- ክቡር ሚኒስትር ምንድነው ነገሩ?
- ምኑ?
- ምዕራብን እንጎበኛለን አይደል እንዴ የተባለው?
- አዎ ደርሰናል፣ ለማረፍ እየተቃረብን ነው።
- ይኼ ባለፈው የመጣንበት አካባቢ አይደል እንዴ?
- አዎ፣ ልክ ነዎት።
- እኔ እኮ ወደ ምዕራብ መስሎኝ ነው ተጣድፌ የመጣሁት።
- የትኛው ምዕራብ?
- የእኛ ምዕራብ።
- አይቀልዱ እንጂ ክቡር ፕሬዚዳንት?
- እንዴት?
- አገሪቱ እኮ ወደ ላይ አይደለም የቆመችው?
- ምን ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የእናንተ አካባቢ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱም አላት ማለቴ ነው።
- ምን?
- ምዕራብ!
- ቢሆንም ሪዞርት ልንመርቅ ነው ተብዬ ብጠራ ይሻል ነበር።
- ለማንኛውም ደርሰናል፣ እየወረዱ።
- ይቅደሙ ክቡር ሚኒስትር፣ የእርስዎ ፕሮጀክት አይደል ይቅደሙ።
- እሺ… እንዴት አገኙት ታዲያ?
- እኔማ ያኔ የሰላሙን ሁኔታ ለመገምገም ስመጣ ያለቀ ነበር የመሰለኝ።
- ከዚያ በኋላ ብዙ ነገሮች ተሠርተዋል፣ ለምሳሌ እዚያ ጋ ያለውን ይመልከቱ… ያኔ አልነበረም።
- አዎ፣ በጣም አረንጓዴ ሆኗል።
- አረንጓዴ መሆኑን ብቻ ነው ያስተዋሉት?
- እሱማ ማለቅ የነበረባቸው ነገሮችም አልቀዋል… በተጨማሪም
- እ…
- በተጨማሪ ምን?
- መከርከም የነበረባቸውም ተከርክመዋል፡፡
- አሁን አንድ ነገር ብቻ ነው የሚቀረን።
- ምንድነው እሱ?
- ማን ያስተዳድረው የሚለውን ገና አልወሰንም።
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አስተዳደሩን ለማን እንስጥ የሚለውን ገና እየተወያየንበት ነው።
- ማን ያስተዳድረው የሚለውማ ተወስኗል፣ በግልጽ ተቀምጧል እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- ማነው የወሰነው? ምኑ ላይ?
- ስምምነቱ ላይ፡፡
- ስለምንድነው እርስዎ የሚያወሩት? አሁንም እዚያው ነዎት እንዴ?
- የት?
- ለማንኛውም ወደ እዚህኛው ቢመለሱ ይሻላል፡፡
- ወደ እዚህኛው ምን?
- ምዕራብ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ስለተከሰሱ ሰዎች የሚተላለፈውን ዜና በተመስጦ እየተከታተሉ አገኟቸው]
- ምንድነው እንዲህ ተመስጠሽ የምታደምጪው?
- ሰበር ዜና ነው።
- ስለምንድነው?
- በሽብርተኝነትና የክልሉን መንግሥት በኃይል ለመጣል ተጠረጥረው ስለተያዙና ስለሚፈለጉ ሰዎች ነው።
- እ… ስለእሱ ነው።
- አዎ፣ ታውቅ ነበር እንዴ?
- እንኳን እኔ እነሱ ራሳቸው የሚያውቁ አይመስለኝም።
- ይደንቃል፡፡
- በአሸባሪነት መጠርጠር የለባቸውም ብለሽ ልትሟገቺ ነው?
- እኔ ምኑን አውቄ እሟገታለሁ?
- ታዲያ ምንድነው ያስደነቀሽ?
- ገና ሲጀመር አዲስ አበባ አካባቢ ያሉ ሰዎች ነበሩ በሽብርተኝነት የተከሰሱት።
- እሺ?
- ከዚያ ወደ ሰሜን ሄደ።
- ወደ ሰሜን ማለት?
- የመጀመሪያው ከሳሽ የነበሩት ራሳቸው ሽብርተኛ ተብለው አልነበር?
- አዎ፣ ለካ እነሱም አልቀረላቸውም።
- አሁን ደግሞ ሌላኛው ሰሜን ተረኛ ይመስላል።
- ካልሽማ ወደ ምዕራብም ዘልቆ ነበር።
- ይህ እኮ ነው ድንቅ የሚለኝ።
- ምኑ?
- የሚንሸራሸረው፣ ማለቴ የሚሽከረከረው ነገር?
- ምኑ?
- የሽብርተኝነት ክሱ ነዋ?
- እንዴት?
- እንደምን ልበልህ፣ አዎ… እንደ እንትን… ስሙ ምን ነበር?
- እንደምን?
- የብሔር ብሔረሰቦች ዋንጫ፡፡
- ኪኪኪ… ወደው አይስቁ አሉ፣ ታሾፊያለሽ አይደል?
- እያሾፍኩ አይደለም።
- ታዲያ ምን እያደረግሽ ነው?
- ከምሬ ነው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እዚህ አገር የሚሽከረከሩ ነገሮች እየበዙ እያየሁ እገረማለሁ።
- ሌላ ምን ተሽከረከረ ልትይ ነው ደግሞ?
- አንዱ እንዳልኩህ ዋንጫው ነው።
- እሺ ሁለተኛ የሽብርተኝነት ክስ ያልሽው መሆኑ ነው?
- አዎ፣ ሌላው ደግሞ ግጭትና የጦር መሣሪያ ነው።
- እሺ ሌላውስ?
- ሌላው ደግሞ ኮማንድ ፖስት ነው።
- ኪኪኪኪ… እሺ ሌላ የሚደንቅሽ ነገር የለም?
- የሚደንቅ ነገር አይጠፋም።
- ለምሳሌ ምን?
- ሽብርተኛ የተባሉት ሰዎች በመጨረሻ ላይ የሚሆኑት ነገር።
- ምን ይሆናሉ?
- የካቢኔ አባል!