Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ለማኅበራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጠው የብድርና የቁጠባ ተቋም

ሰዎች ንግድ ለመጀመር እንዲሁም ለማሻሻል በቂ ገንዘብ መያዝ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን የገንዘብ ምንጭ ማስፋት ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ፣ ነጋዴዎች ለተጨማሪ ገንዘብ ወደ ብድር ተቋማት ማቅናታቸው የተለመደ ነው፡፡ በአዲስ መልክ ወደ ንግድ ዓለም መግባት የሚሹ ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም፣ ወደ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ ተቋም ድረስ በብድር ንግዳቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የተመሠረተው የግሎባል የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ማኅበሩ በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦችን አባል በማድረግ የብድርና የቁጠባ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ሒደቱ ውስጥ ጊዜ ለማይሰጡና አንገብጋቢ ለሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠቱ ተቋሙን ልዩ እንደሚያደርገው ይገለጻል፡፡ አቶ ሞላ ባዘዘው የግሎባል የገንዘብ ቁጠባና ብድር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ስለድርጅቱ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የግሎባል ገንዘብ ቁጠባ፣ ብድር ምሥረታና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ሞላ፡- የግሎባል የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር የተቋቋመው መጋቢት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ 28 ወንዶችና 8 ሴቶች፣ በአጠቃላይ 36 መሥራች አባላት በተገኙበት የመጀመርያ ጉባዔውን አድርጎ ተመሥርቷል፡፡ ከዚያም ሚያዝያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰርተፊኬት ወስዶ በኅዳር 2009 ዓ.ም. ጽሕፈት ቤት ተከራይቶ ወደ ሥራ ገባ፡፡ ምሥረታውን ተከትሎ የአባላት ተሳትፎ እያደረገ መምጣት ችሏል፡፡ በወቅቱም የነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተረጋጋ በመሆኑ፣ ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት የአባላቱ ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ከ36 መሥራች አባላት በየዓመቱ 200 እና 300 አባላት በማፍራት፣ በአሁኑ ሰዓት 900 አባላት በተቋሙ አባል ሆነው እየቆጠቡ ይገኛሉ፡፡ ተቋሙ በምሥረታው ወቅት ከአባላት አንድ፣ አንድ ሺሕ ብር በማዋጣት በ36 ሺሕ ብር መመሥረቻ ካፒታል ተነስቶ አሁን ቁጠባን ሳይጨምር ካፒታሉ 600 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ አገልግሎት የሚሰጠው ለየትኛው ማኅበረሰብ ክፍል ነው?

አቶ ሞላ፡- ተቋሙ በኅብረት ሥራ አዋጅ 985/2009 እንዲሁም በቀድሞ አዋጅ 147/91 የሚተዳደር ሲሆን ለአባላት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ስለዚህ አዋጁ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ክፍት የሆነ ነው፡፡፡ ይህም በፆታና በእምነት የተከፋፈለ አይደለም፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ከማኅበረሰቡ በተቆጠበ ገንዘብ ብቻ ለ150 አባሎች እስከ 18 ሚሊዮን ብር ድረስ የብድር አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ በዚህም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ደረጃ ላይ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ለአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የሥራ ዕድል ለመፍጠር ችሏል፡፡ የተለያዩ ስለማኅበሩ አገልግሎት አሰጣጥ የሚያስረዱ የመረጃ መንገዶችን በመከተል፣ የተለያዩ አባላት ወደ ማኅበሩ እየመጡ ነው፡፡ ተቋሙ በውስን አባላት የተመሠረተ ቢሆንም፣ በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ የፋይናንስ ተቋም ለመሆን እስከ 2025 ዓ.ም. ግብ አስቀምጦ እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በዘርፉ ላይ ከተሰማሩ የብድርና የቁጠባ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አሉ፡፡ በአንፃሩ ዘመናዊ  መንገድ የተከተሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ የማኅበሩ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ሞላ፡- ማኅበሩ የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በተለይ ከባህላዊ የሒሳብ አያያዝ ወደ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ እየተሻገርን እንገኛለን፡፡ በዚህም የተለያዩ ተቋማት እየተገለገሉበት የሚገኙትን ሶፍትዌሮችን በመጠቀም፣ ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ጋር ሳኮሊንክ ከተባለ ምርት ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ ሙከራ ላይ ነን፡፡ አሠራሩ የብድር አሰባሰብ ማንኛውም ሰው በበይነ መረብ መመዝገብ የሚያስችል፣ ከሚገለገልበት የባንክ የሒሳብ ቁጥር መክፈል የሚያስችል ደረሰኝ፣ እንዲሁም ብድር በኦንላይን ማስተላለፍ የሚያስችል ሒደትን ለመከተል እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ አባል ለመሆን ያስቀመጣችሁት መሥፈርት ምንድነው?

አቶ ሞላ፡- አንድ አባል የማኅበሩ አባል ለመሆን በቅድሚያ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አባሉ በማኅበር ውስጥ የአባልነት የድርሻ ዕጣና የቁጠባ ተቀማጭ ሊኖረው እንደሚገባ እናሳውቃለን፡፡ የአንድ አክሲዮን መጠን ዋጋ 1,000 ብር ሆኖ እስከ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ አባል ሆኖ አምስት ወይም ስድስት አክሲዮን እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ ቁጠባ ደግሞ በየወሩ 500 ብር እንዲቆጥብ ይደረጋል፡፡ አባሉ ቁጠባውን እየቆጠበ በመሀል የብድር ፍላጎት ቢኖረው በተለያየ አገልግሎት ማለትም ለሥራ ማስኬጃ፣ ለመኪና፣ ለግንባታ፣ ለኮንዶሚኒየም ቅድመ ክፍያ፣ ለትምህርት፣ ለጤና እንዲሁም ለተፈለገው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ብድሩ ይፈቀድለታል፡፡ ብድሩን ለመውሰድ የመጀመርያው ቅድመ ሁኔታ አባል መሆኑ ነው፡፡ አብዛኛው የብድር ሒደት ስድስት ወርና ከዚያ በላይ እንዲቆጥብ ያስገድዳል። በአንፃሩ ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮች ማለት ጤና፣ ትምህርትና የቤት ጉዳይ ሲያጋጥም ቅድሚያ የሚሰጥበት አሠራር አለን፡፡ አንድ አባል የትምህርት ዕድል ቢያገኝ ወይም የኮንዶሚኒየም ዕጣ ቢደርሰው፣ የግድ ስድስት ወራት ላይጠብቅ ይችላል፡፡ በተለያዩ የማጣሪያ መንገዶች በቅድሚያ ሊስተናገድ የሚችልበት አሠራር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- የግሎባል የብድርና የቁጠባ ማኅበር ምን የተለየ ያደርገዋል?

አቶ ሞላ፡- የእኛ ማኅበር የተለየ የሚያደርገው ሰው ላይ ነው የሚሠራው፡፡ የግሉ የማይክሮ ፋይናንስና በእኛ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የእኛ ተቋም አባል ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ አባሉ የተበደረውን ብድር መመለስ ባይችል በቀዳሚነት መመለስ ያልቻለበት ሁኔታ ይጠናል፡፡ ጉዳዩን ካጤነ በኋላ አባሉ ካጋጠሙ ችግሮች ተላቆ ወደ መደበኛ የቁጠባና የብድር አገልግሎት እንዲመለስ ይደረጋል። ሌላው ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ያቀርባል፡፡ እኛ ሦስት የወለድ ምጣኔ አማራጮች አሉን። ይህም  ለወጣቶች 13 በመቶ፣ ለሴቶች 13 በመቶ እንዲሁም ለጎልማሶች 14 በመቶ አማራጭ አስቀምጠናል፡፡ ሌላው አባሉ በፈለገው ጊዜ ብድሩን የመመለስ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዝቅተኛ ሦስት ዓመት፣ የመካከለኛ አምስት ዓመት እንዲሁም የረዥም አሥር ዓመት የብድር ዘመን አለን።

ሪፖርተር፡- የብድር መጠናችሁና የብድር ፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱ ምን ይመስላል?

አቶ ሞላ፡- ለጊዜው የብድር ጣራችን አንድ ሚሊዮን ብር ነው፡፡ የብድር አሰጣጡም የተከፋፈለ ሲሆን፣ በሥራ ዋስትና የሚወጣና በንብረት ዋስትና የሚመጣ የብድር አሠራር እንከተላለን፡፡ በሥራ ዋስትና የሚወጣ ብድር እስከ መቶ ሺሕ ብር ሲሆን፣ በንብረት ዋስትና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ይፈቀዳል፡፡ ይህ በየዓመቱ የሚሻሻል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ቢያነሱልን?

አቶ ሞላ፡- እንደ ፋይናንስ የኅብረት ተቋማት የሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ለእነዚህ ተቋማት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ አንደኛው ነው፡፡ ይህም ከከተማ አስተዳደር ወረዳ፣ ቀበሌ፣ እንዲሁም በአገር ደረጃ ዘርፉን እየፈተነው ይገኛል፡፡ በከተማዋ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች እየኖሩ፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያሉትን አባላት ቁጥር ቢወሰድ በሺዎች የሚቆጠሩት እንኳን የዘርፉ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ይህም ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ በሌላ በኩል የኅብረተሰቡን ፍላጎት ባማከለ መልኩ የአባላቱን ተጠቃሚነት የሚያሰፋ የብድርና የቁጠባ ማኅበር ሊረዱ የሚችሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሉም፡፡  ይኼ ዘርፉን እየጎዳው ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...