Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹ጤፍ እና ነፃነት››

‹‹ጤፍ እና ነፃነት››

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ከራሱ አልፎ ሌሎችን የሚመግበው የኢትዮጵያ አርሶ አደር አሁንም ከዛሬ አምስት ሺሕ ዓመት ገደማ ሲገለገልበት ከነበረው ማረሻ አልተላቀቀም ዛሬም ‹‹ተራመድ በሬ ተከተል ገበሬ›› ከሚለው ብሒል ሳይወጣ  በትናንቱ መንገድ በመራመድ ላይ ነው፡፡

ከዘመናት በፊት የሚታወቀውን በሬና ገበሬ ሞፈርና ቀንበር ማረሻና ወገል እስከዛሬ ድረስ መጠነኛ መሻሻል እንኳን ሳይደረግባቸው ዛሬም አብረው ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

ይሁን እንጂ በሬና ገበሬ ተዋደውና ተላምደው ገብስና ስንዴውን ማሽላና ዘንጋዳውን፣ አተርና ባቄላውን ማኛና ሠርገኛውን ከማመረት አልቦዘኑም፡፡

በተለይ ደግሞ ከሌሎች አዝዕርቶች በተለየ ሁኔታ የጤፍ አመራረት ከአዘራር ጀምሮ እስከ መዓድ ድረስ ያለው ልፋትና ድካም በእጅጉ የተለየ ነው፡፡

ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ ማሳውን መልሶ መላልሶ በማረስና በማለስለስ ከጥቃቅንና ከተመሳሳይ አረሞች ለይቶ በማውጣት በየቀኑ እንክብካቤን የሚፈልገው የጤፍ ምርት ታታሪና ልባም ገበሬን ይጠይቃል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵዊያን የቅንጦት ምግብ እየሆነ የመጣው ጤፍ አርሶ አደሮች ለብዙ ሺሕ ዘመናት በብቸኝነት በባለቤትነት እያለሙት የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከኢትዮጵያ ተወስዶ በሌሎች አገሮች እየተዘራ ጥቅም እየሰጠ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም ለምግብነት ያለው ጠቀሜታ ይበልጥ ታዋቂነትን እያስገኘለት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ጤፍን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅና ተመራጭ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በገብስና በአጃ እንዲሁም ስንዴና የመሳሰሉት እህሎች ዱቄታቸው ሲቦካ ሊጡ እንደ ላስቲክ እንዲሳብ የሚያደርገው የፕሮቲን ቅልቅል የሆነው ግሉቲን GLUTEN የተባለው ንጥረ ነገር የሌበት በመሆኑ ተመራጭ እንዳያደርገው የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡

በዚህም ‹‹ከግሉቲን ነፃ የሆነ ምግብ›› የሚባለው ዘይቤ በምዕራቡ ዓለም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ውርጭም ሆነ ተባይ በቀላሉ የማያጠቃው እንዲሁም በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመጀመሪያ የምግብ ምርጫቸው የሆነው ጤፍ ብዙ ተመራማሪዎች ጥናትና ምርምሮች ሲያደርጉበት ይስተዋላል፡፡

በሚደረጉ ምርምሮችም ለምርቱ ዕድገትና ጥራት የተሻሉ ናቸው የሚባሉትን ዝርያዎች አርሶ አደሩ ዘንድ በማድረስ ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ በሙያቸው የሚሠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ከዚህ ባሻገር ጤፍ ከምግብነት በዘለለ የኢትዮጵያ መገለጫና መለያ ነው በማለት የባለቤትነት መብትን በዓለም ዙሪያ ለማሳወቅ እንዲሁም የጤፍንና የኢትዮጵያን ጥንታዊና ታሪካዊ ቁርኝት በሥነ ጥበብ ውስጥ ለማሳየት የሚታትሩ ሰዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሠዓሊ ወቀራፂ በቀለ መኰንን አንዱ ናቸው፡፡

ቀራፂ ወሠዓሊ በቀለ መኰንን መሰንበቻውን በሜትሮፖሊታን ጋለሪና በብሔራዊ ሙዚየም ጋለሪዎች ‹‹ጤፍ እና ነፃነት›› (GLUTEN -FREE -DOM) እና ሌሎች ሁለት የተለያዩ የሥነ ጥበብ ትርዒቶችን ለተመልካች አቅርበው ነበር፡፡

ባዘጋጁት ዓውደ ርዕይ ካቀረቧቸው መካከል በተፈጨ ጥቁር ጤፍ የተሠሩ ቅርፆች ይገኙበታል፡፡ ሰብዓዊ ቅርፆቹ በኅብረት ቆመውም፣ ተቀምጠውም ይታያሉ፡፡

‹‹ደረታችንን የምንነፋባቸው የትም አገር ብንሄድ ቀና ብለን የምንሄድባቸው አንዱ የሥጋ ሌላው የህሊና ምግባችንንና መታወቂያችን ነው፤›› ሲሉ ጤፍና ነፃነት ያቆራኙታል፡፡

የዛሬ አምስትና ስድስት ሺሕ ዓመት ገደማ እንደነበረች የሚነገርላት ጤፍ ብልህ አባቶች ከተራ አረም መሀል ነጥለው የሚያወጧት የምትገርምና የተለየች እህል ናት የሚሉት ቀራፂ ወሠዓሊ በቀለ ናቸው፡፡ እስከ ዛሬ ስንመገባት የነበረችው ጤፍ አሁን ላይ ከቅዳሜ ገበያ አልፋ አማዞን ገበያ ላይ መውጣቷን ይናገራሉ፡፡ ከምግብነት ባሻገርም ወደ መድሐኒትነት በመሸጋገር ላይ እንደሆነች ያወሳሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ተሻግራ የሌሎችን ቀልብ እየሳበችና ተፈላጊነቷ እየጨመረ የመጣችው ጤፍ ዜጎች እስኪጠግቡ የሚመገቧት ሳትሆን ከጠኔ ያላዳነቻቸው ሰቀቀናቸው ናት ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚነሱት ምክንያቶች ከተለመደው አሠራር ወጣ በማለት አለመሞከር ሲሆን ከአምስት ሺሕ ዓመት በላይ የቆየው ማረሻ አሁንም ያለምንም መሻሻል በመልኩም ሆነ በመጠኑ ሳይሻሻል አብሮ መኖሩ ነው፡፡ ያለምንም መሻሻል ለዘላለም አብሮን አንድንኖር የተደረገው ለምንድነው ሲሉ ስለ ለውጥና መሻሻል ያነሳሉ፡፡

ጤፍና ነፃነት በሚል የተዘጋጀውን የቅርፃ ቅርፅ ዓውደ ርዕይ ከተመለከቱ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ከሰጡት መካከል የሥነ ጥበብ ሐያሲዋ ፀደይ ወንድሙ አንዷ ነች፡፡ በጤፍና በነፃነት መካከል የሚደረግ ምልልስ አንዱ ሌላውን ይወነጅላል የጋራቸው የሆነው ሐሳብ ግን ሁለቱም ለዘመናት ቢኖሩም ጤፍ ለዘመናት ከረሃብ ነፃ አላወጣም ነፃነትም መሆን እንዳለበት አልሆነም ትላለች፡፡

በሌላ በኩል ጤፍ ነፃነትም ነው የምትለው ፀደይ ግሉቲን ፍሪደም የሚለውን የእንግሊዝኛ ርዕስ እማሪያዊ ትርጓሜ ጋር ታገናኘዋለች፡፡ ግሉቲን የፕሮቲን ዓይነት ሲሆን በስንዴ፣ በአጃና በመሳሰሉት የሚገኝ ነው ይህ ፕሮቲንም ለውፍረትና ለተለያዩ የጤና እክሎች እንደሚዳርግ ታስረዳለች፡፡

ስለዚህ ግሉቲንን ለማስወገድና የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት በዕቅድ የሚመራ የአመጋገብ ሥርዓትን በባለሙያዎች ምክር መከተል ያስፈልጋል የሚል መደምደሚያ ላይ እንደተደረሰ አስቀምጣለች፡፡

‹‹የአመጋገብ ዕቅዱንም ‹gluten free› ይሉታል። ይኸው የዘመን መገለጫ ሆኖ ብዙዎች እየከወኑት ነው። በዚህ ዓይን ጤፍን ስንወስድ፣ በተፈጥሮ ከግሉቲን ፕሮቲን ነፃ የኾነ እህል ነው። ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንጀራም ገንፎም ኾኖ የሚበላ እህል። ከግሉቲን አሉታዊ ተጽንዖዎች ነፃ የሚያወጣ። በተፈጥሮው gluten free የኾነ! (ጤፍ ብዙ ነገር ነው)››፡፡

‹የተቀመጠው ጤፉ ሰው› በሚል ያተተችው ፀደይ እንዳመሰጠረችው፣ በዚህ ዓይነት ጤፍን ስንወስድ በተፈጥሮ ከግሉቲን ፕሮቲን ነፃ የሆነ እህል ነው፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ነፃነት›› የኢትዮጵያውያን  ስያሜ እስከ መሆን ደርሷል ያስብላል ትላለች፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ያለው ታሪክ ከወራሪ በስተቀር ነፃነትን ለረዥም ጊዜ ኢትዮጵያ  ያጣችበት ታሪክ እንደሌለ በማኅበራዊ ትስስር ገጽዋ ከትባለች፡፡

የሥነ ጥበብ ሐያሲዋ ፀደይ በዳሰሳዋ የጤፍን አፈታሪክ ሳታነሳ አላለፈችም፡፡ እንዲሀም አለች፡-

 ‹‹በአፈ ታሪክ ደረጃ ብናየው፣ ብዙ ጥያቄ ሊነሳባቸው ቢችልም፣ መሪ ራስ አማን በላይ፣ በመዝሙረ ዳዊት ‹ለኢትዮጵያውያን ምግብን ሰጣቸው› ሲል የዘመረው ስለ ጤፍ ነው ይላሉ። በዚያ ዘመን ነው ንግሥተ ሳባ ጤፍን የት እንደምታገኘው ራዕይ ታይቷት ያገኘችውና የተራበ ሕዝቧን የመገበችው፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...