Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ሚኒስቴር 3.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በከፍተኛ አሲድ በመጠቃቱ ማምረት እንደማይችል አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በጠቅላላ ከሚታረሰው 16 ሚሊዮን ሔክታር የእርሻ መሬት ውስጥ 3.2 ሚሊዮን ሔክር የሚሆነው በከፍተኛ አሲድ በመጠቃቱ፣ ማምረት የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው የ2015 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን፣ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአገሪቱ በእርሻ መሬት ላይ እየተስፋፋ ያለውን የአሲዳማነት መጠን ለመቀነስና ለማከም፣ በግብርና ሚኒስቴር እንዲሠራ የታቀደው ዕቅድ አፈጻጸም ከዕቅዱ 12 በመቶ ብቻ የሚሆነው ነው የሚለውን በመጥቀስ፣ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነና ለወደፊትም ምን እንደታሰበ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ደኤታ እያሱ ኤልያስ (ፕሮፌሰር) እንዳስታወቁት፣ ከአገሪቱ መሬት 16 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው በእርሻ የሚሸፈን ሲሆን፣ ከዚያ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን የሚሆነው ሔክታር (43 በመቶ) በአሲዳማነት የተጠቃ ነው፡፡

በጠቅላላው በአሲድ ከተጠቃው ውስጥ 3.2 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው መሬት ጠንካራ አሲዳማ በመሆኑ፣ ማምረት የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን እያሱ (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል፡፡

ከአሲዳማነት የተነሳ በርካታ ከምርት ውጪ የሆኑ መሬቶች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ምርታማ በሆኑት አካባቢዎች ጭምር በችግሩ ሳቢያ የምርት መቀነስ በከፍተኛ መጠን ይታያል ተብሏል፡፡ ለአብነትም 50 ኩንታል ምርት የሚሰጥ መሬት አምስት ኩንታልና ከዚያ በታች በመስጠት አቅም የማጣት ደረጃ ላይ መድረሱም ተገልጿል፡፡

በተለይ ትርፍ አምራች ተብለው የሚታወቁት የምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ኦሮሚያ በስፋት፣ አማራ (የምዕራቡ ክፍል) እና ደቡብ ምዕራብ ሙሉ በሙሉ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምዕራባዊ ክፍል፣ እንዲሁም የሲዳማ ክልል ሙሉ በሙሉ በአሲድ ተጠቂ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ችግሩን ለመፍታት መንግሥት መፍትሔ አድርጎ የወሰደው የግብርና ግብዓት የሆነውን ኖራ ማቅረብ እንደሆነ ተገልጾ፣ ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት በአቅርቦቱ  ላይ ማነቆ ማጋጠሙ ተጠቅሷል፡፡

መንግሥት ለኖራ አቅርቦት ግዥ የሚቀርብ 800 ሚሊዮን ብር በዕቅድ ቢይዝም፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችና ከውጭ የሚገባው ማዳበሪያ ዋጋው በመናሩ ምክንያት ለኖራ አቅርቦት ለመመደብ ችግር እንዳጋጠመ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ለአብነትም በተያዘው የበጀት ዓመት ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ በማቅረብ 300 ሺሕ ሔክታር መሬት ለማከም ቢታቀድም፣ የቀረበው 110 ሺሕ ሔክታር የሚሸፍነውን ያህል መሆኑ ለግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተገልጿል፡፡

እያሱ (ፕሮፌሰር) እንዳስረዱት፣ በአሥር ዓመት ዕቅድ ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር ጠንካራ አሲዳማ መሬት ይታከማል ተብሎ ታቅዷል፡፡ ይህም ማለት በየዓመቱ 300 ሺሕ ሔክታር እየታከመ ይሄዳል የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት 300 ሺሕ ሔክታር ለማከም በሔክታር 30 ኩንታል ሒሳብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህም ወጪው በርካታ እንደሆነና ኩንታሉ በአንድ ሺሕ ብር ቢባዛ እንኳን አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህን ማድረግ ባለመቻሉ የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም አነስተኛ እንደሆነ አክለዋል፡፡

በቀጣይ የድርጊት መርሐ ግብር (Action Plan) እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ለኖራ አቅርቦት ሥርዓት ለማበጀትና በሚቀጥሉት ዓመታት ቢያንስ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር የሆነውን ጠንካራ አሲዳማ መሬት በማከም ማዳን እንዲቻል፣ የምክር ቤቱና የቋሚ ኮሚቴው ትልቅ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የግብርና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጠይቀዋል፡፡

በድርጊት መርሐ ግብሩ ውስጥ ከተቀመጡ ጉዳዮች ውስጥ አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ሰብሎች (ሩዝ፣ አጃ፣ ቡናና የመሳሰሉት) ላይ የምርት ቅየራ ማድረግ እንደሚገባ የሚያመለክት እንደሚገኝበት ተጠቅሷል፡፡

 አንድ ሔክታር አሲዳማ መሬት ለማከም የሚፈለገው የኖራ መጠን 50 ኩንታል መሆኑን፣ ይህንን የተፈጨ ኖራ ማጓጓዝ ትልቅ ፈተና ስለሆነ መጠኑን ቀንሶ ከኮምፖስትና ከሌሎች ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎች ጋር አቀላቅሎ ማቅረብ እንደሚጠይቅ፣ የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታው ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

 መሬት በአሲድ መጠቃቱ የምርት መቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ በማዳበሪያ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ምክር ቤቱ ከግንዛቤ ሊይዘው ይገባል ሲሉ እያሱ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡ ከ71 እስከ 90 በመቶ የማዳበሪያ ውጤታማነትን እንደሚቀንስ ግብርና ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት መረጋገጡንም አክለዋል፡፡

‹‹በብዙ ጥረት ከውጭ ያመጣነው ማዳበሪያ 71 በመቶ አቅሙ ሥራ ላይ የማይውል ከሆነ ለአገር ኢኮኖሚ ኪሳራ ይሆናል፡፡ ለአርሶ አደሩም ገቢ የማያስገኝ ኪሳራ ስለሚሆን፣ ለማዳበሪያ የሚውለው ወጪ ራሱ በልዩ ሁኔታ ታይቶ ለኖራ በጀት የሚመደብበትን ሁሉም በጋራ ቢያየው፤›› በማለት እያሱ (ፕሮፌሰር) አሳስበዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የግብርናው ዘርፍ በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እንደተጀመሩት ንቅናቄዎች ሁሉ በቀጣይ በንቅናቄ ደረጃ ሊታይ የሚገባው የአፈር ለምነት ንቅናቄ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹ከዚህ ጋር በተገናኘ ዕቅዱን አዘጋጅተናል፡፡ አጋር ድርጅቶችን በዚህ ሥራ ላይ ለማረባረብ የማወያየት ሥራ ጀምረናል፡፡ የእናንተም ዕገዛ ከታከለበት በእዚህ አካባቢ ያለውን ነገር እናሳካለን፤›› በማለት ግርማ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች