Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዲጂታል ክፍያ የተጀመረው የነዳጅ ግብይት የፈጠረው መጨናነቅ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የነዳጅ ግብይት እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ተግበራዊ መደረግ ከጀመረ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል። በአዲስ አበባ የተጀመረው የዲጂታል ክፍያ ዘዴ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ባሉ የነዳጅ ማደያዎች የሚተገበር መሆኑንም መንግሥት ይፋ አድርጓል።

የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ከነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት እንዲፈጸም የተወሰነው ግብይቱን ዘመናዊ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ከነዳጅ ግብይት ጋር በተያያዘ ያሉ ሕገወጥ ተግባራትን ለመከላከል እንደሆነ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ቦሪአ ሐሰን ገልጸዋል።

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ፕሮግራም በዲጂታል የክፍያ ዘዴ አንዲፈጸም መደረጉ ትምህርት የተገኘበት ከመሆኑም በላይ፣ በአጭር ጊዜ በመላ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ዘዴ እንዲፈጸም ማድረግ የሚችል መሆኑን ያረጋገጠላቸው ስለመሆኑ ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በዚህ ክንውን የወሰድናቸው የዕርምት ዕርምጃዎችና የተገኙ ልምዶች ውጤት፣ አጠቃላይ አገር ውስጥ ያለውን የነዳጅ ትራንዛክሽን በዲጂታል ሲስተም መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ተግባራዊ መደረግ የተጀመረው በዲጂታል የነዳጅ ግብይት የፈጠረው የተሽከርካሪዎች ሠልፍ አሁንም እንደቀጠለና ማደያዎችን እንዳጨናነቀ ነው።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር አመራር የሆኑ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አሁን የተፈጠረው መጨናነቅ ዋና ምክንያት የዲጂታል አገልግሎቱን በተመለከተ ሥራው ከመጀመሩ በፊት በቂ የግንዛቤ ሥራ አለመሠራቱ ነው ይላሉ፡፡

‹‹ይህንን ሥጋት ቀደም ብለን አቅርበን ነበር፤›› ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ አገልግሎቱ ክረምት ላይ ቢጀምር ኖሮ አሁን ያለው መጨናነቅ ይታይ እንዳልነበረ ይጠቁማሉ፡፡

የክረምት ወቅት የነዳጅ ፍላጎት የሚቀንስ በመሆኑ በቀላሉ አገልግሎቱን ማላመድ ይቻል እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን የነዳጅ ፍላጎት የሚጨምርበት ወቅት በመሆኑ በማደያዎች መጨናነቅ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

መጨናቁን ያዩ አሽከርካሪዎች ታንከራቸውን ሙሉ በማድረግ እየቀዱ በሄዱ ቁጥር በቀን ለሽያጭ ይበቃል ከተባለው የነዳጅ መጠን በላይ ስለሚወስዱ ችግሩን ያባብሰዋል የሚል ምልከታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ በአዲስ አበባ በቀን 1.6 ሚሊዮን ሌትር ነዳጅ የሚሠራጭ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ኤፍሬም፣ አሁን እየታየ ያለው የነዳጅ አቀዳድ ግን ከታሰበው በላይ ነዳጅ ስለሚቀዳ እጥረት ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ይህንን ክፍተትም በቂ ነዳጅ በማቅረብ መወጣት እንደሚገባም ያስረዳሉ፡፡

በዘርፉ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ሰርካለም ገብረ ክርስቶስም (ዶ/ር)፤ ሰዎች ነገ ነዳጅ ላናገኝ እንችላለን በሚል ዕሳቤ ታንከራቸውን በሚሞሉበት ጊዜ ለነዳጅ እጥረት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የዲጂታል ክፍያ ዘዴውን በደንብ ለማላመድ ቀድሞ ተገቢ ሥራ አለመሠራቱ አንድ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን በየማደያዎች የሚፈጠሩ መጨናነቆች በሚያጋጥሙበት ወቅት እንደ መፍትሔ ሊወሰዱ የሚገባቸው የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይቻል እንደነበርም አመልክተዋል፡፡ 

አሁንም ሠልፎች የሚታዩ በመሆኑ ነዳጅ ለመቅዳት ረዣዥም ሠልፎች እንዳይኖሩ ሊወሰዱ ከሚገባቸው ዕርምጃዎች መካከል አንዱ ለተሽከርካሪዎች ፕሮግራም በማውጣት በፕሮግራሞቹ መሠረት እንዲስተናገዱ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ አንደኛው ቀን ሙሉ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ፣ በሌላው ቀን ደግሞ ጎዶሎ ቁጥር ያላቸውን ተሽከርካሪዎች እንዲስተናገዱ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወይም የግል ተሽከርካሪዎችን ለብቻ የንግድ ተሽከርካሪዎችና ታክሲዎችን ለብቻ በማድረግ በፕሮግራም መሥራት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በሌላ ወቅትም መጨናነቆች ሲፈጠሩ ሊያገለግል እንደሚችል ያምናሉ።

በሌሎች አገራት 150 ሊትር በደቂቃ የሚስቡ ማሽኖችን እንደሚጠቀሙ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጉኙ አብዛኞቹ ማደያዎች በሊትር በደቂቃ የሚስቡት የነዳጅ መጠን አነስተኛ መሆኑ ሌላው ለመጨናነቁ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ቀጣይነት 

በዲጂታል የክፍያ ዘዴ የተጀመረው የነዳጅ ግብይት አሁን ከገጠሙት መጠነኛ ችግሮች ባለፈ ቀጣይነቱንና አስተማማኝነቱ ማረጋገጥ ከተቻለ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎችና ተዋናዮች ይገልጻሉ።

ሰርካለም ገብረ ክርስቶስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚታይበትን ይህን ዘርፍ ለማዘመን የተደረገው ጥረት በመልካም የሚታይ ቢሆንም፣ አሁን በማደያዎች አካባቢ የሚታየው መጨናቅ ግን ነገም ቀጣይ እንዳይሆን ክትትል ያሻዋል፡፡ 

በክልሎችም ይተግበር ሲባል አዲስ አበባ ላይ የታየው ችግር እንዳይደገም ማድረግም ይገባል ያሉት ሰርካለም (ዶ/ር) የዲጂታል የግብይት ሥርዓቱ እንደተባለው ችግር መስተጓጎል ቢገጥመው በአማራጭነት ሊቀርብ የሚችል አሠራር እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡ 

የኔትዎርክ ችግር ተፈጥሮ የዲጂታል ግብይቱን ማካሄድ ካልተቻለ ምንድነው የሚደረገው? የሚል ጥያቄ የሚያነሱት ሠርካለም (ዶ/ር)፣ አጠቃላይ አሠራሩ አማራጮች እንዲኖሩት ካልተደረገ የጠቀሜታውን ያህል ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር ግን የዲጂታል ክፍያ ዘዴው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገባው ነዳጅ ለታለመለት ተግባር መዋሉን መቆጣጠር የሚያስችል የግብይት ሥርዓት በመፍጠር፣ ‹‹ማን፣ መቼ፣ የት ማደያ ላይ ቀዳ›› የሚለውን ለመቆጣጠር ዕድል ይሰጣል ይላሉ፡፡ ይህ ግን የሚሆነው ሥራው በዕቅድና በሥርዓት ሲመራ ብቻ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ትልቁ ሥጋታቸው ግን ለዲጂታል ክፍያው ውጤታማነት ጠቃሚ የሆኑት የኔትዎርክና መሰል ችግሮች ሲፈጠሩ በአማራጭ የሚተገበረው የክፍያ መንገድ አለመታወቁ ነው። 

ከዚህ ውጪ ግን እያንዳንዱ የነዳጅ ግብይት በሕጋዊ መንገድ በተለይም የዲጂታል የክፍያ ዘዴዎችን በመጠቀም ግብይቱን ማካሄድ ሕገወጥ አሠራሮችንም ለመቆጣጠር የሚረዳ መሆኑን ሠርካለም (ዶ/ር) ያምናሉ፡፡ የነዳጅ ሥርጭቱንና አጠቃላይ የግብይት ሰንሰለቱን ጠብቆ ስለመገበያየቱ ይህ አሠራር የራሱ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለውም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ 

ለዲጂታል የግብይት ሥርዓቱ ጠቀሜታ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የኖክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን በበኩላቸው፣ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ዘዴ መተግበሩ ለነዳጅ ኩባንያዎችም ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይ ጥሬ ገንዘብን ከማዘዋወር ይልቅ በዚህ የክፍያ ዘዴ ኩባንያዎቹ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል መስጠቱ ትልቅ ዕርምጃ አድርገው እንደሚወስዱት አመልክተዋል፡፡ 

‹‹ይህ አሠራር ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አብዛኛውን ገንዘብ ሰብስበን ወደ ባንክ የምናስገባ እኛ በመሆናችን ይህ አሠራር በእጅጉ ይጠቅመናል ብለዋል፡፡

ከየነዳጅ ማደያው ጥሬ ገንዘብ ሰብስበን ወደ ባንክ ከማምጣት በቀጥታ በዲታጂል የገንዘብ ማዘዋወሪያ ከማደያዎች ወደ ባንክ ገብቶ ለሚፈለገው ሥራ ማዋላቸውን ፈጣን የሥራ እንቅስቃሴ እንደሚፈጥርላቸው አስረድተዋል፡፡

ሕጋዊ አሠራርን ከማሳለጥም አንፃር የዲጂታል የክፍያ አገልግሎት ጠቀሜታ እንዳላቸው የሚያምኑት አቶ ታደሰ፣ ‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ ማንኛውንም የገንዘብ እንቅስቃሴ ከጥሬ ገንዘብ ውጪ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ከሆነ በባንክ በኩል የሚተላለፍ በመሆኑ ለቁጥጥር ያመቻል፤›› ብለዋል፡፡ 

የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ከተጀመረ ወዲህ አብዛኛው ተጠቃሚ ወደ ሲስተሙ እየገቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እየቻልን ነው ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ ከ99 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮችም የዲጂታል ክፍያን በመጠቀም ግብይቱን የፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

አሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች የነዳጅን በዲጂታል የክፍያ ዘዴ ለማገበያየት ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ሥራ እየሠሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች