Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት ከተቀናቃኝ ኃይሎች ጋር የሚያካሂዳቸውን ድርድሮች ግልጽ አለማድረጉ እንዳሳሰበው ኢዜማ ገለጸ

መንግሥት ከተቀናቃኝ ኃይሎች ጋር የሚያካሂዳቸውን ድርድሮች ግልጽ አለማድረጉ እንዳሳሰበው ኢዜማ ገለጸ

ቀን:

  • አብንና እናት ፓርቲ ሕዝባዊ ምክክር እንደጂመር አሳስበዋል

መንግሥትም በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ያሉ የዜጎችን ሰቆቃ ለማስቆም ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ድርድር ውስጥ መግባቱ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑና አሁንም እየተካሄዱ ያሉ ድርድሮች ግልጽነትና ከሕዝብ የተደበቁ መሆናቸው አሳስቦኛል ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡

ኢዜማ ትናንት ሚያዚያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረ ጀምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያየ ጊዜ የተካሄዱ ድርድሮች ግልጽነት እንደሌላቸው አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም አፈጻጸማቸው በተገቢ ሁኔታ ሳይከናወን ቀርቶ ብዥታዎችን ስለመፍጠሩ የገለጸው ፓርቲው፣ ለአብነትም በቅርብ ጊዜ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ድርድር አድርጎ ሰላም አውርጃለሁ ባለበት የፕሪቶሪያው ስምምነት በተነገረው ልክ ያልተፈጸሙ ጉዳዮችን መኖራቸውን አስታውቋል፡፡

የድርድሩ ሒደትና አፈጻጸም ምን ላይ እንደሆነ በግልፅ አለመታወቁን የገለጸው ፓርቲው፣ በዚህ ምክንያትም ኢዜማን ጨምሮ የተለያዩ አካላት አሁንም ድረስ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሮባቸዋል ብሏል፡፡

- Advertisement -

መንግሥት ከዚህ ቀደም በለውጡ ሰሞን ኦነግ በስደት ከነበረበት ኤርትራ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ፣ በስምምነቱ መሠረት አልተፈጸመልኝም ሲል የነበረው ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ሥጋት አለኝ ብሏል፡፡

ኢዜማ የድርድሩን ሒደትና ስምምነቱን በተመለከተ ሕዝቡ ሊኖረው የሚገባውን ግልፅ መረጃ፣ እነማን እየተሳተፉ እንደሆነ፣ የስምምነቱን ይዘት፣ እንዴት እንደሚፈጸምና በአፈጻጸሙም ጊዜ ተግባራዊነቱን ለዜጎች ተገቢና በቂ መረጃን በማስተላለፍ ከተጨማሪ ውዥንብርና ትርምስ ማኅበረሰቡን እንዲጠበቅ አሳስቧል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ የአማራ ሕዝብ በተደጋጋሚ አገሩንና የማዕከላዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመጠበቅ በመንግሥት የተደረገለትን ጥሪዎችን በክብር ተቀብሎ መስዋዕትነት ሲከፍል ቢቆይም፣ መንግሥት ለአማራ ሕዝብ ፍትሐዊ ጥያቄዎች፣ ፍላጎቶችና ሥጋቶች በቂ ትኩረት አለመስጠቱ ችግሩን አባብሶታል ብሏል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው አክለው ‹‹መንግሥት የክፉ ቀን አጋሩ ከነበሩትና በእውነትም ከሕዝብና ከአገር ፍላጎትና ጥቅም በተፃራሪ የመቆም ተሞክሮ፣ ዝንባሌና ታሪክ ከሌላቸው የአማራ ገበሬዎች፣ ወጣቶችና ፋኖዎች ጋር ያልተገባ ግብግብ ውስጥ መግባት የለበትም›› ብሏል፡፡ የባለድርሻ አካላት ውይይት ማለትም የክልልና የፌዴራል መንግሥት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የምሁራን መማክርት፣ ታዋቂና ተደማጭ ግለሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ካውንስልን ያካተተ ቡድን በተመረጡ ከተማዎች አንገብጋቢ አጀንዳዎችን ለይቶ ከሕዝቡ ጋር ወይይት እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ አብን እየታየ የመጣውን መካረር በሰላም ማዕቀፍ የሚፈታበትን ዕድል እንዲተገብር በጥብቅ አሳስባለሁ ብሏል፡፡

በተመሳሳይ እናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥነውን የፖለቲካ መሪ በማጣቱ፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት በመነፈጉ እንዲሁም በመከዳቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በታሪኩ አይቶት የማያውቀውን አስቸጋሪ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል፤›› ብሏል፡፡

የፖለቲካው መስመር መሳትና ተለዋዋጭነት፣ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ቀጣናዊ ፍላጎት፣ ስሁት የጎሰኝነት ትርክቶች፣ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ችግሮች ሕዝቡን ማብቂያ በሌለው መከራ ውስጥ እንዲኖር ማድረጉንም ፓርቲው አስታውቋል፡፡ አክሎም ‹‹ይህም መንግሥት ምን ያህል አክሳሪ የፖለቲካ አካሄድ እየተከተለ እንደሚገኝ ያሳያል›› ብሏል፡፡

ፓርቲው መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ሐሳብ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር የጋራ መግባባትን ለማስፈን የሚያስችል ውይይት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

መንግሥት ካለፈ ስህተቱ መማር ሲገባው ወደ ሌላ የግጭት አዙሪት አገርንና ሕዝብን እየከተተ ነው ሲል ወቀሳ ስንዝሯል፡፡ ‹የአማራ ክልልን ወጣት ለአመጽ የሚጋብዝ፣ በዚህም ከቀደሙት መደበኛ ጦርነትና የሽምቅ ውጊያ ሒደቶች ትምህርት ያልተወሰደበት፣ የሚያስከትለውንም መጠነ ሰፊ ጉዳትና መዘዝ በአግባቡ ያላገናዘበ አደገኛ የማንአለብኝነት አካሄድ እየተከተለ መሆኑን እንደሚያምን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...