Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሠራተኞች ተደራጅቶ መብትን የማስከበር ትግል የት ደረሰ?

የሠራተኞች ተደራጅቶ መብትን የማስከበር ትግል የት ደረሰ?

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን (May Day) የሚከበርበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በመሆኑም በመላው ሠራተኛ መብትና ግዴታዎች ረገድ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ኃላፊነትም ዙሪያ መነጋገር ግድ ማለቱ አይቀርም፡፡ በተለይ እኛን የመሰሉ የሦስተኛው ዓለም አገሮች አብዛኛው ሕዝብ ደሃና ዝቅተኛ ተከፋይ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ገና በማደግ ላይ ባለው የኢንዱስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተቀጥሮ የሚሠራው እየበረከተ በመምጣቱ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋልና ወቅታዊ አጀንዳ ለማድረግ ወድጃለሁ፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት የወጣ አንድ የአገራችን የሠራተኞች አደረጃጀት ጉዳይ ላይ ያተኮረ መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ከ400 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን የያዙ (አሁን ሊጨምር ይችላል) ከ900 በላይ ማኅበራትን በዘጠኝ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖች ያቀፈ ግዙፍ ተቋም ነው፡፡ አሁንም ድረስ ግን ይህ ግዙፍ ተቋምም ሆነ ማኅበራቱ በንቃት ተደራጅተው ለመብታቸውና ለአገራቸው በሚፈለገው ደረጃ የሚታገሉበት ሁኔታ አለመጠናከሩ ነው የሚነገረው፡፡

አገራችን የሠራተኞችን መብቶች ለማስከበር የሚያስችል የሠራተኛ አዋጅ አላት፡፡ በዚህ አዋጅ የተጠቀሱ አንቀጾችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ግን የሚታዩና ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ውስጥም መፍትሔ ያላገኙ እንከኖች አሉ፡፡ በዋነኛነት የሠራተኞችን በነፃነት የመደራጀት መብት ማንሳት ይቻላል፡፡ ጊዜውን የዋጀ የጥቅማ ጥቅምና መብት ማስከበር ጥረቱም እጅግም ውጤት አለማሳየቱ ይነገራል፡፡ እርግጥ ሠራተኛው በማኅበር መደራጀቱ የሚያስገኝለት ጥቅም እንዳለ ነጋሪ ሳያስፈልገው ራሱ ያውቀዋል፡፡

መደራጀት ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ነው፡፡ ይህ መብት አሠሪዎቹ የሚሰጡት ወይም የሚነፍጉት አይደለም፡፡ በዚህ የመደራጀት መብቱ ለመጠቀም ሲነሳ ግን በርካታ እንቅፋቶች ይጋረጡበታል፡፡ ሠራተኛውን ለማደራጀት የሚንቀሳቀስ ሠራተኛ ወይም ቡድን በማኔጅመንቱ ዘንድ አይወደድም ይባላል፡፡ በብዙዎቹ የልማት ድርጅቶችና የግል ተቋማት ሳይቀር ተደጋግሞ እንደታየው ሥራውን እስከማጣት የሚደርሱ መከራዎች ያገኙታል፣ ሰበብ ተፈልጎም ይባረራል፡፡

እንደ ምንም ብሎ ማኅበር ለማደራጀት የበቃ ሠራተኛ ቢኖር ደግሞ የማኔጅመንቱ ደጋፊ የሆኑ ሌሎች ሠራተኞች የተደራጀውን ማኅበር በመቃወም፣ አጎብዳጅና አድርባይ የሆነ ሌላ ማኅበር ለመመሥረት እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል፡፡ ማኔጅመንቱ ለእነዚህኞቹ የገንዘብና የትራንስፖርት፣ የምክርና የማጀገን ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ደርግ ከተከተለው የተኮላሸ ሶሻሊዝም አንስቶ እስካሁን ድረስ ነፃ አደረጃጀትና ገለልተኛ ማኅበራት አመራሮች እምብዛም ዓይታዩም የሚባለውም ከዚህ አኳያ ነው፡፡

በእርግጥ የሠራተኛው መደራጀት ለድርጅታቸው የሚያስገኝላቸው ጥቅም መኖሩን የሚያምኑ፣ ሠራተኛውን በማኅበር እንዲደራጅ የሚያበረታቱና ከተመሠረተም በኋላ ግልጽና አሳታፊ በሆነ አሠራር ከማኅበሩ ጋር እጅና ጓንት ሆነው ለጋራ ጥቅም አብረው የሚሠሩ አሠሪዎች መኖራቸው አይካድም፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ የሠራተኛውን መደራጀት የማይፈልጉና የሚያደናቅፉ አሠሪዎች ቁጥር ግን ይበልጣል፡፡

የሠራተኛውን መደራጀት እንደ ሥጋት ሳይሆን እንደ ጠቃሚ ግብዓት የሚመለከቱና ለምርታማነትና ለትርፋማነት ያለውን ውጤታማ አስተዋጽኦ የሚገነዘቡና የሚያምኑ፣ መርሁ የገባቸው ድርጅቶች አሉ፡፡ ፈጽሞ ያልገባቸው አሠሪዎችም አሉ፡፡ ያልገባቸው እንዲገባቸው ስለማይፈልጉ ነው እንጂ የግንዛቤ ችግር ኖሮባቸው አይደለም፡፡ የሠራተኛውን የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በሚመለከት አንዳችም ብዥታ የለም፡፡ ትርፉ የሠራተኞችን መደራጀት ካረጋገጠው ሕገ መንግሥት ጋር መላተም ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ሠራተኞች በማኅበር መደራጀትን የሚመርጡት በቅደም ተከተል እንደሚከተለው የተቀመጡትን ፍላጎቶች ለማስጠበቅ ነው፡፡

  1. ተገቢ፣ ተመጣጣኝና ፍትሐዊ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ሥርዓት እንዲኖር፣
  2. የሥራ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ የሚያደርግ ሥርዓት እንዲኖር፣
  3. የሥራ ሰዓት እንዲቀነስ ለማድረግ፣
  4. ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ መብቶችን ለማስከበር (ለምሳሌ በቦርድ ውክልና ለማግኘት)፣
  5. በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ናቸው፡፡

የአሠሪዎች ፍላጎት ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው

  1. የሠራተኛ ወጪን (ክፍያ) መቀነስ፣ ወይም ባለበት እንዲቆይ ማድረግ ወይም የማይተካ ከፍተኛ ችሎታ ላላቸው ሠራተኞች ብቻ የተወሰነ ጭማሪ ማድረግ፣
  2. ማኅበር ቢመሠረት ጎጂ የሆኑ አለመግባባቶች (ግጭቶች) ስለሚፈጠሩ በድርጅታቸውም ላይ የገጽታ መጠልሸትን ስለሚያስከትል አለመፈለግ፣
  3. በዘርፉ ካሉ ሌሎች ፋብሪካዎች ጋር የሚቀራረብ የክፍያና የጥቅማ ጥቅም ሥርዓት መዘርጋት፣ የድርጅቱ ምርታማነትና ትርፋማነት ከግምት ውስጥ ሳይገባ ሌላው በሚሠራበት ዓይነት ብቻ ለመሥራት መፈለግ ናቸው፡፡

ሠራተኞች የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም፣ የሥራ ሰዓት ቅነሳና በውሳኔ አሰጣጥ መሳተፍን የሚጠይቁት በተረጋጋ ሁኔታ የድርጅቱ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ ትርፋማ ሆነው ለድርጅቱም ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡ አሠሪዎች ደግሞ ደመወዝ መጨመር የማይፈልጉት ትርፉ ሲከማች ድርጅቱ ሌላ የሥራ ዕድሎችን ሊፈጥር ይችላል በሚል ሰበብ ነው፡፡

እስካሁን በሠራተኞችና በአሠሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት (Industrial Democracy) በአብዛኛው በጭቅጭቅ፣ በሙግትና በመወነጃጀል ላይ የተመሠረተ ሆኖ ነበር የቆየው፡፡ በሠራተኞች በኩል ጉድለት የለም ባይባልም ዋናው ግን ከአሠሪዎች በኩል የሚነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም አሠሪዎች ለሠራተኛ ማኅበር ጥንካሬና ጠቀሜታ ዕውቅና መስጠት አይፈልጉም (አሁን አሁን በትራንስፖርት ሰርቪስ አቅርቦት መሻሻል ቢታይም፣ በክፍያና በኑሮ አለመመጣጠን ሠራተኛው በኑሮ ውድነት እየተቸገረ በመሆኑ ቅሬታ እንዳለው የታወቀ ነው)፡፡

አሠሪዎች ከሠራተኞች መካከል ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውና እነሱ (አሠሪዎቹ) ከሚገምቱት በላይ ስለኢንዱስትሪያዊ ዴሞክራሲና ቢዝነስ የሚያውቁ ሰዎች መኖራቸውን ለመቀበልና ለማመን አይፈልጉም፡፡ በተለይ ደግሞ አሠሪዎች ሆን ብለው ጊዜ ያለፈበት ያረጀና ያፈጀ የሠራተኛ አስተዳደር ወይም አያያዝ ዘዴ (Outdated Methods Of Treating Employees) መጠቀምን ይመርጣሉ፡፡ ይህን ማስተካከል ግን ለነገ የማይባል ሥራ መሆን አለበት፡፡

አብዛኞቹ ኩባንያዎች የሰው ኃይል ልማትና የአስተዳደር ሥራን እንደ ጠቃሚና አስፈላጊ ዘርፍ ማየት አይፈልጉም፡፡ በድርጅቱ መዋቅር ውስጥም (ለዚያውም አብዛኞቹ ድርጅቶች መዋቅር የላቸውም) የሚሰጡት ሥፍራና ደረጃም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህን መዋቅራዊ ችግር በጠንካራ ክትትል ለመፍታት የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በቂ ጥረት አለማድረጋቸው ውጤቱን አዳክሞታል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው ያላቸው ንቀት ከፍተኛ ነው፡፡ ለሠራተኞቻቸው ያላቸውን የአመለካከት ዝቅጠትም የተባባሰ ሆኖ የሚታይበት ወቅት አለ፡፡ ሠራተኛው መቀለጃ አለመሆኑ ግንዛቤው ሳይኖራቸው ቀርቶ ግን አይደለም፡፡ ዕውቅና ለመስጠት አለመፈለጋቸው ነው፡፡ ለሠራተኛ መብቶች ዕውቅና መስጠት የሚፈጥርባቸው ሥጋትም አለ፡፡ ከዚህ ሥጋታቸው ይላቀቁ ዘንድ ልንተባበራቸው ይገባል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁንም ሆነ ሜይ ዴይን የማክበሩ  ዓላማም ይህ ነው፡፡

ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣ አዋጅ ራዕይ አሠሪና ሠራተኛ የሥራ ግንኙነታቸውን መሠረታዊ በሆኑ መብቶችና ግዴታዎች ላይ መሥርተው የኢንዱስትሪ ሰላምን በመፍጠር፣ ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት በመተባበር በጋራ እንዲሠሩ ማስቻል ነው፡፡ ይህን በተቀናጀ ጥረት መምጣት ያለበት ስኬት ለማስመዝገብ ግን ብርቱ ትግልና መነሳሳት ይፈልጋል፡፡

የአዋጁ ተልዕኮ ሠራተኞችና አሠሪዎች የየራሳቸውን ማኅበራት በየግላቸው በማቋቋም፣ በመረጧቸው ሕጋዊ ወኪሎቻቸው አማካይነት ጥቅማ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የኅብረት ድርድር የማድረግ መብት እንዲኖራቸውና በመካከላቸው የሚነሳ የሥራ ክርክርም በተቀላጠፈ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡

የአዋጁ ግብ የአሠሪና የሠራተኛ ጉዳይ አስተዳደርን በተለይም የሥራ ሁኔታን፣ የሙያ ደኅንነት፣ ጤንነትና የሥራ አካባቢን በተመለከተ በሕጉ መሠረት ቁጥጥር የሚያደርግ አካልን ሥልጣንና ተግባር አጠናክሮ በሕግ መወሰን ነው፡፡

እነዚህን ዓላማዎች በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት የሚመርጡትን መሠረታዊ ሐሳቦችና የሥራ ሁኔታዎችን የያዘ ከመንግሥት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሶሻል ፖሊሲ ጋር የተገናዘበና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖችና ሌሎች ሕጋዊ ሰነዶች ጋር የተጣጣመ ሕግ ለማውጣት በሥራ ላይ ያለውን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ በተሻሻለ ሕግ ተክቷል፡፡

በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት የአሠሪና ሠራተኛ ሕጎቻቸውን በየጊዜው ማሻሻላቸው ያለና የነበረ አሠራር ነው፡፡ ለምሳሌ ለእኛ ተቀራራቢ አብነት ባትሆንም እንግሊዝ ያላግባብ ከሥራ ማባረርን፣ የእናትነት መብትን፣ ቅጥርን፣ የማኅበር አመሠራረትን፣ ምርጫን፣ የማኅበር አባል መሆንና አለመሆንን፣ ወዘተ የሚደነግገውን የሠራተኛ ሕግ (The Employment Act) እ.ኤ.አ. የ1980፣ የ1988 የሠራተኛ ማኅበራት ሕግ እ.ኤ.አ. በ1984 አዳዲስ የሕግ አንቀጾች እየተጨመሩና የነበሩትም እየተሻሻሉ እንዲሠራባቸው ተደርጓል፡፡

መንግሥት የአሠሪና ሠራተኛን ግንኙነት መልካም ለማድረግ፣ ለማደራደርና የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስገኘት መሥራት ከሚጠበቅበት ዋነኛ ተግባር ጉዳዩን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ማስቀመጥ አዋጅና ደንብ በማውጣት ሥርዓትን መዘርጋት ነው፡፡ የእኛም መንግሥት በዚህ ረገድ ያለበትን ኃላፊነት በሚገባ ተወጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ ስለአሠሪ ኃላፊነቶች፣ ስለሠራተኛ መብቶችና ግዴታዎች፣ ስለኅብረት ስምምነት፣ ስለቦርድ ውክልና፣ ስለማኅበር አመሠራረትና ተግባራት፣ ወዘተ. የሚደነግጉ በሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ ለኢንዱስትሪ ሰላም የሚበጁ ሕጎችን አውጥቷል፡፡

      በእርግጥ እነዚህ ድንጋጌዎች በሌሎች በርካታ አገሮችም የሚሠራባቸው ናቸው፡፡ በሌላ አገር የሚሠራበት ሕግ ሁሉ ለእኛም አገር ችግር መፍትሔ ይሆናል ማለት ግን አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ከአገራችን የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ ሕግ ያለን ቢሆንም አፈጻጸሙ ላይ ቁጥጥርን ማጥበቅ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ችግራችን ሕገ መንግሥቱ ወይም ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣው አዋጅ መኖር ወይም አለመኖር አይደለም፡፡ የእኛ ችግር የወጣውን ሕግ መሬት ላይ አውርዶ ተግባራዊ ለማድረግ ያለብን ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ በተሻሻለ ሁኔታ ከወጣ እንኳን እነሆ ዛሬ 18ኛ ዓመቱ ነው፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ስለሚመሠረት የሥራ ውልና ስለሚያካትታቸው ጉዳዮች በግልጽ የሠፈሩ አንቀጾች አሉት፡፡

እነዚህ ውሎች ሰፊና ብዙ ቢሆኑም ማንኛውም አሠሪ በሥራ ውሉ ከተመለከቱት ልዩ ግዴታዎች በተጨማሪ፣ ሌሎች ግዴታዎች ያሉት ስለመሆኑም ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ አሠሪው በሥራ ውሉ መሠረት ለሠራተኛው ሥራ የመስጠት፣ ለሥራ የሚያስፈልገውን መሣሪያና ጥሬ ዕቃ ለሠራተኛው የማቅረብ፣ ለሠራተኛው ደመወዙንና ሌሎች ክፍያዎችን በውሉ፣ ወይም በኅብረት ስምምነቱ መሠረት የመክፈል፣ ለሠራተኛው የሚገባውን ሰብዓዊ ክብር የመጠበቅ፣ ከሥራው ጋር በተያያዘ የሠራተኛውን ደኅንነትና ጤንነት ለመጠበቅና ከአደጋ ለመከላከል የሚያስፈልጉትን ዕርምጃዎች ሁሉ የመውሰድና እነዚህንም ዕርምጃዎችን በሚመለከት ረገድ አግባብ ባላቸው ባለሥልጣናት የሚሰጡትን ደረጃዎችና መመርያዎች የመከተል ኃላፊነት አለበት፡፡

አንዳንድ አሠሪዎች ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ የሠራተኛውን ስም የሚያጠለሽ፣ ሌላ ቦታ ሄዶ ተቀጥሮ እንዳይሠራ የሚያደርግ ጎጂ ወረቀት ጽፈው ይሰጣሉ፡፡ ሠራተኛው ያን ይዞ ፍርድ ቤት ሄዶ ክስ መሥርቶ አሠሪውን አስቀርቦ የስንብት ወረቀቱ ተስተካክሎ እንዲጻፍለት ያስደረገበት ሁኔታ መኖሩን እናውቃለን (በዚህ ረገድ ማኅበራቱ ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትም ኃላፊነት አለበት)፡፡ አሁን ተደጋግሞ የሚነሳው የተቀጣሪው ወገን ቅሬታ በኑሮ ውድነት እጅግ በጣም የተቸገሩ መሆኑን የተመለከተው ነው፡፡ ጥያቄው ስለአጠቃላይ የአገሪቱ የኑሮ ውድነት ችግር አይደለም ጥያቄው፣ ሠራተኞች ለመደራጀት ባለመቻላቸው የተነሳ የኅብረት ስምምነት ስለሌላቸው ለደመወዝ ጭማሪና ለሌሎች ጥቅማ ጥቅሞቻቸው መከበር በማኅበር መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው፣ በአሠሪዎች በሚደርስባቸው ተፅዕኖ መብቶቻቸው ባለመከበራቸው ምክንያት ስለሚደርስባቸው የኑሮ ውድነት ችግር ነው፡፡

ለዚህም ቢሆን አተገባበሩ ወጥና ጠንካራ አይሁን እንጂ መንግሥት የሕግ ማዕቀፍ አበጅቷል፡፡ ማኅበር ስለማቋቋም መብት፣ ስለማኅበር አመሠራረት፣ ስለማኅበራት ተግባር፣ ስለመተዳደሪያ ደንብ፣ ስለማኅበር ምዝገባ፣ ስለኅብረት ስምምነት፣ ስለመደራደር፣ ስለኅብረት ስምምነት ይዘት፣ ስለድርድር ሥነ ሥርዓት፣ ስለሥራ ክርክር፣ ወዘተ የሚደነግጉ ሕጎች በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ውስጥ አሉ፡፡

የአሁኑን ዘመን ችግር ለመፍታት ሕጉ ከበቂ በላይ ነው፡፡ የቸገረን ተግባራዊ ማድረግ ነው የሚለው የሠራተኞች ምሬት አዳማጭ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው ሦስት ተቋማት ማለትም አሠሪዎች፣ ሠራተኞችና መንግሥት ግንኙነታቸውን አጠናክረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአሠሪዎች ዘንድ ስላለው ችግር ስናወራ ሁሉንም አሠሪ በጅምላ ማለታችን አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ሠራተኛው የራሱን ማኅበር እንዲያደራጅ፣ እንዲደራደር፣ የኅብረት ስምምነት እንዲኖረው ሐሳቡን ያመነጩና ሠራተኛውን ያንቀሳቀሱ፣ ማኅበሩ እንዲመሠረት ድጋፍ ያደረጉ አሠሪዎች መኖራቸውን እናውቃለን፡፡

በሠራተኞች በኩልም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ በማኅበር መደራጀት ለምርታማነትና ለተወዳዳሪነት የሚበጀውን ያህል፣ በአንዳንድ የሠራተኞች ማኅበራት ውስጥ የሚታየው አዝማሚያ መታረም ያለበት ነው፡፡ ሠራተኞች በማኅበራቸው አማካይነት በአሠሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር እጃቸውን ጠምዝዘው የማይገባቸውን፣ ወይም ከሚገባቸው በላይ የሆኑ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጭማሪ ለማስደረግ የሚያስቸግሩ አሉ፡፡ ይህ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡

የሥራ ሰዓትና ንብረት የሚያባክኑ፣ ለአሠሪዎቻቸው ወይም ለድርጅቱ የማያስቡ ማኅበራት ያሉበት ሁኔታም ያጋጥማል፡፡ ማኅበራቱ በአዋጅና በኅብረት ሥራ ስምምነት ውስጥ የተጠቀሱ ግዴታዎቻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ መብትን ማስከበር ጥሩ ቢሆንም ግዴታንና ኃላፊነትን ማክበር ደግሞ የበለጠ ጥሩ ነው፡፡ እነሆ የላብ አደሮችን ወይም የሠራተኞችን ቀን ስንዘክር ማስታወስ የምሻው ምክር ይህንን ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...