን ጮኸህ አትዘልቀውም…›› ሲሉኝ ተናደድኩ። ‘ዱብ ዱብ ባይ እንደ በረዶ’ የሚለው ፉከራችን ለምን ይሆን የጦር ሜዳ ብቻ ወኔ የሚሆነን? ‹‹ሙስናን ከመዋጋት ከአንድ ብርጌድ ጋር መዋጋት ይቀላል…›› ያሉት የአራዳ ልጆች ናቸው አሉ፡፡ ልክ ሳይሆኑ አይቀርም!

ከባሻዬ ጋር እንዲህ ስል እቆይና እግሬ ባገኘው አቅጣጫ ሲያሳብር ልጃቸውን ያገኘሁት እንደሆነ ደግሞ ከእሱም ጋር ቆም ብዬ አንድ ሁለት እባባላለሁ። አንድ ሁለት ስል እጫወታለሁ ማለቴ ነው። በጠራራ ፀሐይ ያላበው ቢራ የሚያንቆረቁር ስታዩ እኔ ትዝ እንዳልላችሁ አደራ፡፡ ግን እንዲህ ያሉት ሰዎች እንዴት ቢደላቸው ይሆን ሕዝበ አዳም ሲራወጥ እነሱ ተረጋግተው የሚጋቱት? ለነገሩ አትፍረድ ነው፣ ምን ይታወቃል የዘንድሮ ሐኪም የማያዘው ነገር አለ ብላችሁ ነው? ‹‹ምነው በቀኑ?›› ብትሉት፣ ‹‹ሐኪም አዞልኝ ነው…›› ሊላችሁ ይችላል። ታዲያ መቀበል ግድ ነው። ዘንድሮ ካመኑበት መድኃኒት የማይሆን ምን አለ ብላችሁ ነው? ጉድ ነው እኮ፡፡ ባለፈው ሰሞን ከእዚህ ጋር በተያያዘ የሰማሁትን የሱስ ቀልድ ላጫውታችሁ። አባት ‘ቼን ስሞከር’ የሚባል ነው። ኋላ ሳንባውን ይታመምና ለጥቂት ጊዜ ማጨስ እንዲያቆም ይነገረዋል። እንዳልኳችሁ ‘ቼን’ አጫሽ ስለሆነ ግን በአንዴ መተው አይችልምና በይዘቱ ቀላል የሚባል ሲጋራ እንዲያጨስ ታዘዘ። ለአባትየው ሁሌ ሱቅ እየተመላለሰ ትምባሆ የሚሸምተው ልጁ ቀላል ተብዬውን አንድ ቀን ሲሞክር አባት ደረሰበት። ወዲያው በመምከርና በመገሰጽ ፋንታ፣ ‹‹አይዞህ አጭስ፣ ያ ዶክተር ግን በእኔ ላይ እየተጫወተ ነው። እሱ ለእናንተ ነው ለእኔ ያንን የለመድኩትን ገዝተህልኝ ቶሎ ና…›› አለና መልሶ ልኮት አረፈው። ከቀልድነቱ አልፎ እውነት ቢሆንስ የሚለው ሐሳብ ሲጫነኝ፣ የዘንድሮ ወላጅና አስተዳደጉ ጉዳይ ሕመሜ ነውና ይነሳብኝ ጀመር። በስንቱ ታምሜ ልችለው ይሆን ግን!

የእኔ ነገር ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ሳገኘው ብዬ ጀምሬ አልጨረስኩላችሁም። ልክ የባሻዬን ልጅ አባቱን አግኝቼ በተለየሁበት ስሜት ሆኜ ሳገኘው የማወራው ዓይተውና ሳያዩ ስለማደግ ነው። ‹‹ዓይተን ስለማናድግ እኮ ነው ብር ብርቃችን ሆኖ አገር በሙስና የታመሰችው…›› ስለው ስለአስተዳደግ ያብራራልኛል። ‹‹ብለህ ነው አንበርብር? ምነው እንደ እሱ ከሆነ በሀብታም አገሮችስ ይኼው ችግር አልተገታ?›› ይለኝና እንዲያው ነው መጨነቃችን በሚል ስሜት ወደ ሰማይ ማየት ይጀምራል። ‹‹ከእሱ ይልቅ የዘመኑ ልጆች አስተዳደግ ያስፈራኛል። የእኛ ወላጆች እያላቸው ደብቀው፣ ማድረግ እየቻሉ ሸሽገው ያሳድጉን ነበር። ለምን ስትላቸው ልጅ ከመጠን በላይ ከበላ፣ ከጠጣና ገንዘብ ከቆጠረ ዓላማና ጉዞ አይኖረውም በሚል ነበር። የአሁኑን ጊዜ ስታይ ግን ሕፃናት በአምስት ዓመታቸው ሁሉንም አውቀው ሁሉም ተሟልቶላቸው የሕይወት ትርጉም እየተዛባባቸው ነው የሚያድጉት። ሳያይ ያደገው አሁን በሙስና አስቸገረን ካልን፣ ዓይቶ ያደገው ምን ሊያመጣብን ነው? የሱስ ቁራኛ ሲሆን ምን እንይዝ ምን እንጨብጥ ይሆን?›› አለኝ ክፉኛ ተብሰልስሎ። አንዱ ሲናገር ሌላው ማድመጥ ትቶ እንጂ የሁሉም ነገር መፍትሔ ሚዛናዊ ይሆን ነበር። የሚቃወመውም የሚደግፈውም፣ ገዥውም፣ ተገዥውም አገርን ማዕከል ቢያደርጉ ምንኛ በታደልን ነበር። ከአይፎን በኢርፎን ሙዚቃ እየሰማ የተደፈነ ጆሮ ባይበዛ ነበራ!

እስኪ በሉ እንሰነባበት። ከባሻዬ ልጅ ጋር ጊዜና ሁኔታ አመቻችተን በወጉ ግሮሰሪያችን ተገኝተናል። ‹‹አየህ እንዴት የባጥ የቆጡን ስናወራ ሳምንቱ ያለ ሥራ እንደሚከንፍ?›› አልኩት የጊዜው ሩጫ ገርሞኝ። ‹‹ምን ታደርገዋለህ? ቫት ያልተጀመረው ወሬ ላይ ብቻ ሆኖ እኮ ነው…?›› ሲለኝ የሳምንቱን ምርጥ ሳቅ ከልቤ ሳቅኩኝ። ‹‹እውነቴን እኮ ነው አንበርብር፣ ልማትን እኮ ሁሌ በመዋጮና በብድር ብቻ ማከናወን አይቻልም። ቆራጥ አስተሳሰብና ድፍረት እኮ ይቀረናል። ሁሌም የሚገመገም የሕዝብ ወኔ፣ የሥራ ተነሳሽነትና ወሬን የማያበረታታ አፈጻጸም ጭምር ያስፈልጋል…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹…ሳይሠሩ መብላትና ሳይሠሩ ማውራት በሚበረታታበት ሁኔታ ውስጥ ልማት ለእኔ ህልም ነው…›› ሲለኝ ቺርስ ልለው ብርጭቆዬን አነሳሁ። ‹‹በወሬ ላይም ቫት እንዲጀመር!›› ሲለኝ ደግሞ ብርጭቆዬን ሞቅ አድርጌ አጋጨሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደሚለው እዚህ አገር ወሬ በጣም በዝቷል፡፡ ፖሊሲው ሳይሳካ ሲቀር የአፈጻጸም ችግር ነበር ተብሎ ይወራል፡፡ ለምን አልተሳካም በማለት ከመገምገምና ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አፈጻጸም አጀንዳ ሆኖ በወሬ ይቀራል፡፡ ‹‹አንበርብር በየደረስንበት ለሻይ፣ ለማኪያቶ፣ ለሳንቡሳና ለመሳሰሉት ሳይቀር ቫት የሚጣልብን ከሆነ በስፋት በሚሠራጨው ወሬ ላይ ቫት ቢጣል ውጤቱን ታየው ነበር…›› ሲለኝ የየዋሁ ሕዝባችን ኑሮ የበለጠ መቀመቅ የሚገባ እየመሰለኝ ተሳቀቅሁ፡፡ የዋሁ ሕዝባችን ያሳዝናል! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት