Sunday, June 23, 2024

የፍረጃ ፖለቲካ በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫ በብዙ መንገዶች የኢትዮጵያን ፖለቲካ የቀየረ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑ ይነገራል፡፡ በአንፃራዊነት በኢትዮጵያ ታሪክ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ ነፃነት የተሞላበት ፉክክር ማስተናገዱ የሚነገርለት የምርጫ ሒደት፣ በስተመጨረሻ ግን የፖለቲካ ውዝግብ ምንጭ ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡ በምርጫው ውጤት ገዥው ኢሕአዴግና ዋነኛው የወቅቱ ተፎካካሪ ድርጅት ቅንጅት ባለመስማማታቸው ግጭትና ተቃውሞ ተበራከተ፡፡ በሒደቱ ደግሞ ቅንጅት ያገኛቸውን የፓርላማ ወንበሮችና የአዲስ አበባ አስተዳደር ሥልጣንን አለመረከቡ ጉዳይ ሌላ ውዝግብ ይዞ መጣ፡፡

በጥቅምት 1998 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንድ ዕቅድ ይዘው ቀረቡ፡፡ ወደ ፓርላማ አንገባም ያሉ የቅንጅት መሪዎችን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉ ከሰሱ፡፡ ቅንጅቶች ከዚህ ባለፈም የአገር ክህደት ወንጀል ስለመፈጸማቸው ክስ ቀረበባቸው፡፡ በአመፅና ብጥብጥ ሥርዓተ መንግሥቱን ለመቀየር እየተንቀሳቀሱ ሐረግ፣ ፓርላማው የቅንጅት ተመራጮችን ያለመከሰስ መብት ያንሳ ሲሉ አቶ መለስ ፓርላማውን ጠየቁ፡፡

በወቅቱ በፓርላማው ከነበሩ አንጋፋ የምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የማይረሳ ምክረ ሐሳብ ሲሰጡ ተሰሙ፡፡ ጉዳዩ በአገር ወግና ልማድ በዕርቅና ሽምግልና ቢፈታ ይሻላል በማለት አቶ ቡልቻ ፖለቲከኞቹ በሰከነ መንገድ ጉዳዩን እንዲይዙት ጠየቁ፡፡ አቶ መለስ ግን ‹የአቶ ቡልቻን ሥጋት እጋራለሁ› ከማለት በዘለለ ያቀረቡትን ዕቅድ የሚሰርዙ አልሆኑም፡፡

የቅንጅቶች ያለመከሰስ መብት በተነሳ በማግሥቱ የቅንጅት አመራሮች በመላ አገሪቱ መታደን ጀመሩ፡፡ በተከታታይ በተወሰደው ዕርምጃ ኢትዮጵያ ከ50 ሺሕ ያላነሱ ሰዎችን ወደ እስር ቤት በመላክ በወቅቱ የዓለማችን አንዷ አፋኝ አገር ተባለች፡፡ ‹‹የጥቅምት 23 የአዲስ አበባ ጭፍጨፋ›› እየተባለ በሚጠራው ክስተት ደግሞ በአዲስ አበባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገደሉ፡፡ ይህ የምርጫ ማግሥት የመንግሥት ተከታታይ ዕርምጃም በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ዓይነት የፍረጃ ፖለቲካ ልምምድን ይዞ የመጣም ነበር፡፡

ከዚያ ወዲህም ቢሆን ሕገ መንግሥቱን በኃይል መናድ፣ ብጥብጥና አመፅ፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማፍረስ፣ ወዘተ የሚሉ የፖለቲካ ክሶችና ፍረጃዎች በኢትዮጵያ ሲሠራባቸው መኖሩ ተደጋገሞ ይወሳል፡፡

መንግሥቱ በሆደ ሰፊነት በዕርቅና በሰላም ጉዳዩን ይፍታ በሚል በ1998 ዓ.ም. በአንጋፋ ፖለቲከኞች የቀረበው ምክር በስተመጨረሻ በውጭ አጋሮች ጫና ቅቡልነት አገኘ፡፡ በዕርቅና በይቅርታ እየተባለ የታሰሩ የቅንጅት አመራሮች በስተኋላ ሲፈቱ ታየ፡፡ ይሁን እንጂ በፖለቲካ ልዩነት መዘዝ እርስ በርስ መፈራረጁና መሳደዱ እስከ ዛሬም ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አለመፅዳቱ በብዙ ታዛቢዎች ተደጋግሞ ይነገራል፡፡

በ2001 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ታሪክ አፋኝ ሕጎች (Draconian Laws) እየተባሉ የሚጠሩት ሦስቱ ማለትም የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የሚዲያ አዋጅ፣ እንዲሁም የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማኅበራት አዋጅ መውጣታቸው የኢትዮጵያን በፍረጃ የተሞላ ፖለቲካ የበለጠ እንዳወሳሰበው ነው የሚነገረው፡፡ ሕግን ለፖለቲካ ማጥቂያነት የማዋል ዕርምጃ በ1993 ዓ.ም. በሕወሓት መከፋፈል ማግሥት ከወጣው የፀረ ሙስና አዋጅ ጀምሮ የነበረ ነው ቢባልም፣ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የበለጠ መጠናከሩን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ ሕግን ተገን በማድረግ የሚቃወሙና የሐሳብ ልዩነትን የሚያራምዱ ኃይሎችን በስፋት ማሳደድ እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን ተፈጽመዋል ለሚባሉ በርካታ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች እንደ የፀረ ሽብር አዋጅ ያሉ አፋኝ ሕጎች በምንጭነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን መሰል አዋጆች የተለየ ፖለቲካ ማራመድ፣ መቃወምና መደራጀትን ወንጀል አድርገዋል በሚልም ይተቻሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ነፃነቱን ተገፎና በፍርኃት ተሸብቦ እንዲኖር ካስገደዱ ምክንያቶች መካከል የፀረ ሽብርና ተመሳሳይ አዋጆች በቀዳሚነት ሲጠቀሱ ኖረዋል፡፡

የሕዝቡ የፖለቲካ ነፃነት ጥያቄ ገፍቶ ከባድ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመስፋፋቱ ነበር፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ ከአምስት ዓመት በፊት የመጣው፡፡ ለውጡን ተከትሎ ለፖለቲካ ማጥቂያነት የሚውሉ የአገሪቱ አፋኝ ሕጎችና አዋጆች ይወገዳሉ የሚለው ተስፋ ጉልህ ነበር፡፡ የፍረጃ ፖለቲካ ጨርሶ ይወገዳል የሚለውም ምኞት ትልቅ ነበር፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ወቅት ከነበራቸው የፓርላማ ውሎዎች በአንዱ፣ ከምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የለውጡ አስተዳደር በወቅቱ ይከተል የነበረውን አቋም በጉልህ የሚያሳይ መሆኑ ይነገራል፡፡

‹የፀረ ሽብር ሕጉን ጨምሮ መንግሥት ፓርላማው ያወጣቸውን ሕጎች ይጥሳል› ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ አስገራሚና የማይረሳ ነበር፡፡

‹‹መጀመሪያ ሽብር ምንድነው? ሽብር ማለት ምን ማለት ነው? አሸባሪስ ማን ነው? ያተረፍነውስ ምንድነው? ሁሉን ነገር ሰፋ አድርጎ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ሽብር ሥልጣን ላይ ለመቆየት ኢሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ኃይል መጠቀምን ይጨምራል፡፡ ማንም ይሁን ማን ሕገ መንግሥትን ማክበር አለበት የሚል ዕሳቤ መያዝን ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ሲሆን ደግሞ፣ በተሃድሶ ወቅት እንደታየው ለዚህ ጉዳይ መዛነፍ ኃላፊነት መውሰድ ያለብን እኛ ነን ብለን መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ የደኅንነት ተቋማት መከላከያውን ጨምሮ የፓርቲ ገለልተኝነትን የተላበሱ መሆን እንዳለባቸው ያስገድዳል፡፡ በዚህ መንገድ ካላደራጀናቸው ኢሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ፈጥረናል ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰረ ሰው ግረፉ ወይም ጨለማ ቤት አስቀምጡ ይላል እንዴ? አይደለም መግረፍ፣ ጨለማ ቤት ማስቀመጥም ሆነ አካል ማጉደል የእኛ የአሸባሪነት ተግባር ነው፡፡ የየወረዳው ፖሊስ ሲገርፍ እንደነበር በሰብዓዊ መብቶች ጥናት ተረጋግጧል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢሕአዴግ በይፋ አምኖ አጥፍቻለሁ፣ በድያለሁ ብሎ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ነገርዬው ጥፋት ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ መልካምና ይቅር ባይ ሕዝብ የሰጠንን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል፤›› በማለት ነበር ዓብይ (ዶ/ር) ለዚያ ጥያቄ ሰፊ ማብራሪያ በወቅቱ የሰጡት፡፡

በለውጡ ወቅት በኢሕአዴግ አስተዳደር ዘመን የፀረ ሽብር ሕጉን ጨምሮ፣ አንዳንድ አዋጆች ለአፈናና ለፖለቲካ ፍረጃ ሲውሉ ቆይተዋል የሚለው ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ መግባባትን የፈጠረ ሐሳብ ሆኖ ነበር የቆየው፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) የመሩት የለውጥ አስተዳደር የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ለመቀየር እንቅስቃሴ ከጀመረባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ የፀረ ሽብር ሕጉና ሌሎች አፋኝ አዋጆችን የማሻሻል ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ እንደቆየም አይዘነጋም፡፡

በጊዜው በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት የሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉባዔ ሥር፣ የሕግ ማሻሻያ የባለሙያዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ በርካታ አዋጆችን የማሻሻል ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው አይረሳም፡፡

ከነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት በመላ አገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ፣ በሚሻሻሉ ሕጎችና አዋጆች ዙሪያ ተከታታይ ሕዝባዊ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውም አይዘነጋም፡፡

በጊዜው እነዚህን አፋኝ የሚባሉ ሕጎችን የማሻሻል ሥራ ማከናወን ያስፈለገበትን መነሻ ተጠይቀው የነበሩት የወቅቱ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደአም ቢሆኑ፣ ሕጎቹ የዜጎችን ነፃነት የሚገድቡ በመሆናቸው እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹በሳይንስና በመርህ ላይ የተመሠረቱ ሕጎችን ለማውጣት እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ታዬ በዩኒቨርሲቲ ሳሉ ከኦነግ ጋር በማበር በሽብር አዋጅ መከሰሳቸውን አስታውሰው፣ ‹‹የእኔም ችግር ከዚያ የተለየ አይደለም፣ በሽብር ሕጉና በሌሎች ሕጎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች እውነት እንደነበሩ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፤›› ብለው  ነበር፡፡

የፀረ ሽብር ሕጉ፣ የሚዲያ ሕጉና የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማኅበራት ሕጉ በኢትዮጵያ ለፖለቲካ ፍረጃና ለአፈና ሲውል ነበር የሚለውን አስተያየት፣ የአሁኑ የሰላም ሚኒስትር ደኤታ አቶ ታዬ በወቅቱ ትክክለኛ ሲሉት ተደምጠዋል፡፡ እነዚህን ሕጎችም ቅድሚያ በመስጠት በባለሙያዎች በመታገዝ ከሕዝቡና ከሚመለከታቸው አካላት ግብዓት በመሰብሰብ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ ታዬ፣ ‹‹እነዚህን ሕጎች ማሻሻሉና ሕግ ማውጣቱ ብቻውን ትርጉም ላይኖረው ይችላል፤›› በማለት ከዚህ በላይ ወሳኙ ጉዳይ፣ ‹‹ሕግን ማክበር፣ የሕግ የላይነት መኖር፣ ሕግ አስከባሪውና አስፈጻሚው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መሥራቱ አስፈላጊ ነው፤›› በማለት ነበር ያስቀመጡት፡፡

ከለውጡ በኋላ የተባለው የሕግ ማሻሻያ ሥራ ቢከናወንም ሆነ ሕጎችን ለፖለቲካዊ ዓላማ ማዋል ቆሟል ቢባልም፣ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች የተወሰዱ የሕግ ዕርምጃዎች ጥያቄ ሲያስነሱ ነው የሚሰማው፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በሽብርተኝነት መፈረጁና ከሽብር መዝገብ መልሶ መሰረዙ ሁሉ ተደጋግሞ መከሰቱን አንዳንዶች ይተቻሉ፡፡

በአማራ ክልል ተከስቶ በነበረውና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኰንን (ዶ/ር) ጨምሮ፣ ከፍተኛ አመራሮችን ለሞት ባበቃው ግጭት ወቅት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በሽብር ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተነሳው ሁከት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች የሽብር ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ ታሳሪዎች አንዱ የነበረው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ፣ ‹‹ለሁለተኛ ጊዜ በአሸባሪነት መከሰሴ ለእኔ ትልቅ ኩራት ነው፤›› ብሎ በፍርድ ቤት መናገሩ የዜና ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን ጃዋርን ጨምሮ በሽብር ተወንጅለው በሌሉበት ሲፈረድባቸው የነበሩ ግለሰቦች፣ በለውጡ ማግሥት ወደ አገር ቤት መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በሌሉበት ለሦስት ጊዜ በአሸባሪነት ተከሰው የሞት ፍርደኛ የነበሩት የቀድሞ የግንቦት ሰባት፣ የአሁኑ የኢዜማ መሪ ዛሬ ከሽብር መዝገብ ተፍቀው በትምህርት ሚኒስትርነት እያገለገሉ መሆናቸው የእነዚህን ዓይነት ክሶች ፖለቲካዊ መነሻ እንደ ማሳያ ተደርጎ በመነሳት ላይ ነው፡፡ ከእሳቸው ጋር በሽብር ሲወነጀሉ የቆዩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎች በርካቶች ዛሬ በነፃነት በአገራቸው መኖራቸው፣ ሕግ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት እየዋለ ነው የሚለውን ለማጉላት ይነሳል፡፡

በሌላ በኩል የሕወሓትና የኦነግ ሸኔ በሽብርተኝነት መፈረጅና ከሽብር መዝገብ መልሶ መፋቅ፣ የፖለቲካ ፍረጃ ጉዳይ አወዛጋቢነት በኢትዮጵያ መቀጠሉን ማሳያ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የሕወሓት አመራሮች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጎን መቆማቸው፣ በኢትዮጵያ በሽብር የመፈረጅ ጉዳይ ጊዜ ጠብቆ የሚቀያየር መሆኑን አመላካች እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስና በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ›› ተብሎ ስድስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ፣ የ11 ሰዎች ስም ይፋ መደረጉ ተመሳሳይ ክርክር እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡ የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአማራ ክልል እየወሰድኩ ነው ባለው የፁጥታ ማስከበር ዕርምጃ፣ እንቅፋት የሆኑና የክልሉን መንግሥት ለመጣል ያሴሩ በአሸባሪነት ተግባር የሚንቀሳቀሱ ያላቸውን ሰዎች ስም ይፋ ማድረጉ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የቆየውን በሽብር የመፈረጅ ክርክር ዳግም እንዲነሳ አድርጎታል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ ‹በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ጥቃት በመፈጸም ሁከትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ በማሰብ ሲንቀሳቀሱ ነበር› በሚል የጠረጠራቸውን የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጨምሮ ወደ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መንግሥት  ማዋሉ፣ አሻሚ ዕርምጃ በማለት ብዙዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

መንግሥት በቅርብ ወራት የታጠቁ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን፣ እንዲሁም የልዩ ኃይል አባላትን ትጥቅ ከማስፈታት ዕርምጃዎች ጋር በተያያዘ እየወሰዳቸው ያሉ የሕግ ዕርምጃዎች በተደጋጋሚ ትችት ሲገጥማቸውም ይታያል፡፡

በርካታ ታዛቢዎች እንደሚያስረዱት አሁን ያለው መንግሥት ባለፉት 30 ዓመታት (በኢሕአዴግ አስተዳደር ዘመን) የነበሩ አሻሚ የሕግ ዕርምጃዎች፣ እንዲሁም ሕግን ተገን ያደረጉ የፖለቲካ ፍረጃዎችና አፈናዎች እንዲቀሩ ሕጎችን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ አዎንታዊ ዕርምጃዎች መውሰዱን በጎ ሲሉ ያስቀምጡታል፡፡ እንደ ኦነግ ሸኔና ሕወሓት ካሉ ኃይሎች ጋር በዕርቅ ችግሮችን ለመፍታት የሄደበትን ርቀት ብቻ ሳይሆን፣ ሥልጣን በያዘ ወቅት በጠበመንጃ ሲታገሉ የቆዩና አሸባሪ ተብለው የኖሩ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የወሰደውን ደፋር ዕርምጃም በአድናቆት ያወሳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሽብር ወንጀሎች የሚከሰሱና የሚፈረጁ ሰዎች ቁጥር መብዛቱ፣ እንዲሁም ሕግን ለማስከበር የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አሻሚ መሆናቸው የቀደመው የፖለቲካ ባህል ዳግም እንዳይጠናወተው በርካቶች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -