Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የከበደው ትርጉም!

ጉዞ ከመብራት ኃይል ወደ የረር ነው። ሕይወት አመሏ ብዙ ነው። መልኳ እያደር ይለዋወጣል። የጠበቁት ይቀርና ያላሰቡት ይከሰታል። የሠጉበት ነገር ጭምድድ አድርጎ እያሰረ በጭንቀት ይንጣል። ይኼኔ ታዲያ፣ ‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› ብለው እንዲተርቱ ይገፋፋል። ይህች ነፍስ ተብዬ በሥጋ ከተማ ውስጥ የተሸሸገች ታላቅ ሚስጥር ነች፡፡ የሁለመናን ሚዛን እየጠበቀች እስከ ፍፃሜ ትገሰግሳለች፡፡ ስለዚህም ሕይወት ምን ብትከብድ፣ ኑሮ ምን እያደር ፊቷ ቢጠቁር መኖር ይፈቀር ዘንድ ግድ ታስብላለች፣ ነፍስ ታሳሳለችና ይባላል። በሕይወት ጎዳና ላይ ወዲያና ወዲህ ስንል ቀናችንና ዘመናችን እየተጠናቀቀ እንቅፋቱ ሲበዛብን፣ በነፍስ በኩል ለፈጣሪ በሥጋ በኩል ለአስተዳዳሪዎቻችን እንናገር ዘንድ እንማስናለን ተብሎም ድምፅ ይሰማል። ፈጣሪ በጊዜው እንደ ፈቀደ መልሱን ሲሰጥ፣ መንግሥታችን በሕንፃ ብዛት ኔትወርክ ተጨናንቆበት የብዙኃኑን ዕንባ አላዳምጥ ይላል እያሉ ያሙታል። ይህ ቢሆንም ቅሉ መኖር ይቀጥላል። ምን መከፋት ቢነግሥ፣ ምን መሰልቸት ቢያሸን መኖር በሕይወት ጎዳና፣ መኖር በጉዞ ውስጥ መቀጠሉን ሁላችንም ለመታዘብ ሁሌም በቦታው እንገኛለን። እንዳልነው ነፍስ ያሳሳልና፡፡ ታክሲ ውስጥ ገብቼ እንደተቀመጥኩ ዓይኔ አንዱ ጥቅስ ላይ ተተከለ። ‹‹ራስን ከመግዛት የበለጠ ትልቅ ሥልጣን የለም›› ይላል። አጠገቤ ደልደል ብሎ የተቀመጠ ተሳፋሪ እንደ እኔ ጥቅሱን እያነበበ፣ ‹‹ባይሆን በዚህ እንኳ እንፅናና እንጂ…›› ብሎ ፈገግ አለ። እኛም ፈገግ እንበል እንዴ! 

‹‹በምኑ?›› በማለት ከኋላችን የተቀመጠ ጎልማሳ ጠየቀው። ‘ራስን ከመግዛት በላይ ሥልጣን የለም’ የሚለውን ጥቅስ አላየህም እንዴ? ባይሆን እንዲህ እያልን እንፅናና እንጂ፡፡ አሁን ይህች ስላቅ አይደለችምና ነው?›› ብሎ አሽሟጠጠ። አንድ ወጣት ተሳፋሪ ፈጠን ብሎ፣ ‹‹እንዴ? እንዴ? ምነው ዴሞክራሲ እየገነባን? በድምፃችን ራሳችንን ማስተዳደር እየቻልን ማሽሟጠጡን ምን አመጣው ወንድሜ?›› ብሎ በቀናነት የመሰለውን አስተያየት ጨምሮ ጠየቀው። መልሱን ከመስማታችን በፊት፣ ‹‹ከታክሲ ውስጥ የመናገር ነፃነትና ከፓርላማችን የትኛው የሚበልጥ ይመስልሃል?›› ብሎ ከኋላ የተቀመጠ ሰው ወዳጁን ሲጠይቀው ሰማን። መልሱ ተድበስብሶ አልሰማን ሲል፣ ‹‹ደጇን ዓይተህ ቤቷ ግባ እናቷን ዓይተህ ልጂቷን አግባ›› የሚሉት ተረት በአዕምሮዬ ተመላለሰ። ተድበስብሶ ማድበስበስ የት ያደርሰን ይሆን? የዚህንም መልስ መስማት አማረን፡፡ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ጥያቄዎችን እንደ ሸቀጥ ማምረት ምን ይፈይድልን ይሆን? እንጃ!

‹‹ምን ዋጋ አለው?›› አለ አሽሟጣጩ ድንገት ጮክ ብሎ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ድምፃችን የሚፈለገው ለምርጫ ብቻ ነው መሰለኝ። ለአቤቱታና ለአስተያየት ጊዜ የሚፀየፈን ብዛቱ አይጣል ነው…›› ሲለው ወጣቱ ዝም አለ። ሰው እየገባ ታክሲያችን እየሞላች ብትሆንም ወያላው ትርፍ ካልጫነ በቀላሉ የሚንቀሳቀስ አልመሰለም። ‹‹ኧረ እንሂድ? ምናለበት ቢበቃህ?›› አለው አንድ ተሳፋሪ መቸኮሉ ከመቁነጥነጡ ያስታውቃል። ‹‹እንደፈለግኩት ጭኜ ነው የምሄደው…›› ብሎ በትዕቢት አነጋገር ወያላው መለሰለት። ይኼ አልበቃው ብሎ ደግሞ፣ ‹‹ከፈለግክ መውረድ ትችላለህ…›› ብሎ ገላመጠው። ‹‹አይ ራስን መግዛት?› በማለት ቅድም ጥቅሱን እያየ ሲያሽሟጥጥ የነበረው ተሳፋሪ መሳቅ ጀመረ። ‹‹ልጅ የአባቱን ይወርሳል ሆነና ለምንለጥፈው ጥቅስ፣ መርህና ዓላማ ታማኞች አልሆን አልን…›› ብሎ ሳቁን ካቋረጠበት ቀጠለው። ሌላው መለሰና እኔ የምፈራው ሥራው በሌለበት ግልጽነትና ተጠያቂነት እየተባለ የሚነገረው ነገር ተረት ተረት እንዳይሆን ነው…›› ብሎ አቀረቀረ። አንዳንዱ ሰው ክፉኛ ነገር ሲገባው አሳሳቅና አለቃቀስን አሳምሮ ይችላቸዋል። በአስመሳዮች ዘመን ሙዚቃው፣ ድራማው፣ ኮሜዲውና ለቅሶው እንደ ማኅበራዊ ተሰናድተው ሲቀርቡ ትወናውም የዚያኑ ያህል ቀጥሏል፡፡ የግድ ነው!

የወያላው ነገረኝነት በእጅጉ ያበሳጫቸው ተሳፋሪዎች አቤቱታቸውን ወደ ሾፌሩ ማቅረብ ጀመሩ። ‹‹ሾፌር? እንዴት እንዴት እንደሚናገር እያየህልን ነው? ገንዘባችንን ከፍለን እንዲህ ተንገላተን ለምንሄደውም ግልምጫ ይጨመርበት?›› አለ አንድ ቀጠን ያለ ተሳፋሪ። ይኼን ጊዜ ሾፌሩ ዞር አለና ወያላውን አተኩሮ አየው። አስተያየቱ የ‹‹አበጀህ›› ይሁን ወይም የ‹‹ተግሳፅ›› አልገባንም፡፡ በዚህ መሀል፣ ‹‹የዛሬ ልጆች የዕውቀታችው ጥግ ይኼ ነው?›› አሉ አንድ አዛውንት ተሳፋሪ። ‹‹ቆይ ግድ የለም…›› አለ ሾፌሩ አሁንም በቁጭት ይሁን በደንታ ቢስነት ስሜት። ጋቢና የተቀመጠ ጎልማሳ ተሳፋሪ፣ ‹‹እስከ መቼ እንዲህ ከሕዝብ እያናከሰህ ትኖራለህ አታባርረውም?›› ሲለው ጆሯችን ሰማ። ሾፌሩም፣ ‹‹ትንሽ ቀን ነው ግድ የለም። ፓርላማ ሥራቸውን በአግባብ አላከናውን ያሉ ባለሥልጣናትን ማባረር ሲጀምር የአንተና የእኔ ነገር ያከትማል…›› ሲለው ሁላችንም በመገረም ተያየን። ‹‹ደግሞ እናንተንና ፓርላማን ምንና ምን ያገናኛችኋል?›› ሲለው ጎልማሳው፣ ‹‹እንዴ? ላይ ያለው ሰው ሥራውን በአግባቡ አላከናወነም ተብሎ የሚሻር ከሆነ፣ ሌላው ምን ቆርጦት ሥራ እያበላሸ ይኖራል? ግን መጀመርያ ከላይ መማር አለብን። የተወራው መተግበር አለበት። ማተኮር ያለብን ቅርንጫፉ ላይ ሳይሆን ግንዱ ላይ ይሁን ተብሎ የለ? ከዚያ እኛ፣ ከእኛ ደግሞ አዲሱ ትውልድ ይኼን አካሄድ እየተከተለ እውነተኛው የዴሞክራሲ ሥርዓት ይሰፍናል…›› አለ ሾፌሩ እንደ ካድሬ፡፡ አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ ‹‹ወይ ዘንድሮ፣ በቃ ሰው የአገሩን ጉዳይ እንዲህ በዓይነ ቁራኛ መከታተል ጀመረ ማለት ነው?›› አለኝ። እንዲህ ሲል የሰማው፣ ‹‹ታዲያስ? ሌላማ ምን አለን ብለህ ነው?›› አለው። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ሁሌም ታክሲ ውስጥ ስሳፈር የተሳፋሪዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ያይልብኛል። የእውነት ነው? ወይስ አጋጣሚ ነው?›› ብሎ ይጠይቃል። አንዱ እየሳቀ፣ ‹‹አይ አጋጣሚ ነው…›› ብሎ በምፀት ይመልሳል። ከምፀቱ ጀርባ ከባድ ምሬት ይታያል፡፡ በኑሮአችን ውስጥ መርህ እየተረሳ አጋጣሚ ሲበዛ ምን ይባላል ታዲያ!

ወያላው እንዳሰኘው አፋፍጎን ሲያበቃ፣ ‹‹እንሂድ!›› ብሎ ሾፌሩን አዘዘው። ‹‹የበላዩ ታዛዥ የበታቹ አናዛዥ የሆነበት ዘመን። እግዚኦ! አሁን ይኼ አንድ ፍሬ ልጅ ከሕግ በላይ ሆኖ መብታችንን በጠራራ ፀሐይ ሲነፍገን ካልተባበርን መቼ ልንተባበር ነው?›› ብለው ከኋላ ተጨናንቀው የተቀመጡ አንድ አዛውንት ተናገሩ። ‹‹እውነት እኮ ነው፣ መቼ ይሆን እኛ እርስ በርሳችን ለመልካም ነገር፣ ለዕድገት፣ ለመብታችን መንግሥትን ሳንጠብቅ ተነሳስተን የምንተባበረው?›› ብሎ አጠገባቸው ያለ ጎልማሳ ተናገረ። ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹እናንተ ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና ብለው ጦርነት ውስጥ የከረሙት ሰዎች እርስ በርስ ሲሸላለሙ እያያችሁ ከእነሱ አትማሩም ማለት ነው…›› ብሎ በስስ ፈገግታ ፊቱን አብርቶ እያንዳንዳችንን ተመለከተን። ‹‹ማለት?›› አለው አጠገቡ ያለው ወጣት። ‹‹ማለትማ በነገር መወጋጋትም ከጦርነት የማይተናነስ ስለሆነ እርስ በርስ እየተሞጋገስን ያሰብንበት ብንደርስ አይሻልም ወይ ለማለት ያህል ነው…›› ሲል ነገሩ ገባን። የወያላው ሁኔታ፣ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ዘመኑ ፖለቲከኞች ሸርና ሴራ የተጋመደበት መሆኑ ያስታውቃል፡፡ ተንኮለኛ!

 ታክሲያችን ወደ መድረሻችን ተቃርባለች። ወያላው በተፋፈገው ሰው ላይ ረጅም እጁን እየሰደደ ሒሳቡን ተቀብሎ መልስ ይወረውራል። አዛውንቱ ተሳፋሪ መልስ እስኪሰጣቸው ጠብቀው፣ ‹‹ልጄ ከሰው ጋር ተግባባ፣ ሥራ የሚሠራው በመግባባት ነው፣ እሺ?›› አሉት። አንገቱን እያቅለሰለሰ፣ ‹‹እሺ…›› አላቸው። ‹‹ተባረክ እሺታ ይልመድብህ፣ ‹እሺ ይበልጣል ከሺሕ› ብለህ ደግሞ አንድ ጥቅስ እዚያ ጋ ለጥፍ…›› አሉት እየሳቁ። እኛም ፈገግ አልን። ‹‹አባት እውነትዎን እኮ ነው። ሥራ የሚሠራው በመግባባት ነው። መሆን የማይገባንን ሁሉ እንድንሆን የሚያደርገን እኮ አለመግባባት ነው…›› ካለ በኋላ፣ ‹‹በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን አልቀው፣ በርካታ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው፣ የምስኪን አገራችን ሀብት ወድሞና ኢኮኖሚያችን ወድቆ እኛም ለባሰ ድህነት የተዳረግነው በቀላሉ መግባባት አቅቶን ተንደርድረን ጦር በመምዘዛችን አይደል?›› ብሎ ሲጠይቅ፣ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ዓይነት እንጉርጉሮ ነው የሰለቸኝ…›› አለው አንድ ጎልማሳ በተሰላቸ ድምፅ። አንዳንዱ የአንጀቱን ሲያወራ የአንዳንዱ ደግሞ መሰላቸት ግርም ይላል። በመሰልቸት የተናገረውን ቀና ብለን አየነው። ሁኔታችንን ተረዳ መሰል፣ ‹‹እኔም እኮ ከአንጀቴ ነው የመለስኩት፣ በፈጠራችሁ አምላክ ተለመኑ ሲባሉ አይደል እንዴት ጎራዴ መዘው ያንን ሁሉ ፍጅት ያመጡብን ዛሬ ደርሰው የሰላም ሰባኪ የሆኑት?›› እያለ አስተያየቱ ከምር እንደሆነ አስረግጦ አብራራ። የአንዳንዱ ሰው አነጋገር ካልተብራራ ትርጉሙ ከባድ ነው። በትርጉም ስህተት ስንት ሰው ጠፍቶ ይሆን፡፡ ጉዞው አልቆ ወደ ጉዳያችን ስንበታተን የሰላም ትርጉሙ ከብዶን ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት