Thursday, June 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የደመኝነት ፖለቲካ የበለጠ ቀውስ እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዋር ከጦርነት ነጋሪነት ጉሰማ አልላቀቅ እያለ ደመኝነት ሲንሰራፋ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከገጠሟት ፈተናዎችና መከራዎች በመነሳት አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው የተሞላው በግጭት በመሆኑ፣ ከአክሳሪና ከአውዳሚ የታሪክ ገጽታዎች ተምሮ በመልካም ጎዳና ላይ ለመራመድ ስክነት ያስፈልጋል፡፡ ካለፉት የልማትም ሆነ የጥፋት ታሪኮች መማር አለመቻል ከፍተኛ ጉዳት አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከመጠን በላይ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የጥፋት ታሪክን በአስከፊ ሁኔታ መደጋገም ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልክ እንደ ዘመነ መሣፍንት ወይም እንደ ዘመነ ነጭና ቀይ ሽብር እርስ በርስ መፋጀት፣ በታሪክና በመጪው ትውልድ የሚያስጠይቅ ወንጀል እንደሆነ ይታሰብበት፡፡ በዚህ ዘመን በሐሳብ ልዩነት ምክንያት እንኳን መገዳደል ቡጢ መሰነዛዘር ሊታሰብ አይገባውም ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን የሐሳብ ልዩነት ለእስር፣ ለዱላ፣ ለስደት፣ ሲከፋም ለግድያ እየዳረገ ፖለቲካውን የደመኝነት እያደረገው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ዜጎች እየተጎዱ፣ ሐዘኑ ለአገር እየተረፈ ነው፡፡ የደመኝነት ፖለቲካ አገር ማፍረሱ አይቀርም፡፡

በየትኛውም አገር ውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ መኖሩ ያን ያህል የሚያሳስብ አይደለም፡፡ ሽኩቻው ሕጋዊና ሰላማዊ የሆነውን የሐሳብ ልዩነት መሠረት እንዲያደርግ ነው የሚበረታታው፡፡ በብዙ አገሮች በምርጫ ጊዜም ሆነ በተለያዩ ወቅቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚካሄዱ ክርክሮች፣ የሕዝብን ቀልብና ልብ በሚማርኩ አቀራረቦች አማራጮች የሚቀርቡባቸው ናቸው፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት በመሆኑ በጣም የሚከበር ሲሆን፣ ከበስተጀርባው ሴራ መጎንጎንም ሆነ የጥፋት ድርጊቶችን ማውጠንጠን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ሕዝብ ሲናቅና ምን ታመጣለህ በሚል መታበይ የሚመራ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፓርቲዎችን ስለሚጎዳ፣ ከምንም ነገር በላይ በሐሳብ ልቆ መገኘት ላይ ርብርብ ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ለማስፈን የተደረጉ ጥረቶች በመምከናቸው፣ ከሐሳብ ይልቅ ጉልበት ላይ ማተኮር የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት አለመግባባትን በጠመንጃ ለመፍታት መሞከር ያተረፈው ሥቃይና መከራ ብቻ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት፣ ሌሎች ግጭቶችና ጥቃቶች በሐሳብ ማረጥ ምክንያት የደረሱ የደመኝነት ታሪክ ማስታወሻ ናቸው፡፡

በፖለቲካ በየጊዜው የሚቀያየሩ አስተሳሰቦችና አሠላለፎች ሲኖሩም፣ አንድነትንም ሆነ ልዩነትን የማስተናገድ ጥበብ በዚያው ልክ መቃኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ትናንት ወዳጅ የነበረ ዛሬ ባላንጣ እንደሚሆነው ሁሉ፣ የትናንት ባላንጣ ደግሞ የዛሬ ወዳጅ ሊሆን እንደሚችል መረዳት የግድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ዘለዓለማዊ ወዳጅነትም ሆነ ጠላትነት የለም›› የሚባለው፡፡ ይህ የፖለቲካው ብልኃትና ጥበብ የገባቸው የፖለቲካ ተዋንያን የሰርክ መርህ ሲሆን፣ ከዚህ በተቃራኒ ያሉት ግን ተቃራኒ ነው ከሚሉት ጋር እንደ ሌሊት ወፍ እየተጋጩ ለአገር የሚጠቅም የሰው ኃይል፣ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ያባክናሉ፡፡ ችግሩ ከከፋም ለዕልቂትና ለውድመት ይዳርጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የቸገረው አንዱ ነገር ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ይዞ ከመነጋገርና ከመደራደር ይልቅ፣ ጉልበትን በማስቀደም ይዋጣልን ማለት የአዘቦት ተግባር መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ልዩነትን ዕውቅና ሰጥቶ ማስተናገድ ሲገባ፣ ‹‹እንቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው›› በሚለው የኋላቀሮች መፈክር መፋጀት አቋራጭ መንገድ ተደርጓል፡፡ ይህ የጥፋት መንገድ ግን ‹‹የዝንጀሮ መንገድ ቢከተሉት ገደል›› እንደሚባለው እየሆነ ነው፡፡

አንድን ግለሰብ ወይም የቡድን አባላት በመግደል ምንም ዓይነት ዓላማ ማሳካት እንደማይቻል፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው አውዳሚ ጦርነት በቀላሉ መማር ይቻላል፡፡ አለፍ ሲልም በዘመነ ነጭና ቀይ ሽብር ከተፈጸመው ፍጅት መገንዘብም እንዲሁ፡፡ ወንድም የገዛ ወንድሙን ገድሎ ከዘለዓለማዊ ፀፀትና ቁጭት ውጪ ምንም ዓይነት ትርፍ እንደማይኖር፣ እስካሁን ድረስ ከተፈጸሙ ግድያዎችም ሆነ ጭፍጨፋዎች መረዳት ተችሏል፡፡ በደርግ ዘመን፣ በኢሕአዴግ ዘመን፣ አሁን ደግሞ በብልፅግና ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ለቁጥር የሚታክቱ እስሮች፣ ድብደባዎች፣ ዛቻዎችና ግድያዎች በተለያዩ የፖለቲካ ተዋንያን ተከናውነዋል፡፡ በደርግ ዘመን ራሱ ደርግ፣ ኢሕአፓና መኢሶን የተጫረሱበት ምክንያት ከጠረጴዛ ዙሪያ የዘለለ ትንቅንቅ አያስፈልገውም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን አሸንፎ የሽግግር መንግሥት የመሠረተበት ጉባዔ፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያለ ልዩነት ያሳተፈ ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ ጭካኔ አይኖርም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ገለል ተደርጎ ብልፅግና ሲመጣ ብዙዎቹ አኩራፊ ፓርቲዎች ከውጭ ተግተልትለው ቢገቡም፣ ትጥቅ አልፈታም ያለውና ሥልጣኔን ለምን አጣሁ ያለው ኃይል አገር እያመሱ ደመኝነቱ እዚህ ደረጃ አይደርስም ነበር፡፡

ሥልጣን የያዘው አካልም ቃል እንደገባው ሁሉ አካታችነቱና አሳታፊነቱ ያልተዋጠላቸው ኃይሎች ማኩረፍ ሲጀምሩ፣ ለሰላማዊ ንግግርና ድርድር በሩን ወለል አድርጎ ቢከፍተው ይህ ሁሉ ጥፋት አይከሰትም ነበር፡፡ በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ሰላም ጠፍቶ ዜጎች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ሲያቅታቸውና በሰላም ውሎ መግባት አሳሳቢ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ችግርን ከመፍታት የበለጠ ምንም መፍትሔ አይኖርም፡፡ የፌዴራል መንግሥት ቀደም ሲል በውጭ ኃይሎች ግፊት ከሕወሓት ጋር በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማድረጉ፣ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከሚባለው ኃይል ጋር በዛንዚባር የሰላም ንግግር መጀመሩ መልካም ተግባር ነው፡፡ እግረ መንገዱንም አማራ ክልል ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ቀውስ በማርገብ፣ ከግጭትና ከውድመት ይልቅ ለንግግርና ለድርድር አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ከደመኝነት ፖለቲካ በመላቀቅ ሰላም ማስፈን የሚቻለው በንግግርና በድርድር ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን የትናንቱን ዕልቂትና ውድመት ዘንግቶ በመሣሪያ እንሞካከር ማለት፣ የማይወጡበት አዘቅት ውስጥ ነው የሚከተው፡፡

ጎረቤት ሱዳን የውጭ ኃይሎችን የውክልና ጦርነት በሚያስፈጽሙ ሁለት ጄኔራሎች ሳቢያ እየፈራረሰች ነው፡፡ ዋና ከተማዋን ማዕከል ያደረገው ሁለቱ የቀድሞ ወዳጆች የጀመሩት የውክልና ጦርነት፣ ከሱዳን አልፎ ጎረቤት አገሮች ላይ ጭምር ከፍተኛ ጣጣ እንደሚያስከትል እየተተነበየ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ ድንበር የምትጋራው ሱዳን ጦርነቱ ሲስፋፋባት፣ እንደ ጎርፍ ከሚፈልሱ ስደተኞች በላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ አደጋ የሚያስከትሉ ችግሮች ተግተልትለው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ሥጋቶች መካከል ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተለያዩ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች፣ አሸባሪዎችና የህዳሴ ግድቡን ደኅንነት የሚፃረሩ ሰላዮች ይጠቀሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላሟ የሚጠበቀው በሠራዊት፣ በመሣሪያ አቅም፣ በቴክኖሎጂ በሚታገዝ ደኅንነት ወይም በሌሎች ዝግጁነቶች ብቻ ሳይሆን በሕዝቧ አንድነት ጭምር ነው፡፡ የሕዝቡን ዘመን ተሻጋሪ አንድነትና አብሮነት ከሚንዱ ድርጊቶች መታቀብ የሚቻለው፣ ከደመኝነት ፖለቲካ ውስጥ በመውጣት ለሐሳብ ልዕልና ክብር ሲሰጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው የደመኝነት ፖለቲካ የበለጠ ቀውስ እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ይደረግ የሚባለው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...

በተቃርኖዎች መሀል የሚዋልለው የብልፅግና መንግሥት

ርዕዮተ ዓለም እንኳ የሌለው ይሉታል የሚቃወሙት ወገኖች፡፡ እሱ ግን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...