Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ማሰብ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል...

አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ማሰብ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል ተባለ

ቀን:

በሥራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ማሰብ አደጋው የከፋ ስለሚሆን፣ ጠንካራ የአገረ መንግሥት ግንባታና የተሻለ የሰላም ሁኔታ ማስፈን የሚለው ቀዳሚ ሥራ መቅደም አለበት የሚለው ጉዳይ ምሁራንን አነጋገረ፡፡

‹‹አገራዊና ቀጣናዊ ትስስር ማዕከል›› የተሰኘ ድርጅት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሥሪትና አጠቃላይ የማሻሻያ መንገዶችን በተመለከተ፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የሕግ ምሁራን በተገኙበት ቅዳሜ ሚያዚያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት ጽንፍ የያዙ አስተሳሰቦችና አካላት በበዙበት፣ አስተማማኝ የሰላም ሁኔታ በሌለበት፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የማይገናኙ አጨቃጫቂና አከራካሪ የታሪክ ትርክቶች፣ ሕገ መንግሥት የማሻሻል ወይም የመቀየር ሥራ ውስጥ ከመገባቱ በፊት ቀዳሚ ምክክር ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተወስቷል፡፡

- Advertisement -

አገራዊና ቀጣናዊ ትስስር ማዕከል የተሰኘው ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂም ሙሉሸዋ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር እንመሥርት ብለው ከሚያስቡት ዕሳቤ ባለፈ፣ በውስጥ አገራዊ ፖለቲካ፣ አገሪቱ የእያንዳንዱን የፖለቲካ አስተሳሰብ ባከበረ መንገድ በትስስሩ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሰፋ ያሉ ውይይቶችና ምክክሮችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ለኢትዮጵያ ሰላሟን ሊያረጋግጥ የሚችልና በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚታየውን አጨቃጫቂ ጉዳይ በውይይት መፍታት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የሕገ መንግሥትና የሰብዓዊ መብት መምህር ዘለዓለም እሸቱ (ረዳት ፕሮፌሰር) ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፣ ሕገ መንግሥቱ መቼ ይሻሻል ሲባል የአገር ግንባታና ሰላምን ለማምጣት ታስቦ የሚደረግ ቢሆንም፣ በዩጎዝላቪያ ሕገ መንግሥትን ለማሻሻል ወደ ሥራ ሲገባ የተፈጠረው ዓይነት አለመግባባት ፈጥሮ የግጭትና ክፍል መንስዔ እንዳይሆን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ወይም ለመቀየር መጀመሪያ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሒደት ካልታለፈ ግን አገር አሁን ባለችበት የተቃርኖ ጎራ በበዛበት፣ ኢመደበኛ ታጣቂዎችና የፖለቲካ ግድያ ባለበት ሁኔታ ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ከታሰበ፣ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም በትንሹም ቢሆን ሰላማዊ ሁኔታ አስፈላጊ በመሆኑ የማሻሻያ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን፣ ሕዝቡን በሚወክሉ የፖለቲካ ኃይሎችና ምሁራንን በማሳተፍ እንዲከናወን፣ በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ሊታረቁ የማይችሉ የሚመስሉ ሐሳቦች ወደ መሀል መምጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ያስቀመጠውን የማሻሻያ አንቀጽ ተጠቅሞ ለማሻሻል መሞከር በራሱ አንቀጹ ድፍን አድርጎ ያስቀመጠው በመሆኑ፣ ሒደቱን የማይሳካና የማይታሰብ ጉዳይ ሊያደርገው እንደሚችል ዘለዓለም (ረዳት ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ሕገ መንግሥቱን አሁን ባለበት ወደ ማሻሻል ቢገባ እንኳ የሚደረጉትን የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ለማፅደቅ የሁሉንም ክልሎች ስምምነት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በተለይ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 እስከ 44 ድረስ ያሉት አንቀጾች በጣም አወዛጋቢ በመሆናቸው፣ አሁን ባለው የፖለቲካ መንሸዋረርና የክልሎች ቁጥር እየበዛ መሄድ፣ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን የማሻሻያ መንገዶች ተጠቅሞ ለማሻሻል ሥራውን ውስብስብና ከባድ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ዘለዓለም (ረዳት ፕሮፌሰር) አከራካሪ በሆኑ የሕገ መንግሥቱ ፍሬ ሐሳቦች ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ አራት ነጥቦችን አቅርበዋል፣ እነዚህም የሕገ መንግሥት ሕጋዊነት፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ወይም መቀየር ሲባል እስከ የት ድረስ ነው የሚሻሻለው ወይም የሚቀየረው፣ እንዴት ብሎ ይሻሻልና መቼ ይሻሻል የሚሉት ናቸው፡፡

በ106 አንቀጾች የተዋቀረው የ1987 ዓ.ም. አራተኛው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በጣም ታምቆ የተቀመጠ መሆኑን ገልጸው፣ የ2010 ዓ.ም. የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ተከትሎ በሕገ መንግሥቱ ላይ ለውጦች እንዲደረጉ በግልጽ ውይይት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ሒደት እየተነሱ ባሉት በርካታ ዕሳቤዎች እንዴት ሊሻሻል ይችላል የሚለው ላይ ግን እምብዛም የማይሰማበት፣ ነገር ግን ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በማኅበረሰቡ፣ በፖለቲካ ሰዎችና በድርጅቶች ዘንድ የሚኖረው ቅቡልነትና የባለቤትነት ጉዳይ በትልቁ የሚታይ እንደሆነ የተናገሩት ምሁሩ የሕገ መንግሥት ባለቤትነትም ሆነ ቅቡልነት የሚመጣው እነዚህ አካላት በአረቃቀቁ ላይ ያላቸው ተሳትፎ የማኅበረሰቡን የጋራ ዕሳቤ ያንፀባርቃል ወይ? ሕገ መንግሥቱ የማኅበረሰቡን ችግሮች ፈትቷል ወይ? የሚሉት ሲመለሱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የሕገ መንግሥቱ ቅቡልነትን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ አንዳንዴ በተወሰኑ አካላት በተለያዩ መንገዶች ቅቡልነት የለውም የሚል ሐሳብ እንደሚሰማ፣ ነገር ግን ይህ ዕሳቤ ጠንካራ የሆነ ግምገማ የተደረገበት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ቅቡልነት ከሥሪቱ ጀምሮ የነበረ አከራካሪ ጉዳይ መሆኑን ሲያብራሩ፣ ኢሕአዴግ በእርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ ሲሆን፣ አብረውት የመጡ አካላት ያዘጋጁት መሆኑንና በዝግጅት ሒደቱ የአንዳንድ ክልሎች የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አኩርፈውና አቋርጠው መውጣታቸውን አክለዋል፡፡ በውል ተሳትፎ ሳይኖር በሕገ መንግሥት ዝግጅት ሒደቱ ሕዝብን አሳተፍን በሚል ብቻ የተወሰኑ አካላት ነበሩ እንጂ፣ ተወያዩ የተባሉትም ሐሳባቸው ሳይካተት የተረቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በላይ ሕገ መንግሥቱ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ሲገባም አፈጻጸሙ ላይ የሚታዩት ከፍተቶች የሕገ መንግሥቱን ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ጉዳዮች መሆናቸውን አብራተዋል፡፡

ይህ የቅቡልነት ጥያቄ ደግሞ ስለሕገ መንግሥቱ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በምሁራን ውስጥ ሌላ ውዝግብ መፍጠሩን አውስተዋል፡፡ የተነሳውም ውዝግብ አዲስ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀት ወይም ያለው በደንብ ጥናት ተደርጎበት የይዘት ለውጥ መደረግ አለበት የሚሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በበርካታ መስዋዕትነት የመጣና ብዙ ችግሮች የፈታ በመሆኑ በማንኛውም መንገድ ተጠብቆ መሻሻል ካለበትም በተቀመጠው አሠራር መሠረት መስተካከል አለበት የሚሉ ቡድኖች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር ዘመላክ አየለ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያን በሚመለከትበት መንገድ፣ ውክልና፣ ቋንቋ፣ የፌዴራሊዝም አወቃቀር፣ የዋና ከተማ ጉዳይ፣ የመንግሥተ መዋቅር፣ የሕገ መንግሥት አወቃቀር፣ የሀብት ክፍፍልና በመሳሰሉ የሚጨቃጨቁ ሁለት ቡድኖች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡ የመጀመርያው ቡድን ብዝኃነት በአገራዊ አንድነት ውስጥ መካተት እንዳለበትና ይህ አገራዊ አንድነት በሕገ መንግሥቱ እንዲፀና መደረግ አለበት የሚል መሆኑን፣ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ መጀመሪያ የብሔር ብዝኃነት ላይ ያተኮረ አገራዊ አንድነት መፈጠር አለበት በማለት እንደሚያቀነቅኑ አብራርተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ በሁለት ቡድን ሆነው ከሚከራከሩባቸው ነጥቦች መካከል አዲስ አበባ የማናት የሚለው ጉዳይ፣ በተለይ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተገናኘ የሚነሳው ጥያቄ፣ የባለቤትነት ወይስ በመንግሥታት መካከል የሚኖር ጥያቄ ነው የሚለው በግልጽ አለመቀመጥን ጠቁመዋል፡፡ ልዩ ጥቅም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ሕግ ወጥቶ መፍታት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን፣ የምርጫ ዓይነቱ ምን ይሁን፣ አሁን ባለበት ይቀጥል ወይስ ሌላ ዓይነት ይተግበርና ሕገ መንግሥቱን ማን ይተርጉመው የሚለው በግልጽ አለመቀመጡንም ዘመላክ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ የሚታየው በብሔር ብሔረሰቦች አማካይነት ወይስ በሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የሚለው፣ የፌዴራልና የክልሎች የሥልጣን ክፍፍል ለማዕከላዊ መንግሥት የበዛ ሥልጣን የሰጠ እንጂ ለክልሎች የማይሰጥ፣ አንዳንዴም ለክልሎች የሰጣቸውን ሥልጣን የቀማ ነው የሚሉ አከራካሪ ነጥቦች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ወይም የመቀየር ሥራ ይቅደም ወይስ? የሰላምና አገረ መንግሥት ግንባታ ይቅደም? በሚለው ሐሳብ ላይ አስተያየት የሰጡት በኮተቤ ዩነቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አየነው ብርሃኑ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሕገ መንግሥቱ ይቀየር፣ ይሻሻል፣ ወይም መሻሻል የለበትም በማለት ጫፍና ጫፍ ይዘው የሚከራከሩ አካላት የመከራከሪያ ነጥቦችን በግልጽ ሊያስቀምጡ ይገባል እንጂ፣ በደፈናው ይቀየር ማለቱ ትርጉም አልባ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር ወይም ለማሻሻል ጠንካራ አገራዊ ግንባታና ሰላም ከተፈጠረ የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ጥቅሙ ምን ላይ ነው? ያሉት አየነው (ዶ/ር)፣ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻለው እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በመሆኑ ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ሌላ ጊዜ ከተጠበቀና አሁንም ችግሩ በቶሎ ካልተፈታ ሳይሻሻል ሊቀር ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...