Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ወቅቱ የሠርግ ነው አይደል? እስቲ እኔ የዛሬ ዓመት የገጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ በቅርቡ የተዋወቅኩት ሰው ወንድም ሠርግ ላይ የተገኘሁት በመኪናዬ ምክንያት ነው፡፡ ቀደም ሲል የደረሰኝ የሠርግ ካርድ ሆቴል የተዘጋጀ የምሣ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም ነበር፡፡ ነገር ግን የሠርጉ ዕለት ሲቀርብ የአጃቢ ፕሮግራም ተልኮልኝ አጀቡን እንድቀላቀል መወሰኑ ተነገረኝ፡፡ ልብ በሉ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በቅርቡ እጄ በአጋጣሚ የገባው ዘመናዊ ሐንዳይ የቤት አውቶሞቢል ነው፡፡ ይህ ዘመናዊና መልኩ የሚያምር አውቶሞቢል የሀብታሞቹ ሠርገኞችና ዕድምተኞች ባልደረባ አድርጎኝ በአንዴ ያላሰብኩት የተንዛዛ የሠርግ ፕሮግራም ውስጥ ከተተኝ፡፡

የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ ሊካሄድ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ሚዜዎችና አጃቢዎች ዘመናዊ መኪኖቻችንን እንደ ባቡር ቀጣጥለን ሙሽሪት ቤት እንድንሄድ ፕሮግራም ተይዟል፡፡ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በደንብ የማላውቀው ጓደኛችን ወንድም ቤት ስደርስ ከሠርግ ያልተናነሰ ድግስ ጠበቀኝ፡፡ ትልቁን ሳሎን በሰፊው የሞላው የቡፌ ጠረጴዛ ላይ የተዘረጋው የምግብ ዓይነት አንድ ባታሊዮን ጦር ይመልሳል፡፡ በዚያ ላይ ጎልድ ሌብልና ግሪን ሌብል ውስኪ በየዓይነቱ ተደርድሮ እንደ ጉድ ይኮመኮማል፡፡ የድግሱ ሥነ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሌላው ዝግጅት መቀጠል ጀመረ፡፡

አመሻሽ ላይ ወደ ሙሽሪት ቤት እንደምንሄድ ተነገረን፡፡ ጥሎሽ ቀርቷል ሲባል ሰምቼ ስለማውቅ ግራ ገባኝ፡፡ እንደ እኔ ግራ የተጋቡ ነበሩ፡፡ የሙሽራውና የሙሽሪት ቤተሰቦች ቀረ የሚባል ነገር የለም ብለው ነው አሉ ይህ መደናገር የተፈጠረው፡፡ ነገር ግን ለሙሽሪት የሚሄደው ጥሎሽ በሻንጣዎችና በተለያዩ ካርቶኖች ተደርድሮ ሲታይ ከመርከብ የተራገፈ የሀብታም ሸቀጥ ይመስላል፡፡ የሙሽሪት አልባሳት፣ መጫሚያዎች፣ ሽቶዎች፣ መጋጌጪያዎችና የተለያዩ ቁሳቁሶች ለጆሮ የሚከብድ ወጪ እንደወጣባቸው የሰማሁት ዘግይቼ ቢሆንም ብዙም አልገረመኝም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በረባውና ባረባው ጉዳይ የሚወጣው ገንዘብ ብዙ ነበርና ነው፡፡

- Advertisement -

በተያዘልን ፕሮግራም መሠረት ሙሽሪት ቤት ስንደርስ መሽቶ ነበር፡፡ ተገቢውን  ባህላዊ ሥርዓት አከናውነን ወደ ውስጥ  ስንዘልቅ፣ እዚህም ሠርግ የሚያህል ድግስ ጠበቀን፡፡ በስንት ውጣ ውረድና ወቀሳ ያመጣነውን ጥሎሽ አስረክበን ምግብና መጠጡን ተያያዝነው፡፡ ከዚያም ጭፈራው ደራ፡፡ እንዲህ ዓይነት ያለ ጎልድና ግሪን ሌብል በቀር የማይስተናገድበት የጥሎሽ እራት አይቼ ስለማላውቅ ያለ ቦታዬ የተገኘሁ መሰለኝ፡፡ እኩለ ሌሊት አካባቢ በስንት መከራ ተሸኘን፡፡ ያውም በየመሀሉ ጥሎሹ ልጅቷን አይመጥንም እየተባልን እየተሰደብን፡፡ አንድ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ የሞላው ጥሎሽ አነሰ ነው የሰዎቹ ቅሬታ፡፡ ይኼ ነገር ከቡቲክ በኪራይ የመጣ ይሆን እንዴ?

ቅዳሜ ከንጋቱ 12 ሰዓት ሲሆን ሠርጉ ቤት እንድንገናኝ በጥብቅ ተነግሮናል፡፡ እኔ የማርፈድ አመል ስላለብኝ አንድ ሰዓት ስደርስ ሁሉም እዚያው ነበሩ፡፡ ሙሽራው እየተጣጠበ፣ ፀጉሩንና ፂሙን በባለሙያዎች እየተስተካከለና በታዋቂ አልባሾች እየለበሰ ሳለ እኛ ደግሞ የተለመደውን ምርጥ ቁርስ አጣጣምን፡፡ ከዚያም መኪኖቻችንን በተሰጣቸው ደረጃ መሠረት ደረደርን፡፡ ሁሉንም ነገር አስተካክለን ከጨረስን በኋላ መልበስ ጀመርን፡፡ ከኢስታንቡል የመጣልንን ሽክ ያለ ሙሉ ልብስ ከእነ ሸሚዙና ከእነ ከረባቱ ለብሰንና ምርጥ ጫማ ተጫምተን ሽቶ መቀባባትና ራሳችንን ማስተካከል ያዝን፡፡ ሚዜዎች አንድ ዓይነት፣ አጃቢዎቹም እንዲሁ በተለየ ቀለም አንድ ዓይነት፡፡ ዓይቼ የማላውቀው የሠርግ ሥርዓት ውስጥ ገብቼ የፊልም አክተር መሰልኩ፡፡ ይኼ ሁሉ ቅንጦት የተሞላበት ሠርግ ላይ በመገኘቴ ከደስታ በላይ አስክሮኛል፡፡ በዚያ ላይ የቆነጃጅቱ ብዛት አይጣል ነው፡፡

ሙሽራውን ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ ከቤቱ አስወጥተን ወደ ሙሽሪት ቤት አመራን፡፡ ሙሽሪት ቤት ረጅም ቆይታ ካደረግን በኋላ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲሆን ወደ ሆቴል ተጓዝን፡፡ ሆቴል 8፡30 ሰዓት ላይ ስንደርስ አዳራሹን ግጥም ብሎ የሞላው የሠርግ ታዳሚ ከሁለት ሺሕ በላይ ይሆናል፡፡ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት በሆቴል በተደረገው የተንበሸበሸ ሥነ ሥርዓት በከፍተኛ ወጪ የተዘጋጁ ምግቦችና መጠጦች ከመቅረባቸውም በላይ ሁለት ዘመናዊ ባንዶች የታደሙበት ነበር፡፡ ከደለቡ ሰንጋዎች የቀረበው ጥሬ ሥጋ፣ ዓይነተ ብዙው ክትፎ፣ የተለያዩ የውጭና የአገር ቤት ምግቦችን በልተው በውስኪ ዓይነቶች የተንበሸበሹ ታዳሚዎች አቅላቸውን የሳቱበት ሠርግ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የሠርጉን ጠቅላላ ወጪ ከመገመት በዘለለ ከባለቤቶቹ ውጪ ማንም እንደማያውቅ ነው የተረዳሁት፡፡ ከሠርጉ በኋላ መልሱና ቅልቅሉን ጨምሮ ከአሥር በላይ ጥሪዎች ላይ ሁለት ሳምንት ሙሉ ስገኝ ሥጋና ውስኪ እንዳንገፈገፈኝ አልረሳውም፡፡

ሁሉም ነገር በሰላም ተጠናቆ ወደ መደበኛው ኑሮዬ ስመለስ የከረምኩበት ሠርግ ህልም መሰለኝ፡፡ ሠርገኞቹ፣ ሚዜዎቹ፣ አጃቢዎችና ሌሎች በቅርብ ርቀት የነበሩ ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸው የእኔና የቢጤዎቼ ዓይነት አልነበረም፡፡ ኑሮአቸው የተንደላቀቀ፣ አመጋገባቸውና አጠጣጣቸው የተለየ፣ ወሬያቸውና አስተሳሰባቸው ሁሉ ከእኔ ቢጤው ዜጋ በእጅጉ የራቀ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚያ ላይ የሚኖሩባቸው መኖሪያ ቤቶች በቃላት ለመግለጽ የማይቻሉ ናቸው፡፡ እኔ እዚያ እንዴት ልገኝ ቻልኩ? አዎ? በቅርቡ ከጓደኞቼ ጋር የተለመደው ቦታ ቢራ ስንጠጣ የተዋወቅነውና ጓደኛ ያደረገን ሰው ነው ሠርግ የጠራን፡፡

ጓደኞቼ ሌላ ጊዜም ቢሆን ሠርግና ድግስ ስለማይወዱ ምክንያት ፈጥረው እንደማይገኙ ሲነግሩት እኔ ፈቃደኛነቴን ገለጽኩለት፡፡ በአጋጣሚ ለቤተሰብ ከውጭ የተላከ ዘመናዊ ሐንዳይ መኪና ከጉምሩክ ሲወጣ ለተወሰነ ጊዜ መያዜን የተረዳው ይህ ሰው ለአጃቢነት መረጠኝ፡፡ ይህንን ሁሉ ጉድ ሲታዘቡ የነበሩ ጓደኞቼ “ሰርጎ ገብ” ብለው ስም አወጡልኝ፡፡ ያለ ቦታዬ ተገኝቼ የከረምኩበት ሠርግ ላይ ከተዋወቅኳት አንዲት ሀብታም ቆንጆ ጋር የጀመርኩት ፍቅር በአጭሩ የተቀጨው ያለ ቦታዬ በአጋጣሚ የተገኘሁ “ሰርጎ ገብ” ስለነበርኩ ነው፡፡ እውነት እላችኋላሁ በመሀላችን ያለው ልዩነት የብርሃንና የጨለማ ያህል ነበር፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ልዩነት አለ እንዴ? እኔ ግን በዓይኔ ስላየሁት ምስክር ነኝ፡፡

(ማቲያስ ልዑል፣ ከአዲሱ ገበያ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...