Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለፕሬስ ነፃነት ሕጋዊ ጥበቃና ከለላ ያስፈልጋል!

የዓለም የፕሬስ ቀን በየዓመቱ ሲታሰብ የሚዲያው ማኅበረሰብም ሆነ ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚተጉ በሙሉ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አካል የሆነው የፕሬስ ጉዳይ ያሳስባቸዋል፡፡ የሚዲያዎች በነፃነት ሥራቸውን የማከናወን፣ የጋዜጠኞች ደኅንነትና የንግግር ነፃነት በምልዓት እንዲከበሩ ማሳሰቢያ ከመስጠት የተቆጠቡበት ጊዜ የለም፡፡ የፕሬስ ነፃነት ሁሉም ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ከማገዙም በላይ፣ በመብቶችና በነፃነቶች ላይ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙም እንደ ዘብ ያገለግላል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲታሰብ ጉዳዩ ሚዲያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ብቻ እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት በሚዲያው ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱን ዜጋ የሚመለከት መሠረታዊ መብት እንደሆነ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህም መሠረት መንግሥትም ሆነ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ለፕሬስ ነፃነት መከበር የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጭው፣ ተርጓሚውና አስፈጻሚው ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሦስቱን አካላት የእርስ በርስ ቁጥጥርና ሚዛናዊ ግንኙነት የሚከታተለው ሚዲያ፣ የአራተኛ መንግሥትነት ሚናውን እንዲወጣ ከማናቸውም ጥቃቶች የመከላከል ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ ለዓመታት በፕሬስ ነፃነት አፈና በግንባር ቀደምትነት ስማቸው ከሚነሳ አገሮች ተርታ ነው የምትገኘው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ከወሰዳቸው የለውጥ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ፣ አፋኝ ተብሎ የሚታወቀውን የሚዲያ ሕግ በአዲስ መተካቱ ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ሚዲያው በነፃነት ለመንቀሳቀስ ዕድል አግኝቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ በሚስተዋሉ ጽንፈኝነት የተፀናወታቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት፣ የሚፈለገው የሚዲያ ነፃነት አቅጣጫውን ስቶ በርካታ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚወጡ የፕሬስ ኢንደክሶች መሠረት ኢትዮጵያ ደረጃዋ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ከመንገድ ላይ እየታፈኑ ለቀናት የማይታወቁ እስር ቤቶች ይታሰራሉ፡፡ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መታሰር የተለመደ ተግባር እየሆነ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ማንም ሊያስቆመው አልቻለም፡፡ ጋዜጠኞች የደኅንነታቸው ጉዳይ ሲያሳስባቸው ፍራቻ ይሰማቸዋል፡፡ ፍራቻ ደግሞ ራስን በራስ ሳንሱር ማድረግ ውስጥ ያስገባል፡፡ ራስን በራስ ሳንሱር የሚያስደርግ የፍራቻ ጋዜጠኝነት ለሙያው የሞት ያህል ነው የሚቆጠረው፡፡ መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት የገባውን ቃል በማክበር፣ ይህንን የፍራቻ ድባብ ማስቆም ይጠበቅበታል፡፡

ከሰላሳ ዓመታት በላይ እያስቆጠረ ያለው የኢትዮጵያ የግል ሚዲያ በሰው ኃይል፣ በሚዲያ ቁሳቁሶችና ዘመን አፍራሽ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያለው አቅም በጣም ደካማ ነው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ባሉበት ውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች ምክንያት፣ የረባ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅሙ እጅግ በጣም ደካማ ነው፡፡ ከተወሰኑ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች በስተቀር ብዙዎቹ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆነው ነው ሥራቸውን ለማከናወን ጥረት የሚያደርጉት፡፡ በአንድ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር የነበረው የኅትመት ሚዲያ አሁን ተመናምኖ ገበያ ውስጥ ያሉት ከአንድ የእጅ ጣት አይበልጡም፡፡ የኅትመት ሚዲያው ከመቶ ፐርሰንት በላይ የማተሚያ ዋጋ ንረት ገጥሞት፣ የህልውናው ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን፣ ‹‹ጋዜጣ ከሌለው መንግሥት ይልቅ፣ መንግሥት የሌለው ጋዜጣ ቢኖር እመርጣለሁ›› ካለው በተቃራኒ፣ በአሁኗ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ጠፍተው መንግሥት ብቻውን ሊቀር ተቃርቧል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም የመጀመሪያዋ ጋዜጣ የሌላት አገር እንዳትሆን ያስፈራል፡፡ ይህ ሁኔታ መላ ዜጎችንና መንግሥትን በእጅጉ ሊያሳስብ ይገባል፡፡

የዛሬ ሰላሳ ዓመት የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ሜይ 3 በየዓመቱ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን እንዲሆን ማወጁ ይታወሳል፡፡ ይህ አዋጅ ነፃ ፕሬስና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በዓለም ዙሪያ ትኩረት እንዲያገኝ ትልቅ ጅማሬ ነበር፡፡ በዚህም የግል ሚዲያ በበርካታ አገሮች እንዲያብብ፣ እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካይነት መረጃ በነፃነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው እንዲሰራጭም በእጅጉ ረድቷል፡፡ ለሦስት አሠርት ያህልም ከሚዲያ ነፃነትና ከሐሳብን የመግለጽ መብት ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርም አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ እንዲህም ሆኖ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ አገሮች የሚዲያ ነፃነት፣ የጋዜጠኞች ደኅንነትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት መጠኑ እየጨመረና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለፕሬስ ነፃነት ተግዳሮት ከሆኑት ውስጥ የሐሰተኛ መረጃዎች መበራከት፣ ከመጠን በላይ ጽንፍ በረገጡ ሐሳቦች ሳቢያ ልዩነቶች መብዛት፣ እያደር መተማመን መሸርሸሩ፣ በአመፆች ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና መሰል ክልከላዎች መብዛት፣ የኢንተርኔት መቋረጥ፣ የግል ሚዲያዎችና የተቃውሞ ድምፆች መታፈን፣ እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመግታት የሚቻለው የሚዲያ ነፃነትንና የጋዜጠኞችን ደኅንነት፣ ከማናቸውም ጥቃቶች በመከላከልና ለመረጃ ተደራሽ ለመሆን የሚያስችል ትኩረት ሲኖር ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን እ.ኤ.አ. በ1948 የወጣው የተመድ ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሳይቀነስ ወይም ሳይሸራረፍ አንቀጽ 29 ተብሎ መደንገጉን ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አንቀጽን ኢትዮጵያ ተቀብላ በሕገ መንግሥቷ ስትደነግግ፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተካተተው ድንጋጌ መከበር አለበት ማለት ነው፡፡ ተመድ ራሱ እንዳስታወቀው ይህ አንቀጽ ከምንም ነገር በላይ ትኩረት የሚሰጠውና ሰዎች ከሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ በቀዳሚነት የሚያጣጥሙት ነው፡፡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ራስ የሆነው ይህ አንቀጽ ሳይከበር፣ ስለሌሎች መብቶች ለመነጋገር እንደማይቻልም ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የዘንድሮ የዓለም የፕሬስ ቀን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ለሌሎች ሰብዓዊ መብቶች እንደ መሪ ሆኖ እንዲታሰብ የተፈለገው፡፡

በኢትዮጵያ ይህ ቀን ሲዘከር ጋዜጠኞች መብቶቻቸው በሙሉ እንዲከበሩ፣ ከሕግ በተቃራኒ እንዳይታሰሩ ወይም እንዳይሳደዱ፣ የሚዲያ ተቋማት ከግራና ከቀኝ የሚደርስባቸውን ጉንተላ በማስቆም በነፃነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ ሕጋዊም ሆነ ሌሎች ድጋፎች ሲያስፈልጓቸው እንዳይነፈጉ መደረግ አለበት፡፡ መንግሥት እጅ ላይ የሚገኙ መረጃዎችም ያላንዳች አድልኦ ለሁሉም ሚዲያ ተቋማት መዳረስ አለባቸው፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎችም ለሚዲያ ትብብር ማድረግ ግዴታቸው ነው፡፡ ጋዜጠኞችም ሆኑ የሚዲያ ተቋማት የአገሪቱን ሕጎች በማክበር፣ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በሥነ ምግባር ደንባቸው መሠረት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት በተለይ የግሉ ሚዲያ ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበትን አሠራር ማስፈን ይኖርበታል፡፡ ሚዲያዎች መዳኘት ያለባቸው በሕዝብ የህሊና ዳኝነት እንደሆነ ግንዛቤ ወይም ፍላጎቱ ሲኖር፣ ማሳደድም ሆነ ፍራቻ ውስጥ መክተት ተገቢ አይሆንም፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር ግን ከሁሉም ነገር በላይ የፕሬስ ነፃነት ሕጋዊ ጥበቃና ከለላ እንደሚያስፈልገው በአፅንኦት ይታሰብበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...