Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በብዙ ችግሮች የተጠለፈው የማር ምርት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በማር ምርት አቅም ካላቸው የዓለም አገሮች ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምትገኝ መረጃዎች ያስረዳሉ። ከዓለም አገሮች በተጨማሪ በአኅጉረ አፍሪካ ደግሞ የመጀመርያዋ እንደሆነች ይነገራል።

ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ ባላት የንብ ኮሎኒ ብዛት ነው። በአንድ የንብ ኮሎኒ (መንጋ) ሥር አንድ ነጠላ ንግሥት ንብ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድ ድንጉላዎቸና ከ20,000 እስከ 80,000 ሴት ሠራተኛ ንቦችን ያቀፈ ነው። በኢትዮጵያ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የንብ ኮሎኒ (መንጋዎች) ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ በዚህ መረጃ ላይ ተመሥርቶም ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ550 ሺሕ ቶን በላይ ማር የማምረት ዕምቅ ሀብት እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የማምረት አቅም እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ፣ አሁን ላይ በዓመት 29 በመቶውን ብቻ እያመረተች ለገበያ ታቀርባለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ለውጭ አገር ገበያ የሚቀርበው ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የማር ሀብት በሙሉ አቅሟ ተጠቅማ በማምረት ለውጭ ገበያ ብታቀርብ ለአገሪቱ ጥሩ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማመንጨት የሚችል ዘርፍ እንደሚሆንላት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ 

ግራን ፌስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለውጭ ገበያ የሚልክ ድርጅት ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርተውን ‹‹ማርዳን›› የተሰኘ የማር ምርት ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ለማስተዋወቅ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ዘርፉ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ ስለ አገሪቱ የማር ሀብት በሰጡት መረጃ፣ አለ ተብሎ ከሚገመተው ሰባት ሚሊዮን የንብ ኮሎኒ ውስጥ 90 በመቶው በባህላዊ ቀፎ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በባህላዊ ቀፎ ከመኖራቸው በተጨማሪ በጫካና ዕፀዋት በበዙበት አካባቢዎች የሚገኙ በመሆናቸው፣ ይህንን ሀብት ለአገር ዕድገት ሳይውል መቅረቱን በቁጭት ያስረዳሉ፡፡

ዘርፉን በአግባቡ ለማልማት መንግሥት ‹‹ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፤›› ከተወጠነበት ጊዜ ጀምሮ በልዩ ትኩረትና ውሳኔ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ቢሆንም፣ ላለፉት ዓመታት በተከሰቱ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ሳቢያ ዕቅዱ በተፈለገው ልክ አለመጓዙን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ‹‹የሌማት ትሩፋት›› በሚል የማርን ሀብት በልዩ ትኩረት በአገር አቀፍ ደረጃ ለማልማት አዲስ ውጥን ተይዞ ወደ ትግበራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

በአጭር ጊዜያት በየዓመቱ የማር ምርትን ለማሳደግ መታቀዱን፣ ቢያንስ በአንድ መንደር 20 ንብ አናቢዎችን ለማደራጀት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህም የዕቅድ አተገባበርን በማዘመን በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ 300 ሚሊዮን ቶን ማር በማምረት ለአገርና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ውጥን መያዙን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ፣ አሁን ላይ የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው ማር የማምረት አቅም አንፃር ከግማሽ በታች የሚሆነው ብቻ በትክክል ተመርቶ ለገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ ከተጠቀሰው አኃዝ መረዳት ይቻላል፡፡

በሚቀጥለው ሦስት ዓመታት አሁን ካለው 129 ሺሕ ቶን የማምረት አቅም ወደ ሦስት መቶ ሺሕ ቶን ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ ያሉ ችግሮች በዝርዝር የተናገሩት አቶ ታሪኩ፣ መጀመርያ ከፍተኛ የጥራት ችግር መኖሩን አንስተዋል፡፡ የአገር ውስጥ የማር ምርትን ከተለያዩ ባዕድ ነገሮች መቀላቀል ከመስፋፋቱ ባለፈ የገበያውን ታማኝነት እያሳጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በግብዓት አቅርቦት በኩል ያለውን ችግር ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ምርቱን ለማሸግና ለማጣራት የሚውሉ ቁሶች ከውጭ አገሮች እንደሚገቡና ይህም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች አነስተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

ይህንን የግብዓት ችግር ለመቅረፍ ግብርና ሚኒስቴር ከ500 በላይ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ ከውጭ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

በሦስተኛነት ያነሱት የገበያ ትስስርን የሚመለከት ችግር ሲሆን፣ ለዚህ መፍትሔ ለመስጠት ‹‹አዋጅና መመርያ›› እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ረቂቁ በተገቢውና በሚመለከተው ባለድርሻ አካል እየታየ መሆኑን፣ ሲጠናቀቅ እንደ ቡናና እንደ ሌሎች ምርቶች ለማር ምርት ግብይትም ሕጋዊ ሥርዓት የሚያበጅ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ሕጎቹን የማርቀቅ ሒደት ተጠናቆ አሁን ላይ ለፍትሕ ሚኒስቴር እንደተላከ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በቅርቡ ረቂቁ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ በቋሚ ኮሚቴ ከታየ በኋላ ሊፅድቅ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡  

በግብርና ሚኒስቴር የንብና ሃር ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ አዝዝ አያሌው በበኩላቸው፣ የማር ሀብትን ለማዘመንና ኢትዮጵያ በዘርፉ የውጭ ምንዛሪ እንድታገን ከብዙ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለማር ምርት ተስማሚ የሆነ አግሮ ኢኮሎጂ፣ ማለትም ለማር ምርት ምቹ የሆኑ ብዛት ያላቸው ዕፀዋቶች ያሉት አገር በመሆኗ፣ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ማር የተፈጥሮ ጥራትን የያዘ በመሆኑ ተፈላጊ ነው ብለዋል። ነገር ግን ይህንን በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። በአገር ደረጃ ያለው ዕምቅ ሀብት ትኩረት ሰጥቶ ማልማት ከተቻለ ከ500 ሺሕ ቶን በላይ ማርና ከ50 ሺሕ በላይ ሰም ማምረት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው አቅም ውስጥ 29 በመቶ ማርና 23 በመቶ ሰም ብቻ ተመርቶ ለገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህም በዘርፉ በርካታ ውስብስብ ጉድለቶች መኖራቸውን እንደሚያሳይ የተናገሩት ኃላፊው፣ በዘርፉ የተሰማራ ባለሀብት አለመኖር በቀዳሚነት የጠቀሱት ችግር ነው።

በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ጠንካራ ማኅበር አለመመሥረታቸው ሌላው ችግር እንደሆነ ጠቅሰው፣ በዘርፉ የሚደረጉ ምርምሮች አናሳ መሆንም ሌላኛው ክፍተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር ከተያዙ ዘርፈ ብዙ ዕቅዶች አንዱ የማር ምርትን ማሳደግ ሲሆን፣ በአሥር ዓመቱ የኢኮኖሚ መርሐ ግብር ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ አንዱ የማር ምርትን በማዘመን ምርቱን ማሳደግ አንደኛው መሆኑን አቶ አዝዝ ገልጸዋል። በቅርቡ የተጀመረው ‹‹የሌማት ትሩፋት›› መርሐ ግብር በማር ምርት ሰፊ ሥራ በመሥራት ለውጥ ለማምጣት እየተሠራበት የሚገኝ ሌላኛው አገራዊ ፕሮግራም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ‹‹የማር›› ምርት ልክ እንደ ቡናና ሌሎች ምርቶች ራሱን የቻለ አዋጅና መመርያ እየተዘጋጀለት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አዝዝ ገለጻ፣ የማር ምርት ላይ ትኩረት በማድረግ ንቦችን በማዳቀል ምርቱን ለማሳደግ ከተሠራ፣ በተዘዋዋሪ ውጤቱ የቅባት እህል የምርት መጠን እንደሚጨምር ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ የቡና ምርት የሚገኝበት አካባቢ የማር ምርትን (ንብ በማርባት) ብቻ የቡና ምርትን በ25 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ እንደሚቻል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የጥራትን ችግር አበክረው ያነሱት አቶ አዝዝ፣ በተለይም ዘርፉ ገበያ ላይ ንፁህ ምርት ማግኘት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ ማር የጥራት ችግር እንዳለበት በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በተለይም ለአገር ውስጥ ገበያ አንዳንድ ጊዜም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የጥራት ችግር እንዳለባቸው ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡

ይህን ችግር አንዳንድ ግለሰቦች የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደግ ሲሉ ከተለያዩ ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል የሚቀርቡ መኖራቸውን ጠቁመው፣ በዚህም ሳቢያ ለውጭ ገበያ በተለይ ባዕድ ነገሮች የተቀላቀለበት የማር ምርት ተመላሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሰፊው የማምረት ችግር (ክፍተት) እንደ አገር መኖሩን ገልጸው፣ የአገር ውስጥ ገበያም ጭምር ከባዕድ ጋር የተቀላቀለ ማር መሸጥ የተለመደ ሆኗል አስታወሰዋል፡፡

በጥራት ምክንያት ከውጭ የተመለሱ ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ እንደሚሸጥና፣ ይህም ተግባር አፀያፊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ ያለውን ችግሮች ለመፍታት የንብ አናቢዎች ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በመተባበር ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል፡፡

የማር ምርትን ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ግራፍ ፌስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በአገር ውስጥ ማቅረብ ጀምሯል፡፡ በአገር ውስጥ ያለውን ንፁህ የተፈጥሮ ማር ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ‹‹ማርደን›› በሚል ስያሜ ከሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል፡፡

በግራን ፌስ ከተመሠረተበት ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ምርቶቹን በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በአሜሪካ ሲልክ መቆየቱን የግራን ፌስ ትወንደንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጆን ግርማ ተናግረዋል፡፡

ከደቡብ ምዕራብ ክልል ምርቱ እንደ ሚሰበሰብ የገለጹት አቶ ጆን፣ ከአናቢዎች ጀምሮ ድርጅቱ ስለሚሰባሰብ የጥራት ችግር አይኖርበትም ብለዋል፡፡ በዋናነት በማር ምርት ላይ የሚነሳው የጥራትና የምርት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከአርሶ አደሮችና ንብ አናቢዎች ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች