Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ 75 በመቶ የሆነው ክፍል ወደ እርሻነት መቀየሩ ተነገረ

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ 75 በመቶ የሆነው ክፍል ወደ እርሻነት መቀየሩ ተነገረ

ቀን:

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የሚገኘው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ 75 በመቶ የሆነው ክፍል ወደ እርሻነት መቀየሩን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆኑ ጥቁር ዝሆኖችን ጨምሮ 31 አጥቢ እንስሳትና ከ220 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች እንዳሉት የሚነገርለት መጠለያ፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተብሏል፡፡

መጠለያው ስላጋጠመው ችግር የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳየች ቋሚ ኮሚቴ፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የቱሪዝም ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ነው፡፡

- Advertisement -

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞንና በሶማሌ ክልል የፋይዳና የረር ዞኖችን የሚያዋስነው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ 6,980 ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሚሆን፣ ከዚህ ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ክፍል በእርሻ መሸፈኑን ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሰቢ ወ/ሮ አሻ ያህያ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ 75 በመቶ የሆነው ክፍል ወደ እርሻነት መቀየሩን፣ በመስክ ምልከታ ወቅት አንድም ዝሆን አለመታየቱን ተናግረዋል፡፡

በመጠለያው መጠነ ሰፊ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ሊጠፋ የተቃረበውን ፓርክ በጊዜ መታደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመስክ ምልከታ ወቅት በባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በሚገኙ ማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የግንዛቤ ችግር መኖሩን መመልከታቸውን በመግለጽ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዘላቂነት መፍታት ይገባዋል ብለዋል፡፡

ፓርኮቹን ከሚያዋስኑ ክልሎች ጋር ያለውን ግጭት በዘላቂነት በመፍታት፣ የአገር ቅርስና ብርቅዬ ዝሆኖችን መታደግ እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባቢሌ ዝርያቸው ለየት ያሉ ዝሆኖች መኖራቸው ከሌሎች ፓርኮች ለየት ያደርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ መጠለያው የገጠመው ችግር እየተበራከተ መምጣቱን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በከፍተኛ የመሬት ወረራ ምክንያት የእርሻ፣ የግጦሽና የደን ምንጣሮ መስፋፋቱን ገልጸዋል፡፡

ከሁለቱም ክልሎች በሚመጡ ዜጎች አካባቢው በነዋሪዎች እየተሞላ በመሆኑ ዝሆኖቹ አካባቢውን ለቀው እየሄዱ ነው ብለዋል፡፡

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በስተደቡብ አካባቢ ሄዶ ለማየትና የችግሩን ስፋት ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን የመጠለያው መካከለኛና በስተሰሜን ባለው ክፍል በተደረገው ዳሰሳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሰዎች መያዙን አስረድተዋል፡፡

ያለውን የችግሩን ስፋት ለማወቅ ጂአይኤስና ሪሞት ሴንስ የሚባሉ መተግበሪያዎች በመጠቀም በተደረገው ዳሰሳ፣ ሙሉ በሙሉ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደሚታይና በአካባቢው የቀረውም ቁጥቋጦ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት በተለይ በሁለቱ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ፖለቲካዊ ውሳኔ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ችግሮችን ለመቅረፍ ባለሥልጣኑ ሰፊ ሥራ እያከናወነ መሆኑን በመግለጽ፣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረትና ዕገዛ የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ በፓርኩ ሠፍረው የነበሩ ከሁለቱም ክልሎች ከ800 በላይ አባወራዎች እንደተነሱ ጠቁመው፣ ይህም ሥራ በቀጣይነት እንደሚተገበር አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...