Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዋጋን በማረጋጋት ረገድ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቢኖሩም፣ በተለይ ዋጋን በማረጋጋት ረገድ የተፅዕኖ ደረጃቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ ቀረበ፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከተቋቋሙባቸው ዓላማዎች አንዱ ገበያን ማረጋጋት ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተደረጉ ግምገማዎች፣ የገበያ ማረጋጋት ጉዳይ ዕውን እንዳልሆነ፣ የግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን በተገመገመበት መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡

ለአብነትም በስምንት ወራት የኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ወቅት፣ በሚያዝያ ወር የሚከበሩ በዓላትን ምክንያት ተደርጎ ሕዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ኮሚሽኑ የቅድሚያ ማረጋጋት ሥራ እንዲያከናውን ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ የዋጋ ንረቱ ግን ከነበረው የተባባሰ እንደነበር የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኮሚሽኑ ከክልሎች፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የጋራ ኮሚቴ አቋቁሞ፣ በተለይ የበዓል ገበያን ለማረጋጋት ሰፊ ሥራ የሠራ ቢሆንም፣ የኮሚሽኑ ሚና ብቻ አጠቃላይ የዋጋ ንረቱን ሊያረጋጋ አልቻለም ብለዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከሌሎች ነጋዴዎች በ25 በመቶ ባነሰ ዋጋ ምርቶችን ማቅረባቸውን፣ ነገር ግን ድርሻቸው በገበያው ውስጥ አነስተኛ መሆኑን፣ በቀጣይ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የመደራደር አቅምና በገበያ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ደረጃ በደረጃ ማስፋት እንደሚያስፈልግ አቶ አብዲ አስረድተዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ኮሚሽነር በመሆን በቅርቡ የተሾሙት ጌታቸው መለሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ 106 ሺሕ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቢኖሩም፣ ማኅበራቱ በሚፈለገው ደረጃ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት በውጭና በአገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ላይ መሥራት የሚገባቸውን ያህል እየሠሩ ስላልሆነ፣ በግብይት ውስጥ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንደ አንድ ተዋናይ እንዲታዩ ይፈለጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቁጥር ብቻ ነው እንጂ የተፅዕኖ ደረጃቸው በጣም ዝቅተኛ ነው የሚለው ታይቷል ያሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ከዚህም በመነሳት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሪፎርም ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹በቁጥር ብቻ የተቀመጡትን የሚጠፉትን እያጠፉ፣ የሚዋሀዱትን እያዋሀዱ የኦዲት አቅማቸው እየጎለበተ ጥቂት ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ ማኅበራት መፍጠር መቻል አለብን በሚል የሪፎርም ሥራዎች ተጀምረዋል፤›› በማለት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የማኅበራቱ ትልቁ ችግር ፈጣን ምላሽ መስጠት አለመቻላቸው እንደሆነና እጥረት ባለ ጊዜ እነሱም ሸማች ሆነው የበለጠ ዋጋውን ከፍ እንዲል ወደ ማድረግ እንጂ፣ ዋጋ ወደ ማረጋጋት እየተሄደ አይደለም ተብሏል፡፡ ስለሆነም ቀድመው በበጀት ተደግፈውና አቅማቸውን አጎልብተው የአርሶ አደሩን ምርት በመሰብሰብ፣ የዋጋ ችግር በሚያጋጥም ጊዜ የዋጋ ማረጋጋት ሥራ ማከናወን አለባቸው የሚለው ተገምግሟል ሲሉ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብይት በመሳተፍ ጤናማ ግብይትን በማስፈን፣ ሕገወጥ ደላላን በማስቀረት፣ ቅሸባን፣ ሰው ሠራሽ የምርት እጥረትንና የዋጋ መናርን ገበያ በማረጋጋት ለሸማቹ ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ዓይነተኛ መፍትሔ እንዳላቸው ቢታመንም፣ ካለው ችግር አንፃር አፈጻጸማቸና ተሳትፏቸው በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ በርካታ ማነቆዎች እንዳሉና ከእርሻ ጋር ተያይዞ ሰፊ ሥራ እንደተሠራና ምርትና ምርታማነት እንዳለ ቢረጋገጥም፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርትን ቀድሞ በማሰባሰብ ረገድ ተልዕኮ ቢኖራቸውም. በነጋዴ ተቀድመው እንደሚገኙ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አስታውቀዋል፡፡

አቶ አብዲ ባቀረቡት ምላሽ በተያዘው የበጀት ዓመት ክልሎችን ቀድሞ በማነጋገር (በተለይ ኦሮሚያና በአማራ) ማኅበራት ከአባሎቻቸው በስንት መግዛት እንዳለባቸው፣ መሠረታዊ ማኅበራት ለዩኒየኖች በስንት መሸጥና መሰብሰብ እንዳለባቸው፣ ዝርዝር ዕቅድና ገለጻ ወጥቶ እስከ ታች ድረስ በንቅናቄ ለመሥራት ሰፊ ጥረቶች ቢደረጉም፣ አስቀድሞ ‹‹መንግሥት በዝቅተኛ ዋጋ ሊገዛችሁ ነው›› በሚል በተሠራ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አርሶ አደሩ ምርቱን በጊዜ እንዳላወጣ፣ የወጣውም ምርት በድብቅ በመሸጡ የሚፈለገው ውጤት አልመጣም ብለዋል፡፡

‹‹ገንዘብ ሚኒስቴር መነሻ ዋጋ (Get Price) ብሎ ያወጣውና ወደ ታች ያወረደው ዋጋ ለአርሶ አደሩና በተለይ ለደላላው ሰፊ ምቹ ሁኔታ ፈይሯል፤›› ያሉት አቶ አብዲ፣ ‹‹ይህም ሆኖ የእነዚህ ችግሮች ዋናው ማነቆ የእኛ የማስፈጸም ብቃት ማነስ ትልቁ ችግር ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተያያዘም የግብርና ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት መድረክ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ፣ ለ2015/16 የምርት ዘመን የሚያገለግለው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት መዘግየትን የተመለከተ ነበር፡፡

የግብርና ሚኒስትር የግብይትና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ለ2015/16 የማዳበሪያ አቅርቦት በተመለከተ ካለፈው ዓመት የከረመውን ጨምሮ 15 ሚሊዮን ኩንታል ለማቅረብ ታቅዶ ነበር፡፡

በዚህ ዓመት ግዥ የተፈጸመው 12.6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ ቀድሞ ጨረታ የማውጣት፣ ፍላጎት የመሰብሰቡና ግዥ የመፈጸም ሥራው በጥሩ ጎኑ ቢሄድም፣ ነገር ግን ግዥ የተፈጸመበትና በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ውስጥ እየገባበት ያለው ፍጥነት ክፍተት እንዳለበት ታይቷል ብለዋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ዕቅድ ከተያዘላቸው 24 መርከቦች የክፍያ ማስተማመኛ (L/C) የተከፈተው ለ13 ብቻ ነው ያሉት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ ከእነዚህ ውስጥ አሥር መርከቦች ጂቡቲ ደርሰው ወደ አገር ውስጥ የማጓጓዝ ሥራ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡

እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ 517,531.9 ሜትሪክ ቶን (5.1 ሚሊዮን ኩንታል) ወደ አገር ውስጥ እንደተጓጓዘ፣ ያለፈው ዓመት የከረመው ማዳበሪያ ሲጨመር ወደ 7.3 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ዕቅዱ በግብርና ሚኒስቴር ብቻ የሚፈጸም አለመሆኑን የተናገሩት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ ትልቅ ተግዳሮት የሆነው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የግብርና ማኒስትሩ ከባንክና ከሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለማዳበሪያ ቅድሚያ እንዲሰጥ በየጊዜው ውይይትና ክትትል እንደሚደረግ ተገልጾ፣ ከንግድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ንግግር ለማዳበሪያ ቅድሚያ ተሰጥቶ ኤልሲ እንዲከፈት በተደረገው ውይይት ‹‹ለማዳበሪያ ቅድሚያ እንሰጣለን›› የሚል ምላሽ እንደተገኘ ተጠቅሷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ከማቅረብ አንፃር አጀማመሩ ጥሩ ቢሆንም፣ አገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች (መድኃኒት፣ ነዳጅ) ተፅዕኖ እንደፈጠሩ ገልጸዋል፡፡ በቅርብ የተከፈቱትን ኤልሲዎች አብዛኞቹን በማድረስ ቀደም ብሎ የደረሰውን ማዳበሪያ በማሸጋሸግ ችግሮቹ ይፈታሉ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች