Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የሚጠና የፖሊሲ ጉዳይ የለንም›› የሚሉ የመንግሥት ተቋማት መኖራቸው ተገለጸ

‹‹የሚጠና የፖሊሲ ጉዳይ የለንም›› የሚሉ የመንግሥት ተቋማት መኖራቸው ተገለጸ

ቀን:

  • ትምህርት ሚኒስቴር አንደኛው መሆኑ ተጠቁሟል

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መንግሥታዊ ተቋማት እንዲጠኑላቸው የሚፈልጉትን የፖሊሲ ጉዳይ እንዲያሳውቁት በሰርኩላር ቢጠይቅም፣ አንዳንዶቹ ‹‹የሚጠና ጉዳይ የለንም›› የሚል ምላሽ እንደሚሰጡ አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ እያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋም ለምርምር የሚበቁና የሚነሱ ጉዳዮችን፣ እንዲሁም በግልጽ መረጃ በሌላቸው የጥናት አካባቢዎች ዳሰሳ እንዲደረግ የጥናት ርዕሶች ዝርዝር ላኩልኝ ብሎ ሰርኩላር ቢያስተላልፍም፣ ምላሹ መቶ በመቶ እንዳልሆነ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

በዕውቀት ላይ የተመሠረተውን ፖሊሲ የመቅረፅ ሥራን የተገነዘቡት አንዳንድ ተቋማት፣ ዝርዝር የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ለኢንስቲትዩቱ ሲልኩ፣ ‹‹እኛ ዘንድ የሚጠና ጉዳይ የለም›› የሚል ምላሽ የሰጠ መንግሥታዊ ተቋም መኖሩን፣ ዋና ዳይሬክተሩ፣ ተቋማቸው ተጠሪ የሆነለት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ይኼን ምላሽ ከሰጡት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ሚኒስቴር ተጠቃሹ መሆኑን በየነ (ፕሮፌሰር) አክለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አለሳ መንገሻ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርቡ በተለይም፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትን የተመለከተ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በምርምር ደረጃ ሠርቶ ያጠናቀቃቸው አጀንዳዎች እንዳሉ ቢታወቅም፣ ነገር ግን አገሪቱ ካለችበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚ ሁኔታ አኳያ እየናጣት ስላለው የኑሮ ውድነት፣ የገቢ ሚዛን እያዛባ ያለውን የታክስ ማጭበርበር፣ የንግድ ሥርዓት መዛባትን በሚመለከት አሁን በተጠናውና ወደፊትም በሚጠናው ውስጥ ጉዳዮቹ ተዳሰዋል ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት ለሚፈልገው ዓላማ ያቋቋመው ኢንስቲትዩት የሥራው ውጤት በብቃት አገሪቱን አገልግሏል ወይ የሚለው ጉዳይ፣ ኢንስቲትዩቱን ራሱን ቅር ያሰኘ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የሚያደርጋቸው ጥናቶች የሕዝቡን ሥጋትና ፍላጎቶች የሚዳስሱ እንደሆኑ ያስረዱት በየነ (ፕሮፌሰር)፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምግቦች ለምንድነው የሚወደዱት? ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የሚከሰቱት የፀጥታ ችግሮች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ምን ያህል ነው? የሚለውም ጥናት እንደተሠራ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩት ሜጋ ፕሮጀክቶች (የስኳርና ሌሎችም) ለምንድነው ያልተሳኩት በሚለውም ላይ የተዘጋጀ ትልቅ ሰነድ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ 14 የጥናት ማዕከላት እንዳሉት፣ ከማክሮ ኢኮኖሚ ጀምሮ እስከ ድህነት ያሉ ጉዳዮችን የሚዳስሱ በስድስት እርከኖች የሚገኙ ተመራማራዎች እንዳሉትም ለምክር ቤቱ ፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተገልጿል፡፡

‹‹ምርምር በጣም ውድ ተግባር ነው፣ ብዙ ወጪ ያስወጣል፣ መንግሥት የሚሰጠው ድጋፍ ለዚህ ቁርጠኝነቱን የሚያሳይ ነው፤›› ያሉት በየነ (ፕሮፌሰር)፣ ስለሆነም ተጠቃሚ የሆኑ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የተቋሙን ጥናቶች በሚገባ መጠቀም እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

ከ2016 እስከ 2018 የበጀት ዓመት ተግባራዊ የሚደረገው የልማትና የመንግሥት ኢንቨስትመንት ዕቅድ በመንግሥት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በዕቅዱ በእያንዳንዱ ዘርፍ በሥራ ላይ ያሉና እየተዘጋጁ ያሉ ፖሊሲዎች ማስፈጸሚያ የልማት ፕሮግራም መለየቱን፣ እያንዳንዱን ፖሊሲ ለመተግበር ምን ዓይነት ፕሮግራም መቀረፅ አለበት የሚለውን ለእንዳንዱ ዘርፍ ተለይቶ በሦስት ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ መካተቱ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...