Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቤትና የኢንዱስትሪ ሠራተኞች መብት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጣሰ መሆኑን ኢሠማኮ አስታወቀ

የቤትና የኢንዱስትሪ ሠራተኞች መብት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጣሰ መሆኑን ኢሠማኮ አስታወቀ

ቀን:

የቤትና የኢንዱስትሪ ሠራተኞች መብት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጣሰ መሆኑ በጥናት እንደተረጋገጠ የኢትዮጰጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈደሬሽን (ኢሠማኮ) አስታወቀ፡፡

በቤትና በኢንዱስትሪ ሠራተኞች በተለየ መልኩ በሥራ ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰትና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን፣ የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እየተፈጸሙ ነው የተባሉ የመብት ጥሰት ዓይነቶቹን ሲያስረዱም፣ ‹‹ለአካላዊና ለወሲብ ጥቃት ሰለባ መሆን፣ ለግዳጅ ሥራና ለተለያዩ መሠረታዊ የሥራ ላይ መብት ጥሰቶች ተጎጅ መሆን፣ አድልኦ፣ ያለምንም እረፍት ለረዥም ሰዓት መሥራት፣ ለሠሩት ሥራ በወቅቱና አብዛኛውን ጊዜ ክፍያ ያለማግኘት፣ በነፃ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ተነፍጎ በአንድ ቦታ ተወስነው እንዲሠሩ መገደድ፣ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰላባ መሆንና የመሳሰሉት የመብት ጥሰቶች ደርሶባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

ይህን ያሉት ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የቤትና የኢንዱስትሪ ሠራተኞች የሥራ ላይ መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ፣ የፖሊሲ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ በተዘጋጀ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በነበረው ውይይት ላይ ነው፡፡

ሁኔታውን የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ፣ እነዚህ ሁሉ የመብት ጥሰቶች እየደረሱባቸው የሥራ ሁኔታዎችና መብቶቻቸው የሕግ ጥበቃ የማይደረግላቸው መሆኑን በጥናት መረጋገጡን አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ መብቶቻቸውን ያስጠብቃሉ ተብለው የሚወጡ ሕጎች ቢኖሩም፣ ከግንዛቤ ማነስ፣ ከሕግ አስፈጻሚ አካላት አቅም ማነስ፣ ከሕጎቹ ክፍተት፣ ከአሠሪዎቹ ሕጎችን ያለመቀበልና ከመሳሰሉት ማነቆዎች የተነሳ፣ ሠራተኞች መሠረታዊ መብቶቻቸው በተጠበቀ ሁኔታ እየሠሩ እንዳልሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ብዙ ሠራተኞች ለመኖር እጅግ በሚያስቸግር መልኩ በአነስተኛ ደመወዝ፣ ለደኅንነታቸው አስከፊ በሆነ የሥራ ሁኔታ እየተጎዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በሕግ አፈጻጸም አብዛኛዎቹ የሥራ ቦታዎች በሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪዎች እንደማይጎበኙ፣ ለጤናና ደኅንነት አስጊዎች እንደሆኑ፣ በዚህም ተነሳ አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ሥራ ያላቸው ግን ‹‹ድሆች (Working Poor)›› እንዲሆኑ መደረጋቸው ተረጋግጧል ተብሏል፡፡

የቤት ሠራተኞችን በተመለከተ አሠሪና ሠራተኞች ጉዳይ አዋጅ፣ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ያወጣል በማለት ድንጋጌዎች ውስጥ ተካቶ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ ይሁን እንጂ ይወጣል ተብሎ የተደነገገው ደንብም እንዳልወጣ፣ የዘርፉን የሥራ ሁኔታዎች የተመለከቱ ውስን ድንጋጌዎችን የያዘው የፍትሐ ብሔር ሕግም ቢሆን በይዘትና በአፈጻጸም ረገድ ክፍተት እንዳለበት፣ ዘርፉ በየጊዜው ሊደርስበት የሚገባቸውን ዕድገት ሙሉ ለሙሉ አካቶ ሊተገበር የማይችል ሆኖ እንደተገኘ፣ በዚህም በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የቤት ሠራተኞች በሥራ ላይ የመብት ጥሰት እየደረሰባቸው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን የተመለከቱ ሕጎችን ሲገልጹም፣ በተቀባይ አገሮች በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው የሚሄዱ ዜጎች መብትና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅላቸው ቢደነገግም፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የቤት ሠራተኞች ያለምንም ሕግ እየሠሩ እንደሚገኙ፣ በዚህም ምክንያት ውጭ አገር ለሥራ የወጡ ሰዎች የመብት ጥሰት፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት እየደረሰባቸው እንዲሠሩ እየተገደዱ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈደሬሽን የመላ ሠራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ሠራተኞቹ ተደራጅተው መብታቸውን በጋር ለማስጠበቅ እንዲደራጁ፣ እንዲደራደሩ፣ መንግሥት የቤት ሠራተኞች የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት እንዲገነዘብ ለማድረግ መታቀዱን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በሜይደይ›› ለመንግሥት በሰላማዊ ሠልፍ ሊቀርብ የነበረው የሠራተኞች ቅሬታ፣ በመንግሥት መታገዱን ተከትሎ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ካሳሁን፣ ጥያቄዎቹን ለመንግሥት ለማቅረብ አዘጋጅተው ማጠናቃቸውን ገልጸው፣ በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረውና እስከ ዛሬ ምላሽ ያልተሰጠው የሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ ወለልን የመወሰን ጥያቄም፣ ምላሽ ሊሰጥበት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ስታቲክስ በ2022 ባወጣው መረጃ መሠረት በዓለም ላይ 3.32 ቢሊዮን ሠራተኞች እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...