Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንገዶች አስተዳደር በፕሮጀክቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ዕገታዎች ለሥራዬ እንቅፋት ሆነውብኛል አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በግንባታ ላይ ባሉ የመንገድ ፕሮጅክቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና የሠራተኞች ዕገታ፣ ፕሮጀክቶችን እያስተጓጎለብኝ ነው አለ፡፡

በ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት የዲዛይን ሥራቸው በፀጥታ ምክንያት ሙሉ በሙሉ የተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች 17 መድረሳቸውን፣ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱራህማን ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በጥናት ዲዛይን ጥገናና ግንባታ ላይ የሚገኙ 570 ፕሮጀክቶች እንዳሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አጠቃላይ ዋጋቸው 850 ቢሊዮን ብር ይደርሳል ብለዋል፡፡

በበርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የፀጥታ ችግር መኖሩን ገልጸው፣ ‹‹ብዙ ፕሮጀክቶች በፀጥታ ምክንያት ተቋርጠዋል፣ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ክርክር የመሸጋገር አዝማሚያ አላቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት በተቋረጡ ፕሮጀክቶች በርካታዎቹ ቀላል የማይባል የንብረት ውድመትና ኪሳራ መድረሱን ጠቅሰው፣ በዚህም የተነሳ አንዳንድ የሥራ ተቋራጮች ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ ጉዳት ስለደረሰባቸው ካሳ እየጠየቁ ነው ብለዋል፡፡

ለመንገድ ፕሮጀክቶች መስተጓጎል በአብዛኛው የሚገጥመው ችግር ከፀጥታ ጋር የተገናኘ መሆኑን የጠቀሱት የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደጀኔ ፈቃዱ (ኢንጂነር)፣ የሚታየው ክስተትም በኢመደበኛ ኃይሎች፣ ከሽፍታና ከታጣቂዎች ጥቃት ጋር የተገናኘ በመሆኑ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ኮንትራክተሮችና ኮንሰልታንቶች ወደ ኮንስትራክሽን ቦታዎች ለመሄድ ፍላጎት እንደማያሳዩ ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አባላት የመስክ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስምንት የመንገድ ፕሮጀክት ባጋጠመ የፀጥታ ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉ የቆሙ መሆናቸውን፣ ግንባታቸው የተጀመሩትም እየፈረሱና እንደገና እንደ አዲስ ጥገና እየተጠየቀባቸው እንደሆነ ገልጸው፣ አስተዳደሩ ለምን ወደ ሥራ አይመለስም በማለት ጠይቀዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተገነቡ ላሉ የመንገድ ፕሮጅክቶች በዋነኛነት እንቅፋት የፈጠረው፣ በራሱ ክልል ውስጥ ያለው የፀጥታ ችግር ሳይሆን በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ነው ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት የተቋረጡትን የመንገድ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ የየትኛውንም ፕሮጀክት ደኅንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን፣ ለኮንትራክተሮችና ለኮንሰልታንቶች ለማሳወቅ ቢሞከርም አንድም ኮንትራክተር ይሁን ኮንሰልታንት ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ኮንትራክተሮችና ኮንሰልታንቶች ወደ ቦታው ለመሄድ ፈቃደኛ ያልሆኑበት ዋነኛው ምክንያት፣ በውሉ መሠረት ኮንትራክተሩ ወደ ፕሮጀክት ዕቃም ሆነ ባለሙያን ለማጓጓዝ የሚጠቀመው መንገድ በኦሮሚያ ከልል ነቀምትን አልፎ ቢሆንም፣ በዚህ አካባቢ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በዚህ መስመር ማለፍ ባለመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም ከወራት በፊት አንድ ሙሉ ቦቴ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ ሾፌሩ ተገድሎ ነዳጁም መወሰዱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ኮንትራክተሮቹ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመግባት በአማራ ክልል በኩል ከውሉ ውጪ ተጨማሪ 300 ኪሎ ሜትር ጉዞ በማድረግ በፀጥታ ኃይሎች ታጅቦ ለመሄድ ተሞክሮ እንደነበር፣ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ሒደት ኮንትራክተሮች ከውል ውጪ ለሚወጣው ተጨማሪ ገንዘብና የደኅንነት ሥጋት ዋስትና የሚፈልጉ በመሆኑ በዚህ ክልል ያሉ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ መመለስ አልተቻለም ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች