- 30ኛው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ዛሬ እየተከበረ ነው
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት፣ የሲቪክና የሚዲያ ምኅዳር ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ክስተቶች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤተ ገለጸ፡፡
ባለፉት ሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የጽሕፈት ቤቱ ኮሚሽነር በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውይይት እንዳደረጉ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በተለይ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በሚዲያ ነፃነት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ፣ የሽግግር ፍትሕና ተጠያቂነት ዙሪያ ክትትል ለማድረግ ጠንካራ ተቋማት በኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡
ከኮሚሽነሩ ጋር ውይይት ካደረጉት አንዱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሲሆን ባወጣው መግለጫ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ጽሕፈት ቤቱ መስማማቱን ገልጿል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት የኮሚሽነሩን የኢትዮጵያ ጉብኝት መጠናቀቅ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ኮሚሽነሩ በጉብኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የከፍተኛ የተመድ ባለሥልጣናት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ጋር በሽግግር ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲሁም የሲቪክ ምህዳርና የሚዲያ ነፃነትን በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ በመግለጫው አክሎም የሰብዓዊ መብት መከበር የዜጎችን ቁስልና በማኅበረሰብ ውስጥ ያለ ክፍፍልን እንደሚጠግን፣ ሰላም፣ አሳታፊና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲመጣ እንደሚያደርግና ለዚህም የመናገር ነፃነት፣ የነቃና ያልተገደበ የሲቪክ ማኅበረሰብ ምሕዳር ያስፈልጋል ብሏል፡፡
የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን በመላው ዓለም ለ30ኛ ጊዜ ዛሬ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. እየተከበረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትም ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል እያከበረ ነው፡፡