Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በባንኮችና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እስከ 200 ሺሕ ብር ተቀማጭ ላላቸው የመድን ሽፋን ሊሰጥ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በባንኮችና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ አስቀማጮች ዋስትና ለመስጠት በቅርቡ የተቋቋመው የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ፣ እስከ 200 ሺሕ ብር ተቀማጭ ገንዘብ ላላቸው ዋስትና እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡ ባንኮችና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በየዓመቱ ከተቀማጭ ገንዘባቸው 0.2 በመቶ ለፈንዱ ገቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በየባንኩ ለእያንዳንዱ አስቀማጭ እስከ 200 ሺሕ ብር ለሚሆን ተቀማጭ ገንዘብ የዋስትና ሽፋን ይሰጣል፡፡

የመድን ሽፋኑ መጠን እስከ 200 ሺሕ ብር ለሚሆነው ተቀማጭ ገንዘብ የዋስትና ሽፋኑ እንዲሰጥ የተወሰነው፣ 96 በመቶ ያህል አስቀማጮች የተቀማጭ ገንዘባቸው መጠን የተጠቀሰውን ያህል ስለሆነ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ መሠረት የመድን ሽፋኑ እንደሚሰጥ የገለጹት ምክትል ገዥው፣ ይህ ውሳኔ አብዛኞቹን አስቀማጮች የሚሸፍን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባንኮች ለዚህ ዋስትና ሽፋን ተቀማጭ የሚያደርጉት የፕሪሚየም መጠን ምን ያህል እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በየዓመቱ ከጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘባቸው 0.2 በመቶ የሚሆነውን በማስላት ለፈንዱ ገቢ በማድረግ ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል፡፡  

የተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና ፈንድ አገልግሎት ሲጀመር ባንኮቹ የሚከፍሉት ክፍያ እንደሚኖር የጠቀሱት ምክትል ገዥው፣ የገንዘቡ መጠን ግን ገና ያልተወሰነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የ32 ባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን 1.87 ትሪሊዮን ብር ሲሆን፣ የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ ገንዘብ ሲታከል፣ አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማቱ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ ሁለት ትሪሊዮን ብር ይደርሳል ተብሏል፡፡

በመሆኑም ለአስቀማጮች ገንዘብ ዋስትና አሁን ባለው የተቀማጭ ገንዘብ ሲሰላ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመጀመሪያው ዓመት፣ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ለፈንዱ ማስቀመጥ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

አሁን ያለው የፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ ገንዘብ በየዓመቱ በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ ስለሚጨምር፣ ወደ ፈንዱ የሚገባው የገንዘብ መጠንም በዚያው ልክ በየዓመቱ እያደገ እንደሚሄድ ታውቋል፡፡

የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው፣ ባንኮችና የማክይሮ ፋይናንስ ተቋማት አደጋ ቢያጋጥማቸው ለአስቀማጮች ዋስትና እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በሌሎች አገሮች የተለመደ ነው፡፡ ፈንዱን በተመለከተ በቅርቡ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ ፈንዱ የሚሰበስበው ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ በሚከፍተው ሒሳብ ነው፡፡ መንግሥት ፈንዱን ሥራ ለማስጀመር ሁለት ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚመድብ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኮች የገንዘብ እጥረት እያጋጠማቸው ነው በሚል እየተነሳ ላለው ጥያቄ አቶ ሰለሞን በሰጡት ምላሽ፣ የገንዘብ እጥረት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በየዓመቱ የኤክስፖርት ምርት በብዛት በሚላክበትና ታክስ በሚከፈልበት ወቅት የሚከሰት ችግር ነው ብለዋል፡፡

በእነዚህ ወቅቶች እጥረቱ ለሁለትና ሦስት ወራት ከታየ በኋላ እንደገና የሚስተካከል ነው በማለት የገንዘብ እጥረት አለ መባሉን አስተባብለዋል፡፡ ችግሩ የሚታይባቸው ሁለት ባንኮች መሆናቸውን፣ እነሱም ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ ሰፊ ሥራ ስለሚሠሩ እንጂ፣ አለ የሚባለው እጥረት የሌለ መሆኑንና ችግሩ ጊዜያዊና በጠቀሷቸው ምክንያቶች የሚፈጠር እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

እነዚህን ሁለት ባንኮች ተጠንቅቃችሁ ሥሩ ከማለት የዘለለ ካልሆነ በስተቀረ፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በጣም ጤነኛ ሆኖ እየተጓዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ባንኮች ጥሬ ገንዘብ የለንም የሚሉበት ምክንያት ታዲያ ምንድነው?›› ለሚለውም ጥያቄ አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ካሽ የለም የሚባለው ካሽ ስለሌለ አይደለም፡፡ ሊኖራቸው ከሚገባው በላይ ጥሬ ገንዘብ ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹ስለዚህ በእኛ መለኪያ ባንኮች ጤናማ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ነገር ግን የጥሬ ገንዘብ ማኔጅመንቱ ላይ በአብዛኛው ገንዘባቸውን ከኤክስፖርት ሥራው ጋር በተያያዘ ሥራ ላይ አውለውታል፡፡ ይህንን በአግባቡ ማስተዳደር ቢችሉ ኖሮ ችግሩ የሚነሳበት ምክንያት የለም፤›› በማለት የጥሬ ገንዘብ ችግር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች