በሱዳን እየተካሄደ ያለው ግጭት ሦስተኛ ሳምንት ውስጥ ገብቷል፡፡ ተዋጊዎቹ ወገኖች ተኩስ ለማቆም ቢስማሙም ቃላቸውን ለማክበር ግን አልታደሉም፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ተቀናቃኞቹ ጄኔራሎች ሕዝብ በሠፈረበት አካባቢ፣ በሆስፒታሎችና ከአገር ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎችን ዒላማ በማድረግ እርስ በርሳቸው እየተካሰሱ አጓጉል ጨዋታ ይጫወታሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አገሪቱ በጦርነቱ እየፈራረሰች መሆኗን ያስጠነቀቀው፣ የጦር አውሮፕላኖች የቦምብ ጥቃትን በካርቱም ላይ በማድረሳቸውና ከባድ ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ ነው፡፡
የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃንና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በሚመሩት ‹‹ሄሜቲ›› በሚል ስማቸው በሚታወቁት ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጀመረው ጦርነት ከ528 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ 4600 ሰዎች ተጎድተዋል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩት ወደ ጎረቤት ቻድ፣ ግብፅ፣ ደቡብ ሱዳን ወይም ኢትዮጵያ አድካሚ ጉዞ መጀመራቸውም እየተዘገበ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በሱዳን ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ወደ ከፋና አሳሳቢ ደረጃ እንዳያመራ አስጠንቅቋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሱዳን ‹‹ታይቶ የማይታወቅ›› ሁኔታ ውስጥ መሆኗን በማመልከት ልዑካቸውን መላካቸውን ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሱዳን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ ነው›› ያሉት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዲጃሪች በሰጡት መግለጫ፣ ጉተሬዝ የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አስተባባሪውን ማርቲን ግሪፍትሰን ‹‹በአፋጣኝ ወደ አገሪቱ እየላኩ ነው›› ብለዋል፡፡ በሱዳን በመታየት ላይ ያለው ነገር አስደንጋጭ ነው ያለው መግለጫው ‹‹በጣሙን ተጨንቀናል›› ብሏል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ዲፕሎማቶች ማርቲን ግሪፍትሰን ‹‹በሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት መጠንና ፍጥነት ከዚህ ቀደም ተከስቶ የማይታወቅ ነው›› ብለዋል፡፡ ዲፕሎማቱ አያይዘውም ለሰላማዊ ወገኖች የውኃ፣ የምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ የተካሄደው ዘረፋ አግዶታል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሱዳን ርዕሰ ከተማ ካርቱም በተንሰራፋው ዘረፋና ሕገወጥ ድርጊት አጋጣሚ፣ አሜሪካዊው ሐኪም ቡሽራ ኢከናውፍ ሱሊማን (ዶ/ር) መገደሉን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡
የ49 ዓመቱ ጎልማሳ ሐኪም፣ በካርቱም ውጊያው እስከተባባሰበት ጊዜ ድረስ በሱዳን ጉዳተኞችን ማከሙን አላቋረጠም ነበር፡፡ ተከታታይ ፍንዳታዎች ቤቶችን ባናወጠበት ጊዜ አካባቢውን ለቅቆ ለመሄድ ቢሞክርም አሸማቂዎች በቤተሰቡ ፊት በስለት ወግተው መግደላቸው ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካ መንግሥትና ዓለም አቀፍ አጋሮች ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉ አሜሪካውያን ሱዳንን ለቀው እንዲወጡ ረድተዋል፡፡
በሱዳን የተፈጠረውን ሁከት በመሸሽ በርካታ ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ በኩል አልፈው ሞቃዲሾ መግባታቸውን የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን አብዱራህማን ኑር መሐመድ ዲናሪ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሶማሊያውያን ከሱዳን በኢትዮጵያ በኩል በአውሮፕላን ወደ ሶማሊያ ተጉዘዋል፤›› ብለዋል፡፡
ባለፈው እሑድ ሞቃዲሾ ከደረሱት ውስጥ 45ቱ የፑንትላንድ ግዛት አስተዳደር ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ጋሮዌ መወሰዳቸውንም ዲናሪ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
በተያያዘም የሱዳን መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል (ፓራሚሊተሪ) ጋር የሚያደርገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለ72 ሰዓታት ለማራዘም መስማማቱን አስታውቋል፡፡ የሱዳን መከላከያ ኃይል አማፅያኑ አንዳንድ ቦታዎችን ለማጥቃት ቢያስቡም የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚያከብሩ ተስፋ አደርጋለሁ ማለቱም ተዘግቧል፡፡
የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ቃል አቀባይ በበኩላቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከእሑድ ሌሊት ጀምሮ ለ72 ሰዓታት መራዘሙን ተናግረዋል፡፡
ግጭቱን ተከትሎ በግጭት ውስጥ ከሚገኙት አካባቢዎች የሚገኙ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ ሆስፒታሎች መዘጋታቸውን ሐኪሞች አመልክተዋል፡፡
የብሔራዊ ዶክተሮች/ሐኪሞች ማኅበር እንደገለጸው፣ ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ሆስፒታሎች በጤና ባለሙያዎች፣ በሕክምና አቅርቦቶች በውኃና መብራት እጥረት ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል፡፡
‹‹የሱዳን የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ሊፈርስ ምንም አልቀረውም፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ ሆስፒታሎች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፡፡ አያሌ የተራድâ ድርጅቶች ሥራቸውን ለማቆም ሠራተኞቻቸውን ከአካባቢው እንዲወጡ ለማድረግ ተገደዋል፡፡››
ቅንብር በጋዜጣው ሪፖርተር